“የዝና” በአዲስ ጎዳና

Wednesday, 21 January 2015 13:12

ተወልዶ ያደገው ጨርቆስ አካባቢ ሲሆን በሰፈሩ ይታወቅ ከነበረው “ነፀብራቅ” ክበብ ጀምሮ ሙዚቃን የሰራ ወጣት ድምፃዊ ነው። ይህ ወጣት ባሳለፍነው ሳምንት “የዝና” የተሰኘ የባህል ዘፈኖችን የያዘ አልበም አውጥቷል። አልበሙ ከዓመታት በፊት በድምጻዊ ተስፋዬ ወርቅነህ የተሰራ ሲሆን፤ የዛሬው የመዝናኛ እንግዳችን ድምጻዊ ዳንኤል ዘውዱ ግን ህጋዊ መንገዶችን ተከትዬና አሻሽዬ በድጋሚ ሰርቼዋለሁ ይለናል። ከወጣቱ ድምጻዊ ዳንኤል ዘውዱ ጋር የነበረንን ቆይታ እነሆ፤

ሰንደቅ፡- “የዝና” ከተሰኘው አልበም በፊት አንድ የኮሌክሽን ስራ ሰርተህ ነበር ስለሱ በመነጋገር እንጀምር?

ዳንኤል፡- በአጋጣሚ ያገኘሁት ዕድል ነው። ይህ ኮሌክሽን “ድሪም ኮሌክሽን” ይባላል። ከ2000 ዓ.ም በፊት የሰራነው ነው። በዚያ ውስጥ ሄለን በርሄን ጨምሮ አስር ድምጻዊያን ተሳትፈን ነበር። እኔ “አንዳንዴ እንዲህ ነው” የተሰኘ ነጠላ ዜማ ነበር የሰራሁት፤ ምላሹም በጣም ጥሩ ነበር። ስራውን የሰራነው የወንድሜነህ አሰፋን ስቱዲዮ ለማጠናከር በሚል ነው። ልጁ በጣም ጎበዝ ነው። የብዙሃየሁ ደምሴን፣ የሄለን በርሄንና የሳያት ደምሴን አልበሞች የሰራው ወንድሜነህ ነው። እኛ ያን ኮሌክሽን የሰራነው የእርሱን ስቱዲዮን ለማጠናከር ነበር፤ ስራውን በአድማጭ ዘንድ ተወዶልን ነበር።

ሰንደቅ፡- አንዳንዴ እንዲህ ነው የተሰኘው ነጠላ ዜማህ ተወዳጅ የነበረ የራስህ ሥራ ሆኖ ሳለ ከሰባት ዓመታት ቆይታ በኋላ ለምን የተስፋዬ ጥሩነህን “የዝና” አልበም በአዲስ መልክ መስራት አስፈለገህ?

ዳንኤል፡- እውነት ነው፤ እንዳልከው “አንዳንዴ እንዲህ ነው” የሚለው ነጠላ ሥራዬ ተወዶልኛል።ነገር ግን በተለያዩ ክበቦች የተስፋዬ ጥሩነህን ሥራዎች በምሰራበት ጊዜ የህዝቡ ምላሽ በጣም የሚያበረታታና በአዲስ መልክ እንድሰራው የሚገፋፋ ነበር። በአጋጣሚ ግን አንድ ቀን እንዲሁ “ከሚላ” የሚለውን ዘፈን በክለብ ውስጥ እየሰራሁ ሳለ ካሙዙ ወደደው። ያለምንም ወጪ ልስራልህ አለኝ፤ ሰራነው። ሰርተነው ሲመጣ የአድማጩ ምላሽ የበለጠ አሪፍ ሆነ። ብዙዎች የአልበሙ ትዝታ አለን በሚል አስተያየት ስላደረሱን ሙሉ አልበሙን በአዲስ ለመስራተ ወሰንኩ እንጂ የተጠናቀቀ የራሴ ኦሪጅናል አልበም ጨርሼ በእጄ ላይ ይገኛል።

ሰንደቅ፡- ኦርጂናል ሥራዎችን መስራት እየተቻለ በዚህ መልክ የቀደምት ሥራዎችን ሥራ መድገሙን ታበረታታለህ? የፈጠራ ንጥፈት ያለ አያስመስለውም?

ዳንኤል፡- በመስራቱ እኔ አምናለሁ። ይህ ነገር እኛ ሀገር ብቻ ሳይሆን በውጪውም የተለመደ ነው። እኛ ሀገርም እኮ በህይወት እያሉ ተደግመው የተሻሻሉ ስራዎች እንዳሉ ይታወቃል። ምክንያቱም የበፊት ሥራ በጥሩ መልኩ ተሰርቶ፣ ሰውን በማይቆረቁር መልኩ በፊት የተሰሩ ስህተቶች ካሉ አሻሽሎ መዝፈን ከተቻለ መበረታታት አለበት ብዬ አምናለሁ። ሁለተኛ ደግሞ ለዚህ ትውልድ በሚሆነው መልኩ ማቀረብ ያስፈልጋል፤ አሁን ለምሳሌ እኔ የሰራሁት የተስፋዬ ወርቅነህ አልበም በካሴት ብቻ እንጂ በሲዲ የለም። ጥራቱም ደግሞ ከወቅቱ ቴክኖሎጂ ጋር የወረደ ነው። ስለዚህ አሁን ላለው አዳማጭ እንዲመች አድርገን ሰርተነዋል።

ሰንደቅ፡- ተስፋዬ ወርቅነህን ታውቀዋለህ? ዘፈኑንስ ከመቼ ጀምሮ ነው የሰማኸው?

ዳንኤል፡- ዘፈኑ እኔ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ የወጣ በመሆኑ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስማዋሁ። ነገር ግን ተስፋዬን በአካል አግኝቼው አላውቅም። በተረፈ ግን “የዝና ተማሪ ነኝና” የሚለው ዘፈን በጣም ትዝታ ያለው ሥራ ነው።

ሰንደቅ፡- ቀደም ብለህ ለክበብና በምሽት ጭፈራ ቤቶች የእነማንን ሥራዎች ነበር የምትሰራው?

ዳንኤል፡- ክለብ እያለሁ የብዙዎቹን ሥራ እዘፍን ነበር። በይበልጥ ደግሞ የነዋይ ደበበ ሥራዎች ይመቹኛል። በተረፈ ግን የመሐመድ አህመድና የአለማየሁ እሸቴን ጨምሮ ሱዳንኛና የባህል ሥራዎችን እሰራ ነበር።

ሰንደቅ፡- ከካሙዙ ጋር “ከሚላ” የሚለውን ዘፈን በነጠላ ደረጃ ከሰራችሁ በኋላ ወደአልበም ሥራው እንዴት ሄዳችሁ? ህጋዊ ሂደቱንስ የተከተለ ነበር?

ዳንኤል፡- ቢሰራ ጥሩ ነው ብለን ካመንን በኋላ መጀመሪያ የሄድነው የኦዲዮ ቪዥዋል መስሪያ ቤት ነው። እዛ ሄደን ሰዎች አማከርን፤ ማለትም መብትና ግዴታችንን በሚመለከት ስለህጉ ጠየቅን፤ በነጠላ ደረጃ ከሆነ ደራሲውን አስፈቅዶ መስራት እንደሚቻል። ይህም የሚሆነው ለሽያጭ ካልሆነና ለሽያጭ ከሆነ ግን የዜማና የግጥም ደራሲውን ጨምሮ ያሳተመውን ሙዚቃ ቤት ሳይቀር ማስፈቀድ እንዳለብን ተነገረን። ከዚያ የዜማና የግጥም ደራሲዎቹ ጋር ሄጄ፤ መስራት እንደምፈልግ በመንገር አሰፈቀድኳቸው። የኔው አካሉ እና ፀሐይ በየነ ይባላሉ። የሁለቱን ፈቃደኝነት እንዳገኘን ሥራው ለገበያ ስለሚውል የዋልያ ሙዚቃ ቤት ባለቤት የሆኑት አቶ ብስራት ጋር በመሄድ አነጋገርናቸው። ፈቅደውልን በህጋዊ መንገድ ውል ፈፅመን ነው የሰራነው።

ሰንደቅ፡- የድምፃዊው መብት በተመለከተ ማንን አነጋገራችሁ?

ዳንኤል፡- ነገሮች ከተስተካከሉ ይሄ እኔ ወደፊት የማደርገው ነገር እንጂ በህጉ እስካሁን ስለሙዚቀኛው የተባለ ነገር የለም። ማለቴ ድምፃዊው እንደዜማና ግጥም ደራሲዎቹ ተከፍሎት ለሙዚቃ ቤቱ የሰራ በመሆኑ የተነገረ ነገር የለም። ለምሳሌ ዘፋኙ ራሱ ገጥሞ፤ ዜማ አውጥቶ በራሱ ገንዘብ የሰራው አልበም ከሆነ መብት ይኖረዋል፤ ግን ደራሲዎቹና ያሰሩት ሰዎች ሌላ በመሆናቸው እነርሱን ማስፈቀድ ነበረብን፤ አስፈቅዶልናል።

ሰንደቅ፡- የዜማና የግጥም ደራሲዎቹም እኮ ተከፍሏቸው ነው የሰሩት። ነገር ግን አሁን በድጋሚ ተጠይቀዋል። ድምጻዊው በህይወት ባይኖር እንኳን ቤተሰቡ ሊጠየቅ አይገባም እያልከኝ ነው?

ዳንኤል፡- እስካሁን ያስፈቀደ የለም፤ ህጉም እንደዚያ አይልም። ሰዎች አነጋግረናል። ነገር ግን ሥራው ከተሳካልህ አንተ በሰብዓዊነት ቤተሰቦቹን መርዳት ትችላለህ። አስገዳጅ ግን አይደለም። ማወቅ ያለብህ ስድስት ሥራዎችን ዜማና ግጥም የሠራው የኔው አካሉን ከታመመበት አንስተን፤ አሳክመን ረድተን ነው በስምምነት ሥራውን የሰራነው። ፀሐይ በየነንም ፈልገናት ተነጋግረን ነው የሰራነው።

ሰንደቅ፡- ከዚህ በኋላ የተስፋዬ ወርቅነህ ቤተሰቦች መጥተው የይገባኛል ጥያቄ ቢያነሱ ምላሽህ ምንድነው?

ዳንኤል፡- እንግዲህ ይገባናል የሚሉ ከሆነ በህግ አግባብ እንነጋገራለን። ለምሳሌ ነጠላ ዜማውን ሰርቼ፤ ክሊፕ አሰርቼ ሁሉ ማንም የጠየቀኝ ሰው የለም። ስለዚህ ቢመጡም ደግሞ እኔ ህጋዊ ነኝ፤ ወረቀት አለኝ።

ሰንደቅ፡- መልካም አሁን በአዲስ መልክ የሰራኸው “የዝና” አልበም ከበፊቱ ምን የተሻሻለ ነገር አለው?

ዳንኤል፡- በመጀመሪያ ደረጃ ከሙዚቃ ሪከርዲንግ ጀምሮ የሙዚቃው ጥራት፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሙሉ በሙሉ ግጥሞቹ ተሻሽለዋል። ያህንን ስል የበፊቶቹ ያስጠላሉ ማለቴ አይደለም። ነገር ግን ፈሩን ይዞ አስሩም የዘፈን ግጥሞች እንደ አዲስ ተሰርተዋል ማለት እችላለሁ።

ሰንደቅ፡- ግጥሙ ሲሻሻልየገጣሚያኑ ፈቃደኝነት ነበረው?

ዳንኤል፡- ገጣሚያኑን አስፈቅደን በውል ነው የሰራነው። አሁን በአዲስ መልክ ግጥሞቹን የሰራልን ጥላሁን ሰማሁ ይባላል የብዙአየሁ ደምሴን ስራዎች የሰራ ጎበዝ ልጅ ነው።

ሰንደቅ፡- የተስፋዬ ወርቅነህን ሥራ ነው የደገምከው ወይስ በራሴ መንገድ ነው የዘፈንኩት ነው የምትለው?

ዳንኤል፡- እኔ በራሴ መንገድ ነው የሰራሁት። ምክንያቱም በመጀመሪያ ደረጃ በዚህ አጋሚ ልነግርህ የምፈልገው ነገር ተስፋዬ ጎበዝ ዘፋኝ ነው። እኔ ደግሞ ማንንም መሆን አልችልም። የራሴን ከለር ነው ይዤ የመጣሁት። ዜማዎቹን ስለማውቃቸው ወደሱ አዘፋፈን እንዳልሆድ በጣም ተጠንቅቄ ነው የሰራሁት። ነገር ግን የሚያዳምጠው ሰው የቀደመውን እንዲያስታውስ ማድረግ ችያለሁ። ያም ሆኖ ይሄ አሰራር አዲስ ነው። የበፊቶቹም የአሁኖቹም አድማጮች የሚወዱት ሥራ ነው የሚል ተስፋ አለኝ።

ሰንደቅ፡- ምን ያህል ኮፒ አሳተምክ? በሳምንት ጊዜ ውስጥ የአድማጩስ ምላሽ ምን ይመስላል?

ዳንኤል፡- ሳተምነው 10ሺህ ኮፒ ነው። በሳምንት ውስጥ ጥሩ ሄዷል ብዬ አስባለሁ። አሁን ከአዟሪዎች እጅ እያለቀ ነው። በቅርቡም ሁለተኛው ዙር መግባታችን አይቀርም። የአድማጩን ምላሽ በተመለከተ ጥሩ ነው።

ሰንደቅ፡- የተጠናቀቀ አልበም እንዳለህ ነግረኸኛል። አንተን የሚገልጽህ የትኛው አልበም ነው?ያወጣኸው ነው ወይስ ወደፊት የምታወጣው?

ዳንኤል፡- ለኔ ሁለቱም ልጆቼ ናቸው። ማበላለጥ አልችልም።

ሰንደቅ፡- በአሁኑ ወቅት ሥራዎችህን ማየት የሚፈልጉ ካሉ የት ነው የሚያገኝህ፤ የት እየሰራህ ነው?

ዳንኤል፡- አሁን ለጊዜው ከለብ አቀሜያለሁ። ከ4 ዓታት በላይ የወሰደብኝ ሥራ ነው። አሁን በማስተዋወቅ ላይ ነኝ።

ሰንደቅ፡- አመሰግናለሁ።

ዳንኤል፡- እኔም አመሰግናለሁ። በዚህ አጋጣም አልበሙን እንድሰራ የፈቀዱልኝንም ያገዙንንም በዙሪያዬ የነበሩ ሰዎችን በሙሉ እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ። በተለይ ለግጥምና ዜማ ደራሲዎቹ ፀሐይ በየነ እና የኔው አካሉ እንዲሁም ግጥሞቹን ላሻሻለልኝ ለጥላሁን ሰማው አመሠግናለሁ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
9470 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us