የ“ሰኔ 30” ቀጠሮ

Wednesday, 15 April 2015 14:51

ፍቅር፣ ትዝታ፣ ፀፀት፣ ያደረ ስህተትና ይቅር ባይነት የሚፈራረቁበት ፊልም ነው፤ በበኃይሉ ዋሴ ተፅፎ፣ በፍቅረየሱስ ድንበሩ ዳይሬክት የተደረገው “ሰኔ 30”። በኩል ፊልም ፕሮዳክሽን ተዘጋጅቶ የቀረበው ይህ ፊልም በአይረሴዎቹ “አይራቅ”፣ “አምራን” እና “እኔና አንቺ” በተሰኙ ፊልሞቹ ልምድ ያለው ዳይሬክተር የሰራው የፍቅር ፊልም ነው።

በብዙዎቻችን ዘንድ “ሰኔ 30” የትምህርት ውጤት የሚለይበት፤ ጎበዝና ሰነፍ የሚነጥሩበት፤ ፍቅር ይፋ የሚወጣበትና ጉልበት የሚፈተንበት ዓመታዊ ክስተት እንደሆነ የሚያስታውሰን ይህ ፊልም፤ በ“ሰኔ 30” ከትምህርት ጊዜ ውጤት ባሻገር የህይወት ውጤትንም የምናይበት ፊልም ሆኖ ተሰርቷል።

ፍቅሯ፣ ሴትነቷና ዕድሜዋ ውሳኔ አስጥተዋት መልህቋ እንደተበጠሰ መርከብ ሰላም ማጣት ከወዲያ ወዲህ የሚንጧት ህይወት (አዚዛ አህመድ)፤ ፍቅር የሚያስከፍላትን እንጥፍጣፊ ዋጋ ስትከፍል እናይበታለን። ትኩረቱ የተበተነው፣ መወሰን የቸገረውና ፍቅሩን ክፍት የሚያሳድረው መሳይ (ሰለሞን ሙሄ) በበኩሉ የዘመናት ስህተቱን በአንድ ቀን አጋጣሚ ሲቀይር በ“ሰኔ 30” ፊልም እናየዋለን። “የትናንት ስህተቱ በቁጭት የሚያነሳው፤ ታሪኩን ለሌሎች መማሪያ የሚያደርገውንና ያጣውን ነገር የሚናፍቀው ዓይነስውሩ የዩኒቨርስቲ መምህር ሰውነት (ሽመልስ አበራ) ወጣትነትን፣ ፍቅርንና ህይወትን የሚገልጽበት መንገድ የታሪኩ ቅያስ ሆኖ በ“ሰኔ 30” እንመለከታለን።

በውጪ ሀገር ለሶስት ዓመት የሚያቆይ የትምህርት ዕድል ያጋጠማት ህይወት ጉዟዋ በተቃረበ ቁጥር የፍቅሯ ነገር መጨረሻው ግር ሲላት፤ በስራው የተወጠረውና ገና ብዙ ይቀረኛል የሚለው ጓደኛዋ መሳይን ስለመጨረሻው መጨረሻ ለመነጋገር ቀጠሮ ትይዛለች። በዚያ ቀጠሮ አፍታ ግን ወደፍቅረኛው ይጣደፍ የነበረው መሳይ የዓይነ ስውሩ የሰውነትን መነፅር በመስበሩ የጥፋተኝነት ስሜት ስለተሰማውና እግረ-መንገዱንም መንገድ ሊመራው አስቦ ጉዞ ይጀምራል። ይህ ግጥምጥሞሽ ሁሉ በ“ሰኔ 30” የተደረገ ቀጠሮ ላይ ያጠነጥናል።

ፍቅረኛው ህይወት ደግማ ደጋግማ ስለምታነሳው የ “መቼ ታገባኛለህ?” ጥያቄ “እንቆይን” መልሱ የደረገው ጋዜጠኛው መሳይ “አርጅተንም ቢሆን እንጋባለን” የሚለው የፀና መልሱ ነበር። ዳሩ ግን እግረ-መንገድ አብሮት እየሄደ ያለው ሰውነት ከ30ዓመታት በፊት የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ የተያዘ ቀጠሮን ምክንያት አድርጎ ያነሳው ታሪክ አስተሳሰቡን ይቀይረዋል። በስኳር ህመም ምክንያት የዓይን ብርሃኑን ያጣው ሰውነት፤ በወጣትነት እድሜው ትውደው የነበረችን ሴት ችላ ብሎ ትምህርቱና ፖለቲካው ላይ በማተኮሩ እንዳጣት በቁጭት ሲናገር በወጣቱ መሳይ ማስተላለፍ የቻለው አንዳች ነገር ነበር።

“ጓደኛ ካለችህና ከተዋደዳችሁ ጊዜ ሳትፈጅ አጋግባት”፤ የሚለው ሰውነት፤ ሴት ልጅ ማረፊያ የሚሆናትን ዛፍ እንደምትፈልግ ወፍ ናት የሚል ሃሳብ እንዳለው አስረድቶ ፍቅር ካለ ትዳር በፍጥነት ይፈፀም ሲል ይመክራል። “ሰኔ 30” በሃሳብና በአካል የተራራቁ ሰዎችን የሚያጣምር የፍቅር ታሪክ ነው።

“ሰኔ 30” ፊልም የዘወትር የሚመስሉ ጥቃቅን ችግሮቻችንን በጉልህና በስላቅ ያሳየናል። ለምሳሌ የትራንስፖርት ችግራችን የመከባበራችንን አጥር ምን ያህል እንዳፈረሰው አዛውንትን ገፍትሮ የሚጓዝ ወጣት በማሳየት ይሳለቃል። የመብራት መጥፋትን ዘወትራዊነት ለማሳየት ደግሞ በፀጉር ቤት ድንገት መብራት እልም ሲል አስተካካዩ “መብራት ሀይሎች ስራ ጀመሩ ማለት ነው” በሚል ሸንቆጥ የሚያደርግ እውነት አዘል ትችቱ ተመልካችን ያስፈግጋል። በሌላም በኩል ጋዜጠኛው መሳይ በሚያዘጋጀው “ሰለምን እንወያይ” ፕሮግራም ላይ የሚነሱት ሃሳቦች ላይ አድማጩ የሚሰጠው አስተያየት በራሱ በኤፍ ኤሞቻችን አሰራር ላይ ብዙ የሚታይና እርምት መሆን የሚችል ሃሳብ አለው። ይህም በመሆኑ እንደሀገር “ሰኔ 30” ብዙ ውጤታችንን የሚናገርና የሚያሳይ ፊልም ነው ማለት ይቻላል።

በፊልሙ ውስጥ እንዲህ ቢሆን ኖሮ የሚያሰኙ ሃሳቦችን የሚከሰቱ ጥቂት ክፍተቶች መታየታቸው አልቀረም። “ሰኔ 30” ፊልም መነገርና መታየት የሚችሉ ብዙ ሃሳቦችን የያዘ ፊልም ነው። ነገር ግን እንደፊልም ቴክኒካል የሆኑ ጉድለቶች ባይኖሩት እንኳን በተመልካች አይን ትዝብት ላይ የሚጥሉ ጥቃቅን ክፍተቶችን መሙላት ነበረበት።

የመጀመሪያው ክፍተት ፊልሙ በምልሰት ታሪክ የተሞላ መሆኑ ነው። ምልሰት በፊልም ውስጥ ችግር የለውም። ነገር ግን ሬድዮ ድራማ ሁሉ ነገር በንግግር ብቻ መገለፅ ከፊልም አይጠበቅም። ፊልም ከሚነገር ይልቅ የሚታይ ነገር ላይ ያተኩራልና። በተለይ የሰውነትንና የሙሉን ወጣትነት በጉጉት ከምንሰማ ይልቅ በቁንፅልም ቢሆን ማየት ብንችል መልካም ነበር።

ሁለተኛው በፊልሙ ውስጥ ተደጋግሞ የሚታየው ጉድለት “የሞባይል ስልክ መርሳት ነው” መሳይ በተደጋጋሚ ሞባይል ስልኩን ይረሳል። ይህ ደግሞ ዳይሬክተሩ ሆን ብሎ እንዲረሳ ሲያስገድደው እና ለታሪኩ ውጥረት ሲጠቀምበት እናያለን።

ያም ሆኖ “ሰኔ 30” ፊልም ምርጥ አተዋወን፤ ምርጥ ታሪክና ዝግጅት የሚታይበት፤ ተመልካች ከሲኒማ ቤቶች ሲወጣም ጥያቄ ብቻ ሳይሆን መልስ የሚያገኝበትና የሚነገር ታሪክ ያለው ጥሩ ፊልም በመሆኑ የዳይሬክተር ፍቅረየሱስ ድንበሩን ጥረት እና የአንጋፋና ወጣት ተዋንያኑን ጥምረት ሳናደንቅ አናልፍም። መልካም የመዝናኛ ሳምንት ይሁንላችሁ።

  

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
15482 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us