በፍቅር መንገድ ላይ የተዘራ ሲበቅል

Wednesday, 18 March 2015 13:17
 •     የፊልሙ ርዕስ      - በመንገዴ ላይ    
 •     አቅራቢው          - ቡዜ ፊልም ፕሮዳክሽን
 •    ፕሮዲዩሰር         - ብዙአየሁ ዘውዴ  
 •    ፊልም ፅሁፍ       - ንጉሡ ጌታቸው
 •    ሲኒማቶግራፊ       - ሽመልስ ጌታቸው እና ሽመልስ ታደሰ 
 •    ፕሮዳክሽን ማኔጀር  - እንዳሻው ጌታቸው 
 •    መብራት           - ዳዊት ቤራ      
 •    ድምጽ             - ሚሊዮን ሽፈራ     
 •    ኤዲተር          - ቴዎድሮስ ወርቁ 
 •   ተዋንያን         - ህፃን አልአዛር ደመላሽ፣ ፍቅርተ ደሳለኝ፣ አለምሰገድ  ተስፋዬ፣ ሔለን በድሉ፣ ሸዊት ከበደ፣ ሜላት ነብዩ እና ሌሎችም።   
 •    ደራሲ           - ሊዛ ተሾመ 
 •    ዳይሬክተሮቹ       - ሽመልስ ጌታቸውና ሽመልስ ታደሰ   

 

“በመንገዴ ላይ” ፊልም በሳቅ በተዋዛ፤ ልብ በሚያንጠለጥል፤ በቁጭትና በፀፀት፣ በተስፋና በፍቅር መንገድ ላይ በሲኒማ ስክሪን ይዞን 1 ሰዓት ከ40 ደቂቃ የሚጓዝ ፊልም ነው። ፊልሙ በወደዳት ሴት ላይ እምነት አጥቶ ከተለያዩ ሴቶች ጋር ግንኙነት በፈጠረ ወጣት የህይወት ውጣ ውረድ ላይ ያተኩራል። ወጣቱ እናቱ ማን እንደሆነች ከማያውቃት ሴት በሩ ላይ የ6 ወር ህጻን ልጅ ማግኘቱን ተከትሎ በስውር የምትከተለውን የህጻኑን እናት ፍለጋ በወጣበት የህይወት መንገድ ላይ የበደላቸውንና የተለያቸውን ሴቶች መለስ ብሎ ሲቃኝ የምንመለከትበት ልብ አንጠልጣይ የፍቅር ፊልም ነው።

“ያልዘሩት አይበቅልም” የሚለው የፊልሙ ገላጭ ሀረግ ብዙ ነገር ይናገራል። ዳዊት (አለምሰገድ ተስፋዬ) በሴቶች ላይ እምነት ያጣ፤ ነገር ግን ክፉኛ በድላኛለች ከሚላት ሮማን (ሜላት ነብዩ) ጋር ብዙ በፍቅር የቆየ እንደነበር ፊልሙ በገደምዳሜ የነገረን ቢሆንም፤ ዳዊትም የሮማንን ከተለያዩ ወንዶች ጋር “ሂያጅነት” በአይኑ በብረቱ በማየቱ በፍቅሩ እምነት ያጣ ሰው ነው። ዳሩ ግን በነጋ በጠባ ቁጥር በነገሮችና በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሚስት እንዲያገባ ከሚወተውቱት እናቱ (ፍቅርተ ደሳለኝ) ጋር የሚኖር ወጣት ነው።

“በመንገዴ ላይ” ፊልም በትወናቸው የማይሰለቹ፤ በአቅማቸውም የተደራጁ ወጣትና አንጋፋ ተዋንያን ተጣምረው የሚታዩበት ስራ ነው። ከሁሉም በላይ ግን የ6 ወሩ ህጻን አልአዛር ደምመላሽ የፊልሙን ፍሰት ጠብቆ እንዲሄድ ዳይሬክተሮቹ የተጫወቱት ሚና ቀላል እንደማይሆን ይታመናል።

በሩ ላይ ተጥሎ የተገኘውን ህፃን ማንነት ሲያጣራ፤ በዲ.ኤን.ኤ. የህክምና ምርመራ አባትነቱን ያረጋገጠው ዳዊት የልጁ እናት ማን እንደሆነች ባለማወቁ ግንኙነት አለኝ ብሎ የጠረጠራቸውንና የተለያቸውን ሴቶች ሁሉ ሲያስስ ማየት በፊልሙ ውስጥ በጣም አግራሞትና ሳቅን የሚያጭር ትዕይነቶችን ፈጥሯል።

ይህ ሁሉ ሲሆን “የልጁን እናት ካለችበት ፈልገህ አምጣ” ለሚሉት እናቱ መልስ የሚሆን ነገር ሲፈልግ፤ ከዚህ ቀደም ወዳጁ የነበረችውና አርግዛለት አስወጪው ያላት ሮማን ጋር ይገናኛል። በፍለጋው ወቅትና ቢሮው ድረስ ሄዳ ልጅ እንዳለው ያረጋገጠችው ሮማን ልጅ እናት እኔ ነኝ በሚል የእርሷ ያልሆነውን ልጅ ወስዳ በዳዊት ላይ የቋጠረችውን የቂም በቀል መወጣጫ ለማድረግ ስትሞክር “በመንገዴ ላይ” ፊልም ያሳየናል።

“በእጅ ያለ ወርቅ እንደመዳብ ይቆጠራል ሆኖበት” የቅርቡን ትቶ የሩቁን ሲያስስ የምናገኘው ዳዊት ከዚህ በፊት የሴት ጓደኛው የነበረችው ሴት ከእርሱ ከተለያት በኋላ አረብ አገር ደርሳ ብትመጣም፤ ችግረኛ እናቷን መርዳት እንኳን ተስኗት በአእምሮ ህመም ሳቢያ የአልጋ ቁራኛ ሆና ባገኛት ጊዜ ፀፀት ክፉኛ ሲፈትነው እናያለን።

ዳዊትን “ፀፀት የስርየት መንገድ ናት” የምትለው ማርታ (ሔለን በድሉ) እንደእህት ሆና ለእረፍት ከመጣችበት ዩኒቨርሲቲ የነበራትን ጊዜ ሁሉ የዳዊትን ችግር ለመፍታት አብራው ስትንከራተት በማየታችን የታሪኩን ጠረፍ በጉጉት እንድንጠብቅ አድርጎናል።

በልጃቸው እንዝላል ባህሪይ የሚቆጩትና በልጅ ልጃቸው ፍቅር የሚተራመሱት የዳዊት እናት ወ/ሮ ፋናዬ (ፍቅርተ ደሳለኝ) ብክን፤ ትክንክን ባሉበት ወቅት የሚተርቱት “የሌሊት ጉዞ አንድም ለጅብ፤ አንድም ለአጅብ” ብዙ ነገር መግለፅ የቻለ ነው።

“በመንገዴ ላይ” ፊልም የሚታይና ለሌሎችም የሚነገር ታሪክ ያለው ልብ አንጠልጣይ የፍቅር ስራ ነው። ሰው በህይወት መንገዱ ላይ የሚሳሳትና ሌሎችንም የሚያሳስት፤ የሚፀፀትና ይቅርታም የሚጠይቅ፤ የሚመለስና በፍቅር ውስጥ የሚፀናም ፍጡር ስለመሆኑ ፊልሙ ይተርክልናል።

በብርሃን ምጣኔው፤ በድምፅ ውህደቱና በቅንብሩ (ኢዲቲንግ) የጎላ ችግር የማይታይበት ፊልም ነው። ያም ሆኖ እንዲህ ቢሆኑ የምንላቸው አንድ ሁለት ጉልህ እንከኖችን መጠቆሙ ግን አይከፋም።

“በመንገዴ ላይ” እንደፊልም ብዙ የሚያሳየን ነገር የመኖሩን ያህል ማየት እየተገባን የጋረደን ትዕይንቶችም አሉ። ለምሳሌ በታሪኩ ውስጥ የቀድሞ ወዳጁ የነበረችና በአሁኑ ወቅት የአእምሮ ህመምተኛ ሆኖ ዳዊት ባገኛት ጊዜ፤ የተሰማውን ጥልቅ የፀፀት ስሜት ለማጉላት ዳይሬክቶቹ በደስታ የተሞላ የፍቅር ጊዜያቸውን በምልሰት አሳይተውናል። ልክ እንደዚህ ሁሉ ዳዊት በጎረቤቱ ማርታ ጋር የነበረውን አይረሴ የፍቅር ጨዋታ ከቃላት ትረካ ባለፈ በጨዋ ካሜራ ውስጥ ማየት ቢቻል ጥሩ ነበር። ለምን ቢባል ፊልም ድርጊትን ከመተረክ ማሳየት ዋነኛ መገለጫው ነውና።

ያም ሆኖ በታሪኩ ፍሰት መካከል ተመልካቹ ልብ እንዲላቸው የሚያስፈልጉ ፍንጮችን በመስጠት በኩል “በመንገዴ ላይ” ፊልም አይታማም። ለዚህም ማርታ ከዩኒቨርስቲ መልስ ተስማምቷት መምጣቷ እና የልጅ እናት ነኝ ባዩዋ ሮማን ህጻኑ በዳዊት ቢሮ ውስጥ ባየችው ጊዜ የምታሳየው “እናትነት የጎደለው ስሜት” በጊዜ መልስ የሚሰጡና የተመልካቹን አስተውሎት የሚጠይቁ ትዕይነቶች ሆነው ተሰርተዋል።

በተረፈ ግን “በመንገዴ ላይ” ፊልም በሁላችንም የህይወት መንገድ ላይ ሊያጋጥም የሚችል ወይም የሰማነውና ያየነውን የቅርብ ታሪክ የሚተርክ በመሆኑ በፊልሙ ውስጥ የተሳተፉትን በሙሉ አድናቆት ልንቸራቸው እንወዳለን። በህይወት መንገድ ላይ በተዘራ ፍቅር በስተመጨረሻ መልካም ዕድሉና ተስፋን አሳይቷል። “በመንገዴ ላይ” ፊልም በግጥም ሲገለል፤

ያመጣል መንገድ

ይወስዳል መንገድ

አንደ የሚጠላ፣ አንድ የሚወደድ።

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
17006 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us