“ኢትዮጵያን ስፔሊንግ ቢ አዝናኝና አስተማሪ ፕሮግራም ነው”

Thursday, 30 April 2015 11:57

አቶ ቶማስ ተሾመ የፕሮግራሙ ማኔጀርና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዘንድሮ ለሶስተኛ ጊዜ የሚካሄደው “የኢትዮጵያ ስፔሊንግ ቢ” (Ethiopian spelling Bee) በበርካታ ታዳጊዎች ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅ አዝናኝና አስተማሪ ፕሮግራም ነው። ይህ ፕሮግራም የታዳጊዎች የቃላት አቅም ከማሳደጉም ባሻገር አዝናኝነቱ ከፍ ያለ ነው ይላል፤ “የኢትዮጵያን ስፔሊንግ ቢ” ፕሮግራም ማኔጀርና ኮሚኒኬሽን ባለሙያ አቶ ቶማስ ተሾመ።

ቅዳሜ ሚያዝያ 24 ቀን 2007 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ዋናው ግቢ ውስጥ በሚገኘው ማንዴላ አዳራሽ ከመላ አገሪቱ ማጣሪያውን አልፈው ለመጨረሻ ውድድር የሚቀርቡ 200 ታዳጊዎች ተገኝተው አሸናፊው እንደሚለይ ይጠበቃል። የፕሮግራሙ ሃሳብ አመንጪ በአሜሪካ የሚገኘው ናሽናል ስክራይፕስ ስፔሊንግ ቢ (National Scripps Spelling Bee) እንደሆነ የሚናገረው ቶማስ፤ በኢትዮጵያና በአፍሪካ ይህን ውድድር አዘል ጨዋታ ለማስፋፋት ጥረት ያደረጉትና መስራቹ ደግሞ በህፃናት ሥነ-ልቦና ጤና ዘርፍ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት ኢትዮጵያዊ አቶ አብይ ተክሌ መሆናቸውን ይናገራል። አቶ አብይ ተክሌ፤ በአሜሪካ ሀገር ቆይታቸው የኢትዮጵያ ብሎም የአፍሪካውያን ታዳጊዎች ተሳትፎ አለመኖሩ የፈጠረባቸው ቁጭት ለዚህ ፕሮግራም መጀመር ምክንያት እንደሆናቸው ሲያስረዱ፤ “የስፔሊንግ ቢ” ግንዛቤዬ በናሽናል ስክራይፕስ ስፔሊንግ ቢ ውድድር ላይ ብቻ የተወሰነ ነበር። ነገር ግን በአንድ አጋጣሚ ከወዳጆቼ ጋር ሜሪላንድ ውስጥ የደቡብ እስያ “ሳውዝ ኤዥያን ስፔሊንግ ቢ” የተሰኘ ውድድር ስመለከት ለምን ለኢትዮጵያውያን ታዳጊዎች በሚሆን መልኩ የራሳችንን የስፔሊንግ ቢ ውድድር አንፈጥርም በሚል በአሜሪካና በኢትዮጵያ በሚገኙ ማህበረሰብ ውስጥ ስራውን ጀመርነው” ይላሉ።

የዚህ ውድድር አሸናፊ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ የአሜሪካን ቪዛ አግኝቶና የአንድ ሳምንት ሙሉ ወጪው ተሸፍኖ በዋሽንግተን ዲሲ በሚካሄደው አለምዓቀፍ የስፔሊንግ ቢ ውድድር ላይ እንዲሳተፍ ዕድሉ ይመቻችለታል።

እድሜያቸው ከ14 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ማለትም ከ3ኛ እስከ 8 ክፍል ያሉ ተማሪዎች ብቻ እንደሚወዳደሩበት የሚናገረው ቶማስ፤ ውድድሩ በመላው አገሪቱ በተደረገ ማጣሪያ ወደመጨረሻው የደረሰ ቢሆንም ተማሪዎቹ ግን ከትምህርት ቤታቸው፣ ከክፍለ ከተማቸው ከአካባቢያቸው አሸናፊ በመሆን የተመረጡ ስለመሆናቸው ያስረዳል። በዚህ ሂደት ውስጥም “የኢትዮጵያ ስፔሊንግ ቢ” ፕሮግራም ታዳጊዎች በማጣሪያ ሂደት የሚያጋጥማቸውን ውድድሮች በሙሉ ከየትምህርት ቤቶቹ ጋር በመተባበር ሰርቷል።

“የፕሮግራሙ ዋና ዓላማ ታዳጊዎች ኢትዮጵያን ወክለው እንዲሳተፉ ማስቻል ነው” የሚለው የፕሮግራሙ ማኔጀርና የኮሙኒኬሽን ባለሙያው አቶ ቶማስ ተሾመ፤ ታዳጊዎቹ ባገኙት ዕድል ተጠቅመው አገራቸውን በማስተዋወቅና ከሌሎች አገር ተማሪዎችም ልምድ በመውሰድ የተሻለ ደረጃ ይደርሳሉ ብለን እንጠብቃለን ይላል። “ፕሮግራሙ ሲዘጋጅ አንደኛ የሚወጡት ተወዳዳሪዎች አሜሪካን ሀገር ሄደው እንዲወዳደሩ ብቻም አይደለም። በሁሉም ተወዳዳሪዎችና ታዳጊዎች መካከል የንባብ ባህልን ማዳበር ሌላኛው ዓላማችን ነው። ይህም ሲባል በእንግሊዝኛ ላይ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ቋንቋ ሊሆን ይችላል” ይላሉ። በመሆኑም ያለንን ዝቅተኛ የማንበብ ባህል በማሻሻል በታዳጊዎቹ መካከል በጨዋታ መንፈስ አዝናኝ የሆነ ውድድር ማድረግ የተሻለ ይሆናል በሚል የተነሳ ፕሮግራሙ እንደሆነ ተናግረዋል።

ታዳጊዎቹ ይህን በየዓመቱ የሚካሄድ ፊደላትን የማንጠር ውድድር ለመሳተፍ የሚገጥማቸው ተግዳሮቶች ስለመኖሩ የሚናገረው ቆማስ፤ ይህን ዕድል አግኝተው ችሎታቸውን አሳይተው የተሻለ ደረጃ መድረስ የሚችሉ በርካታ ልጆች ቢኖሩም መሰናክሎቹ አሁንም እንዳሉ ታዝበናል ይላል።

የፕሮግራሙ ትኩረት ትርፍ አለመሆኑን የሚናገረው ቶማስ፤ ታዳጊዎቹን ለማግኘትና ለከፍተኛ ውድድር ለማብቃት ከ700 ያላነሱ ትምህርት ቤቶችን ስለማነጋገራቸው አልሸሸገም። ፍቃደኛና ተባባሪ የሆኑ ትምህርት ቤቶች ስናገኝ መሞላት የሚገባው ፎርም እንደሚላክ፤ የግል ትምህርት ቤቶች ሁለት ሺህ ብር እንዲከፍሉ ሲደረግ ይህም ለመንግሥት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ድጋፍ ጭምር የሚውል እንደሆነ ያስረዳል። በዚህም ከአንድ ትምህርት ቤት እስከስድስት ተማሪዎች ክፍለ ከተማቸውን (አካባቢያቸውን) እንዲወክሉ ይደረጋል ብሏል። ያም ሆኖ “የኢትዮጵያን ስፔሊንግ ቢ” ውድድር አስፈላጊነትና ጠቀሜታን ሁሉም ትምህርት ቤቶች የሚረዱት ቢሆንም፤ ለተማሪዎቻቸው ዕድሉን ለመስጠት ፍቃደኛ የሚሆኑት ግን ጥቂቶች ብቻ መሆናቸው አሁንም ድረስ ፈተና ሆኗል የሚል አስተያየት ይሰጣል። ይህ አካሄድ ወደፊት የማይቃና ከሆነ ግን በግል ተወዳዳሪዎች የሚከናወን ፕሮግራም እንዘረጋለን የሚል ዕቅድ ስለመያዙ የፕሮግራሙ ማኔጀርና የኮሙኒኬሽን ባለሙያው ይጠቁማል።

ውድድሩ በታዳጊዎቹ ዘንድ የሚፈጥረው የአሸናፊነት መንፈስና ጥረት አዝናኝነቱ ከፍ ያለ ነው የሚለው ቶማስ፤ ተማሪዎቹ በመድረክ ላይ የሚያሳዩዋቸው ድርጊቶች፣ የሚገልጸባቸው መንገዶች ደስታና ጭንቀታቸው በራሱ ለተመልካች አዝናኝ ስሜት አለው ብሏል። በሂደትም ይህ ፕሮግራም ይበልጥ እየታወቀ ሲመጣ ተወዳጅና በርካቶች የሚጓጉለት ይሆናል ብለን ተስፋ እናደርጋለንም ሲሉ አዘጋጆቹ ያስረዳሉ።

ወደዓለም አቀፍ ውድድር ከመሄዳቸው በፊት ታዳጊዎቹ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፊታችን ቅዳሜ የመጨረሻውን አዝናኝና አስተማሪ ፕሮግራም የሚያካሂዱ ሲሆን፤ በዚያም ዕለት አንደኛ የወጣው ተወዳዳሪ ከአንድ የቤተሰብ አባል ጋር ለአንድ ሳምንት በአሜሪካ ሀገር በሚደረገው “የናሽናል ስክራይፕስ ስፔሊንግ ቢ” ውድድር ላይ እንዲታደም ሙሉ ወጪው እንደሚሸፈን የሚገልፀው ቶማስ፤ ከዚያም ባለፈ ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ድረስ ለሚወጡት ተወዳዳሪዎች የኮምፒዩተር፣ የላፕቶፕ፣ የታብሌትና የካሜራ ሽልማቶች ሲኖራቸው፤ በተጨማሪም ለእያንዳንዳቸው ዋንጫ ይበረከትላቸዋል ተብሎም ይጠበቃል። ከዚህም ባሻገር ከ200 ተወዳዳሪዎች መካከል ከአንድ እስከ ሃምሳ ያሉት በሙሉ የሜዳሊያ ተሸላሚ ይሆናሉ። በቅዳሜው ውድድር አንደኛ የሚወጣው ታዳጊ በአሜሪካ ሀገር በሚካሄደው ውድድር ማሸነፍ ከቻለ 35ሺ የአሜሪካን ዶላር ወይም 770ሺ ገደማ የኢትዮጵያ ብር ተሸላሚ ይሆናል፡፡ ውድድሩን በዳኝነት የሚመሩት የቋንቋ ባለሙያዎች፤ ልምድ ያላቸውና ከአሜሪካ አገር ጭምር የመጡ ባለሙያዎች ስለመኖራቸው የፕሮግራሙ ማኔጀርና የኮሚኒኬሸን ባለሙያው አቶ ቶማስ ተሾመ ለሰንደቅ ጋዜጣ አስረድተዋል።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
11438 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us