አዶት ሲኒማ እና ቴአትር የጥበባት - እናት

Wednesday, 11 February 2015 12:20

 

 

የአዶት ሲኒማና ቴአትር ባለቤት እና

ሥራ አስኪያጅ አቶ አልፈረድ ከማል

 

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ካሉ በጣት የሚቆጠሩ የሲኒማ አዳራሾች በይዘቱም ሆነ በዓይነቱ አንድ እርምጃ ቀደም ያለ ነው ተብሎለታል። ባሳለፍነው ቅዳሜ ጥር 30 ቀን 2007 ዓ.ም ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው - አዶት ሲኒማና ቴአትር። አዶትን ለየት ከሚያደርጉት የአዳራሽ ስፋቱ፣ ምቹ መቀመጫዎቹና ከዙሪያ ገብ የድምፅና የምስል ቴክኖሎጂዎቹ በተጨማሪ አዳራሹ ለፊልም ብቻ ሳይሆን ለቴአትር፣ ለስታንድአፕ ኮሜዲዎች፣ ለግጥም ምሽቶችና ለሌሎችም የኪነ-ጥበብ ሥራዎች ምቹ ሆኖ መገንባቱ ነው።

አዶት ሲኒማና ቴአትር 420 መደበኛ እና 180 የልዩ ማዕረግ (VIP) በድምሩ 600 የሚደርሱ ተመልካቾችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የሚችል ሲሆን፤ ከዚህም መካከል ለአካል

ጉዳተኞች አመቺ የሆነ መቀመጫ ተዘጋጅቷል። ይህም ብቻ ሳይሆን በአዶት ኢንተርናሽናል ትሬዲንግና በአናቤ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ ውስጥ ከ180 በላይ ለሚደርሱ ሰዎችም ቋሚ የሥራ ዕድልን መፍጠር የቻለ የመዝናኛ ስፍራ ነው። ይህም ለበርካታ የከተማዋ የኪነ-ጥበብ አፍቃሪዎች እንደ አማራጭ ሆኖ ከመቅረቡም በተጨማሪ ለኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችም የማሳያ ስፍራን በተመለከተ ለሚገጥሟቸው ፈተናዎች እንደመደላድል ሆኖ በምርጥነቱ የሚመረጥ ያደርገዋል።

አዶት ማለት በጉራግኛ ቋንቋ “እናት” ማለት ሲሆን፤ በሲኒማና ቴአትር አዳራሽም ከፊልም፣ ከቴአትር፣ ከሙዚቃና ከግጥም ምሽቶች በተጨማሪ ልዩ ልዩ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን ማስተናገድ መቻሉ አዶትን የኪነ-ጥበብ እናት እና መዳረሻ ያሰኘዋል። የግንባታ ሂደቱን በተመለከተ በአዳራሹ ለታደሙት እንግዶች ንግግር ያደረጉት የአዶት ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና የአልፈሪድና ቤተሰቡ (አናቤ) ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ አልፈሪድ ከማል፤ “የንግድ ተቋማት ትርፍ ማግኘት ዋናው ዓላማቸው ቢሆንም፤ ይህን ውጤት በአጭር ጊዜ ለማሳካት ከሚያስችል መስክ በመውጣት ብዙም ባልተሰራበት ሲኒማና ቴአትር ቤት ኢንቨስትመንት ውስጥ እንድንሳተፍ ስንወስን የዛሬውን ሳይሆን የሩቁን አስበን ነው” ብለዋል። በዚህም የአዶት ሲኒማና ቴአትር መገንባት ከአማራጭ የመዝናኛ ማዕከልነቱ ባሻገር ባህልና ኪነ-ጥበብን በማስተዋወቅ እንዲሁም ለባለሙያዎች ስራዎቻቸውን የማሣያ ቦታ በመስጠት እንደ አንድ ማኅበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት መስራታቸውን አስረድተዋል።

በአዶት ሲኒማና ቴአትር ደማቅ የምረቃ ፕሮግራም ላይ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሙሉጌታ ሰኢድን ጨምሮ በርካታ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የመገናኛ ብዙሃን አባላት ተገኝተዋል።

በ2 ሺህ 350 ካሬ ሜትር ላይ ህንፃውን የገነባው አዶት ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ፤ መሠረቱ አናቤ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ መሆኑ ሲታወስ በቤተሰቡ ጥረት እያደገና እየሰፋ የመጣ ተቋም ስለመሆኑም በምረቃ ፕሮግራሙ ወቅት ተነግሯል። አዶት ሲኒማና ቴአትር ሥራ መጀመሩ ለበርካታ ወጣቶች የመዝናኛና የባህል ማሳያ እንደሚሆን ተስፋቸውን የገለፁት የዕለቱ የክብር እንግዳ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሙሉጌታ ሰኢድ፤ በትርኢት ማሣያ ስፍራዎች እጥረት ምክንያት የፈጠራ ባለሙያዎች ያላቸውን አቅም በሙሉ ተጠቅመው ጥበብን እንዳያበረክቱ የተጋረጠውን እንቅፋት (አዶትን) መሰል የመዝናኛ ስፍራዎች ሊፈቱት እንደሚችሉ ያላቸውንም ተስፋ ገልፀዋል።

በከተማችን ውስጥ ተገንብተው አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት የሲኒማ አዳራሾች ቁጥር ጥቂት ነው ባይባልም አብዛኞቹ ተቋማት ግን የተለያዩ የኪነ-ጥበብ ትርኢቶችን ለማቅረብ በሚያስችል መልኩ ከመነሻው ታቅደው አለመሰራታቸው ወደአገልግሎት በሚገቡበት ወቅት የሚገጥማቸው የአቅም ውስንነት በግልፅ የሚታይ ነው የሚሉት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታው፤ “አዶት ሲኒማና ቴአትር ግን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ታስቦበት የተሰራ በመሆኑ ለተመልካችና ለኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የሚሰጠው እርካታ እንዳለ ሆኖ ኪነ-ጥበብንም አንድ እርከን ከፍ ያደርጋል” ብለዋል።

የሲኒማና ቴአትር አዳራሽን በተሟላና ዘመናዊ መልኩ ገንብቶ ለማጠናቀቅ ከሦስት ዓመታት ያላነሰ ጊዜን እንደወሰደባቸው የተናገሩት ባለቤቱና ሥራ አስኪያጁ አቶ አልፈሪድ ከማል፤ በተለይም የህንፃ ግንባታ ቁሳቁሶች ዋጋ በየጊዜው ማሻቀብና ከውጪ ሀገር የገቡ ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች በርከት ያለ የውጪ ምንዛሬ መጠየቃቸው በቅድሚያ ተይዞ ከነበረው በጀት ከ60 በመቶ በላይ ስለማስጨመሩም አልሸሸጉም። በመሆኑም ይህን ታላላቅ የሥነ-ምህንድስና ባለሙያዎችና አማካሪ ተቋማት የተሳተፉበትን ዓይነ-ግቡ ሲኒማና ቴአትር ቤት ገንብቶ ለመጨረስ ከ180 ሚሊዮን ብር በላይ ፈሰስ መደረጉ ታውቋል። በመድረኩም ሥራው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድጋፋቸውን ላልነፈጉ የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ የግል ተቋማትና ግለሰቦች የምስጋና ሽልማትና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።

የአዶት ሲኒማና ቴአትር አዳራሽ በተመረቀበት ዕለት የሲኒማውን የምስልና ድምፅ ደረጃ የሚያመላክት በ3ዲ መነጽር የታገዘ ፊልም ለታዳሚያኑ የቀረበ ሲሆን፤ በደራሲ ሉዋን.ጂ. ትራዴሎ የተፃፈውና በ1970ዎቹ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት መምህራንና ተማሪዎች ተተርጉሞ በተስፋዬ ገ/ማርያም የተዘጋጀው “ሞርሳው” የተሰኘ አጭር ድራማም ለመድረክ በቅቷል። በትወናው አለማየሁ ታደሰ፣ ሽመልስ አበራ (ጆሮ)፣ መሠረት ህይወትና አዲስዘመን አደላ ናቸው። ከዚያም በመቀጠል የተመሰገን ልጆች በመባል የሚታወቁት የዳንስ ቡድን አባላት በባህላዊና ዘመናዊ ሙዚቃዎች የተቀናበሩ የውዝዋዜና የዳንስ ትርኢቶቻቸውን ለታዳሚው አቅርበው አድናቆትን አግኝተዋል።

     አዶት ሲኒማና ቴአትር ብስራተ ገብርኤል አካባቢ በሚገኘው አዶት መልቲፕሌክስ ህንፃ 4ኛ ፎቅ ላይ በይፋ ሥራውን የጀመረ ሲሆን፤ የከተማችን የመብራት መቆራረጥ የማያሰጋውና ለ24 ሰዓታት ያለምንም መቆራረጥ የኃይል አቅርቦት መስጠት የሚችል ዘመናዊ ጄኔሬተር ተተክሎለታል። አዶት ሲኒማና ቴአትር በተለያዩ የኪነ-ጥበብ ዘርፎች ውስጥ የሚገኙ ባለሙያዎች ጥራታቸውንና ደረጃቸውን የጠበቁ ሥራዎቻቸውን ይዘው በመምጣት ያለ አንዳች ደጅ መጥናት እና ክፍያ አንቱ በተሰኙ ባለሙያዎች አማካኝነት ሥራዎቻቸው ተገምግመው ለዕይታ መብቃት እንደሚችሉ ለማወቅ ተችሏል።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
15579 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us