“የክፉ ቀን ደራሿ” አርቲስት

Thursday, 25 December 2014 10:39

አርቲስት ፍሬህይወት ባህሩ  

በአሁኑ ወቅት በጣት ከሚቆጠሩትና በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ከሚገኙት አንጋፋ ተዋንያን መካከል አንዷ ናት፤ አርቲስት ፍሬህይወት ባህሩ። በ1969 ዓ.ም “ሀ” ብላ ሀገር ፍቅርን ተቀላቀለች። ፍሬሕይወት ከሰራቻቸው የመድረክ ሥራዎች ውስጥ ጉድ ፈላ፣ ቀዩ ማጭድ፣ ታጋይ ሲፋለም፣ የቀለጠው መንደር፣ ረመጥ እና ፎርፌ ጥቂቶቹ ሲሆኑ፤ በፊልም ደግሞ ትውልድ፣ ጉራማይሌ፣ መፈንቅለ ሴቶች፣ አየሁሽ፣ ወራሽና ድባቡ ይጠቀስላታል። ይህም ብቻ ሳይሆን በበርካታ የሬዲዮና የቲቪ ድራማዎቿ ትታወቃለች፡፡ ከአንጋፋዋ አርቲስት ፍሬሕይወት ባህሩ ጋር ያደረግነውን አዝናኝ ቆይታ እነሆ፡-

ሰንደቅ፡- ወደሀገር ፍቅር እንዴት መጣሽ ከሚለው ብንጀመርስ?

ፍሬህይወት፡- ከትምህርት ቤት በቀጥታ ነው ወደሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት የመጣሁት። በአርበኞች ትምህርት ቤት በስካውት አባልነቴና በሩጫ እታወቅ ነበር። በኋላ ላይ ሀገር ፍቅር ማስታወቂያ ወጥቷል ሲባል ከሰፈር ልጆች ጋር ሄጄ ተመዘገብኩ። ባይገርምህ የተመዝጋቢው ቁጥር ከ500 በላይ የነበረ ቢሆንም ከዚያ መካከል በፈተና ተጣርተን ያለፍነው ግን ወንድ ስምንት፤ ሴት ስምንት በአጠቃላይ 16 ልጆች ነበርን። ያኔ ታዲያ ሁለገብ መሆን አለብህ። ድምፅ ትጫወታለህ፣ ውዝዋዜ ትሰራለህ፤ ትተውናለህ፤ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም መድረክ አስተዋዋቂም ትሆናለህ። እኔ ለብዙ ዓመታት ውዝዋዜውንና ቴአትሩን በጥምረት ስስራ ቆይቼ፣ ከ15 ዓመታት ወዲህ ግን ሙሉ በሙሉ ወደቴአትር ክፍል ተዛውሬ እየሰራሁ እገኛለሁ።

ሰንደቅ፡- ፍሬሕይወት በተለየ መልኩ የምትታወቂው ብዙ አርቲስቶችን ተክተሽ ሳትቸገሪ በመስራትሽ ይመስለኛል። ለመሆኑ ምን ያህል ሥራዎችን ተተክተሸ ሰርተሻል?

ፍሬህይወት፡- ከማስታውሳቸው መካከል ለምሳሌ “ጉድ ፈላ” የተሰኘ ቴአትር ላይ አንዲት “አክተር” ቀርታ ድንገት ተጠርቼ ወጥቼ በደንብ ሰርቻለሁ። “ቀዩ ማጭድ” ቴአትር ላይ ደግሞ አሰለፈች አሽኔ ነበረች የምትሰራው፣ የገበሬ ሚስት ሆና በኋላ ታማ ሆስፒታል ስትገባ እኔ እንድሰራው ተደርጓል። ሦስተኛው “ታጋይ ሲፋለም” የተሰኘ ቴአትር ነው። ይህ ቴአትር የሶማሌን ጦርነት የሚያሳይ፣ ቶክስ እና መገለባበጥ ያለበት ቴአትር ነበር። ይህም ቴአትር የአሰለፈች አሽኔ ነበር በይ እንደጀመርሽው አንቺው ተወጪው ተብዬ ገብቼ ሠርቻለሁ። ሌላው በብዙዎች ዘንድ የሚታውቀው ሙናዬ መንበሩን የተካውበት “የቀለጠው መንደር” ቴአትር ነው። ባይገርምህ ሙናዬ ጓደኛዬም ስለነበረች አብራኝ ነው ብዙ ጊዜ የምትሆነው። በዚህ ምክንያት ቃለ-ተውኔቷን በደንብ አውቀዋለሁ። በዚህ ስራ መድረክ ላይ አብረን ነበርን። ያን ጊዜ ሥራ አስኪያጇ ደውላ “ዛሬ የሙናዬን ቦታ ተክተሸ የምትሰሪው አንቺ ነሽ” ስትለኝ እኔ ሙናዬ ታማ አጠገቧ ነበርኩ።

ሰንደቅ፡- ቃለ-ተውኔት ለመያዝ አትቸገሪም ማለት ነው?

ፍሬህይወት፡- ይመስገነው ያኔ ወጣት እና ለስራው በጣም ፍቅሩ ስላለኝ ነው መሰለኝ ተቸግሬ አላውቅም። ሁሉንም ተክቼ ስሰራ አሪፍ ነበርኩ፤ ብዙዎች እንደውም “የክፉ ቀን ደራሽ” ነው የሚሉኝ (ሳቅ) . . . በተለይ ግን “የቀለጠው መንደር” ሲሰራ እኔና ሙናዬ በመድረክ ላይ የምንሰዳደበው ነገር ብዙ ስለነበር እርስ በእርስ እንተዋወቅ ነበር። በቴአትሩ ላይ ጥናቱ የተወሰነ ሆኖ ድንገቴ ፈጠራ ይበዛው ስለነበር ድንገት መንገድ ላይ ሰዎች ተጣልተው ሲሰዳደቡ ሳይ ማስታወሻ እይዛለሁ፤ ሙናዬም እንደዚሁ ታደርግ ነበር። በኋላ መድረክ ላይ ስንገናኝ በነገር መጠዛጠዝ ነው። (ሳቅ) በመሆኑም የቀለጠው መንደር ብዙም አልከበደኝም። ነገር ግን በሳምንቱ ሙናዬ አረፈች። ያኔ እኔ መሆኔ ታወቀ ማለት ነው፤ ተመልካቹ ቢያዝንም በስራዬ ተደስቶ ነበር።

ሰንደቅ፡- ብዙዎች በስራዎችሽ ቢያውቁሽም ለጥሪ ጊዜ ኮሚዲያን ናት ይላሉ፤ በዚህ ትስማሚያለሽ?

ፍሬህይወት፡- ለብዙዎች እምታታባቸዋለሁ። አብዛኞቹ የምሰራቸው ስራዎች የሚያስቁ ስለሆኑ ኮሜዲያን የሚሉኝ አሉ። ነገር ግን ሁለገብ አርቲስት ነኝ ብዬ ነው ራሴን የምገልጸው። ለምን ቢባል የሰጡንን መስራት እችላለሁ።

ሰንደቅ፡- ብዙ ኮሜዲያን ከሰሯቸው ስራዎች በላይ በቅርቡ በተለቀቀው የ8100 ማስታወቂያ ተወደዋል። እስቲ እሱ ማስታወቂያ እንዴት እንደተሰራ ንገሪኝ አንቺስ እንዴት ተሳተፍሽ?

ፍሬህይወት፡- የሚገርም ነገር ነው፤ እኔ ከማርቆስ ኤሊያስ ጋር “ቆራሌው” የሚለውን ዘፈኑን ክሊፕ ለመስራት ነበር የሄድኩት። ያንን ስሰራ “ካሜራማኑ” ያን ዕለት አየኝና “አንድ የምንሠራው ስራ አለ ትረጂኛለሽ” አለኝ። እሽ ብዬ በተዘጋጀ ስራ መሀል ልክክ አልኩልህ እልሃለሁ። አሁን ካሉ ማስታወቂያዎች እንግዲህ በትንሹ በትልቁ ሰው ሁሉ ተወዳጅ ስራ ይመስለኛል። ባይገርም እኛም ደስ ብሎን የሰራነው ማስታወቂያ ነው። በተለይ እኔ መጨረሻ ላይ በስሜት ሆኜ “8100” እልኩ ብቻዬን የደነስኩበትን ጊዜ አስታውሰዋለሁ (ሳቅ) የተሳካ ማስታወቂያ በመሆኑ አንድነት ለአሪፍ ስራ ወሳኝ መሆኑን አሳይቶኛል።

ሰንደቅ፡- እስካሁን በስራሽ የፈተነሽ ገፀ-ባህሪይ አጋጥሞሽ ያውቃል?

ፍሬህይወት፡- እስካሁን ምንም አልገጠመንም። እኔ ፊልምም ድራማም ሆነ ቴአትር ሲሰጠኝ እምሽክ አድርጌ ነው የማጠናው። አሁን ለምሳሌ ፊልም ስንሰራ ዛሬ አንዱን ትዕይንት ነገ ደግሞ ሌላውን እየተባለ ነው የሚጠናው፤ እኔ ግን ሁሉንም አንዴ ነው አጠናቅቄ የምመጣው። ከዚያ በኋላ ፅሁፉ ከኔ ጋር አይገናኝም። ባይገርም 100 ምናምን ገፅ በ15 ቀን ውስጥ በቃሌ እይዛለሁ።

ሰንደቅ፡- ሰዎችን በስራዎችሽ እንደምታዝናኚ ሁሉ አንቺንስ ምን ያዝናናሻል?

ፍሬህይወት፡- ሰው ሲደሰት በጣም ያዝናናኛል። ለሰዎች በማድረግና ባደረኩላቸውም ነገር ሲደሰቱ ማየት በጣም ነው የሚያዝናናኝ። አሁን ለምሳሌ አዳማ ላይ ወጣት የፊልም ሰሪዎች አግኝተውኝ እንደሚያደንቁኝ ነግረውኝ፤ ፊልም ለመስራት እንደሚፈልጉ ሲያማክሩኝ እኔ በሂሳብ አልተደራደርኩም አብሬያቸው በመስራት እንደማግዛቸው ስነግራቸው በጣም ነበር የተደሰቱት ያ ነገር እኔንም ያስደስተኛል።

ሰንደቅ፡- ብዙ ሰዎች ለገንዘብ ድርድር ትኩረት እንደማትሰጪ ይናገራሉ። ታሪክ መረጣ ላይስ እንዴት ነሽ?

ፍሬህይወት፡- ከታሪክ ይልቅ ለኔ የሚመቸኝን “ካራክተር” (ገፀ-ባህሪይ) ነው የምምርጠው። አሁን ለምሳሌ ረጋ ብላ፣ ድክም ብላ የምትሳል ገፀባህሪይ አትሆነኝም። ነገር ግን ግዴታዬ ከሆነ እየታሸውም ቢሆን እሰራለሁ። ምረጪ ከተባልኩ ግን ቀልቃላና ፈጣን ሴት ባገኝ ደስ ይለኛል። (ሳቅ)

ሰንደቅ፡- እስቲ ስለቤተሰብ ሁኔታ አጫወቺኝ?

ፍሬህይወት፡- ሁለት ልጆች አሉኝ። ባለቤቴ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየ ሰባት ዓመት ሆኖታል። ነፍሱን ይማረውና ሀገር ፍቅር እኩል ነበር የተቀጠርነው። በአሁኑ ወቅት የልጅ- ልጅ አይቼ አያት ሆኛለሁ። እህቶቼን ወንድሞቼን ሰብስቤ አንድ ግቢ ውስጥ በሰላምና በፍቅር ነው የምንኖረው።

ሰንደቅ፡- ይሄ የማሰባስብ ነገር በሀገር ፍቅር ቴአትር ጊቢ ውስጥም እንዳለ ሰምቻለሁ፤ ማህበር መስርተሸ አንጋፎችን እያሰባሰብሽ ነው የሚባለው ነገር እውነት ነው?

ፍሬህይወት፡- እውነት ነው።ብዙዎቻችን በሀገር ፍቅር ያለነው አንጋፋ ሰራተኞች ጡረታ የመውጫችን ጊዜ እየተቃረበ ነው። ይሄ ነገር ከሆነ እስከመጨረሻው ተለያይተን ልንቀር ነው የሚል ስጋት ነበረብኝ። ይሄን ያህል ዓመት አብረን ሰርተን ከመበታተናችን በፊት ምንድነው ማድረግ ያለብን? ተባባልንና አሁን በቅርቡ የአንጋፎቹን ስም መዝግበን ማህበር መስርተናል። እና ለኔ ሰዎች ሲከፉም ሆነ ሲበታተኑ አልወድም። እኔ ያለሁበት ቦታ ላይ ማላዘን እንዲኖር አልፈልግም፤ መሳቅ መጫወት ደስ ይለኛል።

ሰንደቅ፡- አሁን የተጓዝሽበትን መንገድ ዞር ብለሽ ስታስቢው ባደርገው ኖሮ ብለሽ የሚቆጭሽ ነገር አለ?

ፍሬህይወት፡- ብዙም አይደለም። ግን ይህን ያህል ዓመት ሰርቼ ቤተሰቦቼን የምሰበስብበት ቤት አለመስራቴ ይቆጨኛል። ነገ ለልጆቼ ምንድነው የምተውላቸው የሚለውን ነገር ሳስብ እቆጫለሁ። ያም ሆኖ ግን ይመስገነው በጣም ደስተኛ ነኝ።

ሰንደቅ፡- ሲያዩሽ በጣም ጠንካራ ሴት ነሽ፤ ስፖርት ትሰሪያለሽ እንዴ?

ፍሬህይወት፡- አዎ! ከልጅነቴ ጀምሮ ስፖርተኛ ነኝ፤ አክሮባት እሰራ ነበር። አሁንም ቢሆን ፈጣን እንቅስቃሴ እወዳለሁ። (ሳቅ) ለዛም እኮ ነው ቀልቃላ ገፀ-ባህሪይ ባገኝ እወዳለሁ ያልኩህ።

ሰንደቅ፡- ላንቺ የሚመችሽ አዘጋጅ ማነው?

ፍሬህይወት፡- እኔ ሁልጊዜ ቢያዘጋጀኝ ብዬ የምመርጠው ተሻለ ወርቁ ነው። በርግጥ እኔ የተቃኘሁት በእነመላኩ አሻግሬና በእነሰሃሉ ነው። በዚህ ዘመን ግን ተሻለ ቢያዘጋጀኝ እመርጣለሁ። ምክንያቱም እኔን ያቀኛል። ድርሰት ሲሰራ እንኳን ለኔ ቀዶ ነው የሚፋልኝ፤ እርሱ ያዘጋጀው ስራ አይሰፋኝም፣ አይጠበኝም።

ሰንደቅ፡- በቅርቡ በምን እንጠብቅሽ?

ፍሬህይወት፡- በቅርቡ እንግዲህ ያልወጡ ወደአራት ፊልሞች አሉ። ከእነሱ በተጨማሪ የሚመጣ ቴአትር አለ በመድረክም እንገናኛለን ማለት ነው።

ሰንደቅ፡- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።

     ፍሬህይወት፡- እኔም እናንተን በጣም አመሰግናለሁ።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
15626 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us