ከሹፌርነት ወደዝነኛ ተዋናይነት

Wednesday, 12 November 2014 13:53

የዛሬው እንግዳችን በያዝነው ሳምንት ብቻ ሁለት ፊልሞቹ ተመርቀው ለዕይታ በቅተውለታል። “የበኩር ልጅ” እና “የፍቅር ቃል”። ይሁን እንጂ ፊልምን “ሀ” ብሎ ከጀመረበት “ውሳኔ” ፊልም በኋላ “ጣምራ፣ ፍፃሜ፣ ሐማርሻ፣ ኒሻን፣ እሷን ብዬ፣ ያልተነገረ፣ ጉደኛ ነችን ጨምሮ ከሃያ በላይ ፊልሞች ውስጥ የትወና ብቃቱን አሳይቷል። ትውልዱ ሰላሌ የሆነው የዛሬው እንግዳችን አዲስ አበባን የተቀላቀላት ገና የ40 ቀን ጨቅላ ሳለ ነው። ተዋናይ ተዘራ ለማ፤ ከሚተዳደርበት የሹፍርና ሙያው ድንገት ወደትወናው ዓለም በመግባት በጥቂት ዓመታት ውስጥ ዝናው የገነነ ባለሙያ ነው። አዝናኝና አጭር ቆይታን አድርገናል፤ መልካም ንባብ።

ሰንደቅለመጀመር ያህል የልጅነት ህልምህ ምን መሆን ነበር?

ተዘራትውልዴ ሰላሌ ፍቼ ከተማ ነው፤ ያደኩት መሿለኪያ አካባቢ ነው። ምን መሆን እፈልግ እንደነበር ዛሬ አንተ ገና ጠየከኝ። እውነቴን ነው የምልህ አርቲስት የመሆን ህልሙ ነበረኝ። ነገር ግን እንዲህ በቀላሉ አገኘዋለሁ ብዬ አስቤው አላውቅም። ዕድሜዬ ከፍ ሲል አብዝቼ ፊልሞችን እመለከት እንደነበር ትዝ ይለኛል። በተለይ የህንድ ፊልም ካየሁ በኋላ አንድን ገፀ -ባህሪይ በውስጤ ማብሰልሰሉ የተለመደ ተግባሬ ነበር።

ሰንደቅአሁን ባለህበት ዕድሜህ ከግማሽ ዘመንህ በኋላ የምትመኘውን አርቲስትነት አግኝተኸዋል። ያለፈው ረጅሙ ዕድሜህን በሹፍርና በማሳለፍህ ይቆጭሃል?

ተዘራበርግጥ አዎ! ግን ፈጣሪ የፈለገው ሆኗል። አሁን ከጀመርኩበት ጊዜ ቀደም ብዬ ሰርቼ ቢሆን ኖሮ ጥሩ ነበር። ቢቆጨኝም እግዚአብሔር ይመስገን የተመኘሁትን ነገር አግኝቼዋለሁ።

ሰንደቅለመሆኑ የኪነቱን ህይወት እንዴት ተቀላቀልከው?

ተዘራአንድ ነገር አስታውሳለሁ፤ በደርግ ዘመን በቀበሌ ደረጃ በተቋቋሙ የኪነት ቡድኖች ውስጥ እዘፍን ነበር። እወዛወዛለሁ፤ በተለይ ደግሞ ኮሜዲ ቴአትሮችንም እሞካክር ነበር። ከዚያ በኋላ ወደከፍተኛ ኪነት ሳድግ በሙዚቃ መሳሪያ ላይ ማተኮር ጀመርኩ። በተለይ ጊታር እና ኦርጋን ላይ አተኩር ነበር። በዚህ እንቅስቃሴ መካከል መንግስት ተለወጠ፤ የኪነት ቡድኑም ተበተነ። ከዚያ በኋላ ከኪነቱ ጋር እንደማልገናኝ ነበር የማስበው። አባቴ ከሞተ በኋላ የእናቴና የእህቴ ኃላፊነት በእኔ ላይ ነበር። ያለኝም አማራጭ መስራት ነበር። በዚህ አጋጣሚ ትልቁን ውለታ ሰርታ ሾፌር እንድሆን መንጃ ፈቃድ እንዳወጣ የረዳችን ባለቤቴ ናት። በሹፍርና ሙያ ያልዞርኩበት ሀገር የለም። ግን አንድም ቀን እረክቼበት አላውቅም። ባይገርምህ ከኔ እኩል ስራውን የጀመሩት ጓደኞቼ ከአንድም ሁለት ሶስት የራሳቸው መኪና አላቸው።

ሰንደቅታዲያ በምን አጋጣሚ ወደኪነቱ በፊልም በኩል መጣህ?

ተዘራየሚገርም አጋጣሚ ነው። በአንድ ወቅት ጉልላት የሚባል ጓደኛዬ መኪናው ይበላሽና ጋራዥ ይገባል። እናም ለእርሱ የመጣለትን ስራ ለኔ አስተላልፎ “ተዜ ወደ አለም ገና ትወስዳቸዋለሁ 500 ብርም ይከፍሉሃል። የምትጭንላቸው አንድ የወተት በርሜል ነው ስላለኝ ተስማምቼ አብሬያቸው ሄድኩ። በቀጣዩ ቀን የፊውዥን አዲስ ፕሮዳክሽን አባላት ከሆኑት ገነትና ቶሚን አገኘሁዋቸው። ዕቃ ሲጭኑ በፊልም መቅረጫ ዕቃዎችን በማየቴ ልቤ ድንግጥ ማለት ጀመረ። ሰዎቹ ለካ ፊልም ሰሪዎች ናቸው። አብሬያቸው ሄጄ “ውሳኔ” ፊልምን ሲቀርፁ በማየቴ ብቻ በጣም ደስ ይለኝ ነበር። በወቅቱ እኔ የተነጋገርኩት በጠዋት የሚፈልጉት ቦታ ዕቃቸውን አድርሼ እስከ 6 ሰዓት ቆይቼ ወደቤቴ እንደምመለስ ነበር። እኔ ግን ወደቤት መሄድ አልፈለኩም፤ እነሱም ሂድ አላሉኝም። ያን ዕለት ማታ አምስት ሰዓት ላይ ገኒ ወደኔ መጥታ “አንቱ” ነበር የምትለኝ፣ “አስመሸንዎት አይደል ይቅርታ” አለችኝ። እኔ ግን በልቤ የሆነ ነገር በፊልሙ ውስጥ እንድሰራ በፈቀዱልኝ የሚል ነበር። አቆየንዎት በሚል የ400 ብር ቴፕ ሰጠችኝ፤ እኔ ግን ብሩ አልታየኝም ነበር። ከዚያ በኋላ በነጋታውም አብሬያቸው እንድሰራ አደረጉኝ፤ በሹፌርነት እያገለገልኩ ቀጠልኩ።

   ሰንደቅትወናው እንዴት ጀመረ?

ተዘራእየተግባባን ስንመጣ፤ ከዚያ አንድ ቀን ወደኔ እያዩ ሲነጋገሩ ሰማሁዋቸው። ቆይ ለምን አንዲት ፓረት አትጫወትልንም አሉኝ? ማመን አቅቶኝ፤ ከመደንገጤ የተነሳ ሰውነቴ ተብረከረከ። የማጠናትን ወረቀት ሰጠችኝ። ለ15 ቀን እንዳጠናው ብትሰጠኝም እኔ ግን ወዲያው በቃሌ ይዤው ነበር። ለመስራት ስዘጋጅ አድማሱ ከበደና ደረጀ ደመቀ ነበሩ አብረውኝ የሚተውኑት። እነሱ ወረቀታቸውን ሲያወጡ እኔ ወረቀት አልያዝኩም። ተገርመው መስራት ስንጀምር ሳንደግም አሪፍ ተሰራ። አድማሱ ከበደና ደረጀ ደመቀ ወዲያው ከዛሬ ጀምሮ “አንቱ” አንልህም አርቲስት ስለሆንክ “አንተ” ብለንሃል ነበር ያሉኝ።

ሰንደቅበውሳኔ ፊልም ውስጥ ተሳትፈህ ለመጀመሪያ ጊዜ ራስህን በሲኒማ ቤት ስታየው ምን ተሰማህ?

ተዘራፊልሙን ያየሁት ከባለቤቴ ጋር ነበር። ፊልሙ በጣም የሚያስለቅስ ታሪክ ነበረው። እኔ ግን በመስራቴ ልቤ በደስታ ይመታ ነበር። ያንን ፊልም በመስራቴ በቀጣይም “ጣምራ” የተሰኘ ፊልም እንድሰራ ተመረጥኩ። በነገራችን ላይ “ጣምራ” እና “ውሳኔ” የፊውዥን አዲስ ፕሮዳክሽኖች ናቸው። ጣምራን እየሰራን ነብዩ እንዳልካቸው የሚባል ባለሙያ ለራሱ ፊልም ይፈልገኝ ነበር። ልጄ አብራው ትሰራ ስለነበር አገናኘችን፤ በጣም ነበር ደስ ያለው። ብዙ አልታየለትም እንጂ “ከኩርባው በስተጀርባ” የተሰኘ ጥሩ ፊልም ሰርተን ነበር።

ሰንደቅከፊልም ውጪ በቴአትር፣ በሬዲዮና በቲቪ ድራማዎችስ ላይ ያለህ ተሳትፎ እንዴት ነው?

ተዘራየሚገርምህ በሬዲዮና የቲቪ ምንም ስራ አልነበረኝም። አሁን ላይ በኢቢኤስ ቲቪ እየታየ ያለው “ሞጋቾቹ” ድራማን እየሰራሁ ነው። ከባለሙያዎቹ ጋር ተግባብተን እየሰራሁትና እየወደድኩት ያለሁት ስራ ነው። ቴአትርን በተመለከተ “የኔ እውነት” የተሰኘ በዓለም ሲኒማ አሳይተን ነበር። ወደፊት ቦታ ከተገኘ የበለጠ ለመስራት ተዘጋጅተናል።

ሰንደቅ እስካሁን ከሰራሃቸው ፊልሞች የትኛውን ገጸ-ባህሪይ በተለየ ታስታውሰዋለህ?

ተዘራአሁን ድረስ የማስታውሰው “ፍፃሜ” የተሰኘ ፊልም አለ። ፊልሙ ብዙ ውጣ ውረድ ያየሁበትና በጭለማና በጭቃ ሱሉልታ ላይ የሰራነው ፊልም ነው። በጣም አድካሚ ነበር፤ ግን በጣም ልዩና ደስ የሚለኝ ስራ ነው። ብዙ ሰዎችም በተለየ ያስታውሱታል። ገፀ- ባህሪው በጣም ጨካኝ ከመሆኑ የተነሳ ትልልቅ ሰዎች እንኳን በመንገድ ላይ ሲያገኙኝ ይደነግጣሉ።

ሰንደቅአሁን ዝና እየመጣ ነው፤ ሹፍርናውስ ቀረ?

ተዘራወዲያው ቀረ። ምክንያቱም ከልጅነቴ ጀምሮ አልመው የነበረውን ሙያ ስላገኘሁት ማለት ነው።

ሰንደቅከሹፌርነት ይልቅ ፊልም ሥራ ጥሩ ክፍያ አለው?

ተዘራአዎ ሁሉም ነገር በደረጃ ነው። ከጊዜ ወደ ጊዜ ክፍያው እየተሻሻለ ነው። እኔ ግን መከራከር አልፈልግም። በቂ ገንዘብ ግን አገኛለሁ።

ሰንደቅ“የበኩር ልጅ” ፊልምን ስትሰራ የተለየ የዝርፊያ ገጠመኝ ነበረህ እስቲ ንገረኝ?

ተዘራበጣም የሚገርምህ ፊልሙን ስንሰራ ከፊልሙ አባላት ጋር በጣም በፍቅርና በደስታ ነበር። ወጣቶች ናቸው ደስ ይላሉ። ፊልሙም ጥሩ ታሪክ ያለው ነው። በስተመጨረሻ ግን ለስራ ሄደን ዝርፊያ አጋጠመን። ሾፌር ሆኜ እንኳን ይዤው የማልወጣውን ልብስ ነው መርጬ ሰብስቤ የሄድኩት። ሲያልቅ ግን ባልታወቁ ሌቦች ተዘረፍን። ባይገርምህ ሾፌር እያለሁ ለበርካታ ዓመታት ስሰራ ዝርፊያ ያጋጠመኝ አንድ ጊዜ ብቻ ነው።

ሰንደቅብዙዎች ስላንተ ሲያወሩ ከወጣቶች ጋር ቶሎ ተግባብቶ መስራት ይችላል ይሉሃል፤ እንዴት ቻልክበት?

ተዘራይሄ የሰው መውደድ ይመስለኛል። እኔ በአብዛኛው ወጣቶች ይመቹኛል። ልክ ስንገናኝ “ሰላም ፋዘር” ይሉኛል። ብዙዎች ሥራ ስንጀምር “አንቱ” ይሉኝና ስራው ሲያልቅ ደግሞ “አንተ” ተባብለን ነው በሳቅና በደስታ የምንለያየው፤ በጣም ነው የምንግባባው።

ሰንደቅፊልማችን እየበዛ፤ እናንተም እያታያችሁ ነው። ስለኢንዱስትሪው ምን ትላለህ?

ተዘራፊልማችን በጣም እያደገ እንደሆነ ይሰማኛል። ከባለሙያና ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም አንጻር እያደግን ነው። ችግሩ ግን ተመሳሳይ ታሪኮች እየተደጋገሙ ነው። እነዚህ ቢሻሻሉ የበለጠ ይሆናል ብዬ አምናለሁ።

ሰንደቅከየትኞቹ ወጣትና አንጋፋ ተዋንያን ጋር መስራት ትፈልጋለህ?

ተዘራበጣም የሚገርምህ ፊልም መስራት ሳልጀምር ሙሉዓለም ታደሰን ማየት በጣም ያስደስተኝ ነበር። ከሷ ጋር መስራት በጣም ነበር የምመኘው፤ አንድ ፊልም አብረን ሰርተናል። ሌሎችም አብሬያቸው መስራት የምፈልጋቸው “አክተሮች” አሉ። እነ ፍቃዱ ተ/ማርያም፣ ከወጣቶቹ ደግሞ ሰለሞን ቦጋለ፣ ሳምሶን ታደሰ (ቤቢ) ግሩም ኤርሚያስ አብሬያቸው ብሰራ ደስ ይለኛል።

ሰንደቅምን ያዝናናሃል?

ተዘራበአብዛኛው በማንበብ እዝናናለሁ፤ ስራ ካልበዛብኝ ፊልምም አያለሁ። ከምግብ ስጋ መብላት ደስ ይለኛል። በተለይ ቁርጥ ሲገኝ፤ አንበሳ ነኝ (ሳቅ)

ሰንደቅየወጣት ፊልም ባለሙያዎች ችግር ምንድነው?

ተዘራብዙዎቹ ጎበዞች ናቸው። ነገር ግን አልፎ- አልፎ ምን ያጋጥመኛል መሰለህ? አንድ ሁለት ፊልም ይሰሩና የወጣትነት ጉራዋ ትመጣባቸዋለች። ባይሆን ጥሩ ነው። ግን ብዙዎቹ ሰውና ስራ አክባሪዎች ናቸው። ገና ብዙ ስራ እንደሚጠብቃቸው አምናለሁ። ይሄንን ደግሞ በስኬት ለመውጣት ስራቸውን በፍቅርና በአክብሮት መስራት ይኖርባቸዋል።

 ሰንደቅበመጨረሻ ማመስገን የምትፈልጋቸው ሰዎች ካሉ?

   ተዘራበመጀመሪያ ቤተሰቦቼን በጣም አመሰግናለሁ። በተለይ ባለቤቴ ወ/ሮ ፋንቱ አርጋውን በጣም እወዳታለሁ፤ አመሰግናታለሁ። በተረፈ ግን የሚያበረታቱኝ ጓደኞቼን እና የሚያደንቁኝን ተመልካቾች በጣም እንደምወዳቸው ንገርልኝ። በተረፈ ለእናንተም እግዚአብሔር ይስጥልኝ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
12893 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us