“ሽልማትን አስቤ ሰርቼ አላውቅም”

Wednesday, 03 December 2014 12:51

 

 

ተዋናይት ሩታ መንግስተአብ

 

ከሳምንት በፊት ለዘጠነኛ ጊዜ በተካሄደው የኢትዮጵያ ፊልም ፌስቲቫል ላይ የዓመቱ ምርጥ ተዋናይት ተብላ የሽልማት ክብርን አግኝታለች። ይህም ብቻ አይደለም መስከረም 24 ቀን 2007 ዓ.ም በተካሄደው በሸገር ሬዲዮ የለዛ ፕሮግራም ሽልማትም እንዲሁ በምርጥ ተዋናይት ዘርፍ ከተወዳዳሪዎቿ ልቃ ሽልማት ተገኝታለች። የዛሬዋ እንግዳችን፤ ተዋናይት ሩታ መንግስተአብ።

ጥብቅ በሆነ ቤተሰብ መካከል ተገኝታ፤ በቄራ አካባቢ ተወልዳ ያደገችው ሩታ ካሜራን የመፍራቷን ያህል ዕጣ-ፈንታዋ ከካሜራ አቆራኝቷት በበርካታ ተመልካቾች ዘንድ ተወዳጅነትን አግኝታለች። እናቷ በትምህርቷ ላይ እንድታተኩር ብፈልጉም ቀልቧ ወደመራት የሞዴሊንግ ሙያ በእህቷ ድጋፍ ስለመጠጋቷ የምትናገረው ወጣቷ ተዋናይት፤ ዳሩ ግን የጀመረችውን የሞዴሊንግ ስልጠና በቅጡ እንኳን ሳትጨርሰው በማስታወቁያ ባለሙያዎችን በዘፈን ክሊፕ አቀናባሪዎች አይን ስር ወደቀች።

በማስታወቂያ ስራ የካሜራን ዓይኖች መላመድ የጀመረችው ወጣቷ፤ ወደዘፈን ክሊፖች በመሻገርም ከአቤል ሙሉጌታ እና ከቴዲዮ ጋር በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ የሆኑ ክለቦችን ሰርታለች።

“የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል” እንዲሉ፤ የወጣት ሩታን አቅም መመዘን የቻሉ አዘጋጆች ፊልም የመስራት ዕድሉን ሰጧት። ምንም እንኳን “ሀ” ብላ የጀመረችው ፊልም ለዕይታ ባይበቃም፤ የሲኒማ ስክሪኖችን ደጃፍ የረገጠችው ግን በ“ሰርፕራይዝ” ፊልም እንደሆነ ታስታውሳለች። ሲለጥቅ ግን ሩን ፍቅር በዝቶላታል፤ ይኸውም ሲባል የሰራቻቸው ፊልሞች አርዕስቶች በሙሉ በፍቅር የተነከሩ ናቸው ማለት ይቻላል። “ፍቅርና ገንዘብ”፣ “ፍቅር በአጋጣሚ”፣ “400 ፍቅር”፣ ከእነዚህ በኋላ ለተመልካች ያለደረሰውን “ፍቅርና ገንዘብ-2” ሰርታለች። ነገር ግን በስተመጨረሻ የሰራችውና በበርካቶችም ዘንድ ከታሪክ ይዙቱና ከአተዋወን አቅሟ ጋር የተወደደላትን “ረቡኒ” ፊልምን ሰርታለች።

“የመጀመሪያዎቹን ፊልሞች ሁሉ ስሰራ እችላለሁ ብዬ ሳይሆን እሞክራለሁ እያልኩ ነበር” የምትለው ሩታ፤ ከተመልካቹ ያገኘችው ምላሽና ከባለሙያዎች የሚደረግላት ድጋፍ የተሻለ ስራን መስራት እንደምትችል ያረጋገጠች ተዋናይ መሆን ችላለች። ራስን ለመጀመሪያ ጊዜ በሲኒማ አቡጀዲ ላይ ማየት የተለየ ስሜትን እንደሚፈጥር ከራሷ እንደታዘበች የምትገልፀው ሩታ፤ ስሜቱ ለበርካታ ስራዎቼ ኃይል ሆኖኛል ባይ ነች።

በበርካቶች ዓይን ስር የገባችበት “ፍቅርና ገንዘብ” የተሰኘ ፊልም ስትሰራ፤ ተመልካቹ የራሷን የግል ባህሪይ የሰራች እስኪመስለው ድረስ ቢወራረድባትም እርሷ ግን አሁንም ድረስ በፊልሞቿ ውስጥ የግል ባህሪዋ ሙሉ በሙሉ እንዳልተገለፀ አፅንኦት ሰጥታ ታስረዳለች። “ፊልም ውስጥ የተዋናዩ ህይወት ሙሉ በሙሉ ሊኖር አይችልም። በ“ፍቅር እና ገንዘብ” ፊልም ላይ ያላቸውን ገፀባህሪይ አይነት ሴት አይደለሁም። በአንፃሩ ደግሞ ብዙዎች ስለሚወዷት በ“ረቡኒ” ፊልም ውስጥ ያለችውንም “አደይ” ባህሪይ የኔ ነው ማለት አልችልም። ተመልካቹ ግን ባየውና ውስጡ ባስቀረው ገፀ-ባህሪይ ልክ ሊገምትህ ይችላል” ትላለች።

ከሰራቻቸው ፊልሞች ሁሉ የ“400 ፍቅር” ፊልም ታሪክ በእጅጉ እንደሚገርማት የምትናገረው ሩታ፤ ገና ከጅምሩ በጽሁፍ ሳየው የወደድኩት ፊልም ነው ትላለች። ስራው ተጀምሮ ከተዋናይ ግሩም ኤርሚያስ ጋር የነበራትን ጥምረት ስታስበው ደግሞ ከግሩም ኤርሚያስ ጋር አብራው እየሰራች እንኳን በአተዋወኑ በእጅጉ ትገረም እንደነበር አልሸሸገችም።

ምንም እንኳን የሰራቻቸው ፊልሞች ብዙ የሚባሉ ባይሆኑም፤ ገፀ-ባህሪይን መደጋገም ግን በፍፁም እንደማትፈልግ ትናገራለች። ዳሩ ግን የድግግሞሽ ፈተና ገጥማት እንደነበርም ታስታውሳለች። “ፍቅርና ገንዘብ የተሰኘው ፊልም ለዕይታ በቅቶ ብዙዎች ከወደዱት በኋላ ተመሳሳይ አይነት ገፀ-ባህሪያትን የያዙ ፊልሞች እንድሰራ ተጠይቄ ነበር፤ ነገር ግን አልፈለኩም” ትላለች።

በፍቅር የተሞሉ የተለያዩ ፊልሞችን በተለያዩ ገፀ-ባህሪያት ሰርታለች። በስተመጨረሻም በብዙዎች ልብ ውስጥ የዋህነቷና ታዛዥነቷ የሚታወስላትን “አደይ” በረቡኒ ፊልም ውስጥ አሳይታናለች። የረቡኒዋ “አደይ” በሬታ መንግስተአብ ዘንድ በእጅጉ የምትወደድ ናት። “እውነቱን ለመናገር አደይን የቱንም ያህል የምወዳት ገፀ-ባህሪይ ብትሆን እንኳን እርሷን የምትመስል “ካራክተር” በድጋሚ ብትመጣልኝ ግን አልሰራም” ስትል ገፀ-ባህሪይን ላለመድገም ስላላት ቁርጠኝነት ትገልፃለች።

ሩታ “ረቡኒ” ፊልም ወጥቶ ተወዳጅነቱ ከበዛና ሽልማቶች ከበረከቱለት በኋላ ይሆን “አደይ” የተባለችውን ገፀ-ባህሪይ የወደደቻት የሚል ሰው ይኖር ይሆናል። ይህ ግን ፍፁም ስህተት ነው” ትላለች፤ “ዝናው የመጣው ፊልሙ ከወጣ በኋላ ይሁን እንጂ እኔ ግን ገና የፊልም ጽሁፉን ሳነበው ነበር “አደይ” ህይወቴን የቀየረችው። ይህን ስልህ አደይ እኔን ጨምሮ ለበርካታ ሰዎች ረቡኒ (መምህር) መሆን የምትችል ገፀ-ባህሪይ ናት ብዬ አስባለሁ” ባይ ናት።

ይህንን ፊልም ተከትሎ ሽልማቶች እየበረከቱላት የምትገኘው ተዋናይት ሩታ መንግስተአብ፣ ሽልማቱ ስለፈጠረባት ስሜትና ስለጨመረባት ኃላፊነት እንዲህ ትላለች። “ሽልማትን አስቤ ሰርቼ አላውቅም። አሁን ግን የሽልማት መድረኮችን ከረገጥኩ በኋላ የተሰማኝ ስሜት የተለየ ነው። ይህም ልፋትህ በህዝብና በባለሙያ ተመርጦ ስትሸለም ደስታው ወደር የለውም። በሌላ በኩል ግን ነገ ደግሞ ምን የተሻለ ነገር ልስራ? የሚል ሀሳብ ውስጥ ትገባለህ። ምክንያቱም ከሽልማቱ ክብር ወርዶ ላለመገኘት የቤት ስራ ሆኖብኛል።”

ያም ሆኖ በቀጣይ የተሻለ ስራን ይዞ ለመምጣት ዕድልም የራሱ ድርሻ አለው ባይ ናት። የብዙ ተዋንያን ችግር ምርጥ የሚባል ታሪክ ማግኘት እንደሆነ የምታስረዳው ሩታ፤ በህይወት መንገድ ውስጥ የኑሮን ቀዳዳ ለመሸፈን ሲባል ግድ ሆኖብን የምንሰራው ፊልም ሊኖር ይችላል፤ ስትል አመክንዮዋን ታስቀምጣለች። “በምሰራቸው ፊልም ታሪኮች ላይ እንጂ በክፍያ ዋጋ ላይ ‘ይሄ ነው ዋጋዬ’ ብዬ የተከራከርኩበት ጊዜ የለም” የምትለው ሩታ፤ አሪፍ ስራን በመስራት ክፍያው ያን ያህልም ቢሆንባት እንደምትመርጥ ትናገራለች። ያም ሆኖ እስካሁን የሚያረካ ክፍያ ስለአለመፈፀሟ በማስታወስ፤ “እኔ አርኪ ክፍያዬ ሽልማቴ ነው” ባይ ናት።

የበርካታ ተዋንያን እንጀራ ማሟሻ እና የአቅም መለኪያ ተደርጐ የሚታሰበውን በመድረክ ተውኔት ላይ መታየትን እንደማትደፍረው የምትናገረው ሩታ፤ “መድረክ ያስፈራል” ስትል ትገልፀዋለች። “አመጣጤ በካሜራ በኩል ስለሆነ መድረክ ይከብደኛል” ስትል ቴአትርን መድፈር እንደማትፈልግ የገለፀች ሲሆን፤ ለአንድም ቀን ራሴን ለመድረክ ስራ አስቤው አላውቅም የምትለው ሩታ፤ ማን ያውቃል አንድ ቀን ጥሩ አዘጋጅ ካገኘሁ ይሳካልኝ ይሆናል የሚል የተስፋ ጭላንጭል እንዳላት ታወሳለች። በቀጣይ ግን የማትሰለች የቴቪ ገፀ-ባህሪን ካገኘች መስራት እንደምትፈልግ ስትናገር፤ በሬዲዮ ድራማ በኩል ግን አሁንም ድረስ ስለመስራቷ እርግጠኛ አይደለችም።

ወጣቷ ተዋናይት ሩታ መንግስተአብ ከሰራቻቸው በጣት የሚቆጠሩ ፊልሞቿ መካከል ሰርታ የተፀፀተችበት ይኖሩ ይሆን? በሚል ለቀረበላት ጥያቄ ስትመልስ፤ “በፍፁም የለም። ምክንያቱም በዚያ ሁሉ የፊልም ህይወት ውስጥ ባላልፍ ኖሮ ዛሬ እንዲህ ያገነነችኝን “አደይ”ን (የ“ረቡኒ” ፊልም ገፀ-ባህሪይ) አላገኛትም ነበር” ትላለች።

በድርጊት የተሞሉ ፊልሞችን እንደምትወድ የምትናገረው ሩታ፤ ወደፊትም ጥሩ ታሪክ ያለው በድርጊት የተሞላ (Action) ፊልም የመስራት ጉጉቱ እንዳላትና፤ ለዚህም የሆሊውዷ ተዋናይት አንጀሊና ጆሊ ተፅዕኖ ሳታሳድርባት እንዳልቀረች ትናገራለች።

ትዳር ከመሰረተች ጥር ሲመጣ ሁለተኛ ዓመቷን የምትይዘው ሩታ፤ ከወራት በፊት ናትናኤል ያሬድ የተባለ የበኩር ልጇን ተገላግላለች። እናትነት የሚሰጠው የተለየ ስሜት አለ የምትለው ሩታ፤ “አሁን ከልጄ ጋር የተለየ ፍቅር ላይ ነኝ” ብላለች።

በፊልም ስራዎቹ በትወና ያላትን አቅም ለማሳየት ቀን ከሌሊት የምትታትረው ይህቺ ወጣት ተዋናይት፤ በፊልም ጽሁፍና በዝግጅት ስራ ውስጥ ስለሚኖራት ተሳትፎ ስትመልስ፤ “ፊልም መፃፍ አልችልም፤ ምክንያቱም ደብዳቤ እንኳን ለመፃፍ የምቸገር አይነት ሰው ነኝ። ፊልም ዝግጅትን በተመለከተ ግን ወደፊት የምናየው ይሆናል። አሁን ባለው ሁኔታ ግን የእኔ ችሎታና አቅም መተወን ብቻ ነው” ትላለች።

ብዙ ጊዜዋን ፊልም በማየት እንደምትዝናና የምትናገረው ይህቺ ወጣት በማያቸው ፊልሞች ሁሉ ትምህርት እንደምወስድ አምናለሁ። ለዚህም ፊልም አልመርጥም ከስህተታቸውም ቢሆን የምማረው ነገር አለና የሚል አቋም አላት። ከዚያ በተረፈ ግን ለመዝናናት ከጓደኞቿ ጋር የምታደርገው ቆይታም ደስታን እንደሚሰጣት ትናገራለች።

ዘመኑ ካፈራቸው የፊልም ተዋንያን አንዷ የመሆኗን ያህል፤ በዘመኑ የሚሰሩ ፊልሞችን አካሄድ እንደአጀማመራቸው መልካም ናቸው ብላ የምታምን ቢሆንም፤ አሁንም ድረስ የታሪክ ድክመት መኖሩ እንደሚያሳስባት ትናገራለች።

    ከተበረከቱላት ሽልማቶች ክብርና መነቃቃትን ከኃላፊነት ጋር እንዳገኘች የምትናገረው ሩታ፤ በቅርቡ ወደፊልም ስራዋ ተመልሳ አዲስ ስራ ይዛ ለመምጣት በዝግጅት ላይ መሆኗን አስታውሳ ጠብቁኝ ትላለች። እኛም ለወጣቷ ተዋናይት ሩታ መንግስተአብ የተሳካ የስራ ጊዜ እንዲገጥማት በመመኘት ቆይታችንን እንቋጫለን።

ይምረጡ
(6 ሰዎች መርጠዋል)
12576 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us