“ውስጣዊ ግለትና እንፋሎት”

Wednesday, 08 April 2015 11:47

በአንፃራዊ የዕይታ ግጭት መነፅር ሲታይ


አሸናፊ መስቲካ 

 

“የወጣቱ ሠዓሊ የፈጠራ ጥበብ መነሻ፣ እንደማንኛውም የጥበብ ሰው ተፈጥሮና የሰው ልጅ ናቸው። በአንፃራዊ የሥርዓተ ተቃርኖ ልዩነትና የአንድነት ሕግ ላይ የተቃኘው፤ ይህ የተፈጥሮ ክስተትና የሰው ልጅ ማኅበራዊ ህይወት የማያቋርጥ ሂደት ነው። በጊዜና በዘመን ዕድሜ ውስጥ አይጠፋም። አይሻርም። ስለዚህ ለአሸናፊ የእነርሱን የተቃርኖ ልዩነትና አንድነት በሥዕላዊ ቋንቋ እና አናስራት (Visual Language and Elements) በሚዛናዊነት መፈለግ፤ በሚታይና በሚዳሰስ ሁኔታ ሥዕላዊ ቅርፅና መልክ አግኝተው ማሳየት መቻል፤ ዋነኛው ጥበባዊ ሙከራው ናቸው። ለአሸናፊ መስቲካ የሰው ልጅ በተፈጥሮአዊ ህልውናውና በማኅበራዊ የህይወት ኑሮው ውስጥ የሚያጋጥሙት አዎንታዊና አሉታዊ ክስተቶች ሁሉ የውስጣዊ ስሜቱንና እሳቤዎቹን ይመስጡታል፤ ያግሉታልም። ያቀዘቅዙታልም።” ይህን ያሉት የጋለሪያ ቶሞካ አርት ዳይሬክተር እና አንጋፋው ሠዓሊ እሸቱ ጥሩነህ ስለወጣቱ ሠዓሊ አሸናፊ መስቲካ ባሰፈሩት ሐተታ ነው።

ወጣቱ ሠዓሊ በቀለም የሚጫወት፤ በመስመር የሚተረጉም፤ ተቃርኖዎችን የሚያጠብና አንድነቶችን የሚያሰፋ ነው ሲሉ የሥዕል ስራዎቹን ተመልክተው የሚናገሩለት ታዳሚያን በርካቶች ናቸው። ይህ በጉልህ የታየው ደግሞ ባሳለፍነው አርብ መጋቢት 25 ቀን 2007 ዓ.ም ሣር ቤት በሚገኘው ጋለሪያ ቶሞካ ውስጥ “ውስጣዊ ግለትና እንፋሎት” የተሰኘ የሥዕል ትርዒት በተከፈተበት ወቅት ነው።

ለአገራችን የሥዕል ጥበብ ዕድገት የራሱን አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ ለሚገኘው ጋለሪያ ቶሞካ፤ ይህ አስራ አራተኛ የሥዕል ትርዒቱ መሆኑ ታውቋል። የወጣቱ ሠዓሊ አሸናፊ መስቲካ ስራዎችም ለቀጣዮቹ ሁለት ወራት በቤቱ ለዕይታ የሚቀርቡ ይሆናል። ሠዓሊው ከዚህ ቀደም በሸራተን አዲስ በተካሄደው “አርት ኦፍ ኢትዮጵያ” የሥዕል ትርዒት ላይ ከተሳተፉ በርካታ ሠዓሊያን ጋር ስራዎቹን ያሳየ ቢሆንም፤ ለብቻው የሥዕል ትርዒት ሲያዘጋጅ ግን ይህ የመጀመሪያው እንደሆነም በፕሮግራሙ ወቅት ተጠቅሷል።

በዕለቱ የሥዕል ትርዒቱን በይፋ ያስጀመሩት ሠዓሊ እሸቱ ጥሩነህ ሲሆኑ፤ የሠዓሊውን እናት ጨምሮ ቤተሰቦቹ ወዳጆቹ፣ የሥዕል አድናቂዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችም በስፍራው ተገኝተው እንደነበር ተመልክተናል። ከታዳሚያኑ መካከል ጥቂቶቹን በሥዕል ትርዒቱ ዙሪያ ያነጋገርናቸው ሲሆን፤ በተመለከቱት ስዕል የተለያየ ስሜት እንደተሰማቸውም ለመረዳት ችለናል።

በቶሞካ አርት ጋለሪ ኮሪደር ላይ ያገኘሁት አጥናፉ ደረሰ ሠዓሊውን በቅርብ እንደሚያውቀው ተናግሮ፤ ከሸራተን አዲስ የሥዕል ትርዒት መልስ ሠዓሊው ለብቻው የራሱን ሥራዎች በዚህ መልክ ማቅረቡ ደስታን እንደፈጠረለት ይናገራል። ስዕሎቹን በተመለከተ ሲናገር፤ “አንድን ስዕል ደጋግመን ባየነው ቁጥር የተለያየ ሀሳብ ልንሰጠው እንችላለን። እንዲያውም አንዳንዴ ሳስበው ስለ ስዕሉ ብንፅፍ ሠዓሊው ራሱ ያላሰበውን ሀሳብ ልንፈጥር እንችላለን ብዬ እገምታለሁ” ይላል።

እንደብዙዎቹ አስተያየት ሰጪዎች በተለያዩ ጥበቦች ውስጥ ተመልካች፣ አድማጭ ወይም አንባቢ ሊገነዘበው የሚችለው የጋራ ነጥብ አልፎ አልፎም ቢሆን በአንዳንድ ጥልቅ የስነ-ግጥምና የሥነ-ስዕል ስራዎች ውስጥ ላይገኝ ይችላል። ለዚህም እንደ ምሳሌ የሚያነሱት አንድን ስዕል ተመልክተው ሰዎች የተለያዩ አስተሳሰቦችና አረዳዶችን ማንፀባረቃቸው ነው። አንድን ሙዚቃ ሰምተን፤ አንድን ፊልም አይተን፤ አንድን መፅሐፍ አንብበን ሊሰማን የሚችለው ተቀራራቢ ስሜት እና ሀሳቡን የመረዳት አቅም በሥዕል ውስጥ ላይከሰት መቻሉን ሠዓሊ አሸናፊ በራሱ “ይህ የሥዕል ነፃነት ነው” ሲል ይቀበለዋል።

ለዚህም “ውስጣዊ ግለትና እንፋሎት” የተሰኘውን የሥዕል ትርዒት በዕድሜ ያልተገደቡ ታዳሚያን ተገኝተው ተመልክተውታል። ከእነዚህም መካከል የ13 ዓመቷ ሔለን አጥናፉ አንዷ ናት። ሔለን በግድግዳ ላይ ከተሰቀሉት የሥዕል ስራዎች ላይ ዓይኖቿን ተክላ ምስጢር በሚፈለቅቅ አኳሃን በስውር የሚታዪአትን ምስለ-ሰዎች ትቆጥራለች። “ስዕል በጣም እወዳለሁ” የምትለው ታዳጊ ሔለን፤ ነገር ግን የወደፊት ምኞቴ ዶክተር መሆን ነው ትላለች።

የሥዕል ጥበብ መምህር እና ባለሙያ የሆነችው ሰናይት ወርቁም በሥዕል ትርዒቱ ላይ ከታደሙት ሰዎች መካከል አንዷ ሆናለች። የወጣቱን ሠዓሊ አሸናፊ መስቲካ ሥራዎች በሚመለከት ስትናገርም፤ “አሼ በቀለም ነው የሚጫወተው፤ ከዚህ ቀደም ከማውቃቸው ሥራዎቹ ይህ በጣም ምርጥና ልዩ ነው” ትላለች። በአንድ ወቅት በአቢሲኒያ አርት ትምህርት ቤት አሸናፊ ተማሪዋ እንደነበር የምታስታውሰው ሰናይት፤ ሠዓሊው እድገት እያሳየ ስለመምጣቱ ምስክርነቷን ትሰጣለች። በጋለሪያ ቶሞካ ለዕይታ የበቁትን የሥዕል ሥራዎቹን በተመለከተ ርዕሳቸውን ወክለዋል ወይ? በሚል ላነሳንላት ጥያቄ ስትመልስ፤ “ለእኔ ርዕሱን ብቻ ተከትዬ አላየሁም። እኔ ስዕሉን አይቼ ለራሴ የሰጠኝን ትርጉም ነው የምወስደው” ትላለች።

ሠዓሊ አሸናፊ መስቲካ በበኩሉ ስለ ሥራዎቹ ሲናገር፤ ሥራዎቼን ሥሰራ “ውስጣዊ መልክ” ነው የምላቸው። በቶሞካ አርት ጋለሪ “ውስጣዊ ግለት እና እንፋሎት” በሚል የሚታየው የሥዕል ትርዒት መሪ ቃሉን የሰጡት ግን አንጋፋው ሠዓሊ እሸቱ ጥሩነህ ናቸው። ይህም የእኔን አሳሳልና ስሜት ተንተርሶ የተሰጠ ርዕስ ነው” ይላል።

“ህይወት ከተቃራኒ ሀሳቦች ነው የተሰራችው” የሚል እምነት አለኝ የሚለው ሠዓሊው፤ “የምሥላቸውን ሥዕሎች በነፃነት ያሰብኳቸውን ቅርጾች ነው በምክንያት የማስቀምጣቸው” ሲል ስለሥራዎቹ ያትታል።

በጋለሪያ ቶሞካ የተገኙት ታዳሚያን በተመለከቱት ስዕል ላይ ተመሳሳይ ሀሳብ እንዳልነበራቸው ስለመታዘባችን ላነሳነው ሀሳብ አስተያየቱን ሲሰጥም፤ “ስዕል ይሄ ነፃነቱ ነው ደስ የሚልህ፤ ተመልካቹ በህይወት ልምዱ ላይ ተመርኩዞ ነው አንድን ነገር የሚመለከተው” የሚለው አሸናፊ፤ “ቀለም በራሱ ለየራሳችን የምንሰጠው ግላዊ ትርጉም ስላለው ሁሉም እንደ ፍቃዱ እንዲተረጉም ስዕሎቹ ክፍት መሆናቸውን ይመሰክራል።” ባይ ነው። “አብዛኛው ተመልካች ስዕልን በማየት እና በመተርጐም ደረጃ ገና ነው። በመሆኑም የእኔን ሀሳብ ቀድሜ በመናገር ተመልካቾቼን ልጫናቸው አልፈልግም። ተመልካቹ የፈቀደውን ትርጉም ይስጥ፤ ያ ለእኔ ለቀጣይ ስራ ተጨማሪ ግብዓት ይሆነኛል” ይላል።

እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ የተመረጡ ስራዎቹን ለተመልካች ዕይታ ያቀረበው ወጣቱ ሠዓሊ አሸናፊ መስቲካ፤ ስዕልን መሳል ለእርሱ “ዲያሪ” (የዕለት ማስታወሻ) እንደመፃፍ ነው ባይ ነው። ስራዎቹ ሁሉ የሥዕል ትርዒትን ታሳቢ አድርገው የተሰሩ ሳይሆን ሀሳቦቼን የምገልፅባቸው ናቸው ሲል ስዕሎቹ የተሰሩባትን ሁኔታ ያስረዳል።

    በስተመጨረሻም ይህን ዕድል ያመቻቹለትን የቶሞካ አርት ጋለሪ አዘጋጆችን ምስጋና ይገባቸዋል የሚለው ሠዓሊው፤ “ተመልካቹም ትርዒቱን በነፃ በመጐብኘት ስዕልን የመተርጐም አቅሙን ለማዳበር ይረዳው ዘንድ ዓይኑን መሰል ሥራዎችን በማየትና በማበረታታት እንዲያለማምደው እጋብዛለሁ” ብሏል። በተቃርኖ የተሞላ እኛነታችንን በተመሠጠሩ መስመሮችና ቀለሞች ለመመልከት በጋለሪያ ቶሞካ የቀረበውን “ውስጣዊ ግለትና እንፋሎት” የሥዕል ትርዒት ለቀጣዮቹ ሁለት ወራት በነፃ መታደም እንደሚቻል አዘጋጆቹ ጠቁመዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
15349 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us