ልዑል ሲኒማ፤ የኢንጂነሩ “አናት”

Wednesday, 18 February 2015 14:10

       ከአፈር ቁፋሮው ጊዜ ጀምሮ “አናት” የተሰኘ ስያሜ በተሰጠው ህንፃ ላይ የተከፈተው “ልዑል ሲኒማ” ባሳለፍነው ቅዳሜ የካቲት 7 ቀን 2007 ዓ.ም የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሙሉጌታ ሰዒድ፣ አንጋፋው የማስታወቂያ ባለሙያ አቶ ውብሸት ወርቃለማሁና የቀድሞ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ሙሉ ሰለሞንን ጨምሮ በርካታ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በይፋ ተመርቋል።

48 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የመጣበት “አናት” የገበያ ማዕከል በ540 ካሬ ሜትር ላይ ተንጣሎ የተገነባ ባለስድስት ፎቅ ህንፃ ነው። በአሁኑ ወቅት ከ36 በላይ የንግድ ድርጅቶች በህንጻው ውስጥ ስራ የጀመሩ ሲሆን፤ በአምስተኛው ፎቅ ላይ የሚገኘው ልዑል ሲኒማም ከወራት በፊት ሀገርኛ ፊልሞችን የማሳየት ስራውን ጀምሯል።

“ልዑል ሲኒማ” የልዩ ማዕረግ መቀመጫዎችን ጨምሮ 412 ተመልካቾችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የሚችል ሲሆን፤ ለተለያዩ የፊልም ስራዎችም ሁነኛ አማራጭ ሆኖ እንደሚያገለግል የሲኒማ ቤቱ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ልዑል አበበ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

በኢንጂነር አበበ አያሌውና ቤተሰባቸው በተገነባው “አናት” የገበያ ማዕከል ላይ ይፋ የሆነው ልዑል ሲኒማ፤ ለጥበብ ሥራዎች ራስ መሆን እንደሚችል በምረቃ በዓሉ ላይ የተገኙ ታዳሚያን ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።  

በክብር እንግድነት በልዑል ሲኒማ ከተገኙት መካከል ወ/ሮ ሙሉ ሰለሞን ይገኙበታል። በሲኒማ ቤቱ መገንባት የተሰማቸውን ስሜት ለታዳሚያኑ ሲገልጹ፣ “ይህን የመሰለ የሲኒማ አዳራሽ ማግኘት መታደል ነው። ጓደኞቼ ፊልም ፅፈው ከሰሩ በኋላ ለማሳየት ከ6 ወራት በላይ ይወስድባቸዋል። ይህን መሰል ሲኒማ ቤት ግን በተለያዩ ሰዓታት ፊልሞችን ማሳየት ከቻለ በጥቂቱም ቢሆን በፊልም ወረፋ ምክንያት የሚከሰተውን ችግር ያቃልለዋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።

በዕለቱ ከተገኙት ንግግር ካደረጉት የክብር እንግዶች መካከል የአንበሳ ማስታወቂያ ድርጅት ባለቤትና ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ ይገኙበታል፤ ኢንጂኒየር አበበና ቤተሰቦቻቸው ከሀሳብ በዘለለ ይህን የመሰለ ህንፃና ሲኒማ ቤት በመገንባታችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ ካሉ በኋላ “ይህን መሰል ውብ አዳራሽ መገንባት ለአፍሪካ መዲናይቱ አዲስ አበባ ትልቅ ስጦታ ነው” ሲሉ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

የአናት የገበያ ማዕከል ባለቤትና ስራ አስኪያጅ የሆኑት ኢንጂነር አበበ አያሌው በምረቃ በዓሉ ላይ ለተገኙ እንግዶች ንግግር ያደረጉ ሲሆን፤ ህንጻው ከአፈር ቁፋሮ ስራው ጀምሮ አናት የተሰኘ ስያሜ የተሰጠው እንደሆነ አስታውሰዋል። አናት ማለት አበበና ትህትና የሚለውን የቤተሰቡን ስም በምህፃረ ቃል የያዘ መሆኑንም ተናግረዋል። ስያሜው የተመረጠው ከ12 ዓመታት በፊት ሲሆን አሁንም ድረስ በንግድና ኢንዱስትሪ በኩል ከፖሊሲ አንፃር መስተካከል አለበት በሚል አለመጽደቁን አስታውሰው፤ የስያሜውን ተገቢነት ተገንዝበው በቅርቡ እንደሚያፀድቁላቸው ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

በአንድ ዓመት ከ6 ወራት ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት የጀመረው አናት ህንጻ፤ የመሬት ግዢውን ጨምሮ 48 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር ወጪም ተደርጎበታል። በአጠቃላይ የውጪው የተሸፈነውም ከቤተሰብ ገቢ እና ከንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በተገኘ ብድር መሆኑንም የህንፃው ባለቤትና ስራ አስኪያጅ የሆኑት ኢ/ር አበበ አያሌው ይናገራሉ። ለህንፃ ግንባታው የዋሉት መሣሪያዎች ሲኒማ ቤት መገልገያ ወንበሮችን ሳይቀር ከቀረጥ ነፃ ያልገቡና ሁሉም ከሀገር ውስጥ ነጋዴዎች የተገዙ መሆናቸውን አስታውሰው፤ ይህም ለህንፃው ስራ በጥራት መጠናቀቅ የነበረውን ጥረት ለዋጋው ከፍተኛነት አስተዋፅኦ እንደነበረው አስረድተዋል።

በአናት የገበያ ማዕከል ህንፃ ውስጥ በሚገኘው የመኪና ማቆሚያ ጨምሮ ራሱን የቻለና የመብራት መጥፋትን ከግምት አስገብቶ መስራት የሚችል ግዙፍና ፈጣን ጀኔሬተር ያለ ሲሆን፤ በህንፃው እስከ 3ኛ ፎቅ ድረስ የተለያዩ የንግድ መደብሮች፤ 4ኛ ፎቅ ላይ ለቢሮ አገልግሎት የሚውሉ ክፍሎች፤ በ5ኛ ፎቅ ሲኒማና ካፌን ጨምሮ የሚገኝ ሲሆን፤ በስድስተኛው ፎቅ ላይ የባርና ሬስቶራንት ቦታዎችን አካቶ የያዘ መሆኑ ተነግሯል።

በልዑል ሲኒማ የምረቃ በዓል ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሙሉጌታ “ሲኒማ ባህላችንን የምናስተዋውቅበትና ትውልድን የምንቀርፅበት መስክ ነው። ባለሀብቶችም ህንፃና መንገድ ብቻ ሳይሆን የሰው አእምሮም መገንባት አለበት በሚል፤ ዜጎችን በጥበብ ጎዳና ለማነፅና የአገሪቱንም ገጽታ ይበልጥ ለማጉላት እንዲህ ዓይነት የጥበብ ማዕከል በመገንባት የራሳቸውን አስተዋፅኦ በማበርከታቸው ሊመሰገኑ ይገባቸዋል” ብለዋል።

ብዙም አትራፊ ባልሆነው የፊልም ስራ ውስጥ በርካታ ወጣቶች ተሰማርተው ይገኛሉ ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ብዙዎቹም የፊልም ማሳያ ቦታ እያጡ ከሚጠብቃቸው በጣም የረዘመ ወረፋ አንፃር ልዑል ሲኒማ ቤት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን አሰልቺውን ጥበቃ ይቀንሰዋልና ለባለሙያዎቹም ታላቅ የምስራች እንደሚሆን ተስፋ አለኝ ብለዋል። በቀጣይም መንግስት የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ መሰል የጥበብ ማዕከላትን የመደገፍ ውጥን እንዳለው ገልጸዋል።

     ልዑል ሲኒማ በይፋ ስራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የተለያዩ የአገር ውስጥ ፊልሞችን በማሳየት በከተማችን ውስጥ አማራጭ ሲኒማ እየሆነ መምጣቱን የሚናገረው የሲኒማ ቤቱ ስራ አስኪያጅና ባለቤት አቶ ልዑል አበበ፤ በስሩም በቋሚነት ለ18 ሰዎች የስራ እድልን ፈጥሯል ብለውናል። ከዚህም ባለፈ ልዑል ሲኒማ የራሱን ፕሮዳክሽን አቋቁሞ ፊልሞችንና ዘጋቢ ፊልሞችን በመስራት የተሻለ ውጤት ለማምጣት ዓላማ አለው ብለዋል።

ልዑል ሲኒማ ደረጃቸውን የጠበቁ ፊልሞችን ያለምንም ውጣ ውረድ ለማሳየት እንደሚሰራ የተናገሩት የሲኒማ ቤቱ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ልዑል አበበ፤ ፊልሞችን ገምግሞ ለስክሪን ለማብቃት በመሰኩ የተመረቁ ባለሙያዎችን ቀጥረን እያሰራን ነው ብለዋል። በዚህም የምዘና ሂደቱ ፍትሃዊ ነው ተብሎ ይጠበቃል ብለውናል።

ምቹ ወንበሮችና የአየር መቆጣጠሪያ የተገጠመለትን ሲኒማ ቤት የሚረግጡ አብዛኞቹ ተመልካቾች ወጣቶች መሆናቸው ከግምት በማስገባት ዋጋችን ተመጣጣኝ ነው ያሉት አቶ ልዑል፤ ከሰኞ እስከ ዓርብም ሆነ ቅዳሜና እሁድ በማንኛውም ሰዓት ወደሲኒማ ቤታችን የሚመጡ ተመልካቾች የሚከፍሉት 35 ብር ብቻ ነው ብለዋል።   

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
15547 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us