ትልቁ “ብላቴና”

Thursday, 08 January 2015 13:23

አቅራቢው               - በሸገር ፊልም ፕሮዳክሽን

ኤዲተር                 - ይታየው አምላከ ዘርጋው

መብራትና ረዳት ካሜራ    - መብራቱ ዮሐንስ

ድምፅ                  - ብዙአየሁ አበራ

ዳይሬክተር ኦፍ ፎቶግራፊ  - ሲዳኪያል አየለ

ዲዛይነርና ማናጀር        - መታሰቢ ሸንቁጤ

ማጀቢያ ሙዚቃ          - ሱልጣን ኑሪ

ተዋንያን                - ታሪኩ ብርሃኑ፣ እዮብ ዳዊት፣ ፍቅርተ ደሳለኝ፣ ብርክት 

                        ሃይማኖት፣ ኤፍሬም ሙላቱ፣ መቅደስ መልካሙ፣ አመኑ ሚጀና

                        እና ሌሎችም

ደራሲ እና ዳይሬክተር     - ክንፈ ባንቡ 

“ብላቴና” ፊልም ባሳለፍነው ሳምንት በይፋ የተመረቀ የቤተሰብ ፊልም ነው። ገና በብላቴናነቱ የተቸገሩ ቤተሰቦቹን ለመርዳት የሚታትርን ህፃን፤ በተማረበትና በተመረቀበት ትምህርት መስክ (የተመረቀበት ትምህርት ምን እንደሆነ በግልፅ ባይታወቅም) ስራ አጥቶ የሚንከራተትን ወጣት ህይወትና ልጆቿን ለማሳደግ ጉሊት የምትቸረችርን እናት ታሪክ የሚተርክ ፊልም ነው።

ቤተሰቡ ችግር ያልፈታው፣ ማጣት ያልበገረው፣ ፍቅር ያልነጠፈው፣ ተስፋን የሰነቀ ተደርጎ ተስሏል። ተመርቆ በስራ ፍለጋና ዕጦት ሲንከራተት የሚታየው ዘላለም (ታሪኩ ብርሃኑ) ፈገግ በሚያስብሉ አጋጣሚዎች መካከል ሁሉ ሸንቆጥ የሚያደርጉ ማህበራዊ ሂሶችን በፊልሙ ውስጥ ያሳየናል። ለዚህም በልምድ ጥየቃ የተሰላቹ ጀማሪ ስራ ፈላጊዎች የሚገጥማቸውን አበሳ ፊልሙ ፍንትው አድርጎ ያሳያል።

ብላቴናው አቢ (እዮብ ዳዊት) ከትምህርቱ በምትተርፈው ጊዜ ሁሉ ሊስትሮ ሰርቶ፣ ማስቲካ አዙሮ፣ ዕቁብ ገብቶ የቤተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል ሲታትር ማየት በፊልሙ የታየ አዲስ መንገድ ነው። የእናታቸው ደግነሽ (ፍቅርተ ደሳለኝ) ድንገት በተፈጠረ እና ስሩን የጉበት በሽታ ምክንያት መሞት የሁለቱን ወንድማማቾች ህይወት የበለጠ ሲያመሰቃቅለው እናያለን። ዳሩ ግን “ችግር ብልሃትን ትፈጥራለች” እንዲሉ፤ የእናታቸውን የደም ምርመራ ውጤት ተከትሎ በተሰራ ሌላ ምርመራ በተለይም ብላቴናው ሄፒታይትስ “B” በተሰኘው የጉበት በሽታ የተጠቃ መሆኑና ለህክምና ከ20 ሺህ ብር በላይ እንደሚያስፈልግ መታወቁ የታሪኩ ጡዘት መጀመሪያ ይሆናል።

“በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ይሉት ነገር ወንድማማቹ ከእናታቸው ሞት በኋላ የህክምናው ነገር ሲያምሳቸው ይታያል። በዚህም በዘርፉ በህክምናው ሊደረግ የሚገባውን የተሻለ ህክምና ሁኔታ እንዲመቻች በመጠቆም፤ የችግረኛ ቤተሰቦችን እንግልት የት ይደርስ እንደሆነ “ብላቴና” ፊልም ያሳየናል።

ለዓመታት ተምሮ እንጀራውን በየመስሪያ ቤቱ የሚያድነው ዘላለም፤ በታዋቂ ቡና ቤቶች ውስጥ በዘውግ ዳንስ የምትታወቅን ቲና (ብርክት ሃይማኖት) መተዋወቁ ጋሬጣ የበዛበትን መንገድ ሲደላድልለት እናያለን። ለወንድሙ (ለብላቴናው) የበሽታውን አይነትና ደረጃ ያልተናገረው ዘላለም ዕረፍት የሚያስፈልገውንና ታታሪውን ህፃን ከቤት እንዲውል በማድረግ በሊስትሮና በማስቲካ ንግድ ለውጥ ለማምጣት ሲጣጣር ማየቱ የተመልካችን ሀሳብ የሚፈታተን ትዕይንት ነው። ለክብሩ ብዙ ሲጨነቅ የምናየው ይህ ገፀ-ባህሪይ ከወንድሙ ህይወት የሚበልጥ ነገር የለምና ራሱን ዝቅ አድርጎ ሲሰራ ማየቱ የወንድማማቾቹ ፍቅር ያሳየናል።

ድህነት የቱንም ያህል ቢከብድ ጠንካራ ስብዕና ያለው ሰው ፀንቶ እንደሚቆይ ያሳየው “ብላቴና” ፊልም፤ በተለይም ለመድሃኒት መግዣ የቸገረው ወጣት በምሽት ማጅራት መቺነት ተሰማርቶ ገንዘብ ለማግኘት ሲሞክር የሚገባበትን የህሊና ፈተና ፍንትው አድርጎ ያሳያል።

በብላተናው የጉበት ህመም ምክንያት ቤተሰቡ አለኝ የሚለውን ንብረት ሁሉ በሰጥም መድሃኒቱ በቅርበት ለማግኘት ያለውን ፈተናና ስለበሽታው አፅንኦት ሰጥቶ መጠቆም የቻለ ፊልም ነው። በዚህም ኪነ-ጥበብ (በተለይም ፊልም) ሊጫወተው የሚችለውን (የሚገባውን) ማህበራዊ ፋይዳ በማጉላት አሳይቶናል። ከበሽታው በተጨማሪ በማህበረሰባችን ውስጥ የእዝን ስነ -ሥርዓት በሚገባ አመላክቷል።

ለቤተሰቡ ኑሮ ከአቅሙ በላይ ሲለፋ የሚታየው “ብላቴና” በስተመጨረሻም በተለያዩ ሰዎች መካከል ፍቅርን፣ አንድነትን፣ መተሳሰብን፣ ተስፋን በሚገባ እንዲታይ አድርጓል። የሀብቱን ሽራፊ በመስጠት የጉበት ህክምናውን ተከታትሎ መድሃኒቱን እንዲያገኝ ያደረገው ባለሀብት ለወንድሙም የእንጀራ መንገድ ሲቀጥልም እናያለን።

“ብላቴና” ፊልም የወንድማቾችን ፍቅር፣ የተስፋ ማጣትን ስቃይ፣ የማህበረሰባችንን አስተዋይነትና ቁስል በመጎንጎን የሚያሳይ ፊልም ነው።

ያም ሆኖ ግን በተመልካቹ ዘንድ ጥያቄን የሚያጭሩ ሃሳቦች መከሰታቸው አይቀርም። አንድ ሁለቱን ለመጥቀስ ያክል፤ የትንሽ ትልቁ “ብላቴና” ይህን መሰል ሃይል ከየት የመጣ እንደሆነ ጥቂትም ቢሆን በገፀ- ባህሪው ግንባታ ወቅት ሥነ-ልቦናዊ ጥቆማ ቢኖረው መልካም ነው። በሌላ በኩል ፊልሙ የሥራ አጥነትን ምን የማሳየቱን ያህል፤ ስራ ለማግኘት ሰው እንደሚያስፈልግ ማሳየቱ ደግሞ በብዙዎች ልብ ውስጥ ተስፋ መቁረጥ መፍጠሩ ፊልሙን ጎርባጭ ያደርጉታል። ይህም ሲባል በአንዲት ሴት አማካኝነት ያሳየውን ታሪክ ደግሞ በዚህም ማሳየቱ ብቸኛ የስራ ማግኛ መንገዱ “ዘመድ/ሰው” ነው የሚያስብል ይሆናል። ነገር ግን ባለታሪኩ ዘላለም በራሱ ጥረት ተወዳድሮ ስራ ሲያገኝ ብናይ መልካም ይሆን ነበር።

በተረፈ ግን ድህነት በሚያንከራትተው ማህበረሰብ ስር ጥቂት የማይባሉ ባለሀብቶች ብራቸውን የትም ሲረጩ የሚያሳየን፤ የተማረ የሰው ሃይል ያስፈልጋታል በምትባል ሀገር የተማረው ወጣት በልምድ ዕጦት የሚታመስባት ሀገር፤ በችግርም መካከል ቢሆን ቅን መንፈስ ያልሞተ መሆኑን የሚያሳይ ፊልም ነው ብላቴና።

 

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
12169 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us