“አንተንና የምትሰራውን ገፀ-ባህሪይ የመለየት ችግር አለ”

Wednesday, 28 January 2015 12:44


ተዋናይ አለባቸው መኮንን

 

የዛሬውን እንግዳችን ተዋናይ አለባቸው መኮንን ብዙዎች በሚሰራቸው በርካታ ፊልሞቹ ያውቁታል። አለባቸው ከሰራቸውና በእጅጉ ከሚታወሱለት ሥራዎቹ መካከል ለመጠቃቀስ ያህል፤ መስዋት፣ የተዋቡ እጆች፣ የባህር በር፣ ስርየት፣ ኒሻን፣ መልህቅ፣ ነቄ ትውልድ፣ የቤት ልጅ፣ ቦዲጋርድ፣ ጉደኛ ነች እና ሌሎችም ይጠቀሱለታል። በቅርቡም ”በቀናት መካከል” የተሰኘ ተከታታይ የቲቪ ድራማ ላይ በኢቢኤስ ቴሌቪዥን በኩል ልናየው ነው። በስራዎቹና በህይወቱ ዙሪያ ያደረግነው ቆይታ እነደሚከተለው ቀርቧል።

ሰንደቅ፡- ዘግይተውም ቢሆን ወደፊልሙ ዓለም በመግባት የተሳካላቸው ጥቂት ሰዎች አሉ። አንተ አንዱ ነኝ ብለህ ታስባለህ?

አለባቸው፡- ባይገርምህ እኔ ገና ከልጅነቴ ጀምሮ ፊልም የመስራት ጉጉቱ ነበረኝ። ነገር ግን በወቅቱ በሀገራችን ውስጥ የፊልም እንቅስቃሴው ልክ እንደአሁኑ አልተስፋፋም ነበር። በኋላ ግን ፊልም ለመስራት ምን ማድረግ አለብኝ ብዬ ሳስብና ከወዳጆቼ ጋር ሳወራ አንድ ሀሳብ መጣልኝ፤ ያም ምንድነው ወይ ማስተር ወይም ደግሞ ቶም ቪዲዮ ግራፊ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ገብቼ መማር የሚለው ነው። አንድ ቀን ግን ድንገት ወደ ፒያሳ ሄጄ የቶም ቪዲዮን ማስታወቂያ ሳይ በቀጥታ ወደ ቢሮአቸው ገብቼ ምን ዓይነት ኮርሶችን እንደሚሰጡ ምን ያህል ጊዜና ክፍያው ስንት እንደሆነ ሁሉ አጣርቼ ተመዘገብኩ።

ሰንደቅ፡- በትምህርት ላይ እያለህ ግን ፊልም የመስራት አጋጣሚውን አገኘህ?

አለባቸው፡- በጣም ዕድለኛ ነበርኩ። መምህሬ ይድነቃቸው ሹመቴ ነበር። የኔ “ሲኒየሮች” (ቀዳሚ ተማሪዎች) የመመረቂያ ፊልም ለመስራት በዝግጅት ላይ ሳሉ እኔን አብሬያቸው እንድሰራ መረጡኝ። እኔ እኮ ልምድ የለኝም ብልም በስራ ውስጥ ትማራለህ ብሎ ይድነቃቸው እንድሰራ ነገረኝ። ከዚያም የ18 ወይም 19 ደቂቃ የመመረቂያ ፊልም ከልጆቹ ጋር ሰራሁ።

ሰንደቅ፡- ለአንተ የመጀመሪያው ፊቸር ፊልም የቱ ነው? እንዴትስ ነበር?

አለባቸው፡- ባይገርምህ የመጀመሪያውን ፊቸር ፊልም ለመስራት የመረጠኝ ሰው ተማሪ እያለሁ ለመመረቂያ የሰራሁትን ፊልም አይቶ ነው የወሰደኝ። ፊልሙ “መስዋት” ይሰኛል። ዳይሬክተሩ ሄኖክ አየለ ሲሆን፤ እኔን ጨምሮ ግሩም ኤርሚያስ እና ይገረም ደጀኔ አሉ። በአጋጣሚ ሁላችንም ወደ ፊልም ስራ የመጣነው በመስዋት ፊልም ነው። መስዋት ታይቶ ብዙዎች ወደውት ነበር፤ ይህን ፊልም ያየ ሰው ደግሞ እፈልግሃለሁ ብሎ “የተዋቡ እጆች” የተሰኘ ፊልምን እንድሰራ ጋበዘኝ። ሁለተኛ ፊልሜን ሰራሁ ማለት ነው። ከዚያ በጣም የገነነው “ስርየት” መጣ። ከስርየት ቀጥሎ “የባህር በር” ተሰራ እንዲህ እያለ በርካታ ፊልሞችን የመሥራት አጋጣሚው እየሰፋ መጣ ማለት ነው።

ሰንደቅ፡- ከራስህ ሥራዎች በየትኛው ገፀ-ባህሪይ አሁን ድረስ ትናደዳለህ?

አለባቸው፡- ይኖራል። ለምሳሌ “የቤት ልጅ” ፊልምን መጥቀስ እንችላለን። እኔ ህፃናትንና ሴቶችን የምወድና የምንከባከብ ሰው ነኝ በባህሪዬ፤ እዛ ፊልም ላይ ግን ያለው ገፀ-ባህሪይ ከእኔ ባህሪይ ፍፁም የራቀ ነው። እኔ አሁን ሴት ልጅ መንገድ ላይ ስትመታ ባይ ከማላውቀው ሰውም ጋር ቢሆን ልጣላ እችላለሁ። እኔ ምን አምናለሁ መሰለህ፤ እግዚአብሔር ሲፈጥር ሴትና ወንድን በእኩል አቅም አልፈጠረም፤ በተፈጥሮም እንለያያለን። እኩልነት ስለተባለ ብቻ በሁሉም ነገር እኩል ነን ማለት ተገቢ አይመስለኝም። ከዚህ በኋላም ተመሳሳይ ጨፍላቂ ገፀ-ባህሪይ መቶልኝ ነበር አይሆንም ብዬ መልሻለሁ።

ሰንደቅ፡- የወደድከው ገፀ-ባህሪስ?

አለባቸው፡- “ጥሎ ማለፍ” ፊልም ውስጥ ያለው ኢንጂነር ገፀ-ባህሪይ በጣም ደስ ይለኛል። ሚስቱ ሞታበት እርሷን የምትመስል ሴት ተዋውቆ እርሷን ለማስደሰት ሲጣጣር፤ ገንዘቡን ይዛ ስትጠፋ ምናምን ታሪኩ ቢያሳዝንም፤ የሰውየው ስብዕና ግን ጥሩ ነበር። ሌላው ደግሞ አሁን በቅርቡ የሰራነው “ነቄ ትውልድ” ፊልም አለ። ገና የፊልም ጽሁፉን ሳነበው የወደድኩት ታሪክ ነው።

ሰንደቅ፡- በስፖርት ዙሪያ እንዴት ነህ?

አለባቸው፡- ጥሩ ስፖርተኛ ነበርኩ። አሁንም ቢሆን አልፎ - አልፎ ስፖርት እሰራለሁ። ከአዲስ አበባ ወጣ ብዬም ብስክሌት መንዳት ደስ ይለኛል። ለምሳሌ እስከ 50 ኪሎ ሜትር ደርሶ መልስ መንዳት እወዳለሁ። አሁን-አሁን ግን ሥራ በዝቶ ነው መሠለኝ የስፖርት ጊዜዬን እየተሻማብኝ ነው።

ሰንደቅ፡- እስካሁን ያላገኘኸው ነገር ግን ብሰራው የምትለው ገፀ-ባህሪይ ምን ዓይነት ነው?

አለባቸው፡- በጣም አለ፤ እኔ የሚፈትነኝን ገፀ-ባህሪይ መጫወት እፈልጋለሁ። እስካሁን ፊቴ ላይ ሜካፕ ተቀብቼና ተለውጬ የሰራሁት ፊልም የለም፤ እስካሁን ባለኝ መልክ ነው የምሰራው። ለዚህ ሁሉ ምኞቴ መሳካት ግን ታሪኩና የፕሮዳክሽኑ አቅም ወሣኝ ነው።

ሰንደቅ፡- አንድን ፊልም ለመስራት ክፍያው ነው ወይስ ታሪኩ የሚቀድመው?

አለባቸው፡- ሁለቱም ወሣኝ ነገሮች ናቸው። ነገር ግን ከሁሉም በላይ ለተመልካቹ የምናቀብለው መልዕክት (ጭብጡ) ምንድነው የሚለው ነገር እኔን ያሳስበኛል። ተመልካች ከሲኒማ ቤት ሲወጣ በጭንቅላቱ ቁም ነገር ይዞ የማይወጣ ከሆነ መስራቱ ምን ዋጋ አለው? እኔ ቁም ነገር አጥቼባቸው የመለስኳቸው ብዙ የፊልም ጽሁፎች አሉ። አንድ ጊዜ እንዳውም አስታውሳለሁ ገና ፊልም መስራት ስጀምር አካባቢ ነው። የፊልሙ ጽሁፍ ተሰጥቶኝ ማንበብ ጀምሬ ከ18ኛ ገጽ ማለፍ አልቻልኩም። ይሄን አይነት ታሪክ መስራት አልፈልግም ብዬ ነው የመለስኩት። የፈለገውን ያህል ጥሩ ክፍያ ቢከፈለኝም ያልወደድኩትንና ያላመንኩበትን ፊልም አልሰራም።

ሰንደቅ፡- ቴአትር ስለመስራትህ ብዙዎች አያውቁም፤ አንተ ግን ሰርተሃል?

አለባቸው፡- አይታወቅ ይሆናል እንጂ ሁለት ቴአትሮችን ሰርቻለሁ። ሁለቱም በእንግሊዝኛ ቋንቋ የቀረቡ ናቸው። አንደኛውን እንደውም ከአባተ መኩሪያ ጋር ነው የሰራሁት። በነገራችን ላይ ጋሽ አባተን በጣም የማከብረውና የምወደው ባለሙያ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ መናገር እፈልጋለሁ። አብረን የሰራነው “ዘ ሂድን ኢንስፔክተር” የተሰኘ የሱራፌልን ጽሁፍ ነው፤ ለኢስት አፍሪካ ቴአትር ፌስቲቫል ሁሉ የታየ ሥራ ነው። ከዚያ በፊት ግን በብሪቲሽ ካውንስል ውስጥ “አዲስ ስቴጅ” የሚባል የቴአትር ቡድን ነበር። ቡድኑ ለብሪቲሽ ኮሚኒቲና ለሌሎችም ቴአትር የሚሰራ ቡድን ነው። ታዲያ በአንድ ወቅት ላይ አንዱ ተዋናይ በሆነ ምክንያት ወደ ጣሊያን ሀገር ተጠርቶ ይሄዳል። ተዋናዮቹ የተውጣጡት ከኦስትሪያ፣ ከጣሊያን፣ ከአሜሪካና ከብሪቲሽ ኤምባሲ ነበር። በኋላ ላይ እዛ ውስጥ አንድ እኔን የሚያውቀኝ ሰው ነበር። ያ ተዋናይ ሲሄድ እኔን ለመተካት ይፈልግና መጥቶ ያናግረኛል። ከዚያ ጣይቱ ሆቴል ከቴአትሩ ዳይሬክተር ግር ተገናኝተን አወራን፤ ስታየኝ ገና ወደደችኝ። የቴአትሩን ጽሁፍ ሰጠችኝ በ15 ቀን ውስጥ አጥንቼ መቅረብ ነበረብኝ። በሳምንት ውስጥ ቤቴን ዘግቼ ዲያሎጉን በቃሌ አጥንቼ ጨረስኩ። ከዚያ ልምምድ ስንገባ በችሎታዬ መደነቅ ጀመሩ። ከሳምንት በኋላ በአልባሳት ሆነን ሰራን፤ ለሦስት ቀናት በትሮፒካል ጋርደን ለተመልካች ቀረበ።

ሰንደቅ፡- በፊልም ሥራዎችህ በተለይ በተቃራኒ የሚታወሱ ሥራዎች ብዙ መጥቀስ ይቻላል። ከእነዚህ መካከል “ኒሻን” ፊልም ላይ ያለው የቅርስ ዘራፊ እና መልህቅ ላይ ያለው ካፒቴን እንዴት ታስታውሳቸዋለህ?

አለባቸው፡- ሁለቱም ለእኔ ምርጥ ፊልሞች ናቸው። “ኒሻን” ብዙ የሚፈትን ነበር፤ እንዳየኸው የገፀ-ባህሪው እጅ የተቆረጠ ነው። በመሆኑም እጅህ ወደኋላ ወይም ከሱሪህ ውስጥ እንዲታሰር ይደረጋል። በጣም የሚገርምህ ከዚህ ቀደም ያላዩኝ ተመልካቾች አንድ እጅ የለውም ብለው የተከራከሩ ሁሉ አሉ። መልህቅ ላይ ያለው ደግሞ በጣም ታማኝ ገፀ-ባህሪይ ነው። በነገራችን ላይ ፊልሙን ለመስራት ጅቡቲ በቆየንበት ጊዜ በሙቀት ብዛት የመታፈን አደጋ አጋጥሞኝ ነበር፤ አብሮኝ የሚያድረው ልጅ “ኤሲውን” የአየር ማቀዝቀዣውን አጥፍቶት ኖሮ ለጥቂት ከሞት ተርፌያለሁ። “መልህቅ” ፊልምን ሳስበው ይህ አጋጣሚ ለእኔ የማልረሳው ነው።

ሰንደቅ፡- ከማን ጋር መሥራት ትመኛለህ?

አለባቸው፡- ከፍቃዱ ተ/ማርያም ጋር በጣም እናፍቃለሁ። ሌሎችም አንጋፋና ወጣት ተዋንያን አሉ። ገና እንሰራለን፤ ሁሉንም አከብራቸዋለሁ።

ሰንደቅ፡- ከዚህ በኋላ በቴአትር እናይሃለን?

አለባቸው፡- አይመስለኝም፤ ቴአትር በጣም ነው የሚጨንቀኝ፤ ሙያውን ጠልቼው አይደለም። መድረክ ዕውቀትም ችሎታም የሚጠይቅ ቦታ ነው። ግን እኔ በተፈጥሮዬ አንድ ቦታ መቀመጥ አልወድም። የተለያዩ ሥራዎችን እሰራለሁ፤ ምናልባትም እኔን ተማምኖ ተመልካች ገብቶ ብቀር ወቀሳውን አልችለውም። ስለዚህ እኔ ወደመድረክ የምሄድ አይመስለኝም።

ሰንደቅ፡- የቴቪ ተከታታይ ድራማዎች ላይስ እንዴት ነህ?

አለባቸው፡- ከዚህ ቀደም “ሰው ለሰው” ላይ አጭር ቦታ ተሰጥቶኝ ሰርቻለሁ። አሁን ደግሞ በመሪ ገፀ-ባህሪይ ደረጃ “በቀናት መካከል” የተሰኘ ተከታታይ የቴቪ ድራማ ላይ እየሰራን ነው። በቅርቡ በኢቢኤስ ቲቪ መታየት ይጀምራል።

ሰንደቅ፡- ምን ያዝናናሃል?

አለባቸው፡- እኔ ፊልም በመሥራት ብቻ ሳይሆን በማየትም እዝናናለሁ፤ በተረፈ ከቤተሰቤ ጋር ስሆን በጣም ደስተኛ ነኝ።

ሰንደቅ፡- በብዙዎቹ በሰራህባቸው ፊልሞች “ፖስተር” ላይ ፊትህ አለ፤ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆኛለሁ ብለህ ታስባለህ?

አለባቸው፡- እኔ እንደውም የሚገርምህ በዚህ ነገር ላይ ማሰብ ካቆምኩ ቆይቻለሁ። ይህ የዳይሬክተሩና የፕሮዲዩሰሩ ሥራ ነው። ነገር ግን እንዳልከው ብዙ ጊዜ የፊልም “ፓስተር” ላይ አለሁ፤ ይህ እግዜአብሔር የሰጠኝ ፀጋ ይመስለኛል። ፖስተርና የፊልም ርዕስ ተመልካች ላይ ተፅዕኖ እንዳለው የታወቀ ነው። ምርጫው ደግሞ የዳይሬክተሩና የፕሮዲዩሰሮቹ ይመስለኛል።

ሰንደቅ፡- እስካሁን ከፊልም የሚገባኝን ክፍያ አግኝቻለሁ ብለህ ታስባለህ?

አለባቸው፡- እሱን በሆድ ይፍጀው ብንዘጋው ደስ ይለኛል። ዛሬ ጠዋት ከሌሎች ሰዎች ጋር ስለ ክፍያ ነገር ተነስቶ እያወራን ነበር። ሰው ሥራውን የሚሰራው ለፍላጐቱና ለውስጡ ነው። እዚህ ምድር ላይ ስትኖር ብዙ ገንዘብ ስላለህ ብቻ ደስተኛ ላትሆን ትችላለህ፣ ስለሌለህም ደግሞ አትጐዳም። የሰው ልጅ በምድር ላይ የሚኖረው በፀጋ ነው።

ሰንደቅ፡- ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።

    አለባቸው፡- እኔም ለተሰጠኝ ዕድል በጣም ነው የማመሰግነው።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
11276 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us