የስደታችን ማሳያ “የገጠር ልጅ”

Wednesday, 31 December 2014 12:40

 

ስደት የበርካታ ኢትዮጵያውያንን ቤት ያንኳኳ የዘመናችን አንኳር ክስተት ነው። የተሻለ ኑሮ ፍለጋ፣ ቤተሰብን ለመለወጥ፣ ከጓደኛ ለመመሳሰል፣ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ ችግሮችና በአጋጣሚ ስደት ይከሰታል። ለዛሬ ዳሰስ ልናደርግበት የመዘዝነው “የገጠር ልጅ” ፊልም ግን ስደት የራስና የቤተሰብን ማቅ የለበሰ ህይወት ለመለወጥ ሲባል የተከፈተን የህሊናና የገንዘብ ጦርነት ፍንትው አድርጎ በኪነ-ጥበባዊ ለዛ የሚያሳይ ነው።

“የገጠር ልጅ” ፊልም በእውነት ፊልም ፕሮዳክሽን እና በነይ ኢንተርቴንመንት የቀረበ ሲሆን፤ በወንደሰን ይሁን ተፅፎ፤ በወንደሰን ይሁንና በእውነት አሳየህኝ ዳይሬክት የተደረገ የአንድ ሰዓት ከ43 ደቂቃ ፊልም ነው። በውስጡም ተሻለ ወርቁ፣ ሰለሞን ሙሄ፣ አለማየሁ በላይነህ፣ ሜላት ሰለሞንና ቶማስ በየነን ጨምሮ በርካታ ወጣትና አንጋፋ ተዋንያን ተሳትፈውበታል።

የፊልሙ ዋነኛ ማጠንጠኛ ሆኖ የቀረበው አንዲት የገጠር ልጅ አባቷን ከእዳ ለማውጣትና የቤተሰቦቿን ህይወት ለመቀየር በሚል፣ ገጠር ድረስ እየመለመለ በሚወስድ ደላላ አማካኝነት ወደአረብ አገር ብትሄድም፣ ዕድል ሳይቀናት ቀርቶ በአራት ወር ውስጥ ሕገ-ወጥ ተብላ በመመለሷ ምክንያት የሚገጥማትን ውጣ ውረድና ህይወቷ ወደሌላ አቅጣጫ ሲለወጥ የሚተርክ ፊልም ነው።

ደሃና ገበሬ አባቷ የእናታቸውን ህይወት ለማትረፍ ሲል ለህክምና የተበደረው ገንዘብና ለማዳበሪያ ያወጣው ወጪ አጣብቂኝ ውስጥ እንደከተተው የሚያሳየውን የፊልሙ ቀዳሚ ትዕይንት፤ አስከትሎ ግን ህሊና (ሜላት ሰለሞን) ወደትምህርት ቤት ስትገባ ጓደኞቿ አረብ አገር ከሚገኙ እህቶቻቸው የተላከላቸውን ልብስና ጫማ እንዲሁም የኑሮ ሁኔታ ሰምታ የሃሳብ ለውጥ ስታደርግ ያሳየናል።

“የልጄ ወግ ማዕረግ ትምህርቷ ነው” የሚል የፀና አቋም የነበራቸው የህሊና አባት አያ በላይ (ቶማስ በየነ) የልጃቸው “ልሂድ!” ውትወታና የቤተሰቡ ችግር እየጨመረ ሲመጣ “የጉድ ቀን አይመሽም” ይሉትን ተረት ተርተው የልጃቸውን የአረብ አገር ጉዞ ሲያፀድቁ እንመለከታልን። ያውም የክብር መገለጫ የሆነውን ሽጉጣቸውንና ያሏቸውን ከብቶች ሸጠው መሆኑን ስንመለከት የችግራችንን መጠን ያሳየናል። ይህ ክስተት በብዙዎቻችን ቤት የተከሰተ መሆኑን ልብ ይለዋል።

የበርካታ ገበሬ ልጆችን ገጠር ድረስ እየዘመተ በመመልመል የሚታወቀው ደላላው ቸሩ (ተሻለ ወርቁ) ጤፍ በሚቆላው ምላሱ እያግባባ፤ የብዙዎች ህይወት ወዲያው እንደሚቀየር፤ የሰው ቤቶች በቆርቆሮ የሚለውጡ መሆኑን በመናገር ወጣት ሴቶችን ከገጠር በህገወጥ መንገድ ወደአረብ ሀገራት ይነዳል። በዚህም ጥቂቶች ሲሳካላቸው አንዳንዶች ደግሞ ለሞራል ዝቅጠት ብሎም ለዕብደት ይዳረጋሉ ይለናል፤ የ“ገጠር ልክ” ፊልም። ህገወጥ ተብላ በአራት ወሯ ወደሀገሯ የተመለሰችው ህሊና የአባቷን አይኖች ማየት ተስኗት ግራ በተጋባችበት አፍታ ያገኛት ደላላው አዲስ አበባ ውስጥ የሚያውቀው አረብ መኖሩንና ከእርሱ ጋር ሆና የምትፈልገውን ብር እና እርሱም የሚያስፈልገውን ቪዛ ለማግኘት ሲያመቻች እናያለን።

በዚህ ሁሉ መካከል በፊልሙ ውስጥ የሳቅ ዘርን የሚበትነው የወንድማማቾቹ (የአብሮ አደጎቹ) የአባተ (አለማየሁ በላይነህ) እና የዮሴፍ (ሰለሞን ሙሄ) ሁኔታ ነው። እዚህ ላይ ፊልሙ በታሪክ አወቃቀሩና በገፀ-ባህሪያት አሣሣሉ በእጅጉ የተዋጣለትና እስከመጨረሻውም የፀና መሆኑን መናገር ይቻላል።

ለምሳሌም ዮሴፍ (ሰለሞን ሙሄ) በቅርፃቅርፅ ስራ የሚተዳደርና በእምነቱ ፅኑነት ተወዶ ከአሳዳጊው ትልቅ ግቢ የተበረከተለት ወጣት ነው። ይህ ወጣት በቃሉ ለመኖር ሲታትር ፊልሙ ቀነጫጭቦም ቢሆን ደጋግሞ ያሳየናል። ለመጠቃቀስ ያህል ቀብድ የተቀበሉበትንና ያከራየውን ቤት አንዲት ወጣት መጣች ብሎ ቃሉን ያጠፈው አባተን ሲገስፀውና ቤቱ መከራየቱን ሲናገር እንመለከታለን( ምንም እንኳን መጨረሻው ባይሆንም)፣ በሌላ በኩል ደግሞ ቃል በገባው መሠረት ቅርፃቅርፁን ለማስረከብ ሌሉቱን ሲሰራ ስናየው ለገባው ቃል ምን ያህል ታማኝ እንደሆነ በጥቂቱም ቢሆን መመልከት ይቻላል።

በአንፃሩ አባተ (አለማየሁ በላይነህ) ገፀ-ባህሪይን በተለይ ከሥነ-ልቦና አንፃር በእጅጉ የሚያስቅና የሚያሳዝንም ገፀ-ባህሪይ ነው ማለት ይቻላል። “ሁሉ አማረሽን ገበያ አታውጣት” እንዲሉ ያየውን ሁሉ መሆን የሚያምረው አባተ የእግር ኳስ ወሬ በተጧጧፈበት ሰሞን ኳስ ተጫዋች፣ የሩጫ ወሬ በገነነበት ሰሞን ሯጭ ለመሆን ሲታትር የሚያጋጥመውን መመልከት ተመልካችን ዘና የሚያደርጉ ትዕይንቶች ናቸው።

“የገጠር ልጅ” ፊልም በአንዲት ኢትዮጵያዊት የገጠር ልጅ ተመስሎ የቀረበ ይሁን እንጂ የህብረተሰባችንን የክብር መውረድ፣ የሞራል ዝቅጠትና ገመናችንን በአደባባይ የሚገልጥ ወቅቱን የጠበቀ ስራ ነው። በፊልሙ ውስጥ ስደት ስስ ብልታችን ሲቦረቡረው እና ያለን።

በፊልሙ ውስጥ ይህን የህገወጥ ዝውውር መረብ መነሻ የሚያነፈንፍ ግብረ-ሃይሎች ተስለዋል። አንዱ በሁለት ቢላዋ የሚበላ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ለስራው ሟች የሆነ መርማሪ ነው። የአንድኛው የደላላው ሽፋን መስጠትና የሌላኛው ወደምንጩ ለመድረስ የሚደረገው ትርምስ ፊልሙን ልብ አንጠልጣይ አድርጎታል ማለት ይቻላል።

በፊልሙ ውስጥ ዳይሬክተሮቹ አቅደው ይሁን በድንገት ያሳዩዋቸው ሁለት ተምሳሌታዊ ጉዳዮችን ልጥቀስ፤ የመጀመሪያው ህሊና ከገጠር ስትወጣ ይዛው የወጣችው ፌስታል እንደልብሷና እንደ አያኗኗሯ ተለውጦ (ዘመናዊነት ተክቶት) መመሰሏ ራሱን የቻለ ተምሳሌታዊነት የሚታይነበት ነው። ሌላውና ዋነኛው ተምሳሌት ግን ገበሬ አባቷ አያ በላይ አለኝ የሚሉትን ከብት ብቻ ሳይሆን ሽጉጥም ጭምር ለደላላው ሲያስረክብ ድህነት ምን ያህል የክብር መከለያችን ጭምር እንደሚያሳጣን ያሳዩበት ይመስላል።

“የገጠር ልጅ” ፊልም በድምፅ፣ በካሜራ፣ በብርሃንና በኤዲቲንግ የጎላ ስህተት ያልታየበትና ማሳየት የሚፈልገውን ያሳየ ስራ ነው። በትወናው ረገድም ቢሆን ወካይ ገፀ-ባህሪትን በብቃት በማሳየት ዳይሬክተሮቹ ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል።

በስተመጨረሻ ግን “የገጠር ልጀ” ፊልም የብዙ ኢትዮጵያውያንን ህይወትና ማህበራዊ ትስስር በቅጡ የሚያሳዩን መታየት ያለበት ፊልም ነው ብለን ከመዝጋታችን በፊት ሊነሳ የሚገባውን ጉድለት መጠቆሙ ለባለሙያዎቹ ቀጣይ ስራ እንደማስጠንቀቂያ ሊታይ ይችላል።

ይህውም ፊልሙ በታሪክ ረገድ መነገር የሚችል ታሪክ ቢኖረውም፤ ከስራም አንፃር ትስስሩ ጥብቅ ነው ሊባል ቢችልም፤ ገጸ-ባህሪያቱም የራሳቸውን ቀለም ያላቸው ናቸው ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ቢሆንም፤ ከአነጋገር ለዛ (ዘዬ) አንጻር ግን ብዙ ይቀረዋል ለማለት ያስደፍራል። በተለይም ዋናዋ ገፀ-ባህሪይ ህሊና በሂደት ሊና እስክትባል ድረስ ወይም ከሆችም በኋላ የገጠር ልጅ የአነጋገር ለዛ (ዘዬ) ፈፅሞ ያልታየባት መሆኑ ለፊልም ተመልካቹ ይጎረብጣል።

    “የገጠር ልጅ” ፊልም ማህበራዊ ቀውሳችንን፣ ስነ-ልቦናዊ ጣጣችንን፣ ቤተሰባዊ ፍቅራችንን፣ ልቅ የሆነ ስግብግብነታችንና ለክብርና ለዓላማ መሮጣችንን በጥምረት እያሰላሰለ የሚያሳይ ፊልም በመሆኑ ይበል ያሰኘ ሥራ ነው።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
11527 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us