የጉማ ሽልማት ከፍና ዝቅ

Wednesday, 04 March 2015 13:24

ከአምናው ዘንድሮ በጥቂቱም ቢሆን መሻሻል የታየበት የጉማ ፊልም ሽልማት ፕሮግራም ባሳለፍነው ሰኞ የካቲት 16 ቀን 2007 ዓ.ም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ተከናውኗል። ከ60 ያላነሱ ፊልሞች ቀርበው 26ቱ በዕጩነት የቀረቡበት የሽልማት ፕሮግራም ስለመሆኑም ታውቋል።

በርካታ ዕጩዎችና ተሸላሚዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የመንግስት ባለስልጣናትን ጨምሮ የተሸላሚዎቹ ወዳጆችና ዘመዶች ሁሉ በምሽቱ በአዳራሹ ተገኝተው ነበር።

አምና የመጀመሪያው የጉማ ፊልም ሽልማት ሲካሄድ ተቀዳሚውን የህይወት ዘመን ሽልማት ያገኙት የጉማ ፊልም ዳይሬክተር የሆኑት ሜሺል ፓፓታኪስ መሆናቸው ይታወሳል። ዘንድሮ ደግሞ የፊልሙን መሪ ገፀ-ባህሪይ የተጫወተው አርቲስት ደበበ እሸቱን ለሁለተኛው የጉማ ፊልም የህይወት ዘመን ተሸላሚነት ክብር አብቅቷል። አርቲስት ደበበ እሸቱ ይህን ክብር ማግኘት እንደሚገባው ከወዳጆቹ መልዕክትና በአዳራሹ የነበረው ጣሪያ የነካ ክብርና አድናቆት ምስክር ይሆናል ማለት እንችላለን።

ከዚህ ባለፈ ጉማ በአስራ ሰባት ዘርፎች ዕጩዎችን አወደድሮ ደማቅ የሽልማት ፕሮግራምን አካሂዷል። በምርጥ የተማሪዎች አጭር ፊልም ዘርፍ “ሃጢያት የሌለበት”፣ “ጅራፍ” እና “ጊዜ” የተሰኙ ፊልሞች በዕጩነት የቀረቡ ሲሆን፤ ዳዊ አቤል በ“ሃጢያት የሌለበት” ፊልሙ ተሸላሚ ሆኗል።

በምርጥ ድምፅ ዘርፍ ባለሙያዎቹ ከስሌት ኤፍሬም ምስጋና፣ ከኒሻል ኦያላ ዊንስተርስ፣ ከአይራቅ አቤል ተስፋዬ፣ በቀሚስ የለበስኩለት ዳንኤል ታምራትና ኤልያስ ሰብስቤ እና በ400 ፍቅር አበበ አሰፋ ዕጩዎች ሆነው ሲቀርቡ አሸናፊ የሆነችው ኦሪያላ ዊንተርስ ከኒሻን ፊልም ተሸላሚ ሆናለች። ሽልማቱን በዕለቱ በአዳራሽ የነበረው የፊልሙ ዳይሬክተር ይድነቃቸው ሹመቴ ተረክቧል።

በምርጥ የማጀቢያ ሙዚቃ ዘርፍ በዕጩነት የቀረቡት ቀሚስ የለበስኩለት፣ ረቡኒ፣ በጭስ ተደብቄ፣ እና ከመጠን በላይ ፊልሞች ላይ የሰሩት ባለሙያዎች ሲሆኑ፤ በዕለቱ አሸናፊ የሆነው አበጋዝ ክብረወርቅ በቀሚስ የለበስኩለት ፊልም ሆኗል። ይህንን ሽልማት በዕለቱ የፊልሙ ፀሐፊና ድምፃዊት ዘሪቱ ከበደ ከመድረክ ተቀብላለች።

በምርጥ ስኮር ዘርፍ ደግሞ በዕጩነት የቀረቡት ኒሻን፣ ረቡኒ፣ ቀሚስ የለበስኩለት፣ በጭስ ተደብቄ እና የብርሃን ፊርማ የተሰኙ ፊልሞች ሲሆኑ፤ በዘርፉ አሸናፊ ሆኖ የተሸለመው አሁንም አበጋዝ ክብረወርቅ ከቀሚስ የለበስኩለት ፊልም ሆኗል።

በምርጥ ገፅ ቅብ (ሜክአፕ) ዘርፍ ደግሞ በዕጩነት የቀረቡት ፍሬህይወት እሸቱ - ከኒሻን፣ መሠረት መኮንን - ከያልታሰበው፣ ኢየሩሳሌም ሀ/የሱስ - ከአብሮ አበድ እና ዳግማዊ አለማየሁ - ከበጭስ ተደብቄ ፊልም ሆነዋል። የዘርፉ ተሸላሚ የሆነው ዳግማዊ አለማየሁ ከበጭስ ተደብቄ ፊልም ሆኗል።

በምርጥ የፊልም ጽሁፍ ዘርፍ በዕጩነት የቀረቡት ይድነቃቸው ሹመቴ - ከኒሻን፣ ቴዎድሮስ ፍቃዱ - ከአብሮ አበድ፣ ፍፁም ይላቅ - ከያልታሰበው፣ በኃይሉ ዋሴ - ከአይራቅ እና ቅድስት ይልማ - ከረቡኒ ፊልሞች ሲሆኑ፤ በጉማ ፊልም ሽልማት ቅድስት ይልማ በረቡኒ ፊልሟ ተሸላሚ ሆናለች።

በመቀጠል የሽልማት ዘርፉ ያረፈው በምርጥ ቅንብር (ኤዲተር) ዘርፍ ላይ ነው። በዚህም በዕጩነት የቀረቡት አምስት ባለሙያዎች ሲሆኑ፤ ይድነቃቸው ሹመቴ - ከኒሻን፣ ሳሙኤል ተስፋዬ - ከነቄ ትውልድ፣ አብይ ፈንቴ - ከ400 ፍቅር፣ ምትኩ በቀለ - ከቀሚስ የለበስኩለት እና ተካበ ታዲዮስ - ከዘውድና ጎፈር ፊልም ነበሩ። የዚህ ምድብ አሸናፊ የሆነው አብይ ፈንቴ - ከ400 ፍቅር ነው።

በዓመቱ ምርጥ ሲኒማቶግራፊ ዘርፍ በዕጩነት የቀረቡት ባለሙያዎች ሙሉጌታ መገርሳ - ከኒሻን፣ ጆሴፍ ኢቦንጐ - ከረቡኒ፣ ታሪኩ ደሳለኝ - ከቀሚስ የለበስኩለት፣ ሰው መሆን ይስማው - ከያልታሰበው እና አብይ ፈንቴ - ከ400 ፍቅር ፊልሞች ሲሆኑ፤ አሸናፊው ታሪኩ ደሳለኝ - ከቀሚስ የለበስኩለት ሆኗል።

በምርጥ ተስፋ የተጣለባት ተዋናይት ዘርፍ ዘሪቱ ከበደ - በቀሚስ የለበስኩለት ፊልም ተሸላሚ ስትሆን፤ በወንዶቹ ምርጥ ተስፋ የተጣለበት ተዋናይ ተብሎ የተሸለመው በቅርቡ በበርካታ ፊልሞቹ ብቃቱን እያስመሰከረ የመጣው ህፃን እዮብ ዳዊት ነው ከያልታሰበው ፊልም።

በምርጥ ሴት ረዳት ተዋናይት ዘርፍ በዕጩነት የቀረቡት ሸዊት ከበደ - ከያልታሰበው፣ አዚዛ መሐመድ - ከበጭስ ተደብቄ፣ ህፃን ማርታ ሰለሞን - ከ45 ቀን፣ ቃልኪዳን ታፈሰ - ከቀሚስ የለበስኩለት ሲሆኑ፤ አሸናፊዋ አዚዛ መሐመድ ከ“በጭስ ደብቄ” ፊልም ሆና ሽልማቷን አግኝታለች።

በምርጥ ረዳት ወንድ ተዋናይ ዘርፍ ዕጩ የነበሩት አለባቸው መኮንን - ከኒሻን፣ ህፃን ናሆም ጌታቸው - ከረቡኒ፣ ካሳሁን ፍስሃ - ከያልታሰበው እና መስፍን ሀ/የሱስ - ከአይራቅ ፊልም ናቸው። የዚህ ዘርፍ አሸናፊ ሆኖ የተሸለመው አርቲስት አለባቸው መኮንን ሆኗል።

በምርጥ ዋና ሴት ተዋናይት ዘርፍ ሜላት ነብዩ - ከስሌት፣ ማህሌት ሹመቴ - ከአብሮ አበድ፣ ዘሪቱ ከበደ - ከቀሚስ የለበስኩለት፣ ሩታ መ/አብ - ከረቡኒ እና ማህደር አሰፋ - ከ45 ቀን ፊልሞቻቸው ቀርበዋል። የዚህ ዘርፍ አሸናፊ ሆና ሽልማቱን ያገኘችው ሩታ መ/አብ - ከረቡኒ ፊልም ሆናለች።

በወንዶች ምርጥ ዋና ተዋናይ ዘርፍ በዕጩነት የቀረቡት ፈለቀ አበበ - በኒሻን፣ ግሩም ኤርሚያስ - በጭስ ተደብቄ፣ ሚካኤል ሚሊዮን - በአይራቅ እና በያልታሰበው ፊልሞቹ እንዲሁም ግሩም ኤርሚያስ - በ400 ፍቅር ነበሩ። በዚህ ዘርፍ ሚካኤል ሚሊዮን እና ግሩም ኤርሚያስ በሁለት በሁለት ፊልሞች ለዕጩነት የቀረቡ ቢሆንም አሸናፊ መሆን የቻለው ግን ግሩም ኤርሚያስ - በጭስ ተደብቄ ስራው ነው።

በተመልካቾች ምርጫ የዓመቱ ምርጥ ፊልም ዘርፍ የመጨረሻዎቹ ተደርገው የቀረቡት ስራዎች 400 ፍቅር፣ ህይወትና ሳቅ፣ ረቡኒ፣ በጭስ ተደብቄ እና አይራቅ የተሰኙት ፊልሞች ሲሆኑ፤ ረቡኒ የምሽቱ አሸናፊ ሆኗል። ያም ሆኖ በዳኞችና በባለሙያዎች ዓይን የዓመቱ ምርጥ ፊልም ዘርፍ ኒሻን በአንደኝነት ተመርጦ ተሸላሚ ሆኗል።

የዓመቱ ምርጥ ዳይሬክተር ዘርፍ ይድነቃቸው ሹመቴ - በኒሻን ፊልም አሸናፊ ሲሆን፤ ቅድስት ይልማ በረቡኒ ፊልም በእኩል ነጥብ ተሸላሚ ሆናለች። አብረዋቸው በዕጩነት የቀረቡት ደግሞ ሔኖክ አየለ - በቀሚስ የለበስኩለት፣ ፍቅረየሱስ ድንበሩ - በአይራቅ እና ሔርሞን ኃይላይ - በያልታሰበው ፊልም ነበሩ። ይህ ዘርፍ ሁለት አሸናፊዎችን በማሳየቱ ለታዳሚው ግር ማሰኘቱ አልቀረም።

በበደሌ ስፔሻል የክብር ስፖንሰርነት በተካሄደው በዚህ ደማቅ የሽልማት ፕሮግራም ላይ እንዳይደገሙ የምንመኛቸው ጉልህ ክስተቶች (ክስረቶችም) ተገልጠዋል።

የጉማ ፊልም ሽልማት የምሽቱ ክስተትና ክስረት

በፊልም ኢንዱስትሪው ክበብ ውስጥ እንደ አብይ መነቃቂያም ሆነ ማንቂያ ደውል ሊታይ የሚችለው ይህ የጉማ ፊልም የሽልማት ፕሮግራም በምንም መልኩ እንዲስተጓጐል አይፈለግም። ይህም በመሆኑ አዘጋጆቹ ጉማ ከመክሰሩ በፊት የሚከተሉትን ጥቆማዎችና ትዝብቶች ነገሬ ቢሏቸው መልካም ይሆናል የሚል ተስፋ አለን።

የመጀመሪያውና አሁንም ድረስ በጉልህ የተንፀባረቀው የጊዜ አጠቃቀም ነው። በጥሪ ካርዱ ላይ 10፡30 ሰዓት የሚል ቢሆንም፤ ፕሮግራሙ ሲጀምር ግን ከሁለት ሰዓት ከግማሽ በላይ የሆነ ጊዜን አባክኖ ከምሽቱ 1፡13 ሰዓት ነው። ይህም አስተናጋጆችን ከትዝበት የሚጥል ስህተት ነው። ፅድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነኑኝ እንዲሉ ልብ የሚያረጋጋ ይቅርታን እንኳን ከወደ መድረኩ አለማግኘት በእጅጉ ያሳዝናል።

ሁለተኛው በአዳራሹ ውስጥ የነበረው ክስተትና ክስረት ተገቢውን የህይወት ዘመን ሽልማት ያገኘው አርቲስት ደበበ እሸቱ፤ የህይወት ዘመን ተሸላሚ ሆኖ በመድረክ ሲገኝ የተደረበለትን ውብ ካባ እንግዶቹን አመስግኖ እንኳን ሳይቀመጥ ለመግፈፍ መጣደፍ በእጅጉ አስተዛዛቢ የነበረ ነገር ሆኗል። ምናለ ዓይኖች ሁሉ ከእርሱ ላይ ገለል እስኪሉ እንኳን ቢጠበቅ የሚያስብል ክስረት ነው።

ዋናውና በምሽቱ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የሽልማት ፕሮግራም ላይ ክስተትም ክስረትም ሆኖ የተገኘው “የስታንድአፕ ኮሜዲ” ዝግጅት ነው።

ኮሜዲያን አብይ እና ፍልፍሉ በመፈራረቅ ሰውን ለማሳቅ የሞከሩበትና ስታንድአፕ ኮሜዲ የተሰኘው ዝግጅት ዕለቱንና መድረኩን የሚመጥን እንዳልነበረ እነርሱ እንደደፈሩን ሁሉ እኛም በድፍረት እንናገራለን። ምናልባት ኮሜዲያን አብይ ይሁን ብሎ የሚታለፍ ነው ብንል እንኳን ፍልፍሉን ሳይጠቅሱ ማለፍ ግፍ ነው።

በተለይም የኮሜዲያን ፍልፍሉ ወዝ አልባና በእፍረታችን ላይ የሚሳለቁ ቀልዶች እዚህ ግባ የማይባሉና እርሱንም አዘጋጆቹንም ትዝብት ላይ የጣሉ ናቸው። ታላላቆችን ለመሸለምና ለማክበር በተዘጋጀ ይህን የመሰለ መድረክ ላይ ባለስልጣናት፣ አዛውንቶችና ህፃናት እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው በርካታ እንግዶች እና ቤተሰቦች ሁሉ ባሉበት አዳራሽ ውስጥ ልቅ ቀልዶችን መለቃለቅ ከመሳደብ አይተናነስምና መድረኩን የሚመጥን አልነበረም ለማለት እንወዳለን። ሰዎች የማይደፍሩትን ብልግና በአደባባይ መለፈፍ እና በሚወዱና በሚያምኑት የመፅሐፍ ቅዱስ ቃል ላይ መቀለድ ኢ-ሞራላዊን ጭምር መሆኑን ለቀልደኛ ተብዬው የምር ልንነግረው እንወዳለን።

በተረፈ ግን ጉማ ፊልም ሽልማት ከአንድ ወደ ሁለት ሲመጣ ከፍታን እንዳሳየን ሁሉ በቀጣይ ዓመታትም የተሻሉ ሥራዎችን በመስራት በሀገራችን የፊልም ዕድገት ውስጥ አሻራው የጐላ እንደሚሆን ባለሙሉ ተስፋ ነን። የዝግጅት ክፍላችንም ለዕጩዎችም ሆነ ለተሸላሚዎች እንኳን ደስ ያላችሁ ለማለት ይወዳል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
16152 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us