የጣይቱ “ጃዝ አምባ”

Wednesday, 14 January 2015 12:32

በኢትዮጵያ ቀዳሚ ሆቴል ነው። የኢትዮጵያ ዘመናዊነት መነሻ የኪነ-ህንጻ እና የኪነ-ጥበብ ማሳያም ሆኖ አገልግሏል። በ1898 ዓ.ም በግርማዊት እቴጌ ጣይቱ አማካኝነት የተከፈተ የመጀመሪያው ሆቴል ነው፤ ጣይቱ ሆቴል። ይህ ሆቴል ከቅርስነቱ፣ ከታሪካዊነቱና ከቱሪስት መስህብነቱ በተጨማሪ ለአዲስ አበቤዎችና ለኪነጥበብ አፍቃሪዎች እንደአማራጭ መቅረብ የቻለ የኪነ -ጥበብ መናገሻም ነበር - የጣይቱ “በጃዝ አምባ”።

ይህ ሁሉ ስምና ክብር ያለው እቴጌ ጣይቱ ሆቴል ግን ባሳለፍነው እሁድ ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም እንደዓይን እማኞች ግምት ከጠዋቱ ሁለት ተኩል ሰዓት አካባቢ ጀምሮ እስከ አምስት ሰዓት መዳረሻ ድረስ እንደደመራ በሚንቀለቀል እሳት ሲታመስ ቆይቷል። በወቅቱ የአይን እማኝ ሆነው በስፍራው የነበሩ የግቢው ሰዎች እሳቱ ተንቦግቡጓል። መልኩ በቁጥጥር ስር መዋል ይችል ነበር” የሚል ቁጭት አላቸው። ከነዚህም ሰዎች መካከል በጣይቱ ሆቴል ግቢ ውስጥ በጉዞ ወኪልነት ከሚሰሩት ተቋማት የአንዱ ሥራ አስኪያጅ የሆነው ወጣት አድማሱ ይገኝበታል። እንደሱ አገላለፅ፣ “እሳቱ ኃይል የነበረው በጃዝ አምባ በኩል ነው፤ ነገር ግን ብዙ ሳይስፋፋ እሳት አደጋ ሊደርስ አልቻለም” ሲል የአደጋ ጊዜ የመከላከል አቅማችን በጣም ደካማ ነው ሲል ይተቻል። ይህም በመሆኑ ከጥበብ ቤቱ - “ጃዝ አምባ” ሙሉ በሙሉ የመጎዳት አደጋ ደርሶበታል ይላል።

ሌላኛው የዓይን ምስክር የባላገሩ አስጎብኚ ድርጅት ስራ አስኪያጅ የሆነው አቶ ተሾመ አየለ ይገኝበታል። አደጋው በደረሰበት ሰዓት ከቤቱ ተጠርቶ እንደመጣ የሚናገረው ተሾመ፤ “የእሳት አደጋው ይህን ያህል ጉዳት ከማድረሱ በፊት በቁጥጥር ስር መዋል ይችል ነበር” ከሚሉት ወገኖች አንዱ ነው። በዚህም የእሳትና ድንገተኛ አደጋ ኤጀንሲ እሳቱን ለመቆጣጠር ከሰራው ስራ ይልቅ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የእሳት ማጥፊያ መኪኖች በቦታው ተገኝተው ያደረጉት ርብርብ ይበልጥ ስኬታማ ነበር” ይላል።

በጣይቱ ሆቴል የእሳት ቃጠሎው ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰበት “ጃዝ አምባ” አዳራሽ አጠገብ የሚገኘው የህብረት ባንክና አዲስ ተስፋ ኢንተርቴይመንት ኤንድ ኮሚኒኬሽን ቃጠሎው ከደረሰባቸው ውስጥ ይጠቀሳሉ። በፊቸር ፊልምና በዘጋቢ ፊልም ስራዎቹ የሚታወቀው የዚህ ተቋም ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ አዲስ ተስፋ ገ/መስቀል በቦታው ተገኝተን ካነጋገርናቸው ሰዎች አንዱ ነው።

የእሳት አደጋው መድረሱን የሰማሁት ይርጋለም ከተማ እያለሁ ስልክ ተደውሎልኝ ነው የሚለው አዲስ ዓለም፤ ጣይቱ ሆቴል መቃጠሉ በራሱ ትልቅ ውድቀት እንደሆነ ብናምንም እኛ በግላችንም በገንዘብ የማናገኛቸው ዶክመንቶች ወድመውብናል” ሲል አጋጣውን በሀዘኔታ ይገልፀዋል። ከልጅነቱ ጀምሮ የሰበሰባቸው ዶክሜንቶች፤ በቅርብ ጋብቻውን ሲፈፅም የተቀረፃቸው ፊልሞችና ፕሮዳክሽናቸውን ሰርቶ ያጠናቀቀው ፊቸር ፊልምም ያለምንም ኮፒ መውደሙን ተናግሯል። ከዚህም በተጨማሪ የቲቪ ማስታወቂያዎችና በተለይም የጠቅላይ ሚኒስትር መለስን ሞት ተከትሎ ጠቅላላ አርቲስቶች የተሳተፉበትን የሀዘን ፕሮግራም በብቸኝነት ሰርቼ ያስቀመጥኩትም ፊልም ወድሟል ሲል ክስረቱ ከዋጋ በላይ እንደሆነ ይናገራል።

ይህን ከመሰሉ የቃጠሎ ውድመቶች በተጨማሪ የጥበብ ቤት የነበረው “ጃዝ አምባ” ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ መሆኑን ተመልክተናል። ጃዝ አምባ ከመነሻው በተለይም የኢትዮጵያን ሙዚቃ ለሌሎች ዓለም ሰዎችና ለሆቴሉ ታዳሚያን የሚያሰናዳ ነበር። በዚህ አዳራሽ ውስጥም በርካታ አንጋፋ እና ወጣት ድምጻዊያን ስራዎቻቸውን ማቅረባቸው ይታወቃል። ለመጠቃቀስ ያህሉም አለማየሁ እሸቴ፣ መርዓዊ ስጦት፣ ባህታ፣ ጌታቸው፣ ማህመድ አህመድ፤ ከወጣቶቹ ደግሞ ሚካኤል በላይነህና ዳዊት መለስን ጨምሮ አዳዲስ ባንዶችም ስራቸውን በተከታታይ በማቅረብ ይታወቃሉ። በዚህም ሳያበቃ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ የቴአትር ትርኢቶችንና የሽልማት ፕሮግራሞችን በማሰናዳት “ጃዝ አምባ” ይታወቃል። ከሽልማት ፕሮራሞቹ መካከል “ለዛ ሬዲዮ የአድማጮች ምርጥ” ሲጠቀስ ከቀረቡት በመድረኩ ታይተው ከሚታወሱት ቴአትሮች ደግሞ በቅድሚያ ቤተሰቡ አሁን ደግሞ ከሰላምታ ጋር ተጠቃሾቹ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት በቤቱ ዘወትር ሰኞ በመታየት ላይ የሚገኘው “ከሳላምታ ጋር” ቴአትር በኪባ መልቲ ሚዲያ ፕሮዳክሽን የሚቀርብ ሲሆን የተቋሙ ስራ አስኪያጅና የቴአትሩ ፕሮዲዩሰር አቶ ዘካሪያስ ካሱን ስለተፈጠረው ሁኔታ አነጋግረናቸው ነበር።

ከ2006 ዓ.ም ግንቦት ወር ጀምሮ በጃዝ አምባ አዳራሽ ውስጥ ከሰላምታ ጋር ቴአትርን በማቅረብ ላይ እንደነበር የሚናገረው አቶ ዘካሪያስ፤ በቋሚነት ከሳምንት አንዴ፤ በልዩ ፕሮግራም ሲሆን ደግሞ በሳምንት ሁለቴም በአዳራሹ የቴአትር ስራቸውን የማቅረብ ዕድል አግኝተው እንደነበር ይናገራል።

የጣይቱ “ጃዝ አምባ” አዳራሽ አንድ መቶ ሃምሳ ተመልካቾችን መያዝ የሚችል ሲሆን፤ ከቴአትር ቤቶች በተጨማሪ እንደአማራጭ የቀረበ ተመራጭ ቦታ ስለመሆኑ “የሰላምታ ጋር” ቴአትር ፕሮዲዩሰሩ ዘካሪያስ ይናገራል። ወደዚህ የሚመጡ ተመልካቾች የተለዩ ናቸው የሚለው ዘካሪያስ፤ ተመልካቹ ቴአትርን በክብር ለማየት የሚመጡና ወደ እራት ቴአትርነት የተቀየረበት ቦታ እየሆነ መጥቶ እንደነበር ይናገራል። በመሆኑም “ጃዝ አምባ” አዳዲስ ተመልካቾችን መፍጠር የቻለ መድረክ ስለመሆኑ ያስታውሳል።

በአዳራሽ ላይ በደረሰው አደጋ ምክንያት ብዙ ንብረቶች ከመውደማቸው ጋር ተይዞ ለቴአትር መስሪያ የሚያገለግሉ የመድረክ ቁሳቁሶች፤ አልባሳትና የመብራት መሣሪዎች ሙሉ በሙሉ ስለመውደማቸው አስታውቆ ቤቱ ወደነበረበት ሲመለስ አብረው የመስራት ፍላጎታቸው እንዳለ መሆኑንና ለአስተዳደሩ አካላትም ለነበራቸው ጊዜ ላደረጉላቸው እገዛ ምስጋናውን ገልጿል።

በብዙዎች ዘንድ ጣይቱ ሆቴል በቅርቡ ሙሉ በሙሉ ዕድሳት ተደርጎለት ወደቀድሞው አገልግሎቱ ይመለሳል የሚል ተስፋ ያለ ሲሆን፤ ጃዝ አምባም በተመሳሳይ ሥራዎቹን ለህዝብ አይንና ጆሮ እንደሚያደርስ ተስፋችን ነው። በዚህ አጋጣሚ በአደጋው ለደረሰው ውድመት የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን በዝግጅት ክፍላችን ስም እንገልጻለን።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
10652 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us