“የማለዳ ኮከቦች 24 ምርጦችን አግኝቷል”

Friday, 24 April 2015 12:25

 


 

ፀደይ ፋንታሁን፣ የፕሮግራሙ ዋና አዘጋጅ ፍጹም አስፋው እና ሙሉጌታ ዘሚካኤል

 

ወጣቶች ተሰጥኦቸውን አውቀው እና አዳብረው የተሻለ ደረጃ እንደደረሱ ደጋፊና መንገዱን የሚያሳይ ያስፈልጋቸዋል። ከነዚህም ተቋማት መካከል ትምህርት ቤቶችና ኮሌጆች፣ የስልጠና ማዕከላትና የተሰጥኦ ውድድር ስፍራዎች “ኢትዮጵያን አይድል ተጠቃሾች ናቸው። እንደሚታወቀው በሙዚቃው ዘርፍ “ኢትዮጵያን አይድል”፣ “ባላገሩ አይዶል”፣ ቀጥሎም “ኮካኮላ ሱፐር ስታር” አሁን በቅርቡ ደግሞ “መረዋ” እንዲሁም “ኢትዮ -ታለንት ሾው” የተሰኙ የተሰጥኦ ውድድሮች በስፋት በቴሌቭዥን መስኮቶች እያየን እንገኛለን።

በቦጋስ ፊልም ፕሮዳክሽን እየተዘጋጀ በየሳምንቱ በኢቢኤስ ቲቪ በመታየት ላይ የነበረውና ባሳለፈውን ሳምንት የተጠናቀቀው “የማለዳ ኮለቦች” የተሰጥኦ ውድድር ደግሞ አንዱና የተለየ መልክ የነበረው ነው ማለት ይቻላል። “በፊልሞቻችን ላይ የምንመለከታቸው ተዋንያን ተደጋጋሚ እየሆኑ በመምጣታቸው፤ አዳዲስ ፊቶችንና ችሎታ ያላቸውን ልጆች ለማስተዋወቅ የተፈጠረ ፕሮግራም ነው” ሲል የፕሮግራሙ ስራ አስኪያጅ አቶ እስከዳር አስፋው ይገልጻል። “የማለዳ ኮከቦች” ችሎታው ያላቸውን ወጣቶች ወደ አደባባይ በማውጣት በትውውቅና በዝምድና እየተንደረደረ ያለውን የፊልም ስራ አካሄድ እንዳይቀጥል እንደአንድ እርምጃ የሚያገለግል ስለመሆኑ ብዙዎች ይስማሙበታል።

ፕሮግራሙ ቀጣይነት ባለውና በተወሰነ ጊዜ ውስጥ እንዲቀጥል ለማድረግ እየሰሩ ስለመሆናቸው የሚናገረው ስራ አስኪያጁ፤ “የማለዳ ኮከቦች” በየስድስት ወሩ አንድ ዙር ጨርሶ ተሸላሚዎችን ይፋ ለማድረግ ይጥራል ብለዋል።

ይህ የመጀመሪያ ነው የተባለለት ፕሮግራም ከመነሻው 415 ተመዝጋቢዎችን የተቀበለ ሲሆን፤ ለተመልካች እይታ ያበቃቸው ተወዳዳሪዎች ግን 120 ብቻ መሆናቸውንም ስራ አስኪያጁ ይናገራል። ለዚህም ምክንያቱን ሲያስረዱ፤ “ብዙዎች ፍላጎት ብቻ ኖሯቸው የሚመጡ ይሆናሉ። ሁሉንም ተመዝጋቢዎች በቲቪ ለተመልካች ማድረስ ለራሳቸውም ሞራል ሆነ ለተመልካች ክብር ሲባል በዳኞች ታይተው ተቀንሰዋል። በሌላ በኩል ፕሮግራሙ ላስቀመጠው የጊዜ ገደብ የሚሆኑትን ብቻ ይዘን ቀርበናል” ይላሉ።

በዚህ መልክ ተጣርተው ተመልካቹና ባለሙያ ዳኞች በሰጧቸው ድምፅ መሠረት ወደመጨረሻው ዙር ያለፉትን ስድስት ተወዳዳሪዎች ብቻ ሳይሆን በርካቶችን አፍርተናል የሚሉት ስራ አስኪያጁ፤ “በተለያዩ የትወና ዘውጎች ተፈትነው ከመጡት ውስጥ 24 ምርጥ አክተሮች ወጥተዋል ብለን እናምናለን” ባይ ነው። እነዚህን ወጣቶች በተለያዩ ድረ-ገፆች ማስተዋወቅና ተከታታይ ድራማ የመስራት ዕቅድ የነበረ ቢሆንም አለመሳካቱን የሚናገረው ስራ አስኪያጁ፤ በቀጣይ ግን (ተዋንያንን ከሚመለምሉ ካስት ኤጀንቶች ጋር በመተባበር ወጣቶቹ በፊልም ስራዎች ላይ የሚሳተፉበትን እድል ለማመቻቸት እየሰራን ነው ይላሉ።

በዘንድሮው የመጀመሪያ ዙር አሸናፊ የሆኑት ፀደይ ፋንታሁን እና ሙሉጌታ ዘሚካኤል ናቸው። በቀጣይም በጋቦስ ፊልም ፕሮዳክሽን የሚሰራና የፊልም ፅሁፍ በተጠናቀቀ ፊልም ላይ ይሳተፋሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ በባለፈው እሁድ ሚያዚያ 4 ቀን 2007ዓ.ም በፍሬንድ ሺፕ አዳራሽ በተካሄደ የሽልማት ፕሮግራም ቦጋስ ፊልም ፕሮዳክሽን ከዳሽን ቢራ ጋር በመተባበር ለእያንዳንዳቸው የ50ሺ ብር ሽልማት (ማለትም ለመጀመሪያ ፊልማቸው ስራ የውል ክፍያ) ተፈፅሞላቸዋል።

“የማለዳ ኮከቦች” ፕሮግራም ላይ የሚቀርቡ ተወዳዳሪዎች የሚዳኙት ሙያውን ጠንቅቀው በሚያውቁና ልምድ ባላቸው ዳኞች ነው የሚለው ስራ አስኪያጅ፤ አርቲስት ቴዎድሮስ ተስፋዬ በትወና በዳይሬክቲንግ ጥሩ ስምና ዝና ያለው ነው። ማህሌት ሰለሞን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቴአትር ምሩቅ ስትሆን ከዚህም ባለፈ በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት የቴአትር መምህር በመሆንም እያገለገለች ትገኛለች። ሌላው ተወዳጅ ተዋናይና ዳይሬክተር ሚካኤል ሚሊዮንም እንዲሁ ለዳኝነቱ ብቁ ይሆናሉ ያልናቸው ባለሙያዎች ናቸው ሲል ገልጸዋል። ዳኞቹ እስካሁን ሙያዊ አስተያየት በመስጠትና ለተወዳዳሪዎቹም ድጋፍ በማድረግ ሰርተዋል። ለቀጣይም ከተጋባዥ ዳኞች ጋር በመሆን አብረውን ይሰራሉ የሚል ተስፋ የሚለው እስከዳር፤ ለጊዜው በሚዲያ ሊነገር የማይችል የክፍያ መጠንም ለዳኞቹ ስለመቅረቡ፤ ነገር ግን ክፍያው እንደዋና ነገር በሁሉም ወገን እንዳልተነሳ ያስረዳሉ።

አንድ ተዋናይ በሚሰራው ስራ ጥሩነትና መጥፎነት የራሱ አቅም እንዳለ ሆኖ በአዘጋጁ የሚሞረድበት ሂደት እንዳለ የጥበቡ ተከታታዮች ይመሰክራሉ። ታዲያ ወጣቶቹ በጥንድ እንዲሰሩት ለተመረጡበት የ10 ደቂቃ ስራ የእነርሱን ችሎታ ብቻ ሳይሆን የአዘጋጆቹንም አቅም ይናገራል ማለት እንችላለን? በሚል ላቀረብንለት ጥያቄ ሲመልስም፤ “እኛ በስራው ሂደት ወጣቶቹ ወደፊልም ሙያ ሲገቡ አዘጋጆቻቸውን በምን ያህል ደረጃ ይሰማሉ፤ የሰሙትንም በተግባር ያሳያሉ የሚለውን ለመፈተሸ እንጂ የአዘጋጆቻቸውን ችሎታ ለማየት አይደለም፤ የተፈተኑት ተዋንያኑ እንጂ ፊልሙ አይደለም” ሲል መልሰዋል።

ቦጋስ ፊልም ፕሮዳክሽን ይህን የተሰጥኦ ውድድር ሲጀምር ምንም አይነት ግዙፍ ካፒታል ያልነበረው እንደሆነ የሚናገረው ስራ አስኪያጁ፤ ዋነኛው አላማችን ፊልም የመስራት ፍላጎት ያላቸውን ወጣቶች ተሰጥኦአቸውን ገምግሞ ለአደባባይ በማብቃት መሸለም ነው ይላል። ያም ሆኖ የስፖንሰር ጉዳይ አሳሳቢ ሳይሆን ስራው መጠናቀቁን በመጥቀስ፤ ፕሮግራማችን ከተወደደ ስፖንሰር የሚያደርጉ አካላት አይጠፉም ሲል ያለውን ተስፋ ይገልፃል።

“የማለዳ ኮከቦች” የተሰጥኦ ውድድር ትወናን ብቻ በሚመለከት የመጀመሪያ ቢሆንም ከተመልካቹ የነቀፌታ አስተያየት እንዳልደረሳቸው የሚያስረዳው አቶ እስከዳር፤ “በግለሰብ ደረጃ ቅሬታ ሊኖር ይችል ይሆናል ነገር ግን ፕሮግራሙን በምክንያት የተቸ አንድም አስተያየት አልደረሰንም” ብሏል።

በፕሮግራም ሂደት አይረሴና የወጣቶች ተሰጥኦ በአስገራሚ ሁኔታ ያየንበት ነበር የሚለው፤ የቦጋስ ፊልም ፕሮዳክሽን ስራ አስኪያጅ አቶ እስከዳር አስፋው፤ በተለይም የመሪ ትወና (ትራጀዲ) ወቅት አገሪቱ ሀብተጊዮርጊስ የተባለች ተወዳዳሪ ከተጠባባቂ መጥታ የሚያስገርም ብቃቷን አሳይታለች። በዚህም ዳኞችን ጨምሮ አዳራሹን በሙሉ በማስለቀቅ የትወና ችሎታዋን አሳይታለች። ይህ ክስተት ደግሞ እኔ ብቻ ሳልሆን ፕሮግራሙን የተከታተሉትም ይመሰክራሉ ይላል። ሌላው አይረሴ ገጠመኙን ይናገራል። በሌላም በኩል ተወዳዳሪዎቹን ወደ 10 ለማምጣት በነበረው ሂደት አንደኛ ሆና የተሸለመችው ፀደይ ፋንታሁን ይዛው የመጣችው ገፀ ባህሪይ በብዙዎች ዘንድ ያልተጠበቁና አስደናቂ ነበር ሲሉ ይገልፀዋል። የወጣቷ የትወና ብቃት ለሌሎች ምሳሌ መሆን የሚችል ጭምር ነበር በሚል ይገልፀዋል።

በውድድር ሂደቱ ከዚህ በኋላ በድጋሚ የመወዳደር ዕድል እንደማይኖር የሚናገረው እስከዳር፤ ለሌሎች አዳዲስ ልጆች ዕድል መስጠት ስለሚያስፈልግ እድሉን ያገኙት 120 ዎቹ ከዚህ በኋላ የሚመጡ አይመስለኝም ባይ ነው። በአሁኑ ወቅት ራሱ ለቀጣዩ ውድድር ከ400 በላይ ሰዎች መመዝገባቸውን ተናግሮ፤ ልምድ ያላቸውን ከአዳዲሶቹ ጋር ቢወዳደሩ ተጽዕኖ ሊኖር ስለሚችል አዳዲሶችን እንጂ ነባሮችን አናወዳድርም ይላል። ነገር ግን በባለፈው የመጀመሪያ ውድድር ጊዜ ጥሩ ናቸው ተብለው ለተመልካች የታዩት 120 ሰዎችን ለማስተዋወቅ የሚረዳ አዲስ ድረ-ገፅ አዘጋጅተናል። በዚያ መንገድ እንዲተዋወቁና ከሌሎችም ፕሮዳክሽኖች ጋር ቢሆን ፊልም የመስራት እድል እንዲያገኙ እየሰራን ነው ብሏል። “120ዎቹን ተወዳዳሪዎች በሙሉ ጥለናቸዋል ማለት አይደለም” ሲል ተስፋ እንዳላቸው የሚገልፀው ስራ አስኪያጁ፤ “የማለዳ ኮከቦች” በትወና ዙሪያ ባለተሰጥኦዎችን ለማውጣት የሚሰራ ፕሮግራም ሲሆን፤ በቀጣይ የፊልም ስራዎች ውስጥ የመታየት አቅም ያላቸው ልጆች አሉ” ይላል። የፕሮግራሙ ሁለተኛና ቀጣይ ዝግጅትም በቅርቡ እንደሚጀምር አዘጋጆቹ አስታውቀዋል።

ይምረጡ
(6 ሰዎች መርጠዋል)
15910 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us