ወንድ በሌለበት ወንዶች የሞሉበት ቴአትር

Wednesday, 25 March 2015 11:13

 


የቴአትሩ ርዕስ - ወንድ አይገባም

አቅራቢው - ጄ. አዲ ኪነጥበብ

ድርሰትና ዝግጅት - ዓለምፀሐይ በቀለ

ተዋንያን - ጀንበር አሰፋ፣ ቅድስት ገ/ስላሴ፣ ማርታ ጌታቸው፣ መሠረት መኮንን፣ ባንቺ አምላክ ስለሺ፣ መክሊት ገ/የስ፣ ሰላማዊት ማሬ

“ወንድ አይገባም” ቴአትር ከትወና እስከ ዝግጅትና ድርሰቱ አልፎም እስከ ፕሮዳክሽን ሂደቱ በሴቶች ስብስብ የሴት “ጋላክቲኮ” ቴአትር ነው። ቴአትሩ ሴቶችን ማዕከል አድርጉ በርካታ ማህበራዊ ህፀፆችን የሚዳስስ ማህበራዊ ስላቅ የበረታበት ኮሜዲ ቴአትር ነው። “ወንድ አይገባም” ዘወትር ሰኞ በሀገር ፍቅር ቴአትር መታየት የጀመረ ሲሆን እኛም ባሳለፍነው ሰኞ በቴአትር ቤቱ ታድመን አስደሳች ጊዜን አሳልፈናል።

ገና ከበሩ ብዙዎች “ወንድ አይገባም” ስለተባለ ይመስላል ተጋፍተው ቴአትሩን ለመታደም ወደአዳራሹ ገብተዋል። በርግጥም ከ1፡30 ሰዓት በላይ በሚታየው ቴአትር ውስጥ በመድረኩ አንድም ቁጥር ወንድ አይታይ እንጂ በአዳራሹ ግን የበረከተው ወንድ ሳይሆን እንዳልቀረ መታዘብ ይቻላል።

“ወንድ አይገባም” ቴትር በቀላል የመድረክ አቀራረብ በርካታ ቁምነገሮችን በሳቅ እያዋዛ የሚያሳይ ቴአትር ነው። ቴአትሩ በጡረታ ላይ ያለችን የቀድሞ የኮሌጅ መምህርትን፤ ልጃቸውን ውጪ ሀገር ልከው ባዶ ቤት ከመኖር ከሰዎች ጋር በህብረት መኖር ይሻላል በሚል ቪላቸውን አከራይተው ሰው ፍለጋ የመጡ እናት፤ ቤተሰቦቿን ለመርዳት ስትል ወደ ሴተኛ አዳሪነት ህይወት ገብታ የምትዳክርን ሴት፤ በወንዶች ምርጫ የምትታመስን ነርስ፤ ከባሏ ተፈታ በህብረት መኖርን መርጣ ወደቤቱ የመጣችን ተዋናይትና የአንዲት የዩኒቨርስቲ ተማሪን ህይወት በአንድ ጣሪያ ስር የሚያሳይ ታሪክ ነው።

ከፆታቸው ውጪ በአስተሳሰብ በዕድሜ፣ በፍላጎትና በአቅም የሚለያዩት ስድስቱ ሴቶች ህብረት ፈልገው እንደቤተሰብ በሚኖሩበት ቤት ውስጥ አንድ ፍጹም ተከባሪ ህግ አለ፡፤ ያም ህግ “ወንድ በፍፁም ወደቤት ይዞ መምጣት አይቻልም” የሚል ነው። ይህ ሕግ እንደተጠበቀ ሆኖ ቤቱን ያከራዩዋቸው ሰው ህንፃ ለመገንባት (ለልማት) በሚል ቤቱን ስለሚፈልጉት ለቀው እንዲወጡ የቀራቸው ከሁለት ሳምንት ያልበለጠ ጊዜ ነው። ቤት ፍለጋውና ቀጣይ ዕጣ ፈንታቸው የቤተሰቡ (የስድስቱ ሴቶች) ራስ ምታት ሲሆን እንመለከታለን።

“ወንድ አይገባም” ቴአትር በመድረኩ ላይ አንድም ወንድ በፎቶም ጭምር አያሳየን እንጂ በሁሉም ሴቶች ልብ ውስጥ ዋነኛ ማጠንጠኛው ወንድ ሆኖ እናገኘዋለን። ለዚህም ኮርኳሪው ታሪክ የሚጀምረው የቤቱ አንድ አባል የሆኑት የወ/ሮ ምንትዋብ (ጀንበር አሰፋ) ልጅ “ደስታ” ሚስት ፍለጋ ከውጪ የመምጣቱ ወሬ ነው። ይህንንም ሲስተር ምህረት (መክሊት ገ/የስ) ስትገልፀው፤ “ዲያስፖራው እመጣለሁ ካለ በኋላ የእያንዳንዱ ሰው ድብቅ ባህሪይ እየወጣ ነው” ማለቷን ማስታወስ ይበቃል። ዝሆንም ለሆዱ ትንኝም ለሆዷ” እንዲሉ የወንድ ጓደኛ ያለውም ሆነ የሌለው ዲያስፖራውን ለማጥመድ የሚያሳዩት ሽኩቻ ተመልካችን በአግራሞት ለሳቅ የሚኮረኩር ነው። በቴአትሩ ውስጥ ያልተነሳ የሴቶች ጉዳይ የለም ማለት ይቻላል። ስለድንግልና፣ ስለወር አበባና ሞዴስ፣ ስለዕድሜና እርጅና ስለአስገድዶ መድፈርና ልል ስለሆነው ህጋችን ሁሉ ቴአትሩ ይጠቃቅሳል።

“መኖር ማለት ክፉና ደጉን ማለፍ ነው” የሚሉት ወ/ሮ ምንትዋብ (ጀንበር አሰፋ) ሴቶቹን በምክር ከማጠነክር ባለፈ፤ ዕድሜ ሳይቀድማቸው ማግባት እንዳለባቸው ይወተውታሉ።

የቤቱን ሴት ሁሉ እንደእናት ለማስተዳደር ደፋ ቀና ስትል የምናያት ፋናዬ (ቅድስት ገ/ስላሴ) ለሰው ልጅ ያላትን ፍቅርና ክብር ለሴተኛ አዳሪዋ ኤልሳ (መሰረት መኮንን) እና ለዩኒቨርስቲ ተማሪዋ ውዴ (ባንቺአምላክ ስለሺ) በምታሳየው መቆርቆር እንመለከታለን።

ትወናን ከልቧ የምትወደው ሮዛ (ማርታ ጌታቸው) ከልጇ አባት ጋር ብትለያይም ማሰቧን አላቆመችም። ያም ሆኖ እልህ ይሉት ነገር ስልክ ለመደወል እንኳን ጠፍሮ ሲይዛት የሴትነት ጓዟን የሚያሳይ አስቂኝ ትዕይንት ይሆናል።

በ“ወንድ አይገባም” ቴአትር ውስጥ ከተነሱና ትችት ከተሰነዘረባቸው ማህበራዊ ጉዳዮቻችን መካከል ጥቂቱን እንጥቀስ። የህክምና ሥነ-ምግባር በእጅጉ እየተጣሰ ብቻ ሳይሆን እየተደረመሰም ስለመሆኑ የሚተቸው ይህ ቴአትር፤ በተለይም ህሙማን ሀኪሞችን ጥበቃ የሚያጠፉት ውድ ጊዜ በህይወት የሚከፈል ትልቅ ዋጋ ስለመሆኑ አፅንኦት ሰጥቶበታል። ባለሙያዎቹ ለፊልምና ለስልክ እንጂ ለሰው ህይወት ያላቸው ትኩረት የወረደ ስለመሆኑም ይናገራል።

በመንግስት ቤት ያለውን የሰዓት ቁጥጥርና የስራ ውጤት አለመጣጣም የምትተቸው ፋናዬ (ቅድስት ገ/ስላሴ) ወደስራ የምትሄደውን ሮዛን (ማርታ ጌታቸው) “ሂጂ እናቴ መንግስት ቤት የሰዓት እንጂ የስራ ቁጥጥር የለም” ትላለች።

በሴተኛ አዳሪነት ህይወቷ ብዙ ያየችው ኤልሳ (መሠረት መኮንን) ስለከተማችን የምሽት ሁኔታ ስትናገር፣ “አዲስ አበባን በማታ ካየሻት ትዳር ያለም አይመስልም” ስትል ትገልጻለች። ይህቺ ሴት በወንዶች ባህሪይ ላይ ኤክስፖርት የሆነች ያህል የሚከተለው አስተያየትም ትሰነዝራለች። “አብዛኛው ወንድ ክፍተት ካገኘ የማይሰርቅበት አጋጣሚ የለም” ስትል ተመልካቹን በነገር እየሸነቆጠች በሳቅ ታስጠነቅቀዋለች።

በአስገድዶ መድፈር ህጋችን ደካማነትም ላይ ቴአትሩ ሸንቆጥ የሚያደርግ አስተያየት ይሰጣል። ከተለያዩ ወንዶች ጋር ግንኙነት እንዳላት የምናየው ሲስተር ምህረት (መክሊት ገ/የስ) አንድ ምሽት በማታውቃቸው ሰዎች በመኪና ተወስዳ መደፈሯ ይነገራል። ያም ሆኖ ተገቢውን ፍትህ ባለማግኘቷ በዚህ መንገድ ወንጀል ሲፈፀም ማህበረሰባችን የተፈጠነ እና የሚክስ ሕግ እንደሚያስፈልገው ቴአትሩ ይጠቁማል።

    “ወንድ አይገባም” ቴአትር የቆየውን ኢትዮጵያዊ ብሂል ማለትም፤ “ከሩቅ ዘመድ የቅርብ ጎረቤት ይሻላል” የሚለውን በአፅንኦት ማሳየት የቻለና ወንዶች ባልታዩበት መድረክ ላይ ወንዶች የሚናፈቁበት፣ ወንዶች የሚታሙበትና ወንዶች የሚፈቀሩበት ቴአትር ሆኖ በትወና በተዋጣላቸው እንስቶች ተሰርቶ ቀርቧል።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
16274 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us