በህብረዝማሬ የተሳካለት ገጣሚ

Wednesday, 11 March 2015 12:18

 

አዘጋጅና ገጣሚ ቢኒያም ኃ/ስላሴ   

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በ1986 ዓ.ም የመጀመሪያ ዲግሪውን በቴአትር ጥበባት አግኝቷል። ሥራውን የጀመረው በህፃናትና ወጣቶች ቴአትር ቤት በትወና ሲሆን፤ ለመድረኩ የሚሆኑ አራት ቴአትሮችን ከመፃፉም ባሻገር ስድስት የሚደርሱ ሥራዎችን በአዘጋጅነት ሰርቷል። ከህጻናትና ወጣቶች ቴአትር ቤት ወደ ራስ ቴአትር ሲመጣ የሕዝብ ግንኙነት በመሆን አገልግሏል። ቀጥሎም በቴአትርና ባህል አዳራሽ፤ በባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት፣ በራስ ቴአትር ቤቶች በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች ሠርቷል። በአሁኑ ወቅት በራስ ቴአትር “በስቴጅ ማኔጀርነት” እየሰራ የሚገኝ ነው። ይህም ብቻ አይደለም እንግዳችን በተለያዩ ሚዲያዎች ከሚሰሙ በሀገራዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ ህብረ ዝማሬዎች መካከል አብዛኞቹን በግጥም በመስራት ይታወቃል። ይህ ተዋናይ፣ አዘጋጅና ገጣሚ ቢኒያም ኃ/ስላሴ ይባላል።

“ግጥምን መፃፍ የጀመርኩት መፃፍ እንደምችል ሳላውቅ ነው” የሚለው ቢኒያም፤ ከአንደኛ ደረጃ እስከ ዩኒቨርሲቲ በነበረው ቆይታ አንድም ቀን ግጥምን ሞክሮ እንደማያውቅና የግጥም ተሰጥኦ እንዳለው ያወቀው በህፃናትና ወጣቶች ቴአትር በነበረው የሥራ ቆይታ ወቅት እንደነበር ይናገራል። በተለይም የቅርብ ወዳጄ ነው ከሚለው የግጥምና የዜማ ደራሲው ሙሉ ገበየሁ ጋር መተዋወቁ የግጥም ተሰጥኦውን አውጥቶ እንዲጠቀምበት እንደረዳው አይዘነጋም። ለህጻናትና ወጣቶች የሚሆኑ ሙዚቃዎችንና ህብረ ዝማሬዎችን በማየትና ሀሳብ በማዋጣት የተጀመረው የግጥም ስራ ሙከራዎቹ ከቀን ወደቀን መሻሻል እያሳየ መምጣቱን ከተለያዩ ባለሙያዎች በሚሰጠው አስተያየት እያረጋገጠ ስለመምጣቱም ይናገራል።

የመጀመሪያውና ከሕዝብ ጋር የተዋወቀበት ሥራው በ2000 ዓ.ም ለአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት የሚሆን የህብረ ዝማሬ መሪ መዝሙር በሰራበት ወቅት ነው። ቀጥሎም “ብሔር ብሔረሰቦችን” የገለፀበት የህብረ ዝማሬው ይጠቀሳል። የበርካቶችን ጆሮ ማግኘት የቻሉ ለህብረ ዝማሬ የሚሆኑ ግጥሞችን የሰራው ቢኒያም ኃይለስላሴ በአሁኑ ወቅት ከ95 በላይ የሚደርሱ ስራዎችን ለህዝብ አድርሻለሁ ይላል።

“ግጥም የምፅፈው ነፍሴን ደስ እንዲላትና የትርፍ ጊዜ ስራዬም በመሆኑ ለሀገርና ለማህበረሰባዊ ጉዳዮች ትኩረት እሰጣለሁ” የሚለው ቢኒያም፤ አልፎ አልፎም ቢሆን ከድምጻዊያን ጋር ተገናኝቶ የመስራት አጋጣሚን እንዳላጣ ይገልፃል። ከዚህም መካከል በጉልህ የሚጠቀስለት “ለአባይ ወይስ ቬጋስ” ፊልም ማጀቢያነት ድምፃዊ ማዲንጎ አፈወርቅ እና ድምፃዊ ጎሳዬ ተስፋዬ የሰሩት ሙዚቃ የእርሱ ስለመሆኑ እማኝነት ይጠቅሳል። ከዚህ ውጪ በአባይ ላይ ያለውን ተስፋ የገለፀበት “ከፍ እንበል በስራ!”፣ “ጀምረናል- ጉዞ ጀምረናል” እና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ዜና እረፍት በተሰማበት ወቅት የሰራው “ምነው ሞት?” የሚሉት ስራዎች ተጠቃሾች ናቸው።

“የህብረ ዝማሬ ግጥሞች ከሌሎቹ የሚለዩበት ትልቁ ምክንያት በዓላት ሲዘጋጁ ህብረ-ዝማሬዎች የሚፈለጉ መሆኑ ያም ሆኖ በዓሉ ሊደርስ ጥቂት ቀናት ሲቀረው የሚታስብ መሆኑ ስራውን በጣም ፈታኝ ያደርገዋል የሚለው ቢኒያም፣ አብዛኞቹ ስራዎች ተብላልተውና በቂ ዝግጅት ተደርጎባቸው የሚሰሩ ሳይሆኑ ጥድፊያ የበዛባቸውና “ሱሪ በአንገት” አይነቶች ይሆናሉ ይላል። ከሰራቸው በርካታ ግጥሞች ውስጥ የሚበልጡት በትዕዛዝ የሰራቸው ስለመሆኑ የሚናገረው ቢኒያም፤ ከዚያም ውጪ ልምድን፣ ገጠመኙንና ትዝብቶቹን የከተበባቸው የንባብ ግጥሞች ስለመኖራቸው ይናገራል።

ከተለያዩ ድምጻዊያን ጋር ስለመስራት ያለውን ተነሳሽነት በሚመለከት፣ “ድምጻዊያን አያወቁኝም፤ እኔም ራሴን ለማስተዋወቅ አልጣርኩም። እስካሁንም የምሰራቸው ግጥሞች ለራሴ ደስ ሲለኝና ይህን ሥራ ስባል እንጂ ተወዳድሬና ልስራላችሁ ብዬ አይደለም” የሚለው ቢኒያም፤ “ምናልባት ስራዎቼን የሚመለከቱ ድምፃዊያን ፈልገው ያሰሩኝ ይሆናል” ሲል ተስፋ ያደርጋል።

እንጀራውን “ሀ” ብሎ የጀመረው በተመረቀበት የቴአትር ጥበባት ዘርፍ ቢሆንም አሁን-አሁን በህብረ ዝማሬ ስራዎቹ እየተወሰደ ስለመሆኑ ለቀረበለት ጥያቄ ሲመልስ፤ “ቴአትርን መተወን፣ መፃፍና ማዘጋጀትን አልተውም” ባይ ነው።

በተለይም በትዕዛዝና በአስቸኳይ የሰራቸውን ግጥሞች በሚመለከት አሁን ላይ የሚፀፀትባቸው ስራዎች ስለመኖራቸው ሲጠየቅ፣ “በሁሉም የህብረ-ዝማሬ ግጥሞቼ ላይ ቅር የሚለኝ ነገር አለ። ምክንያቱም ስራዎቹ በትዕዛዝ ስለሚሰሩ ምናለ ትንሽ ሰፋ ያለ ጊዜ ባገኝ ኖሮ የሚያሰኙ ናቸው። እንደነገርኩህ የመዝሙር ግጥም አንድ ጉዳይ ኖሮ ስለዛ ነገር እንድትሰራ የሚፈለግ ነው። በዚህ መካከል ስነ-ፅሁፋዊ ደረጃውን ጠብቆ መስራት ያንተ ጉዳይ ነው። ስለዚህም ሁሉም ስራዎቼ ላይ ምናለ ትንሸ ጊዜ ቢኖረኝ፤ ትንሽ በሰል ባደርጋቸው እላለሁ” ባይ ነው።

“መዝናኛዬ ንባብ ነው” የሚለው ቢኒያም ኃ/ሥላሴ፤ በተለይም በጥቂቱም ስነ-ፅሁፉን ለሚሞክር ሰው ማንበብ ወደር የለሽ መዝናኛ ስለመሆኑም ይመክራል። መጨናነቅ በበዛበት ኑሯችን መካከል ሆኖ ማንበብ መንፈሳችን እንዲፍታታ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ይላል።

በጥድፊያና በትዕዛዝ ከሰራቸው የህብረ-ዝማሬ ስራዎቹ በቂ የሚባል ክፍያን አግኝቶ ስለመሆኑ ለተነሳው ጥያቄ ሲመልስ፤ “ከዘጠና በላይ የሚደርሱ የህብረ ዝማሬ ግጥሞችን እንደሰራው ነግሬህ የለ? ከዚያ ውስጥ ወደሃምሳ የሚጠጋው ያለክፍያ የተሰራ ነው። ጉዳዬ ገንዘቡ አይደለም። ነገር ግን የተሰጠኝን የቤት ስራ በሚገባ መወጣቴ ለራሴ ደስታና መደነቅን እንዲጨምርልኝ ያደርገኛል” ይላል። ያም ሆኖ ግን በተለየ ሊጠቀስ የሚችል ከሆነ “ብሔር- ብሔረሰቦች” የተሰኘው ህብረ-ዝማሬ እንደመነሻ 600 ብር ብቻ የተከፈለው ስለመሆኑ አስታውሶ በዚህ ስራ ምክንያት ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ ባዘጋጁት የእራት ግብዣ ላይ 5000 ብር በሽልማት መልክ ተበርክቶለታል። ይህም ብቻ ሳይሆን መቀሌ ላይ በተካሄደ ፕሮግራም አቶ ተክለብርሃን አምባዬ 25 ሺህ ብር እንደሸለሙት ያስታውሳል። “ይህ እንግዲህ በአንድ መዝሙር የተገኘ ትልቅ ዋጋ ነው” ይላል።

በአሁኑ ወቅት ጠንካራ ሀሳቦችን ማንሳት የሚችሉ ምርጥ -ምርጥ ገጣሚያን እንዳሉ ስለመመልከቱ የሚናገረው ቢኒያም፤ “ከግጥም ስራዎች (መፅሐፍት) የሚገባቸውን ያህል ግን አልተጠቀሙም” ባይ ነው። ለዚህም ግጥም በባህሪው ለነፍስህ የምትሰራው እንጂ ለክፍያ የምትጨነቅበት አለመሆኑ ነው” ይላል። ከዘመናችን ገጣሚያን በዕውቀቱ ስዩምን፣ ቴዎድሮስ ፀጋዬንና ይልማ ገብረአብን በእጅጉ እንደሚያደንቅም ይገልጻል።

በቀጣይ ለመስራት ካሰባቸው ስራዎች መካከል ቴአትር፣ ፊልምና ዝግጅት እንዳሉ ሆነው የፃፋቸውንና በህብረ ዝማሬ መልክ የተቀነቀኑትን መዝሙሮች በመፅሐፍ መልክ የማቅረብ ፍላጎት እንዳለው ይናገራል። “ይህን የማደርገው ግጥሞቹ በመፅሐፍ መልክ ቢዘጋጁ አንድም ከዓመታት በኋላ ለሚመጡ ተመራማሪዎች በዘመናችን መንግሥትና ህዝብ ምን ያስብ እንደነበር ለማሳየት ይረዳል። ሁለትም ግጥሞቹን በቃሉ ይዞ ለመዘመር የሚፈልግ ሰው ካለ ለማገዝ ይሆናል ብዬ አስቤነው” ሲል ስለእቅዱ ያትታል።

በሀዘንና በደስታ ስሜት ውስጥ ሆኖ ከሰራቸው ግጥሞች ውስጥ በተለየ የሚያስታውሳቸውን ሲገልጽ፤ “እነዚህ አሁን መርጬ የምነግርህ በትዕዛዝ የሠራኋቸው ሳይሆኑ ስሜቴ ተነክቶ በደስታ ወይም በሀዘን ውስጥ ሆኜ የፃፍኳቸው ናቸው። ለምሳሌ በጣም አዝኜ የፃፍኩት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት ጊዜ የፃፍኩት ግጥም ነው። ሞት ክፉ ቢሆንም ተሸውዷል በሚል ቁጭት ነው የፃፍኩት። በጣም ደስ ብሎኝ የፃፍኩት ደግሞ “ከፍ-ከፍ እንበል፣ ከፍ እንበል በስራ” የሚለውና እነባህታ ገ/ህይወት የሚያዜሙት የአባይ ህብረ-ዝማሬን ነው። ሌላው እነሞገስ ተካ የሚያዜሙት “ጀምረናል- ጉዞ ጀምረናል” የሚለውም እንዲሁ በጥሩ ስሜት ውስጥ ሆኜ የሰራኋቸው ግጥሞች ናቸው ማለት እችላለሁ” ይላል።

በተለየ መልኩ ግጥሞቹን እንዲያቀነቅኑለት ከሚመኛቸው ድምጻዊያን መካከል ማዲንጎ አፈወርቅ፣ ጎሳዬ ተስፋዬ፣ አብነት አጎናፍር፣ ሐመልማል አባተ፣ ሚካኤል በላይነህ ጋር ብሰራ ደስ ይለኛል የሚለው ቢኒያም፤ ነገር ግን ከማንም ጋር ቢሰራ እንደማይጠላም ይናገራል።

    “ግጥም ለመፃፍ መታመም ያስፈልጋል” የሚለው ቢኒያም ኃ/ስላሴ፤ እንደኛ አይነት ሀገርና ማህበረሰብ ውስጥ የሚፃፉባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ ባይ ነው። ለዚህም ብዙ ችግር ያለብን ህዝቦች በመሆናችን የመፃፊያ ብዙ ጉዳዮች አለን ይላል።

ይምረጡ
(9 ሰዎች መርጠዋል)
16765 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 177 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us