የፍቅር “ማርትሬዛ”

Wednesday, 10 December 2014 13:18

     የፊልሙ ርዕስ            ማርትሬዛ

አቅራቢው               ታምራት ፊልም ፕሮዳክሽን

ድርሰትና ዝግጅት         ብስራት መሐመድ

ፕሮዳክሽን              ጋራድ ፊልም ፕሮዳክሽን

ተዋንያን            ታሪኩ ብርሃኑ (ባባ)፣ ሰላም ተስፋዬ፣ ቴዎድሮስ ስዩም፣ መቅደስ ትዕዛዙ፣ እስከዳር አባይ (ፒና)፣ ኤፍሬም ታደሰ እና ሌሎችም ተሳትፈውበታል።

ኤክስኪዮቲቭ ፕሮዲዩሰር    ታምራት ጳውሎስ

ስክሪፕት ሱፐርቫይዘር      ታሪኩ ብርሃኑ እና እስማኤል ሃሰን

ካሜራና ኤዲቲንግ         ዳንኤል ግርማ

ላይት                  አቤ አሰፋ

ድምፅ                 ዳምጠው ታሪኩ

የተዳፈነ ፍቅርን፣ የተወጠነ ዓላማን፣ ያልታሰበ ክስተትንና ገንዘብ ያልገዛውን እውነተኛ ማንነት የሚያሳይ ፊልም ነው፤ ማርትሬዛ። “የፍቅር ዋጋው ስንት ነው…?” ሲል የሚጠይቀው ይህ ፊልም ከአስር ዓመታት የውጪ ሀገር ቆይታ በኋላ ወደ ሀገሩ የተመለሰን ዶክተር፤ ትርምስ የበዛበት የፍቅር ታሪክና ድንገት ሳይታሰብ በፈነዳ ክስተት መካከል እውነተኛ ፍቅር እንዲሁም ገንዘብና ውለታ ካቆሙት ጓደኝነት ጋር ሲታገል ያሳየናል።

ዶክተር ሰለሞን (ታሪኩ ብርሃኑ (ባባ)) ራሱን ከጐዳና ህይወት አንስቶ በጥረቱና በዶ/ር ቤዛ (መቅደስ ትዕዛዙ) ረዳትነት የውጪ የትምህርት ዕድሉን አሳክቶ ህይወቱን መለወጥ የቻለ ሰው ነው። ያም ሆኖ በእጅጉ በግል ተፅዕኖዋ ስር የከተተችውን ዶክተር ቤዛን ተሰናብቶ ለጋራ ፕሮጀክታቸው መሳካት ከዓመታት በኋላ ወደ አገሩ፤ አዲስ አበባ ሲገባ እንመለከታለን።

እናቷን በልጅነቷ ያጣችው ሃና (ሰላም ተስፋዬ) አባቷ እናትም አባትም ሆነው ያሳደጓት ሲሆን የስዕል ችሎታዋን አዳብራ በራሷ “ስቱዲዮ” ውስጥ ዓለሟን አጥራ የምትኖር ተደርጋ ተስላለች። ስለምን የወንድ ጓደኛ አታበጂም? ወይም ጓደኛዋ በቀልድ መልክ እንዳለችው “መቼ ነው የራስሽን ሰው የምትስይው?” ለሚለው ጥያቄ የሰጠችው መልስ፤ “ሸራና ብሩሽ ሲገኝ ነው” ስትል ለፍቅር የተዘጋጀ ንፁህ ልብ እንዳላት ትናገራለች።

ዶ/ር ቤዛ (መቅደስ ትዕዛዙ) የጐዳና ተዳዳሪዎችን ለመርዳት በሚያቅደው ፕሮጀክት ውስጥ ዶ/ር ሰለሞንን ከኋላ ሆና በመደገፍና በማስተባበር ከባህር ማዶ የምትጫወት አይነት ሴት ናት። ቤዛ የዶ/ር ሰለሞን ፍቅረኛና ከወራት በኋላም የትዳር አጋር መሆኗን ለማወጅ ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት የተነሳች ቢሆንም፤ የታሰበው ቀርቶ ያልታሰበው ሲሆን “ማርትሬዛ” ያሳየናል።

ለዶ/ር ሰለሞን እንደ ጓደኛም እንደሾፌርም የሚያገለግለው ዮሐንስ (ቴዎድሮስ ስዩም) እንደ ብዙ ፊልሞቹ ሁሉ እዚህም ሣቅ ፈጣሪ ሆኗል። ከተለያዩ ሴቶችና ከባለትዳሮች ጋር ሳይቀር “መውጣት” የሚያምረው ይህ ገፀ-ባህሪ ወሲብ የሱስ ያህል የተጣባው፤ ሴት አውል ተደርጐ ተስሏል። ከሁሉም ጐልቶና አስቂኝ ትዕይንቶችን የሚያሳየው ግን ከአለቃው ሚስት ጋር በተደጋጋሚ ወስላች መሆኑ ነው።

ዶክተር ሰለሞን በጐዳና ህይወቱ መካከል የሃናን አባት አግኝቶ የኑሮው አቅጣጫ መለወጥ መጀመሩን ለጓደኛው ለዮሐንስ ሲነግረው እንሰማለን። ያም በመሆኑ አዲስ አበባ በገባ በሁለተኛው ቀን ፍለጋው “ጋሼ” ብሎ የሚጠራውን የሃናን አባትና ሃናን ያገኛቸዋል።

“ገንዘብና ውለታ ፍቅር አይሆንም” የሚለው ዶ/ር ሰለሞን፤ ከዶ/ር ቤዛ ጋር ለአስር ዓመታት ያሳለፈው ህይወት የፍቅር ጐጆውን አለመስራቱን አረጋግጧል። ለዚህም ከሃና ጋር የነበረው የእህትና ወንድምነት ግንኙነት፣ እርሷ ለእርሱ ያላት ፍቅርና እርሱ ለእርሷ እንደታናሽ እህት የሚያደርግላት እንክብካቤና ጥንቃቄ ግድቡን እንዳፈረሰ ወራጅ ውሃ ሁለቱንም ድንገት አጥለቅልቆ ሲወስዳቸው እናያለን።

“ዲያስፖራዎች ስትባሉ አገራችሁ የምትታያችሁ ለሠርግና ለለቅሶ ጊዜ ብቻ ነው እንዴ?” ሲል የሚጠይቀው ቀልድ አዋቂው ዮሐንስ፤ ዶክተር ቤዛ ጋብቻዋን በኢትዮጵያ ከፈፀመች በኋላ ተመልሳ ወደ ውጪ ሀገር የመሄድ ጽኑ ፍላጐት እንዳላትና እዚህ (ኢትዮጵያ ውስጥ) የመኖር ምንም ሀሳብ እንደሌላት ስትናገር፤ ሀሳቧ ግር የሚለው ዶ/ር ሰለሞንን እናየዋለን።

ውሎ ሲያድር ፍቅር ከመሰለው የዶ/ር ቤዛ እስር እየላላ የመጣው ዶ/ር ሰለሞን፤ በአለባበስም ሆነ በአስተሳሰቧ ነፃነት እየተማረከባት በመጣችውና የታናሽ እህቱ ያክል ከሚሳሳላት ሃና ጋር በፍቅር ይወድቃል። ይህ ፍቅራቸውም የቀድሞ ወዳጁን ዶ/ር ቤዛን ብቻ ሳይሆን ዱብ-ዕዳ ለሆነባቸው የሃና አባትም ክፉኛ ሐዘን ሲፈጥር እንመለከታለን።  

በአዲሱ ፍቅርና በከረመው ፍቅር መካከል ሲዋልል፣ ሲደሰትና ሲፀፀት የምናየው ዶ/ር ሰለሞን፤ የመጣበት ፕሮጀክት ሰዎች ሁሉ ገንዘብ ላይ የሚያተኩሩና ከመንስኤው ይልቅ ውጤቱ ላይ ብቻ አተኩረው መስራታቸው የሚያስጨንቀው ሆኖ፤ ውጤቱን የተሻለ ለማድረግ ሲለፋ “ማርትሬዛ” ያሳዩናል።

“ለነገሮች ሁሉ ከውጤቱ ይልቅ ለመፍትሄው የሚረዳን መንስኤው ነው” ሲል የሚሞግተው ዶክተሩ፤ ፕሮጀክቱን በራሱ መንገድ ሲያሳካ የፍቅር ህይወቱ ግን ግራና ቀኝ የሚያመሳቅለው ሆኖ እናየዋለን። መጨረሻውን ለናንተ እተወዋለሁ።

ፊልሙ አዝናኝ ታሪክን በተዋዛና በቀላል መንገድ መናገር ችሏል፤ ያም ሆኖ “ማርትሬዛ” የራሱ ጥቃቅን ስህተቶች አላጣውም። ከእነዚህ ግር የሚያሰኙ ተጠቃሽ ክስተቶች መካከል አንደኛው ለአስር ዓመታት ውጪ ሀገር ቆይቶ የእነሃናን ቤተሰብ የተቀላቀለው ዶክተሩ በዛ መልኩ ወዲያው መዋሃድ መቻሉ ጥቂትም እንኳን ቢሆን ደንቀፍ የሚያደርግ የፀባይ ለውጥ እንዴት አላሳየም የሚያሰኝ ነው። ሁለተኛውና በጉልህ የሚነሳው ግን ዶክተሩ የመማሩንና የመብሰሉን ያህል አልፎ አልፎ ለነገሮች የሚሰጠው ስሜታዊ ምላሾች ከእርሱ የሚጠበቁ አይደሉም።

በተረፈ ግን “ማርትሬዛ” በቀላል እንደማይገኝ ጽኑ እና የከረመ ፍቅር በውለታና በገንዘብ ሳይሸነፍ በሦስት ወር ውስጥ ሲመነዘር የ1፡40 ደቂቃ ፊልም ነው።    

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
16441 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us