“ሥዕላዊ ስላቅ” - በጋለሪያ ቶሞካ

Thursday, 05 February 2015 11:56

     በእድሜ ጠገቡና በታሪካዊው ቶሞካ ካፌ ለሁለት ወር የሚዘልቅ የስዕል አውደ ርዕይ ካሳለፍነው አርብ ጥር 22 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ የአርቲስት ቴዎድሮስ መስፍንን (ቴዲማን) ተወዳጅ “ሥዕላዊ ስላቅ እና ሥዕላዊ ምፀት” ስራዎች በአዝናኝ መልኩ ለተመልካች በማሳየት ላይ ይገኛል። በጋለሪያ ቶሞካ ለሁለት ወር በሚቆየው በዚህ የስዕል አውደ-ርዕይ ላይ ቡና ለመጠጣት ብቅ ያሉ ተመልካቾች አይኖቻቸውን በተሰቀሉት ስዕሎች ላይ አሳርፈው በመደመም፣ በመመራመር፣ በመጠያየቅና በመዝናናት መንፈስ እንደሚቆዩ ይሰማኛል የሚለው የቶሞካ አርት ጋለሪ ማኔጂንግ ዳይሬክተር የሆነው ጋዜጠኛ ነብዩ ግርማ ነው።

በመክፈቻው ዕለት አመሻሽ ላይ ሳር ቤት አካባቢ በሚገኘው ቶሞካ አርት ጋለሪ በተገኘንበት ወቅት ያስተዋልነውና በስፍራው የነበሩ ሰዎች የነገሩንም ይህንኑ ነው። ለመሆኑ በቶሞካ አርት ጋለሪ ውስጥ የስዕል ሥራዎችን ማቅረብ ምን የተለየ ስሜት አለው? በሚል ላነሳነው ጥያቄ ስዕሎቹን ያቀረበው አርቲስት ቴዎድሮስ መስፍን ሲመልስ፤ “የመጀመሪያው ነገር ቶሞካ ታሪክ ያለውና ብዙ ቡና ወዳጆች የሚሰባሰቡበት ቤት መሆኑ ነው። በመቀጠል ግን ለኔ እንደአርቲስት ወደዚህ ቤት ሥራዎቼን ላቀርብ ስመጣ ውጣ ውረድ የሌለበት ሆኖ አግኝቼዋለሁ። የጋለሪው ባለሙያዎች ራሳቸው አስተባብረው የጥሪ ወረቀትና በራሪ ፅሁፎችን መጽሔቶችን ሁሉ በራሳቸው አሳትመው ነው የሚያሳዩልኝ፤ ከዚህ ባለፈ የምታሳይበት ሰፊ ጊዜ አለህ፣ ይህ ለሰዓሊያን ጥሩ ነገረ ይመስለኛል” ባይ ነው።

ለቤቱ ሲባል የተለየ ሥራን እንዳልሰራ የሚናገረው አርቲስት ቴዎድሮስ፤ ሰላሳ አራት የፖርትሬት አርት (ስእላዊ ስላቅን) የያዙ አዝናኝ የታዋቂ ሰዎችን ምስል ለተመልካች ማብቃቱን ይናገራል። ሥራዎቹ በእርሳስ ብቻ የተሳሉ ከመሆናቸው ባሻገር አነጋጋሪነታቸውና አዝናኝነታቸው ከፍ ስለማለቱ በዕለቱ በሥራዎቹ ዙሪያ አስተያየት ከሰጡ አድናቂዎቹ ለመረዳት ችለናል።

ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ቶሞካ ካፌ ከሚያገኘው የቡና አቅርቦት ትርፍ ላይ ማድረግና መስራት የሚቻለውን የማህበራዊ ኃላፊነት ለመውጣት አስቦ ተግባሩን ያለአንዳች የትርፍ ፍላጎት ስለመጀመሩ የሚናገሩት የቶሞካ አርት ጋለሪ አርት ዳይሬክተር ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ ናቸው። ዋነኛ ዓላማውም የአገራችንን ሰዓሊያንና ስራዎቻቸውን ከህብረተሰቡ ጋር እንዲተዋወቁና እንዲቀራረቡ እድል ማመቻቸት እንደሆነ ይናገራሉ። ይህም በመሆኑ የቶሞካ አርት ጋለሪ ክፍት ሆኖ ይህንን ተግባር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ሶስት የፎቶግራፍ ባለሙያዎችን ሥራዎች እና የዘጠኝ ሰዓሊያንን ስራዎች ለታዳሚያን እንዲታዩ አድርጓል። በአጠቃላይም አስራ ሶስት የሚደርሱ ስራዎችን ለወራት ጊዜና ቦታን በመስጠት ባለሙያውንና ታዳሚውን በቶሞካ አርት ጋላሪ ውስጥ ለማቀራረብ እየተሰራ ስለመሆኑ ተነግሯል። በዚህም ሂደት ሰዓሊያኑ (ባለሙያዎቹ) ለማሳያ ቦታ ምንም አይነት የኪራይ ክፍያን እንደማያወጡ፣ ለሚታተሙት መፅሔቶችና በራሪ ወረቀቶች እንደማይጠየቁና ከሰዓሊያኑ የሚጠበቀው ብቸኛ ነገር ሰርዓቱን የጠበቀና ለተመልካቹ የሚመጥን ስራዎችን ይዞ መቅረብ እንደሆነ ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ ይናገራሉ። ይህም ሲባል የስዕል ሥራዎቹ ከሀይማኖትና ከፖለቲካ ነፃ መሆናቸው ቅድሚያ ይሰጠዋል ሲሉ ያስምሩበታል።

በቶሞካ አርት ጋለሪ የስዕል ስራዎች ለተመልካቹ ከመቅረባቸውም ባሻገር ሥራዎቹ የመታያ ጊዜያቸውን አጠናቀው ከጋለሪው ከመውጣታቸው በፊት የውይይት ፕሮራሞችና የባለሙያ አስተያየቶችም እንደሚስተናገዱበት ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ ይናገራሉ። ያም ሆኖ ምንም አይነት ሽያጭ በቤቱ ውስጥ እንደማይከናወን የጋለሪው ማኔጂንግ ዳይሬክተር የሆነው ጋዜጠኛ ነብዩ ግርማ አፅንኦት ሰጥቶ ይናገራል።

ለቀጣዮቹ ሁለት ወራት በቤቱ ተረኛ የሆነው የአርቲስት ቴዎድሮስ መስፍን (ቴዲማን) ስራዎችን በተመለከተ ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ ሲመልሱ፣ “ስራው ስዕላዊ ስላቅ በመሆኑ የተለየ ጠዓም አለው” ሲሉ ይገልፁታል። አክለውም ሰዓሊው ይህንን የስዕል ዘውግ ሙያዬ ብሎ አጥብቆ መያዙ በራሱ ሊያስከብረው ይገባል ያሉ ሲሆን፤ እስካሁን በቶሞካ አርት ጋላሪ ከቀረቡት የቅብ የስዕል ስራዎች የተለየ በመሆኑም የብዙዎችን ቀልብ ይስባል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ግምታቸውን አስቀምጠዋል። ኢትዮጵያውያን የሥነ-ቃል ወዳጆች ከመሆናችን የተነሳ በሰው ፊት ላይ ይህን መሰል የስዕል ጥበብን መስራት ከባድ እንደሆነ የሚያስረዱት የጋለሪው አርት ዳይሬክተር ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ በትንሽ - በትንሹም ቢሆን መሰል የስዕል ስራዎችን ማስለመዱ መልካም ነው።

በመክፈቻው እለት የስእል ዐውደ-ርዕይውን ለመታደም በቶሞካ አርት ጋለሪ ከተገኙት ተመልካቾችም መካከል ይህንኑ የሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህን ሀሳብ የሚያጠናክር ምላሽ የሰጡን በርካቶች ነበሩ። በመጀመሪያ ያናገርነው የተባለ ወጣት አልፎ አልፎም ቢሆን የስዕል ዓውደ-ርዕይዎችን የማየት አጋጣሚው እንዳለው የሚናገረው ፍሬው ዮሴፍ ባህልን በማስተዋወቅ ስራ ላይ የተሰማራው ወጣት ነው። በቀረቡት ስራዎች በጣም ደስተኛ መሆኑንና ከዚህም ቀደም በጋዜጦችና መፅሔቶች ላይ መሰል የካርቱን ስራዎችን የሚከታተል እንደሆነ በማስታወስ በቶሞካ አርት ጋለሪ የቀረቡት የአርቲስት ቴዲማን ስራዎች ደግሞ የበለጠ አዝናኝና አመራማሪ ሆነው እንዳገኛቸው ይገልፃል። “ስራዎች በታዋቂና አርአያ መሆን በሚችሉ ሰዎች ፊት ላይ በመሰራቱ ከአዝናኝነቱ በተጨማሪ በራስህን ግምት የምትዝናናበት ቦታ ነው” ብሏል።

ከቀረቡት ስራዎች መካከል የትኛውን ገምቶ እንደተሳካለት የጠየኩት ወጣት ፍሬው፤ “እጅግ ደስ ያለኝ ስራ የአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ገጽ ላይ የተሰራው ስራ ነው” ሲል መልሷል። ይሁን እጂ ሲመጣ አንዳቸውንም ሊለያቸው አዳግቶት እንደነበር ያስታውሳል።

ቶሞካ ቡና ለመጠጣት የመጣን ተሰተናጋጅ እግረ-መንገዱን በነፃ የስዕል ስራዎቹን እንዲመለከት ማስቻል የቶሞካ አርት ጋለሪ ቀደምት አላማ ስለመሆኑ የሚናገረው የጋለሪው ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ነብዩ ግርማ፤ ቶሞካ ተከፍቶ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ 63 ዓመታትን ያስቆጠረ ታሪካዊ ቤት መሆኑን ጠቅሶ፤ እነሆ በሁለት ዓመታት ውስጥ ለ13ኛ ጊዜ መሰል የስዕል ስራዎችን በማሳየት ላይ እንደሚገኝና በቀጣይም በዓመት ውስጥ አራት የስዕል አውደ-ርዕይዎች የማዘጋጀት እቅድ መኖሩን አስታውቋል። በቤቱ ውስጥ ምንም አይነት የስዕል ሽያጭ እንደማይከናወን የሚናገረው አቶ ነብዩ፤ “የአውደ-ርዕይው” አላማ ቡና ለመጠጣት የመጣን ተመልካች ከስዕል እና ከሰዓሊው ጋር ማስተዋወቅና ማቀራረብ ነው ይላል።

በዓውደ-ርዕይው ከታደሙት ተመልካቾች መካከል በሽያጭ ባለሙያነት የምትሰራ ወጣት አግኝተናል፤ ወጣቷ ቃልኪዳን ትባላለች። በስፍራው በአግርሞት በምትመለከታቸው ስራዎች መካከል እንዳለች ምን እየደተሰማት ጠይቀናታል። “ከሁሉም ያስደሰተኝ ስራዎቹ በሙሉ በእርሳስ ብቻ መሰራታቸው ገርሞኛል። ሌላው ደግሞ ሰዎቹ የቱንም ያህል ታዋቂ ሰዎች ቢሆኑም እንዳየሃቸው ወዲያው አታውቃቸውም። ከዚህም ውጪ የቀረቡት ስራዎች የሰዓሊውን የተለየ አሳሳል በጉልህ ማሳየት የቻለ ነው” ስትል ምላሽ ትሰጣለች። ከዚህ ቀደም ካየቻቸው የስዕል ዓውደ-ርዕይዎች ፎርም የተለየ ነው የምትለው ቃልኪዳን፤ በሰዓሊው አስተውሎት በመገረም በቅርብ የምታወቃትንና የምታደንቃትን አርቲስት ሜሮን ጌትነትን እንኳን መለየት አለመቻሏ እንዳስገረማት፤ ነገር ግን በኋላ ስትገነዘብ ቅንጣት የሚመስሉ ነገሮች ጭምር መሳላቸው ሰዓሊው ያለውን አስተውሎት እንድታደንቅ ማድረጉን ትናገራለች።

በቶሞካ አርት ጋለሪ ለሁለት ወራት በሚቆየው የስዕል ዓውደ-ርዕይ በርካቶች በድጋሚ የመታደም ፍላጎት እንዳላቸውና ከሰዓሊውም ጋር የመገናኘት እቅዱ እንዳላቸው ሲናገሩ የተደመጠ ሲሆን፤ አርቲስት ቴዲማን በበኩሉ በሳምንት ውስጥ ሙሉውን ጊዜ ባይሆን እንኳን የሳምንቱ መጨረሻ ቀናትን ከተመልካቹ ጋር በመገናኘት የስዕሉ ተመልካቾች የሚሰማቸውን ስሜት ለማወቅ ዝግጁ መሆኑን ይናገራል።

“ቤቱም የተለየ ነው የሰዓሊው ስራዎችም የተለዩ ናቸው” የሚለው የቶሞካ አርት ጋለሪ ማኔጀር ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ነብዩ ግርማ፤ መሰል ለህብረተሰቡ አገልግሎት በመስጠት ስራ ላይ የተሰማሩ ተቋማት የቶሞካን አርአያነት ቢከተሉ በርካታ ጥበቦችንና ጥበበኞችን ለአደባባይ ማብቃት ይቻላል ባይ ነው።

በቶሞካ አርት ጋለሪ የሚታየው የስዕል ስራዎች ከተሰባጠሩ የሙያ አካላት በተወከሉ የቦርድ አባላት አማካኝነት የሚመረጥበት መስፈርት እንዳለ የሚያስረዳው ጋዜጠኛ ነብዩ፤ ስራዎች አሉን የሚሉ ሰዓሊያንም የመሳተፍ ዕድሉ እንዳላቸው አስታውቋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
10910 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us