“ገፀ-ባህሪይ መደጋገም አልወድም”

Wednesday, 19 November 2014 11:20

 

 


ተዋናይ ካሌብ ዋለልኝ

 

ተወልዶ ያደገው በአርሲ ነገሌ ነው። ለቤተሰቡ ሰባተኛ ልጅ የሆነው የዛሬው እንግዳችን ካሌብ ዋለልኝን በርካቶች በስራዎቹ ያውቁታል። ከቴአትር የሚስት ያለህ፣ ማን ያግባት፣ ለእረፍት የመጣ ፍቅርና የተከፈለ ልብ የሚጠቀስለት ሲሆን፤ ከቲቪ ድራማዎችቹ ደግሞ “ቅ” ነው፣ ትንቅንቅ፣ ከል ፀዳል፣ ፈተና፣ ፅናትና ሽምግልና ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው። በሬዲዮ ድራማዎቹም አሁን ድረስ የሚታወስለትን ስራዎች ያበረከተው ካሌብ፤ ዳዴ በሚለው የኢትዮጵያ ፊልም ኢንዱስትሪ ውስጥም የራሱን አቅም ያሳየባቸውን ፊልሞች ተጫውቷል። ከነዚህም ውስጥ ማን ያውጣው፣ ደማሚት፣ ትንቅንቅ፣ ሳምራዊ፣ ፍላፃ፣ ፍርቱና፣ ሃኒሙን እና በቅርቡም የዳይሬክተርነት ችሎታውን የሚያሳይበትን “ያለ ሰው” የተሰኘ የቢኒያም ወርቁን ድርሰት ይዞልን ሊመጣ በዝግጅት ላይ ነው። በቴአትርም ሊሆን አልቦዘነም ዝግጅቱን ተያይዞታል። ከጨዋታ አዋቂው ተዋናይ እና ዳይሬክተር ጋር የነበረንን አዝናኝ ቆይታ እነሆ፡

ሰንደቅ፡- ለመነሻ ያህል ለቤተሰብ ሰባተኛ ልጅ መሆን የሚሰጠው ዕድል ምንድነው?

ካሌብ፡-ለኔ ሰባተኛ ልጅ መሆን ብዙ መልካም ዕድሎችን ይዞልኛል። ቤተሰባችን የተጠነሰሰው አዲስ አበባ ላይ ነው። አባቴ ፖሊስ በመሆኑ ከወልዲያ እዚህ አጎቱን ለማየት ይመጣል፤ እናቴ ደግሞ ከምንጃር ሸንኮራ ወደ አዲስ አበባ በመምጣቷ እዚህ ነው የተዋወቁት ማለት ነው። የሚገርምህ የመጀመሪያዎቹን ሁለት ልጆች እዚህ ይወልዳሉ። ቀጥሎ አባቴ በስራው ምክንያት ወደዝዋይ ሲዛወር ዝዋይም ልጅ ይወለዳል። አርሲ ነገሌ ላይ እኔ ደረስኩ ማለት ነው። (ሳቅ) ለአርሲ ነገሌ እኔ የመጀመሪያ የቤተሰቡ ልጅ ነኝ። ከዚያ በኋላ አባቴ ወደመቀሌ ሲዛወር ቤተሰቡ ሁሉ መንቀሳቀስ ስለከበደው እኛ ኑሯችንን በአርሲ ነገሌ አድርገን ከእህት ወንድሞቼ ጋር እዚያው ከተማ መማር ጀመርን ማለት ነው።

ሰንደቅ፡- ታዲያ አንተን ምን የተለየ ባለተሰጥኦ አደረገህ? ቤተሰብህ ድጋፍ ያደርግልህ ነበር ወይ? አርሲ ነገሌስ ተሰጥኦን ለመግለፅ ምቹ ነበረች?

ካሌብ፡- እንዳልሁክ እኔ ለቤተሰቤ ሰባተኛ ልጅ ነኝ። ታናሽ ስትሆን ዕድለኛ ነህ፤ የመሳሳት ዕድልህ ይቀንሳል። በተቻለህ ሁሉ ታላላቆችህ ላይ የምታያቸውን ስህተቶች አትደግምም። በአርሲ ነገሌ የኔ ታላላቆች በሚማሩበት ወቅት እስከ8ኛ ክፍል ብቻ ነበር ትምህርት ቤት ያለው፤ ከዚያ በኋላ ዝዋይ ወይም አዲስ አበባ ነው የተማሩት። አዲስ አበባ ወይም ዝዋይ ለትምህርት ቆይታው ሲመጡ በጣም ተነፋፍቀን ነበር የምንገናኘው። በዚህ አጋጣሚ ያዩትን እነሱ ሲያወሩልኝ እኔም የገጠመኝን ሳወራላቸው ገና በህፃንነቴ የመደመጥ አጋጣሚውን አገኘሁ ማለት ነው። ያ ለኔ የመግለፅ አቅሜን እንዳዳብር ረድቶኛል። ምክንያቱም የመደመጥ ዕድልን ባገኘህ ቁጥር ራስህን የመግለፅና የመፍጠር አቅምህ ይጨምራል። ሌላ ትምህርት ቤት የገጠመኝን ነገር ልንገርህ፤ የ8ኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ ክፍል ውስጥ ሁላችንም እንጮህ ነበር። በአጋጣሚ አንድ ቀን ተማሪው ሁሉ እየረበሸ ባለበት ጊዜ እኔ ቆሜ እያወራሁ፤ ዳይሬክተራችን መጡ። ተማሪው ሁሉ ፀጥ ሲል እኔ ስላላየዋቸው ቆሜ ነበር። ምን እየረኩ እንደነበር ሲጠይቁኝ ከፊቴ ያለውን አንድ ደብተር አንስቼ ለተማሪዎቹ ጥቅስ እያነበብኩላቸው እንደነበር ተናገርኩ። በአጋጣሚ ደብተሩ ላይ ብዙ ጥቅሶች ነበሩ። መምህሩ ማንበቤን እንድቀጥል አዘዘኝ፤ ሳልደነግጥ አንድ ጥቅስ አንብቤ እርሱን ማብራራት ቀጠልኩ። በኋላ ቢሮ ተጠርቼ ስገባ ልቀጣ መስሎኝ ነበር። ነገር ግን ትምህርት ቤቱ ለሚያቋቁመው የሚኒ-ሚዲያ ክበብ እንድሰራ ጠየቁኝ። ያኔ ነው ሰዎች ፊት መናገርን የለመድኩት ይመስለኛል።

ሰንደቅ፡- ወደአዲስ አበባ እንዴት መጣህ?

ካሌብ፡-በአርሲ ነገሌ “የንጋት ጎህ” የተሰኘ የቴአትር ክበብ አቋቁመን ከጓደኞቼ ጋር እንሰራ ነበር። የሚገርመው ግን በዛን ወቅት ቴአትር ሰርተን ለማሳየት ተመልካቹ ሳይሆን እኛ ብዙ ወጪ እናወጣ ነበር። እንዲያውም ከፍለን ነበር ቴአትር የምናሳየው ማለት ትችለለህ (ሳቅ)። ማትሪክ እንደተፈተንን ግን ከሁለት ጓደኞቼ (ኃ/ማርያም ብሩ እና እሸቱ ለገሰ) ጋር በመሆን ወደ አዲስ አበባ በመሄድ ቴአትር መስራት አለብን ተባብለን ተነሳን።

አዲስ አበባ ስንገባ እንደአጋጣሚ የተስፋዬ ሲማ የቴአትር ኮርስ ማስታወቂያ ወጥቶ ሰዎች ሲመዘገቡ ደረስን። የተመዘገበው ወደ 2000 አካባቢ ነው፤ የሚፈለገው ደግሞ ዘጠና ሰው ብቻ ነበር። እንደዕድል ሆኖ ሶስታችንም ተወዳድረን አለፍን። ይህ የኛ ግሩፕ ለቴአትር ስራ ብሎ የተሰደደ የመጀመሪያው ግሩፕ ሳይሆን አይቀርም።(ሳቅ)

ሰንደቅ፡- የመጀመሪውን የፕሮፌሽናል መድረክ እንዴት አገኘኸው?

ካሌብ፡- በጣም ዕድለኛ ነኝ፤ በወቅቱ ስልጠና እየወሰድን ሳለ ነፈሱን ይማረውናአርቲስት አለሙ ገ/አብ “ውድቅት” የተሰኘን ቴአትር ከወጣቶች ጋር ለመስራት ለምልመላ ሲመጣ አወዳድረው መረጠኝ። በአጋጣሚ “ድንቁ” የሚባለውን መሪ ገፀ-ባህሪይ የመተወን ዕድል ተሰጥቶኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ህዝብ ፊት ቀረብኩለት ማለት ነው። የሚገርምህ ቴአትሩ ተመርቆ “ፖስተሩ” (ማስታወቂያው) ጊዮርጊስ አካባቢ በትልቁ ተሰቅሎ ስሜን ያየሁት ዕለት ለረጅም ሰዓት ሰው እስኪታዘበኝ ቆሜ ቀርቻለሁ (ሳቅ) ለኔ ያ አጋጣሚ ትልቅ መነሻ ነበር። ቴአትሩ የሚታየው ረቡዕ ማታ ሰዓቱ እስኪደርስ፤ በጣም ይጨንቅ ነበር፤ ለነገሩ አሁንም ድረስ ብዙ ተዋናዮች መድረክን እስኪረግጡ ትንሽም ብትሆን ፍርሃት አይጠፋቸውም።

ሰንደቅ፡- በፕሮፌሽናል መድረክ የመተውን አጋጣሚውን ካገኘህ በኋላ አርሲ ነገሌ ለሚገኙት “የንጋት ጎህ” ክበብ አባላት መነቃቂያ ትሆናለህና ምን አደረክ?

ካሌብ፡- አሁንም ቢሆን አርሲዎችን አልረሳቸውም። መነሻዬ ስለሆኑ ብቻ አይደለም። የሚገርምህ ህልም እንኳን ብዙ ጊዜ ሳልም “መቼቱ” እዚያ ነው የሚሆንብኝ። ባይገርምህ እነርሱም ለኔ ያልሰራሁትን ያህል ነው የሚያከብሩኝ። አሁን ላይ በስሜ የቴአትር ቡድን አቋቁመዋል። በስሜ መንገድ ተሰይሟል፤ ይህ ለኔ ትልቅ ነገር ነው። መንገድ ብቻ አይደለም፤ መንደርም ሰይመውልኛል (ሳቅ)። እውነቱን ለመናገር እነርሱን ለመርዳት እኔ ጎበዝ ነኝ ብዬ አላስብም። ግን በተቻለኝ አቅም በሄድኩ አጋጣሚ ልምዴን “ሼር” አደርጋለሁ፤ አጫጭር ኮርሶችን ለመስጠት እሞክራለሁ፤ ከዚህ ወደዚያ ቴአትሮችን በመውሰድ እንዲታዩ ለማድረግ እሞክራለሁ። ከዚያ ውጪ ግን ዕድሜ፣ ፆታ፣ ሀብትና ዕወቅት የማይለያየው ማህበርም አለን፤ ስለዚህ “የአርሲ ነገሌ” ልጆች በየወቅቱ እንገናኛለን ማለት ነው።

ሰንደቅ፡- ማንኛውም ስራ የመጀመሪያ ሲሆን ያስፈልጋል። ላንተ በተለየ የምታስታውሰው የመጀመሪያ ገጠመኝህ እስቲ አጫውተኝ?

ካሌብ፡- የመጀመሪያ ስትለኝ የሬዲዮ ድራማ ትዝ አለኝ። ለቅዳሜ መዝናኛ የሚሆን ድራማ ለመቅረፅ አቡነ ጴጥሮስየሚገኘው የሬድዮ ጣቢያ ስቱዲዮ ውስጥ ተገናኘን። ተለማምደን፤ አጥንተን ከጨረስን በኋላ ድንገት ሲያቀብጠኝ የሚያደምጡንን ብዙ ሚሊዮን ህዝብ አሰብኩኝ። ያኔ በራሴ ላይ ጫና ፈጠርኩና መስራት እስኪያቅተኝ ድረስ ለተወሰነ ጊዜ ተረብሼ አቋረጥኩኝ። ከዚያ አይዞህ ተብዬ ተረጋግቼ ነው ወደስራ የተመለስኩት ይሄ ለኔ በሬዲዮ ድራማ ታሪክ አሁን ድረስ የሚገርመኝ አጋጣሚ ነው፡

ሰንደቅ፡- የቲቪ ድራማና ፊልም ትንሽ ተመሳሳይነት ይኖራቸዋል። እስቲ ስለእነሱ አንድ ነገር በለኝ?

ካሌብ፡- የቲቪ ድራማን መለማመድ የጀመርኩት ለባህል በሚሰሩ አጫጭር ጭውውቶች ነው። ለዛም ሳይሆን አይቀርም ተከታታይ የቲቪ ድራማዎችን ስንሰራ ያን ያህል ስጋት አልነበረብኝም። ነገር ግን ወደፊልም ስመጣ የመጀመሪያ ስራዬ የሰለሞን አስመላሽ ስራ የሆነው “ሁለቱ” የሚል ነው። በጣም የማልረሳው አጋጣሚ በአዲሱ ቀለበት መንገድ ጦር ሃይሎች አካባቢ ይመስለኛል። ገና መንገዱ ሳይመረቅ ነበር እኛ የቀረፅነው። በፊልም ደረጃ አዳዲስ ቴክኒኮችን ያወኩበት ስራ ነው ማለት እችል ነበር። ባይገርምህ ያኔ ፊልሙ ሲመረቅ ወርቅ ነበር የተሸለምነው፤ እንደአሁኑ በሰርተፊኬት አልተሸኘንም (ሳቅ)

ሰንደቅ፡- ፊልም ስትሰራ ከክፍያ እና ከታሪኩ የቱ ያጓጓሃል?

ካሌብ፡- እዚህ’ጋ አንድ ገጠመኝን ላንሳልህ። አንድ ወቅት በመንገድ ስሄድ አንዲት ሴት ወደኔ መጣችና “እንደው በፈጠረህ በዓመት ሁለት ፊልም ብቻ ስራ” አለችኝ። መነሻ ምክንያቷን በትክክል አላውቀውም፤ ነገር ግን እኔም በዓመት ሁለት አሪፍ- አሪፍ ፊልሞችን ብሰራ ጥሩ ነው ብዬ ነው የማምነው። ይሄንን ስልህ በዓመት 10 ፊልሞችን ሰርቶ 10 የተለያዩ ብቃቶችን የሚያሳየን ተዋናይ የለም እያልኩህ አይደለም። ግን ከእኔ አቅም አንጻር ሁለት በቂ ነው። አንድ ነገር ግን ልንገርህ እኔ ከፊልም ይልቅ በጣም የምወደው ቴአትርን ነው። ከዚያ ውጪ ግን ታሪክ እመርጣለሁ፤ ታሪኩን ከወደድኩ ክፍያው ላይ መደራደር ነው። ነጋዴ ፊልም ሰሪ ከመጣ ደህና ብር ትጠይቃለህ። የኔ ብጤዎቹ ባለሙያዎች ከመጡ ግን የማገዝ ግዴታ አለብኝ ብዬ ስለማስብ ክፍያው አያስጨንቀኝም።

ሰንደቅ፡- ስራዎች ሁሉ የሚሰጡህ አንድ የተለየ ልምድ ይኖራል፤ ላንተ በተለየ የምታስታውሰው ስራ ይኖራል?

ካሌብ፡- እንዳልከው እያንዳንዱ ፊልም፣ ቴአትር፣ የቲቪ ወይም የሬዲዮ ድራማ ለኔ እንደአንድ ኮርስ ነው። ብዙ ልምድ፣ ብዙ ዕውቀት፣ ብዙ አዳዲስ ነገሮችን ታውቃለሁ። እንዲሁ በስራ ከማልረሳቸው ውስጥ “ማን ያውጣው?” የተሰኘውን ፊልም ስንሰራ፤ ባቦጋያ ሃይቅ ውስጥ የምንቀርፀው አስፈሪ “ሲን” (ትዕይንት) ነበር። እኔ ደግሞ በጣም የምፈራው እና በጣም የምወደው ነገር ውሃ ነው። ታዲያ ፊልሙ ቀረፃ ተጀምሮ ከመስፍን ኤፎክሩ ጋር ለመስራት ተዘጋጀን። እሱ ውሃ ውሰጥ ሆኖ እኔ ከነልብሴ ገብቼ የማወጣው ቦታ ነበር። አስበው ውሃው ጥልቅ እንደሆነ ሰምቻለሁ፡፤ ጀምሩ ስንባል እየተንደረደርኩ የሚገርም “ዳይቭ” ነው የገባሁት። በህይወቴ እንደዛ ውሃ ቀዝቅዞኝ አያውቅም። በፍጥነት ወጥቼ የደመ-ነፍሴን አወጣሁት። ለተወሰነ ጊዜ ራሴን ሁሉ አላውቅም ነበር፤ ያን አጋጣሚ በፍፁም አልረሳውም።

ሰንደቅ፡- “ማን ያውጣው” ፊልም በወቅቱ ለየት ያለ አስፈሪ ይዘት ያለው ከመሆኑ የተነሳ ብዙ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። የተመልካቹ ምላሽ ምን ነበር?

ካሌብ፡- እንደእውነቱ ለእኛም አዲስ ልምድ ያገኘንበት ስራ ነው። ሁላችንም ተባብረን ነበር የሰራነው። ከተመልካቹም ያገኘነው ምላሽ ጥሩ ነበር። ወደፊት ፊልም ለመስራት የሚያስችል አቅም እንዳለ ያሳየንበት ስራ በመሆኑ ለኔ የተለየ ስራ ነው ማለት እችላለሁ።

ሰንደቅ፡- ስለሀገራችን የፊልም ሂደት ምን ይታይሃል?

ካሌብ፡- እንደእውነቱ ከዚህም በላይ ብዙ መሰራት ይኖርበታል ባይ ነኝ። ነገር ግን መሪውን ተመልካቹ ባይዘውረው መልካም ነው። ተመልካቹ የሚወደውን ብቻ ባለሙያው የሚሰራ ከሆነ አደገኛ ነው። ያ ከሆነ አሰልቺ ጥበብ ይሆናል። ከተመልካች ቀጥሎ ሲኒማ ቤቶችም ተፅዕኗቸው መቀነስ አለበት። ዳኝነቱን መስጠት ያለበት ተመልካቹ ነው። ለተመልካቹ ደግሞ የተለየ ዘውግ ያላቸውን ስራዎች ማቅረቡ ተገቢ ይመስለኛል። ከተመልካች ጫና፤ ከሲኒማ ቤቶች አቋም ጋር የሚታገለውን የፊልም ባለሙያ መንግስት ደግሞ ሊያግዘው ይገባል። የፊልም መስሪያ ዕቃዎች በቀላሉ ማስገባት ቢቻል፤ አሁን እኮ ፊልም ልስራ ብለህ ፈቃድ ስታወጣ ሲጃራ ለመሸጥ ከሚፈልገው ሰው እኩል ነው ውጣ ውረዱ። መንግስት ባለሙያውን የበለጠ ሊያግዘው ይገባል።

ሰንደቅ፡- ብሰራው ብለህ የምትመኘው ገፀ-ባህሪይ አለ?

ካሌብ፡- እንደአጋጣሚ ወደቴአትር ቤት ከመምጣቴ በፊት ከNGOዎች ጋር እሰራ ነበር። አተኩረን በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ ሰርተናል። አንድ አይነት ገፀ-ባህሪይ መደጋገም አልወድም። ብዙ ጊዜ ዳይሬክተሮች አንድ ቦታ ያዩህና እንደዛ ሆነህ እንድትሰራላቸው የመፈለግ ነገር አለ። እኔ አሁን ፈጥሮ የሚያሰራኝ ዳይሬክተር ባገኝ ደስ ይለኛል። እስካሁን ከሰራሁት የተለየ ነገር ብሞክር እመኛለሁ። በተለይ ከአካል ጉዳተኝት ጋር በተያያዘ።

ሰንደቅ፡- ከሰራሃቸው ገፀ-ባህሪያትስ የትኛውን በተለየ መልኩ ታስታውሰዋለህ?

ካሌብ፡- “ለመድረስ” የተሰኘ ፊልም ውስጥ በጣም የተለየና ሴቷ ሴት የሆነ ገፀ-ባህሪይ ተጫውቻለሁ፤ እሱን በፍጹም አልረሳውም። ሰውዬው የሞዴሎች አሰልጣኝ ነው። ነገር ግን ሳያስበው እሱም አኳኋኑ ሁሉ እንደሴት ነው፤ ጥፍሩን አሳድጓል ፀጉሩን አሳድጓል በቃ በሴቶች መካከል ተገኝቶ ሴት የሆነ ገፀ-ባህሪይ ነው። የተለየ ስለሆነ በጣም ደስ ይለኛል። ሌላው ደግሞ “ማን ያግባት?” የተሰኘ ቴአትር ነበር። የአለሙ ገ/አብ ድርሰት ነው። ገፀ-ባህሪው “ዳንሰኛ” ነው የተለየ ነበር። ኢንጂኒየር፣ ዳሰኛውና ተዋናይ አንድ ግቢ ውስጥ ተከራይተው የአከራዩን ልጅ ወደው የሚያቀርቡትን ነገር በጣም በሚያዝናና መልኩ የሚያሳይ ቴአትር ነበር። ትዝ ይለኛል ቴአትሩ ሲመረቅ የአለሙ ገ/አብ ባለቤት ወ/ሮ አስቴር ከአድናቆቷ ብዛት ለባለቤቷ ያመጣችውን አበባ ለኔ ሰጥታኝ ነበር የሄደችው፤ ያን አጋጣሚ በፍጹም አልረሳውም።

ሰንደቅ፡- በም ትዝናናለህ?

ካሌብ፡- አሁን ላይ ከቤተሰቦቼ ጋር በማሳልፈው ጊዜ ነው የምዝናናው። ባለቤቴ ማህሌት ሰማይነህ ትባላለች። የመጀመሪያ ልጄ ሶሲኒዮስ ካሌብ ይባላል፤ ሁለተኛው ልጄ ደግሞ ገብርኤላ ካሌብ ትባላለች። በጣም ነው የሚያስደስቱኝ።

ሰንደቅ፡- በቀጣይ ምን ለመስራት አስበሃል?

ካሌብ፡- አሁን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በዕይታ የሚበቃ ፊልም ዳይሬክት አድርጌያለሁ። “ያለ ሰው” ይሰኛል ርዕሱ፤ የቢኒያም ወርቁ ድርሰት ነው። ፕሮዲዩሰሩ ተስፋዬ ለታ ይባላል፤ የልጅነት ጓደኛዬ ነው። በፊልሙ ውስጥ ፍቃዱ ከበደ፣ ድርብ ወርቅ አሰፋ፣ ህሊና ሲሳይ ተውነውበታል። ቀረፃችን በአዲስ አበባና አቡዳቢ ነበር ጥሩ ስራ ነው ብዬ አስባለሁ። ሌላው አሁን በቅርብ የምጀምረው አንድ የመድረክ ስራ አለ፤ የቴዎድሮስ ተ/አረጋይ ድርሰት ነው። በዚህ ቴአትር የጠፉ ባለሙያዎችን ወደመድረክ ማምጣት ነው ዋነኛው አላማዬ፤ እንደነሰራዊት ፍቅሬ፣ ሽመልስ በቀለና ሰለሞን ቦጋለ ያሉ ጎበዝ ተዋንያን ከመድረክ እየራቁ ስለሆነ ለዚህ ትውልድ በአንድ ላይ የማሳየት ሀሳብ ይዘን እየሰራን ነው። ሽመልስና ሰለሞን ተገኝተው እያጠኑ ነው። ሰራዊት ግን ትንሽ በዕቅድ የያዘው ስራ ስለነበረበት ዘግይቷል፤ እንደሚቀላቀለን ግን ተስፋ አደርጋለሁ።

ሰንደቅ፡- በመጨረሻ ማመስገን የምትፈልገው ሰው ካለ ዕድሉን ልስጥህ?

    ካሌብ፡- በመጀመሪያ የድንግል ልጅ መድሃኒያለም የተመሰገነ ይሁን። በተረፈ ግን በህይወቴ ውስጥ ላለፉ ሰዎች ሁሉ በጣም አመሰግናለሁ። ጓደኞቼና ተመልካቹንም ሁሉ በጣም አመሰግናለሁ። ኢትዮጵያ ተለውጣ ሁላችንም ተዋደን፣ ተከባብረን እንድንኖር እመኛለሁ። እናንተም ይህን ዕድል ስለሰጣችሁኝ በጣም አመሰግናለሁ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
11005 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us