“የኢትዮጵያ ፊልም ፌስቲቫል”

Wednesday, 26 November 2014 12:49

     9ኛው የኢትዮጵያ ፊልም ፌስቲቫል ከትናንት በስቲያ ሰኞ ህዳር 15 ቀን 2007 ዓ.ም በሒልተን ሆቴል በተካሄደ ደማቅ የሽልማት ሥነ-ስርዓት ተጠናቋል። በ1999 ዓ.ም አንድ ብሎ ሲነሳ ከ60 በላይ ለሚደርሱ የፊልም ባለሙያዎች ዕውቅናና ሽልማትን በመስጠት ያለፉት ዓመታትን ተጉዟል። የኢትዮጵያ ፊልም ፌስቲቫል ለሀገራችን የፊልም ኢንዱስትሪ የራሱ የሆነ ከፍታ ያለው አስተዋፅኦ እንዳለው የሚያስረዳው የፌስቲቫሉ ዳይሬክተር አቶ ይርጋሸዋ ተሾመ፤ ባለሙያው ወደፊልም ኢንደስትሪው የሚደረገው ጉዞ አጥጋቢና የተመቻቸ አለመሆኑን ይጠቅሳል።

      ፊልሞች በሚሰሩባቸው አገሮች ሁሉ ደረጃውን የጠበቁ የፌስቲቫል ፕሮግራሞች አስፈላጊ ስለመሆናቸው የሚናገረው ዳይሬክተሩ ይርጋሸዋ፤ አሁን ባለንበት ሁኔታ በአገራችን የፊልም ፖሊሲ የለም፣ ጠንካራ የሙያ ማኅበር የለም፣ የፊልም ካውንስልና ቀጣይነት ያለው ፌስቲቫል የለም። ይህንን ችግር ለመቅረፍም እንደ አንድ እርምጃ የፊልም ኢንዱስትሪውን ጉዞ ለማገዝ ታቅዶ የተመሰረተ የፊልም ፌስቲቫል እንደሆነ ያስረዳል።

      ለመጨረሻ ጊዜ ያለፉትን ሥራዎችና ባለሙያዎች ለመዳኘት ከባህልና ቱሪዝም ሚ/ር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ ከደራሲያን ማህበርና ለዘርፉ ቀረቤታ ያላቸው ሰዎች እንዲዳኙ ተደርጓል።

      ከዚህ ቀደም በተለያዩ የፊልም ዘርፎች ውስጥ በተወዳደሩ ከ60 በላይ ባለሙያዎች፣ ከኢትዮጵያ ፊልም ፌስቲቫል አዘጋጆች እጅ ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን፤ ዘንድሮ ባሳለፍነው ሰኞ በሒልተን ሆቴል በተካሄደው ፕሮግራምም በምርጥ የወንድ ተዋናይ ዘርፍ፤ አማኑኤል ሀብታሙ ከ“ረቡኒ” ፊልም፣ ተዘራ ለማ ከ“የበኩር ልጅ”፣ መሳይ ተፈራ ከ“ትመጣለህ ብዬ”፣ ደሳለኝ ኃይሉ ከ“የመሀን ምጥ”፣ ሰለሞን ሙሄ ከ“ታሽጓል” ፊልሞች በእጩነት ሲቀርቡ አሸናፊ የሆነው ተዋናይ ተዘራ ለማ ከ“የበኩር ልጅ” ፊልም ነው።

      በምርጥ የሴት ተዋንያን ዘርፍ ደግሞ፤ ሰላማዊት ተስፋዬ ከ“ወይዘሪት ድንግል”፣ ሩታ መንግስተአብ ከ“ረቡኒ”፣ ወይንሸት አበጀ ከ“ባጣ ቆዪኝ”፣ ዘሪቱ ከበደ ከ“ቀሚስ የለበስኩለት” እና ሄለን በድሉ ከ“ነቄ ትውልድ” በዕጩነት ቀርበዋል። በዚህም ዘርፍ በምሽቱ ሽልማት ያገኘችው ተዋናይት ሩታ መንግስትአብ ከ“ረቡኒ” ፊልም ሆናለች።

      በምርጥ የወንድ ረዳት ተዋናይ ዘርፍ በዕጩነት ቀርበው የነበሩት፤ መኮንን ላዕከ ከ“ጥቁር እንግዳ”፣ ባህሬን ከድር ከ“ባትመጪም ቅጠሪኝ”፣ ፀጋዬ አበጋዝ ከ“ነቄ ትውልድ”፣ ቴዎድሮስ ፈቃዱ ከ“ትመጣለህ ብዬ”፣ ዓለምሠገድ ተስፋዬ ከ“ስር ሚዜዋ” ሲሆኑ፤ የአሸናፊነቱን ውጤት ያገኘው ተዋናይ ደግሞ ቴዎድሮስ ፈቃዱ ከ “ትመጣለህ ብዬ” ፊልም ነው።

      በሴት ምርጥ ረዳት ተዋናይት ዕጩ ዘርፍ፤ አዚዛ አህመድ ከ“በጭስ ተደብቄ”፣ ማህሌት ፈቃዱ ከ“ሕግ በላይ”፣ ቃልኪዳን ታደሰ ከ“ቀሚስ የለበስኩለት”፣ ፍሬህይወት ስዩም ከ“ወይዘሪት ድንግል” እና ዕድለወርቅ ጣሰው ከ“ስር ሚዜዋ” ፊልም ናቸው። በዚህም ዘርፍ አሸናፊ የሆነችው ተዋናይት እድለወርቅ ጣሰው ከ“ስር ሚዜዋ” ፊልም ናት።

      በምርጥ የፊልም ጽሁፍ ዘርፍ፤ ብስራት መሐመድ ከ“ስር ሚዜዋ”፣ ቅድስት ይልማ ከ“ረቡኒ”፣ ልዑል ሰፈፍ ከ“ወይዘሪት ድንግል”፣ ሰለሞን ጋሻው ከ“ባጣ ቆዪኝ”፣ ሚካኤል ታምሬ ከ“ጥቁር እንግዳ” ፊልም በዕጩነት የተመረጡ ሲሆን፤ የምሽቱ ተሸላሚ መሆን የቻለው በቅድስት ይልማ የተፃፈው “ረቡኒ” ፊልም ነው።

      ከዓመቱ ምርጥ ፊቸር ፊልም ዘርፍ በዕጩነት የተመረጡት፤ ስር ሚዜዋ፣ ረቡኒ፣ ባጣ ቆዪኝ፣ ጥቁር እንግዳ እና ቀሚስ የለበስኩለት ፊልም ናቸው። በዚህም ዘርፍ በዳኞች አሸናፊ ተብሎ ሽልማቱን ያገኘው ረቡኒ ፊለም ሆኗል።

      ከምርጥ ሲኒማቶግራፊ ዘርፍ ደግሞ በዕጩነት የቀረቡት ባለሙያዎች መላኩ ክፍሌ ከ“በኩር ልጅ”፣ ብስራት ጌታቸው ከ“የመሀን ምጥ”፣ ሳሙኤል ተስፋዬ ከ“ስር ሜዜዋ” እንዲሁም ዳንኤል ኢቦንጐ ከ“ረቡኒ”፣ ሰው መሆን ይሰማውና ታሪኩ ደሳለኝ ከ“ቀሚስ የለበስኩለት” ፊልሞች ተመርጠው ነበር። የዘርፉን ሽልማት ያገኘው በ “ቀሚስ የለበሰኩበት” ፊልም ብቃታቸውን ያሳዩት ታሪኩ ደሳለኝና ሰው መሆን ይሰማው ናቸው።

      በዘንድሮው የዓመት ምርጥ የፊልም ዳይሬክተርነት ዘርፍ በዕጩነት የቀረቡት ባለሙያዎች ሳምሶን ታደሰ ጓንጉል ከ“በኩር ልጅ”፣ ሰለሞን ጋሻው ከ“ባጣ ቆዪኝ”፣ ዶ/ር መልካሙ ባዬ ከ“ሕግ በላይ”፣ ቅድስት ይልማ ከ“ረቡኒ” እና ሔኖክ አየለ ከ“ቀሚስ የለበስኩለት” ፊልሞች ሲሆኑ፤ በምሽቱ የአዘጋጅነት ዘውዱን የደፋችው ግን ቅድስት ይልማ ከ “ረቡኒ” ፊልም ሆናለች።

      በተለየ መልኩ በዚህ ዓመት ለኢትዮጵያ ፊልም ፌስቲቫል ዕጩና ተሸላሚዎች መካከል ለመጀመሪያ ጊዜ በተፈጠረው የታዳጊ ልጆች (Promising Actors) ዘርፍ ፍራኤል በዳዳ ከ“በጭስ ተደብቄ”፣ የአብስራ ግርማቸው ከ“ታሽጓል”፣ የአብስራ ተክሉ ከ“ረቡኒ” እና ህፃን ኤርሚያስ ጌታቸው ከ“ባትመጪም ቅጠሪኝ” ፊልም ባሳዩዋቸው ድንቅ ብቃቶች የተመረጡ ሲሆን፤ የመጨረሻው አሸናፊም ህፃን የአብስራ ተክሉ ከ“ረቡኒ” ፊልም ሆኗል።

      በዓመቱ ተሰርተው ለተመልካች ከቀረቡ ፊልሞች መካከል በተመልካቾች ምርጫ “ረቡኒ” ፊልም ብልጫን አግኝቶ የተሸለመ ሲሆን፤ ይህም ፊልሙ በድምሩ በስድስት ዘርፎች ተሸላሚ እንዲሆን አስችሎታል ማለት ነው። በምሽቱ በሂልተን ሆቴል በተካሄደው ፕሮግራም ላይ የህንዱ አምባሳደር ሳንጃይ ቬርማ በክብር እንግድነት ተገኝተውበታል።

      ይህ የፊልም ሽልማት ፕሮግራም በፌስቲቫልነቱ ከሚፈጥረው በጐ የሆነ የውድድር ስሜት በተጨማሪ የሌሎች አገራት የፊልም ባለሙያዎች ወቅቱን ጠብቀው ወደ እኛ በመምጣት የመታየት ዕድልን ይፈጥራል የሚለው የኢትዮጵያ ፊልም ፌስቲቫል ዳይሬክተር አቶ ይርጋሸዋ ተሾመ፤ የልምድ ልውውጡ የመማማር አቅምን ያዳብራል ብሏል።

     በዘርፉ የሚካሄዱ መሰል የሽልማት ፕሮግራሞች የራሳቸው ጠቀሜታ እንዳላቸው ሳይታለም የተፈታ እንደሆነ ቢታወቅም፤ በኢትዮጵያ ፊልም ፌስቲቫል የተሸለሙ ባለሙያዎች የሚያገኟቸው ጥቅሞች ምን ምን ናቸው የሚል ጥያቄን አንስተናል፤ አቶ ይርጋሸዋ ተሾመ ሲመለሱ፤ “የሽልማቱ ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። አንድ ባለሙያ በስራዎቹ የተሻለ ደረጃን እያሳየ በመጣ ቁጥር የመጀመሪያው ነገር ዕውቅናው ከፍ ይላል። ከዚህም ሌላ በባለሙያዎቹ ተመርጠው የተሸለሙ በመሆናቸው ለተጨማሪ ስራና የዋጋ ድርድር የተሻሉ ይሆናሉ። ይህም ከቀደመ የገበያ ዋጋቸው ሲያድግ የተመለከትንባቸው ቀደምት አጋጣሚዎች አሉ። ከሁሉም በላይ ግን ሽልማቱ በዋጋ የማይተመን ክብርን ያጎናፅፋል” ሲል ያስረዳል።

       የኢትዮጵያ ፊልም ፌስቲቫል የ9 ዓመታት ጉዞ መልካምና ፈታኝ እንደነበር በንፅፅር የሚያስቀምጠው ዳይሬክተሩ አቶ ይርጋሸዋ ተሾመ፤ እንደፈተና ከሚጠቅሳቸው መካከል የአዳራሽና ፌስቲቫሉን የማከናወኛ ቦታ ማጣት አንዱ እንደሆነ ይናገራል። አዳራሾች ከጊዜ ወደጊዜ ውድ እየሆኑ መምጣታቸው ለዝግጅታችን ፈተና ሆኗልም ይላል። ለዚህም እንደመፍትሄ፤ የሚመለከታቸው አካላት በዓመት አንድ ጊዜ በሚካሄደው ለዚህ ፕሮግራም የሚሆን ቦታ በመፍቀድ ከማሳያ ጊዜ ውጪ የሚሰራበት አዳራሽ ቢገኝ ሲሉ ይጠይቃሉ። ለበርካቶች አስደሳች ምሽትን፤ ለጥቂቶች ቁጭትና በውጤት አልባነት መከፋትን የፈጠረው የኢትዮጵያ ፊልም ፌስቲቫል የዘንድሮው ተጠናቆ የዓመቱን እየጠበቀ ይገኛል። 

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
16319 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us