“ደማም አርቲስት ነኝ”

Wednesday, 17 December 2014 11:33

አርቲስት አስረስ በቀለ

 

ብዙዎች በቀድሞው ኢቲቪ የልጆች ክፍለ ጊዜ ሥራዎቹ፤ በተለይም በቼሪ ያስታውሱታል። ከሰራቸው የቲቪ ድራማዎች መካከል ግቢው፣ ቃልቻው ዝቄ፣ አሞራው፣ የአቶ በላቸው ጫማ እና ሶስቱ ወፎች የሚጠቀስለት ሲሆን ከነዚህም ውስጥ በፅሁፍ በትወናና በዝግጅት የሠራቸው ይገኙበታል። በፊልም የጎላ ተሳትፎ ባይኖረውም በይፈለጋል እና በሰማያዊ ፈረስ ላይ ብቅ ብሏል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከጥቂት ማስታወቂያዎች ጋር እያየነው ያለ ኮሜዲያን፣ ደራሲ፣ አዘጋጅ ነው። ከዓመት በፊት “ቶላ አባ ፈርዳ” በእንግሊዝኛና በአማርኛ የፃፋቸው መፅሐፍት አሳትሞ ለንባብ ያበቃ ሲሆን፤ በያዝነው ሳምንት ደግሞ እንዲሁ ለልጆች የሚሆኑ “ማሪቱና ኤሊዋ” እና “አቶ ጥጋቤና የታፈሰ ዳንሰኛ ዶሮዎች” የተሰኙ የተረት መፅሐፍትን እነሆ ብሏል። ከጠፋው አርቲስት፤ ኮሜዲያን፣ ፀሐፊና አዘጋጅ አስረስ በቀለ ጋር የሚከተለውን ቆይታ አድርገናል።

ሰንደቅ፡- ከመጨረሻው ለመጀመር ያህል አስረስ አሁን በምን ሁኔታ ላይ ነው ያለኸው?

አስረስ፡-አሁን ያለሁት እንደበፊቱ ነው። በርግጥ ቋሚ ስራ የለኝም። በተረፈ ግን የተለያዩ ፅሁፎችን በመፃፍ ነው እየተዳደርኩ ያለሁት። ሌላው ህይወት ከቤተሰብና ከልጆች ጋር ደስ ብሎኝ እየኖርኩ ነው። በተረፈ ስለራሴ ለመናገር ሚዲያ ብዙም አልፈልግም። ዛሬም አንተን ያገኘውኸ ገፍተህ ስለመጣህብኝ ነው።

ሰንደቅ፡- አንተ ባለብዙ ዘርፍ ሙያተኛ ነህ፤ ከስምህ በፊት ኮሜዲያን፣ ተዋናይ፣ ፀሐፊ ወይም አርቲስት ከሚለው የቱ ይመችሃል?

አስረስ፡-ጥሩ ጥያቄ ነው፤ እኔ ለራሴ ደማም አርቲስት ነኝ ብዬ ነው የማምነው። ባይገርምህ ሰው ራሱ አይቼ ገና ትልቅ አርቲስት እንደሚሆን ለይቼ አውቃለሁ። አሁን ለምሳሌ ሸዋፈራሁ፣ ፍልፍሉ፣ ማህደር፣ ቴዎድሮስ፣ ራሱ ሰይፉ ፋንታሁንን ገና ከመጀመሪያው “ታለንታቸውን” ገና ከጅምራቸው አይቼ ትልቅ ቦታ እንደሚደርሱ ተስፋ የሰጠኋቸው ሰዎች ናቸው። ከዘፋኞች ምናሉሽ ረታ፣ ነፃነትን እኔ ነኝ አይዟችሁ ያልኳቸው።

ሰንደቅ፡- ኮሜዲ ድሮና ዘንድሮ ላንተ የሚሰጥህ የተለየ ነገር አለ?

አስረስ፡-እውነቱን ለመናገር ኮሜዲ በኛ ጊዜ እንዲህ ነበር፤ አሁን ደግሞ እንዲህ ነው ብዬ ፍርድ መስጠት አልፈልግም፤ አልችልምም። ነገር ግን እኔ ከሌሎቹ የምለይበት ብቃት አለኝ ለማለት እደፍራለሁ። ይህን ስልህ ከሌሎቹ በተለየ በስራዎቼ ውስጥ ከበድ ያሉ አይነኬ ርዕሰ- ጉዳዮችን በማንሳት ማሳየት እወዳለሁ።

ሰንደቅ፡- በድፍረት ከሰራሃቸው የተለያዩ ስራዎች መካከል የቱን ስራ ታስታውሰኛለህ?

አስረስ፡-ለምሳሌ “ቃልቻው ዝቄ” በሃይማኖት ረገድ ከባድ ነበር። እኔ ኦርቶዶክስ ነኝ፤ ግን የማይሆን ትምህርት የሚያስተምሩ ሰዎችን ሳይ እናደድ ስለነበር ያንን ነገር በኮሜዲ ለመተቸት አስቤ የሰራሁት ስራ ነው። ባይገርምህ ይህ ኮሜዲ ስራ ከታየ በኋላ ጦር ይዘው ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ድረስ የመጡ ሰዎች ነበሩ። አሁን ግን የማስተማሪያ ቴክኒኩ ተቀይሮ አሁን የምታያቸው ወጣቶች ሁሉ መጥተዋል። ያኔ እኔ ከሰራሁ በኋላ እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎች የሉም እየተባለ ስወቀስ ወዲያው ግን አንድ ክስተት ተከስቶ እውነትነቱ ተረጋግጦ ነው የተረጋጋሁት። ከዚያ ሌላ በጎዳና ተዳዳሪዎችን ህይወት ለማሻሻል ሲባል የተሰራውን ስራ ድርሰት ፅፌ፣ ተውኜ አዘጋጅቼ በአጠቃይ 600 ብር ነው የተከፈለኝ። ርዕሱ “አሞራው” ይሰኛል። ይህም ስራዬ አሁን ድረስ የማልረሳው ነው። እንደውም ሙሉ ታሪኩን ፅፌው አለ፤ አንድ ቀን መስራቴ አይቀርም።

ሰንደቅ፡- ከድሮ ኢቲቪ የልጆች ጊዜ ፕሮግራም ዝግጅት ክፍል የተባረራችሁበትን ሁኔታ እንዴት ነው የምታስታውሰው?

አስረስ፡-ምን መሰለህ፤ የአባባ ተስፋዬን እንተወውና የኔን ልንገርህ፤ ወቅቱ 1997 ዓ.ም ነበር። ያኔ ደቡብ ወሎ ሄጄ አንድ የህጻናት ፕሮግራም እየሰራሁ ነበር። ታዲያ ያኔ ልጆቹ የሚዘምሩት መዝሙር “ቅንጅት ወደቀ ፍርክስክሱ ወጣ፣ እንግዲህ ያገር ልጅ ምናምን ተመጣ” የሚል አይነት ነበር። ይህ መዝሙር ከቼሪ ጋር በእስክስታ ተሰራ፤ ያ ደግሞ ስነ-ምግባሩ አይፈቅድም። ልጆች በፖለቲካ ውስጥ መግባት የለባቸውም ይባላል። ከዚያ በወቅቱ ኃላፊ የነበረው ሰይፉ ስዩም የተባለ ሰውዬ ይህ ነገር ተቆርጦ ሳይወጣ ፕሮግራሙ መተላለፍ አለበት አለ። እኔ ደግሞ ፈፅሞ አይተላለፍም አልኩ። ጀርባህ መጠናት አለበት ተብዬ ለሶስት ወራት ታግጄ ቆየሁ፤ ከዚያም ደጅ መጥናቱ ሲሰለቸኝ በዛው ቀረሁ ማለት ነው።

ሰንደቅ፡- በልጆች ክፍለ ጊዜ ወቅት የማትረሳው ክስተት ምንድነው?

አስረስ፡-ምንጊዜም የማልረሳው ነገር ቢኖር ለልጆች ክፍለ ጊዜ ቼሪን ለመቅረፅ ስቱዲዮ ውስጥ ያለው ወከባና ፍቅር በተለይ የካሜራ ባለሙያዎቹ አይረሱኝም። በዛ ላይ 60/70 ህጻናት ስቱዲዮ ይመጣሉ። ብዛታቸው እኮ ትርምስምስ ነበር፤ ሀገር ውስጥ ገቢ እንኳን እንደኔ ብዙ እንግዳ አላስተናገድም (ሳቅ). . . ልጆችን አሳምኖ ለመስራት በጣም ብዙ ስቃይ ነበረው። ግን በፍቅር የሰራሁት በመሆኑ በጣም ደስተኛ ነኝ። ባይገርምህ ክፍያው እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም። 200 ብር ለመቀበል ብዙ ጣጣ ነበረው። አንዳንዴ እንደውም 60 እና 70 ህፃናት መጥተው ቀረፃ ዘግይቶ ይርባቸዋል። ለልጆቹ ምሪንዳና ዳቦ የምገዛው እኔ ነበርኩ። ከገንዘብ አንፃር ብጎዳም ግን በልጆቹ ፍቅር በጣም ደስተኛ ነበርኩ።

ሰንደቅ፡- ቼሪን በተመለከተ የተሰጠህ ለየት ያለአስተያየት ይኖራል?

አስረስ፡-ባይገርምህ አንዳንድ ሰዎች ቼሪን ሆኜ በመስራቴ ልጆቻችንን አታለልክ እንጂ አጫወትክ ብለው አያመሰግኑኝም። ስለቼሪ በጣም ያስደሰተኝ አነጋገር ግን ጎንደር ላይ ሰውዬው ሽማግሌ ናቸው፤ በልጆች ፕሮግራም ቼሪ ስትተላለፍ እያዩ “እንዴት ያለች ልበ ሙሉ አውሬ ናት!” ብለው አሞግሷት (ሳቅ) በጣም ነበር ሰውዬው ያስደሰቱኝ። ነገር ግን እኔ መሆኔን አላወቁም።

ሰንደቅ፡- በአሁኑ ወቅት ለልጆች የሚሆን ምን እየሰራህ ነው?

አስረስ፡-የልጆችን መልካም ሥነ-ምግባር በተረትና በንግግር ለመቅረፅ ዋናው መሣሪያ አርቲስቱ ጋር እና መገናኛ ብዙሃን ጋር እንዳለ አምናለሁ። ከዚያ በተጨማሪ የስነ-ዜጋ ትምህርት ወሳኝ ነው። ነገር ግን እኔ አሁን ሁለት መፅሐፍትን ለልጆች ፅፌያለሁ ይሄን ለልጆቹ የሚያደርስ ትምህርት ቤትና ወላጅ በብዛት የለም፤ ምንም የሚያበረታታ ነገር የለም። ያም ሆኖ አሁንም ተስፋ፣ ሳልቆርጥ ለልጆች ስነምግባር የሚረዱ መፅሐፍትን አዘጋጅቻለሁ።

እውነቱን ለመናገር ራሱ ትምህርት ሚስቴር መፅሐፍቱን ገምግሞ በመግዛት በየትምህርት ቤቱ እንዲደርሱ ማድረግ አለበት። ይህን የምለው እኔን እንዲያበለፅገኝ አይደለም። ለልጆቹ ዕድገት ነው። በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ ለልጆቹ እየደረሱ ያሉት ተረቶች የውጪ ታሪኮች ናቸው። ያ ደግሞ ቋንቋ ከማሻሻል በስተቀር ባህላቸውና ትውፊታቸውን እንዲያውቁ አያደርጋቸውም። በመሆኑም የሀገር ውስጥ መፅሐፍት በተለይ ለልጆች የሚሆኑት በትኩረት ሊሰራባቸው ይገባል።

ሰንደቅ፡- በአሁኑ ወቅት በርካታ ፊልሞች እየተሰሩ ነው። ያንተ ተሳትፎ ግን በጣም ቀንሷል፤ ለምንድነው?

አስረስ፡-አላውቅም። እኔ የማውቀው በደንብ መተወን እንደምችል ብቻ ነው። ይሄን ማንም ሊመሰክር ይችላል። እንግዲህ አሁን ያሉት ባለሙያዎች አላዩኝ ይሆናል። ባይገርምህ በቅርቡ መምህሬ የነበረው ተስፋዬ ሲማ “እኔ ያንተ መጥፋት ብቻ ነው የሚያሳስበኝ” ብሎኛል። ያም ሆነ በፊልሙ ብጠፋም ከዚህ ቀደም ሁለት የህጻናት መፅሐፍትን ፅፌ መጥቻለሁ፤ አሁን በዚህ ሳምንት ደግሞ ሁለት የህፃናት መፅሐፍትን ለማስመረቅ በዝግጅት ላይ ነኝ። የመፅሐፎቹ ርዕስ “ማሪቱና ኤሊዋ” እና አቶ ጥጋቤና የታፈሰ ዳንሰኛ ዶሮዎ” ናቸው። በዚህ አጋጣሚ መፅሐፉን ለማሳተም የረዱን አቶ ከተማ ከበደን በጣም አመሰግናለሁ። በተረፈ ግን የረሴ የፊልምና ድራማ ፅሁፎችም አሉኝ። ግን ሰው መለማመጥ ስለማልችልበት ቁጨ ብለዋል። እኔ ሰርቼ ያሳፈርኩት ሰው ያለ አይመስለኝም።

ሰንደቅ፡- እስቲ ደግሞ ትንሽ ስለጦሩ ቤት አጫውተኝ፤ በነገራችን ላይ ሠራዊት ፍቅሬንም የተዋወከው እዚያ ነው አይደል?

አስረስ፡-ሠራዊትን ቀደም ብዬም አውቀው ነበር። ነገር ግን ጦላይ ጦር ማሰልጠኛ ተመዝግበን ስንማር በርሄ ስዩም የተባለ መምህር ተመደበልን። ባይገርምህ ጥሩ ወታደር ነበርኩ፤ ነገር ግን ፀበኛ ሰው ነበርኩ። ለምን እንደምጣላ ራሱ ከተጣላው በኋላ ነው የማውቀው (ሳቅ)። ወደኪነጥበቡ የገባሁት በአጋጣሚ የብርጌዶች ውድድር በኪነ-ጥበብ ተካሄደ። ሰፈር ውስጥ የምቀላልዳት ነገር፤ ድምፄን የምቀያይራት ነገር ውጤት አመጣች። ሚያዚያ 3 ቀን 1977 ዓ.ም የወዛደሮች በዓል ነበር፤ አንዲት አጭር ድራማ ሰራሁ። ከእኛ ብርጌድ ውስጥ እኔና አብርሃም የሚባል የትግራይ ልጅ ማሲንቆ ነበር የሚጫወተው አለፍን። እነሠራዊትና ሌሎቹ ከስድስተኛ ብርጌድ ነው ያለፉት። የኪነት ስልጠና ተሰጠን። ከዚያ ሁሉ ሰው በኋላ ላይ አስራ አንድ ሰዎች ቀረን። ከዚያ አንድ ሰው ይቀነስ ተብሎ ዕጣ ሲወጣ እኔ ላይ ደረሰ። ተቀንሼ የጦር መሃንዲሶችን ተቀላቀልኩ። ነገር ግን ብዙ ጓደኞቼ ቅር ብሏቸው ነበር። በኋላ ላይ ወደአዲስ አበባ ስመለስ መምህር ተስፋዬ ሲማ የቴአትር ስልጠና ሲሰጥ ደረስኩ፤ ያኔ ተማሪዎቹ ጓደኞቼ እነህይወት አራጌ፣ ጥላሁን ዘውገ፣ አለልኝ መኳንንት ፅጌና ፈለቀ አበበን ጨምሮ ብዙ ተማሪዎች የነበሩበት ጊዜ ነው። ስልጠናውን ወስጄ ጠቅልዬ ወደ ኪነጥበብ ሙያ ገባሁ ማለት ነው።

ሰንደቅ፡- በምንድነው የምትዝናናው?

አስረስ፡-አንደኛ ተፈጥሮ ያዝናናኛል። ብዙ ጊዜ ወደገጠር በመሄድ ከማያውቁኝ ሰዎች ጋር መጨዋወት ያዝናናኛል። ባይገርምህ ትንሽ ብር ካለኝ ስጋ ገዥቼ ጠላና አረቄም ቢሆን ይዤ ገጠር እገባና ከሰዎች ጋር አወራለሁ። አንዳንዶቹ በጣም ይገርማቸዋል። እንደውም “ቶላ” ብለው ስም አውጥተውልኛል፤ ተፍኪ አካባቢ የሚያውቁኝ። ለዛም ነው “ቶላ አባ ፈርዳ” የተሰኘ መፅሐፍ የፃፍኩት። የገበሬዎች ስራ በጣም ያስደስተኛል። ባለፈው እንደውም የሆኑ ገበሬዎች ዝናብ መጣብን ብለው ሲጨነቁ አብሬያቸው ተጨንቄ፤ ሲያጭዱም ለማጨድ ሞክሬ ሁሉ እንደነበር አስታውሳለሁ።

ሰንደቅ፡- ወደፊት ከእነማን ጋር መስራትን ትመኛለሁ?

አስረስ፡-ከጀግና ጋር መስራት ደስ ይለኛል። ጀግና ስልህ ያልተደፈረ ሃሳብ የሚደፍር፤ አዲስና የተለየ ነገር ለመስራት የሚፈልግ ሰው ቢያጋጥመኝ አብሬው ብሰራ በጣም ደስ ይለኛል።

ሰንደቅ፡- ከኮሜዲ ውጪ ብሰራ አሳምናለሁ የሚል እምነት አለህ?

አስረስ፡-አዎ፤ እችላለሁ። “ሶስቱ ወፎች” በተሰኘው ድራማ ላይ ኮስታራ ፖሊስ ሆኜ ነው የሰራሁት። ሰዎች ባልጠበቁኝ መንገድ ነው የሰራሁት፤ ብዙዎች ደስ ብሏቸዋል። በነገራችን ላይ ያንን ፖሊስ እንዴት እንደመረጥኩት ልንገርህ። እኛ ሀገር ሰው ሁሉ ፖሊስ ትክክል ነው ብሎ ያምናል። እንደሰው የሚሳሳት አይመስላቸውም፤ ፖሊስም እንደሚሳሳትና እንደሚሸወድ ነው በድራማው ያሳየነው። ታዲያ ያንን ድራማ ያዩ ፖሊሶች “አሳቅክብን” ያሉኝ አሉ፤ እኔ ግን ደስ ብሎኛል።

ሰንደቅ፡- ከዚህ በኋላ በፊልም እንጠብቅህ?

አስረስ፡-አንድ ነገር ልንገርህ፤ ከዚህ በኋላ እኔ በጣም ቆንጆ ታሪክ ያለው ፊልም ካልሆነ አልሰራም። ታዋቂነትን አውቄዋለሁ፤ ገንዘብንም አይቼዋለሁ፤ ጓደኝነትንም አይቼዋለሁ። ብዙ ነገር ያየሁ በመሆኑ ያን ያህል የሚያጓጓኝ ነገር የለም። መስራት ግን እንደምችል አውቃለሁ። ስራ ከሆነ አሪፍ ስራ ከአሪፍ ባለሙያዎች ጋር መስራት እንጂ መርመጥመጥ አልፈልግም። ይህ ማለት ሰዎች ጭንቅላት ውስጥ የማይገባ ስራ መስራት አልፈልግም።

ሰንደቅ፡- የምር ጓደኞዬ ነው፤ ወዳጄ ነው የምትለው ማነው?

አስረስ፡-እግዚያብሔር!

ሰንደቅ፡- ከጓደኞችህና ከአብሮ አደጎችህ በተለየ የምትጠራው ሰው የለም?

አስረስ፡-እንግዲህ ጓደኝነት ሂደት ነው። እኔ የምታወቀው ሰው በመውደድ ነው። ሰው ወደደኝ፣ አልወደደኝ አያስጨንቀኝም። ግን ለጥያቄህ መልስ እንዲሆን በተለይ የምወደው ጓደኛዬ አማን ሙሉጌታ ይባላል። በተረፈ ግን ደስታ ገ/ስላሴ፣ ሠራዊት ፍቅሬ፣ ኪያ ስዩም፣ ብዙአየሁ ይርጋ፣ ዳንኤል ደምሴ፣ ሻለቃ ተገኝ መከተ እና መልካምዘር ስመወርቅ በጣም የምወዳቸው ጓደኞቼ ናቸው። በስራ በኩል ግን ሁሌም የማማክረውና የምወደው ወዳጄ ደረጄ ሃይሌ ነው፤ ብዙ ጊዜ የማገኘውም እርሱን ነው።

ሰንደቅ፡- በመጨረሻ ልታመሰግናቸው የምትፈልጋቸው ሰዎች ካሉ እድሉን ልስጥህ?

    አስረስ፡-የፃፍኩትን መፅሐፍ እንዳሳትም የረዱኝን አቶ ከተማ ከበደን ሻማ ቡክስን እና ስፓት ላይት የትምህርት ማበልጸጊያ ድርጅትን በጣም አመሰግናለሁ። በተረፈ ግን ከልጅነት እስከ እውቀት አብረውኝ የነበሩትን ጓደኞቼንና አይዞህ ባዮቼን ሁሉ በጣም አመሰግናለሁ። በመጨረሻም ወላጆች ለልጆቻቸው “ማሪቱና ኤሊዋ” እና “አቶ ጥጋቤና የታፈሰ ዳንሰኛ ዶሮዎች” የተሰኙትን መፅሐፍት ገዝተው እንዲያነቡላቸው እጋብዛለሁ። እናንተንም በጣም አመሰግናለሁ።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
11265 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us