“ብራና” እንደንባብና መዝናኛ ፕሮግራም

Wednesday, 25 February 2015 12:10

 


የብራና ፕሮግራም አዘጋጅ በፍቃዱ አባይ

 

በንባብ ዙሪያ ትኩረቱን አድርጎ ላለፉት አምስት ዓመታት በኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ዘወትር እሁድ ምሽት ሲተላለፍ የቆየው ብራና የተሰኘው የንባብና የመዝናኛ ፕሮግራም በርካታ አድማጮች አሉት። ባሳለፍነው የካቲት 9 ቀን 2007 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሆቴል በተካሄደው የ5ኛ ዓመት በዓሉ ላይ በርካታ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። ለዛሬ ከፕሮግራሙ መስራችና ዋና አዘጋጅ በፍቃዱ አባይ ጋር ስለፕሮግራሙ አነሳስና አካሄድ ጥቂት ተጨዋውተናል። በፍቃዱ አባይ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ ሲሰራ የቆየ ባለሙያ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ፈቃድ ባገኘበት እናት የማስታወቂያ ሥራዎች ድርጅት ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ሆኖ የብራና ፕሮግራምን በመስራት ላይ ይገኛል። መልካም ቆይታ. . .

ሰንደቅ፡- የብራና ፕሮግራም ዝግጅት ዓላማው ምን ነበር?

በፍቃዱ፡- ከአምስት ዓመት በፊት ኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ሬዲዮ ጣቢያ ማስታወቂያ አውጥቶ ነበር። በማታወቂያው ለጣቢያው የሚመጥኑ ትምህርታዊና አዝናኝ ፕሮግራሞችን እንፈልጋለን የሚል ነገር ነበረው። ማስታወቂያውን እንደሰማው እንደማህበረሰብ የሚጎድለን ምንድነው? በሚለው ዙሪያ በጣም አስብ ነበር። ሚዲያ ላይ ከመስራትና ገንዘብ ከማምጣት ባሻገር ህብረተሰባችንን አንድ ደረጃ ከፍ ሊያደርግ የሚችል አስተማሪና አዝናኝ ፕሮግራም ለመቅረፅ ብዙ አስብ ነበር። እንደጋዜጠኛነቴ ለንባብ ቅርብ ነኝ። ስለንባብም ብዙ አስብ ስለነበር በዙሪያዬ የተሻለ ሀሳብ ካላቸው ጓደኞቼ ጋር አወራንበት። ከዚያም የዕቅድ ሃሳቡን (proposal) ሰርቼ፤ ለርዕሰ ጉዳያችን የሚስማማ የፕሮግራም ስም ስንፈልግ “ብራና” የሚለው መጣ። እንደሚታወቀው ብራና ከኢትዮጵያ ታሪክና ፅሁፍ ጋር የተቆራኘ ነው። አባቶቻችን እስካሁን ድረስ ታሪክ ያቆዩልን በብራና ላይ ፅሑፍ ነው። ዋናው ዓላማችን ግን የንባብ በዓልን ለማበረታታት ታስቦ የተጀመረ ፕሮግራም ነው ማለት ይቻላል።

ሰንደቅ፡- የብራና ፕሮግራም ምን ለውጥ አመጣ?

በፍቃዱ፡- ብዙ ለውጦችን አምጥተናል ማለት እንችላለን። ለመነሻ ያህል እኛ ፕሮግራሙን ከመጀመራችን በፊት ምንም አይነት በንባብ ላይ የሚሰሩ የሬዲዮ ፕሮግራሞች አልነበሩም። አሁን በግምት አምስትና ስድስት የሚሆኑ መሰል ፕሮግራሞች በተለያዩ ጣቢያዎች የአየር ሰዓት አግኝተዋል። ይህ በእኛ ኩርኮራ የፈጠረ ተፅዕኖ ነው ብዬ አምናለሁ። ሌላው ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት ይህን ያህል የመፅሐፍት አዟሪዎች አልነበሩም። አሁን ግን እንደምታየው ነው። ምንድነው መሰለህ እኛ እሁድ ማታ ያስተዋወቅናቸው መፅሐፍት ጠዋት ላይ በአዟሪዎች እጅ ሲገቡ እናያለን። ይህም የፕሮግራማችንን ተፅዕኖ ፈጣሪነት የሚያሳይ ይመስለኛል።

ሰንደቅ፡- ስለንባብ ሲታሰብ በኑሮ ደረጃ ከታችኛውና ከላይኛው የህብረተሰብ ክፍል አንፃር የትኞቹ በጥሩ አንባቢነት መጠቀስ ይችላሉ?

በፍቃዱ፡- እውነቱን ለመናገር በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያለው የህብረተሰባችን ክፍል የማንበብ ፍላጎቱ በጣም ከፍተኛ ነው። በርግጥ ጥናት የሚፈልግ ጥያቄ ነው። ነገር ግን እንደኔ ምልከታ በዝቅተኛ ኑሮ ላይ ናቸው የሚባሉቱ ብዙ ያነባሉ የሚል ግምት አለኝ። እነዚህ ሰዎች የንባብ ፍላጎቱ አላቸው። የማንበቢያ ጊዜም አላቸው፤ ነገር ግን መፅሐፍቱን የማግኘት ችግር ያጋጥማቸዋል። በተቃራው ኑሯቸው ደህና ነው፤ ሀብት አላቸው የሚባሉ ሰዎች በትላልቅ ቤቶቻቸው ውስጥ አንድም መፅሐፍ ላይኖር መቻሉን በስራ አጋጣሚ ታዝቤያለሁ።

ሰንደቅ፡- በስራ አጋጣሚ የታዘብከው ነገር ካለ በጣም ዝነኛ ከሆኑና በአገራችን ከሚከበሩ ሰዎች መካከል በአንባቢነታቸው የምታመሰግናቸው አሉ?

በፍቃዱ፡- በርግጥ ብዙ የሚያነቡ ዝነኞች እንዳሉ አውቃለሁ። አንደኛው ፀጋዬ ዮሐንስ ነው። ከእርሱም ሌላ በኮሜዲ ስራ፣ በትወናና በአርት ውስጥ ያሉ ብዙ አንባቢያን አሉ።

ሰንደቅ፡- እነዚህን ዝነኛ ሰዎች ከንባብ ጋር ወደሚዲያው ማምጣት ለሌላው ህብረተሰብ እንደማነቃቂያ መጠቀም አያስችልም?

በፍቃዱ፡- በትክክል ይቻላል። በቀጣይ ለመስራት ካሰብናቸው ፕሮግራሞች መካከል አንዱ እሱ ነው። እንደአጋጣሚ ሆኖ ዝነኞቻችን በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ፊት ይቀርባሉ። አንድም ቀን ግን ስለንባባቸው ሲጠየቁ ሰምቼ አላውቅም። እንደውም አንድ ታዋቂ ሰው በኢቲቪ ቀርቦ “ከንባብ ነፃ” መሆኑን በኩራት ሲናገር በመስማቴ በጣም አፍሬያለሁ። ባይገርምህ ይህን ሃሳብ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ፅሁፍ ፅፎበታል። ልጁ የሰውዬውን ንግግር ሰምታ አባቷን፤ ይህው “እገሌ” እኮ ዝነኛና ሀብታም ሆኖ አያነብም እኔን ለምን አንብቢ ብለህ ወጥረህ ትይዘኛለህ? ብላ እንደጠየቀችው ይናገራል። ይህ በጣም ከባድ ነገር ነው። እንደአርአያ የምናያቸው ሰዎች የማያነቡ ከሆነ ትውልዱንም ነው የሚቀጥፉት።

ሰንደቅ፡- እስቲ ደግሞ ግላዊ ጥያቄ ልጠይቀህ፤ ንባብ ለአንተ ምን ጨመረልህ?

በፍቃዱ፡- ንባብ በግሌ ሙሉ ሰው እንድሆን አድርጎኛል ብዬ አምናለሁ። የማላነብ ሰው ብሆን ኖሮ ያለኝ ዲግሪ ብቻ የአሁኑ በፍቃዱን ላይፈጥረው ይችላሉ። ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ አነባለሁ። ከሰው ጋር ተቀጣጥሬ ካፌ ውስጥ ላነብ እችላለሁ። በታክሲ ውስጥ ላነብ እችላለሁ። ቢያንስ ደግሞ ማታ ከመተኛቴ በፊት የተወሰኑ ገፆችን ማንበብ ልምድ አድርጌያለሁ።

ሰንደቅ፡- ምን አይነት ፅሁፎች ያዝናኑሃል?

በፍቃዱ፡- ለመዝናናት ወጎችን፣ ግጥሞችንና የተለያዩርዕሰ ጉዳዮችን በሚያዝናና መልኩ የሚያቀርቡ ስራዎችን እመርጣለሁ። ብዙ ጊዜ እኔ የምወዳቸው እያመሙኝ የሚስቁኝን ስራዎች ናቸው። እነዚህን ስራዎች ከጋዜጣና ከመፅሔትም ላይ ቢሆን ፈልጌ አነባቸዋለሁ። በተረፈ ግን የተለየ ነገር ይዞ ካልመጣ ልቦለድ ከማነብ ይልቅ ኢ-ልቦለድ ስራዎችን ማንበብ እመርጣለሁ።

ሰንደቅ፡- ካነበብካቸው ስራዎች መካከል በተለየ የምትወዳቸው?

በፍቃዱ፡- ከልቦለድ ከተነሳሁ የዘነበ ወላ “ልጅነት” ለኔ የተለየ ስራ ነው። ልጅነቴን በደንብ ያየሁበት ስራ ነው። ሰዎች ንባብ ሲጀምሩ “ልጅነትን” በማንብ ቢጀምሩ እመክራለሁ፡፤ ከወግ ስራዎች ደግሞ የጋሽ መስፍን “የቡና ቤት ስዕሎች” ይጠቀሳል። ሌላው ግን መሀመድ ስልጣን አዲስ የአፃፃፍ ዘይቤን ይዞ ስለመጣ “ፒያሳ መሀሙድ’ጋ ጠብቂኝ” ደስ ይለኛል። ከኢ-ልቦለድ ስራዎች ግን ብዙ የምጠቅሳቸው አሉ። ለምሳሌ በቅርብ ካነበብኩት “Twor in the sky” (ማማ በሰማይ ተብሎ ተተርጉሟል)፣ የዶ/ር መረራ ጉዲና እና የዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ መፅሐፎች በጣም ተመችተውኛል። ሌላው የገብሩ አስራት “ሉአላዊነት በኢትዮጵያ” ጥሩ ስራ ነው። ሰዎች እንዴት ጥናትን መሰረት አድርገው መፃፍ እንዳለባቸው የሚያስተምር ስራ ነው። ሌሎችም አሉ።

ሰንደቅ፡- በብራና ፕሮግራም ምክንያት የመጡመልካም የምትላቸው አጋጣሚዎች ምንድናቸው?

በፍቃዱ፡- አሁን አሁን የሚያስደስተኝ ነገር በሁሉም ጆሮዎች ውስጥ “ብራና” አለች ብዬ አስባለሁ። ፕሮግራሙ ብቻ ሳይሆን “ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል የምትለዋ ሃይለ መልዕክት ራሱ በደንብ ሰርጿል ብዬ አስባለሁ። ሌላው ከምናገኛቸው መልዕክቶች መካከል በአንደኛ፣ በሁለተኛና በኮሌጅ ደረጃ ያሉ ተማሪዎች በጣም በንባብ ጉዳይ ላይ እየሰሩ ነው። በአንዳንድ መስሪያ ቤቶች ደግሞ የንባብ ክበባት፣ የንባብ ማህበራት ብሎም የመፅሐፍት እቁቦች እየተቋቋሙ መሆኑን ስንሰማ በእጅጉ ነው የሚያስደስተን።

ሰንደቅ፡- ንባብ ለሁሉም ሰው ያስፈልጋል። ነገር ግን በይበልጥ ለደራሲያን፣ ለመምህራንና ለጋዜጠኞች ንባብ ወሳኝ ይመስለኛል። እነዚህ ሰዎች ካላነበቡ በሀገር ላይ የሚፈጠረውን ተፅዕኖ ስታስበው ምን ይሰማሃል?

በፍቃዱ፡- ትልቁን ነጥብ ነው ያነሳኸው። የሚዲያው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም። ለምሳሌ የካቲት 7 ቀን 2007 ዓ.ም አብዛኛውን ሚዲያ ያስጨንቀው የነበረው “የፍቅር ቀን” ወሬ ነው። መጠየቅ ግን እንፈልጋለን፤ እርግጥ ኢትዮጵያ ራሷ የንባብ ቀን ቢኖራት ይሄን ያህል ሽፋን ሚዲያዎቻችን ይሰጣሉ? ሚዲያዎቻችን ስለአድዋ ይህን ያህል ሽፋን ሰጥተው ያውቃሉ? ሌላው ደግሞ ፀሐፊያኑም እንደዚያው ናቸው። የሚፅፉ እንጂ የሚያነቡ ፀሐፊያን እያጋጠሙን ነው። በርግጥ ሁሉንም አይመለከትም። መምህራንም የማያነቡ ከሆነ በጣም ትልቅ ችግር ነው። ምክንያቱም እነዚህ ሶስቱ ዘርፎች አገርን ብቻ ሳይሆን አለምን መምራትና መለወጥ የሚችሉ ናቸው ብዬ አምናለሁ። በተለይ ሚዲያው ከፍተኛ ተፅዕኖ ይፈጥራል።

ሰንደቅ፡- ብራና በቀጣይ ምን ለመስራት ያስባል?

በፍቃዱ፡- ቅድም ከጠቃቀስኳቸው በተጨማሪ የብራና የንባብ ክበብ እንዲኖር እንፈልጋለን፤ በተለያዩ የክልል ከተሞች የመፅሐፍት ዓውደ-ርዕይ ለማዘጋት እየሰራህ ነው። በተረፈ ደግሞ ብራና በበለጠ የአየር ሰዓት ብዙ ለመስራት እንድትችል በኃላፊዎች ጋር እየተነጋገርን ነው፤ ይፈቀድልናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ሌላው ደግሞ ድርጅቶች ማህበራዊ ኃላፊነትን ለሚወጡ ፕርግራሞች ስፖንሰር ማድረግ ላይ ችግር አለባቸው። ለምሳሌ የፍቅር ቀን ሲከበር ብዙዎች ብዙ ብለዋል። በነገራችን ላይ ስለፍቅር መስበክ መልካም ነው፤ ነገር ግን ፍቅርን ከውጪ መኮረጃችን ያሳፍረኛል። ለምሳሌ አንድ ካምፓኒ “ለቫላይንታይን ዴይ” 1ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ስፖንሰር ሆኖ እንደነበር ሰምቻለሁ። ይህ ነገር ንባብን ለሚደግፉ ፕሮግራሞች ቢሆን ብዙ መፅሐፍትን ይገዛ ነበር የሚል ሃሳብ አለኝ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
11764 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us