“ጥበብ ስስት አትወድም”

Wednesday, 01 April 2015 14:07

“ጥበብ ስስት አትወድም”

ድምፃዊ፣ ገጣሚና የዜማ ደራሲው

ጌትሽ ማሞ

 

ለበርካታ አንጋፋና ወጣት ድምፃዊያን ግጥምና ዜማ በመድረስና በመስጠት ይታወቃል። ለራሱ በጣት የሚቆጠሩ ተወዳጅ ነጠላ ዜማዎችን ሰርቶ ለአድናቂዎቹ ያቀረበው የዛሬው እንግዳችን “እያሴ” የተሰኘ የመጀመሪያ አልበሙን 2001 ዓ.ም እነሆ በረከት ማለቱ ይታወሳል። ዛሬ (ረቡዕ መጋቢት 23 ቀን 2007 ዓ.ም) ደግሞ ለድምፃዊ፣ የዜማና የግጥም ደራሲው ጌትሽ ማሞ ሁለተኛ የሆነውን “ትወደኛለች” የተሰኘ አልበሙን ይፋ ያደርጋል። ከአርቲስት ጌትሽ ማሞ ጋር አዲሱን አልበሙንና በሌሎችም ስራዎቹ ዙሪያ አጠር ያለ አዝናኝ ቆይታ አድርገናል። መልካም ንባብ ...

ሰንደቅ፡- በርካታ ግጥምና ዜማዎችን በመስራት ትታወቃለህ፤ ምን ያህሉን ታስታውሳቸዋለህ?

ጌትሽ፡- እንደሚታወቀው ከዚህኛው አልበሜ በፊት የራሴ ሙሉ አልበም አለኝ። ከዚህ በተጨማሪ “መብቴ ነው” የሚለውን አካትቼ በርካታ ነጠላ ዜማዎችን ለአድማጭ አድርሻለሁ። በኮሌክሽን ደረጃ “ኤሌአባ” እና “ባላገሩ” ኮሌክሽን ከቁጥር አንድ እስከ ሦስት ላይ ሠርቻለሁ። እንዳልከው ደግሞ ለሌሎች ወጣትና አንጋፋ ድምፃውያንም ግጥምና ዜማ ሰጥቻለሁ ማለት ነው። ስራዎቹ ከ300 በላይ ይሆናሉ ሁሉንም ማስታወስ ያዳግተኛል።

ሰንደቅ፡- ግጥምና ዜማ መስራት እንደምትችል ያረጋገጥክበት አጋጣሚ ምን ይመስላል? እስቲ ስለ አነሳስህ አጫውተን?

ጌትሽ፡- እኔ ወደዚህ ሙያ የገባሁት ገና የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሳለሁ ነው። ተወልጄ ያደኩት 4ኪሎ በመሆኑ “ፎረም 84” የተሰኘ ክበብ ውስጥ ነው ኪነት መስራት “ሀ” ብዬ የጀመርኩት ማለት እችላለሁ። ከዚያ ደግሞ ቀስ በቀስ ወደ “ቢፍቱ ኦሮሚያ” ቡድን ተቀላቀልኩ። ከዚያም ወደሚሊተሪ ቤት ገባሁ። በዚያን ወቅት ሚሊቴሪው ቤት ስትሰራ የራሳችንን ዜማና ግጥም ፈጥረን አዲስ ነገር ማምጣት ይጠበቅብን ነበር። ዜማና ግጥም መድረስ ጀመርኩ የምለው እንግዲህ ያኔ ነው።

ሰንደቅ፡- እንደምትችል እርግጠኛ ሆነህ ለመጀመሪያ ጊዜ ግጥምና ዜማ የሰጠኸው ለማነው?

ጌትሽ፡- ባልሳሳት ለድምፃዊ ታደለ ገመቹ ነው። የኦሮምኛ ስራ ነው፤ ከዚያ በኋላ ወደ አማርኛ ስንመጣ ለሔለን በርሔ፣ ታምራት ደስታ ሰጥቻለሁ። አሁን ላይ እስከ አንጋፋው ድምፃዊ መሐመድ አህመድ ድረስ የሰጠሁዋቸው አሉ። እውነቱን ለመናገር ከጥቂት ድምፃውያን ውጪ ለብዙዎቹ በሀገር ውስጥ ለሚገኙ ድምፃዊያን ግጥምና ዜማ ሰጥቻለሁ ማለት እችላለሁ። ለቴዲና ለነዋይ ያልሰጠሁት ራሳቸው ስለሚደርሱ ነው። ለክቡር ዶ/ር ጥላሁን ገሰሰም ልሰጠው ተዘጋጅቼ ነበር ሳይሳካ ሞት ቀደመው እንጂ።

ሰንደቅ፡- ግጥምና ዜማ ለመስራት ምን አይነት ሁኔታዎች ይመቹሃል?

ጌትሽ፡- ዜማና ግጥም ስሰራ ብዙ ጊዜ እኔ ቦታ አልመርጥም። የሆነ ስሜት ሲሰማኝ ወይም ከአንድ ሰው ጋር ስጨዋወት ሀሳብ ከመጣልኝ ምናልባትም እዛው ዜማና ግጥም ልሰራ እችላለሁ። ለምሳሌ የጆሲ “መቼ ነው” የሚለውን ዘፈን የሰራሁት ከጆሲ ጋር ስናወራ የትዝታ ይዘት ያለው (Slow) ዘፈን ብሰራ ደስ ይለኛል ብሎ ነገረኝ። ከዚያ ከእሱ ተለይቼ በመኪና እየሄድኩ ነው የመጣልኝ በስልክ ቀርጬ ነው በኋላ በአሪፉ የተሰራው። ብዙዎቹን ስራዎች ወዲያውኑ እንደወረደ መስራት ይመቸኛል።

ሰንደቅ፡- ለብዙዎች ተወዳጅ የሆኑ ዜማና ግጥሞች እንደመስጠትህ ለራስህ ሁለት አልበሞችን ብቻ በመስራትህ አቅሙን ለራሱ አልተጠቀመበትም የሚሉህ ሰዎች አሉ። ያንተ አስተያየት ምንድነው?

ጌትሽ፡- እርግጥ ነው እኔም ለዜማና ግጥም አደላለሁ። ነገር ግን መዝፈኑም ላይ አለሁበት። የምወደውን ደስ እንዳለኝ እሰራለሁ። አሁን አሁን ደግሞ እንደሚታወቀው የቅጅ መብት ጥሰት መኖሩ ፈታኝ ነው። ይሄን ይሄን ጨምሮ ነው በአልበም ስራዬ ላይ የዘገየሁት እንጂ ሁሉንም በጣም ወድጄ ነው የምሰራቸው።

ሰንደቅ፡- ለአንጋፋና ወጣት ድምፃውያን ሰጥተሃቸው በአድማጭ ዘንድ ከመወደዳቸው የተነሳ ምናለ እኔ በሰራሁት ብለህ የምትቆጭበት ስራ አለ?

ጌትሽ፡- በፍፁም የለም። ጥበብ ስስት አትወድም። ስለዚህ ሰዎች ሰርተዋቸው የተመኘሁት ስራ የለም። እኔ የሰራኋቸው ዘፈኖች ሁሉ ለእኔ ያስቀመጥኳቸው ናቸው። በነገራችን ላይ አንድ ድምፃዊ ስራዬን ስለጠየቀኝ ብቻ አይደለም የምሰጠው። ለጠየቀኝ ድምፃዊ አዘፋፈን የሚመች ስራ ነው የምሰራው። ያን ስራ ደግሞ መልሼ ለራሴ ማድረግ አልችልበትም።

ሰንደቅ፡- ሌላው ጥያቄ ለሰራኸው ለዜማና ግጥም የሚመጥን በቂ ክፍያ አግኝተሃል?

ጌትሽ፡- ብዙ ተከፋይ ነኝ ብዬ አላስብም። ግን እስካሁን ከሰራኋቸው የማልረሳው ጋሽ መሐሙድ አህመድ ለአንድ ዜማና ግጥም 20 ሺህ ብር ከፍሎኛል። ይህም አዲስ ለሚያወጣው አልበሙ የሰራሁት ነው። በነገራችን ላይ ጋሽ መሐሙድ በሚሰራው አዲስ አልበሙ ውስጥ ሦስት ስራዎችን ሠርቼለታለሁ። በተረፈ ግን በተለይ ለጀማሪ ድምፃዊያን በትንሹ ነው የምሰራው። ዋናው ከገንዘቡ በላይ ስራውን በሚገባ ይሰራዋል? ያሳምረዋል? የሚለው ነው የሚያሳስበኝ። ያም ሲሆን ለራሱም እንጀራ ከፍቶ የእኔንም ስም በጥሩ ያስነሳል እያልኩ ነው የማስበው። መክፈል የሚችለውን አስከፍላለሁ። ነገር ግን መስራት እየቻሉ የገንዘብ አቅሙ የሌላቸውንም ማገዝ ደስ ይለኛል።

ሰንደቅ፡- በዚህ ሳምንት የሚለቀቀው አዲሱ “ትወደኛለች” አልበምህ ውስጥ የተካተቱት ስራዎችህ ለራስ ሰስተህ ያቆየሃቸው ስራዎች ናቸው ማለት እንችላለን?

ጌትሽ፡- በስስት የተቀመጡ አይደሉም። እኔ ለራሴ ብዬ ያዘጋጀዋቸውን ስራዎች ለሌላ ሰው አልሰጥም። እንደዚያም ለሌላ ሰው ያዘጋጀሁትን ስራ ለራሴ አልወስድም። አሁን ለምሳሌ እኔ ለአንተ ይሆናል የምለውን ዜማን ግጥም ስሰራልህ የአንተን ስልት ተመልክቼ ነው የምሰራው። ስለዚህ ይህ ስራ ለአንተ እንጂ ለእኔ አይሆንም። አስተካክዬ ለእኔ እንዲሆን ከማደርገው ይልቅ አዲስ ስራ መፍጠር ይቀለኛል ብዬ አስባለሁ። እናም አሁን በአዲሱ አልበሜ የሰራሁዋቸው ስራዎች ሁሉ ከመነሻው ለእኔ ብዬ የሰራዋቸው ናቸው።

ሰንደቅ፡- እንደው ግን ለሰዎች ሰጥተህ ከተወደደልህ ስራዎች መካከል በዚህ አልበሜ የማካተት ዕድሉ ቢሰጠኝ ብለህ ያሰብከው ስራ የለም?

ጌትሽ፡- በእውነት ምንም የለም። በጥበብ ስስት አላውቅም። ጥበብ ማለት ደግሞ ከእግዜር የሚሰጥ ነው። ያንን ነገር እንዴት ልቆጥበው እችላለሁ። ከሰሰትኩት ደግሞ ከላይ ሌላ የሚሰጠኝ አይመስለኝም።

ሰንደቅ፡- ይህ “ትወደኛለች” የሚለው አልበምህ ምን ያህል ጊዜ ወሰደብህ? ምን ያህል ባለሙያዎችስ ተሳትፈውበታል?

ጌትሽ፡- “ትወደኛለች” አልበም ከአራት ዓመት ያላነሰ ጊዜ ወስዷል። በዚህ ስራ ላይ እዩኤል ብርሃኑ በአንድ ግጥም ተሳትፏል። አልበሙ 16 ስራዎችን የያዘ ሲሆን፤ ከአንዱ በስተቀር ሁሉም የራሱ ፈጠራዎች ናቸው። 10ሺህ ኮፒ አሳትመናል፤ በአጠቃላይ አልበሙን ሰርቶ ለመጨረስ እስከ 350ሺህ ብር ወጪ ሆኗል።

ሰንደቅ፡- የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥሰት አሳሳቢ እንደሆነ ይታወቃል፤ አንተ ግን ያለስፖንሰር ነው የመጣኸው በምን ተማመንክ?

ጌትሽ፡- እውነቱን ለመናገር ስራው መሰማት የሚችል ነው። ነገር ግን ስፖንሰር የለውም። እንደዚህ መውጣቱ ጥሩ ነው። እስቲ ደግሞ ያለ ደጋፊ እንየው። ስራውም ጥሩ ስለሆነ ዋጋውን ይመልሳል የሚል ተስፋ አለኝ።

ሰንደቅ፡- በዚህ አልበም ውስጥ ከተካተቱት ስራዎች መካከል ለአንተ የተለየ ትርጉም የሚሰጥህ ስራ የቱ ነው?

ጌትሽ፡- “ሰው ያስፈልገኛል” የሚለው ዘፈን ለእኔ የተለየ ነው። ግጥሙን ለማስታወስ ያህል፤

ለሰው መድሐኒቱ ሰው ነው ከተባለ

የታመመ እንጂ በሰው የዳነ የታለ?

ምነው ታዲያ በአፍ በተረት ተነግሮ

መድሐኒት የሚሆን ሰው ጠፋ ዘንድሮ

ከመቼውም በላይ ዘንድሮ ከፍቶኛል

ውስጤን የማዋየው ሰው ያስፈልገኛል።

ሰንደቅ፡- ሙዚቃ ስራህ ነው፤ አንተ በምን ትዝናናለህ?

ጌትሽ፡- ሙዚቃን በመስራት በጣም ነው የምዝናናው። በተጨማሪ ደግሞ ማንበብና ፊልም ማየት ያዝናናኛል።

ሰንደቅ፡- ለአድናቂዎችህ ምን መልዕክት አለህ?

ጌትሽ፡- ያው ቅድም እንዳልኩህ አልበማችን ስፖንሰር የለውም። ወድጄው የሰራሁት ስራ በመሆኑ አድናቂዎቼም ሰምተው አስተያየታቸውን እንደሚሰጡኝ እጠብቃለሁ፤ ሁሉንም ስራዎች ጋብዤያቸዋለሁ። በጣም እወዳችኋለሁ በልልኝ። አመሰግናለሁ።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
11269 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us