በሳታየር የተሟሸው “ከራስ በላይ ራስ”

Wednesday, 13 May 2015 11:20

“አንዱ ባንዱ ሲስቅ

ጀንበር ጥልቅ” እንዲል ባለቅኔው፤ ሁሉም በራስ ወዳድነት ጥላ ስር ሆኖ የማይሆነውን ሲሆን የምናይበት ቴአትር ነው። ራስን የመውደድ ጠረፍ፣ የብር አምላኪነት አፋፍ፣ የተደበቀ ማንነትና ድንገት የተፈጠረ ሰውነት ፊት ለፊት የሚፋጠጡበት ኮሜዲ ቴአትር ነው፤ “ከራስ በላይ ራስ”

በፕሮሜቲዎስ ፕሮዳክሽን ፕሮዲዮስ የተደረገው “ከራስ በላይ ራስ” ቴአትር በአንጋፋው ደራሲ ኃይሉ ፀጋዬ ተፅፎ በአርቲስት ተስፉ ብርሃኑ ተዘጋጅቷል። ይህ ቴአትር ዘወትር ማክሰኞ በሀገር ፍቅር ቴአትር አዳራሽ ውስጥ ነፍስን እንዳሞቀ በሳቅ እያጥለቀለቀ ለሁለት ሰዓታት ገደማ ያቆየናል።

በቀላል የመድረክ ገፅታ፤ የአራት ተዋንያን ብዙ ታሪኮችን የምናይበት ይህ ተውኔት ሰው ለክብሩ፣ ሰው ለምኞቱ፣ ሰው ለሀብቱና ሰው ለፓስፖርቱ የሚከፍለውን መሰዋዕትነት በአስቂኝ አቀራረብ ያሳየናል። በተለይም በመድረክ አተዋወን ብቃቷ ለማናውቃት ሄለን በድሉ (እንከን የለሽ/ ኪኪ) ጥሩ ራስን ማሳያ የሆናት ይመስላል። በርግጥም ፍቃዱ ከበደ፣ አበበ ተምትምና ሔኖክ ብርሃኔ ከእርሷ በተሻለ በመድረክ ስራዎቻቸው የሚታወቁ ቢሆንም ብቸኝነቷ ብቻ ሳይሆን ችሎታዋችም በቴአትር ውስጥ ጎልቶ ታይቷል ማለት ይቻላል።

“ከራስ በላይ ራስ” ቴአትር ገና ከጅምሩ ሳቅ በሚያጭር የቆየ ሙዚቃ የአዳራሹን የጨለማ ክበብ ይገፋል።

“እስቲ እንከተት

መንጋ ወንደላጤ፣

ትዳር ይሻለናል

አንሁን ወጠጤ።”

የዩኒቨርስቲ ምሩቃንና የመንግስት ሰራተኛው ሙሴ (ሔኖክ ብርሃኔ) ከስግብግብ ነጋዴ ወንድሙ ዘንድ በጥገኝነት ይኖራል። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የኑሮን አቀበት ዳዴ በሚልበት በዚህ ወቅት ፍቅረኛው እንከንየለሽ (ሔለን በድሉ) ቅፅል ስሟ ኪኪ ነው። የሁለት ወር ነፍሰጡር መሆኗን ትነግረዋለች። የማስወረጃ ዘጠኝ መቶ ብር ያጣው ሙሴ ይባስ ብሎ የእንከንየለሽ አጎት ከውጪ መጥተዋል በመባሉ የውጪ ዕድሏ እንዳይበላሽባት ብሩን እምጥም ይሁን ስምጥ ገብቶ ፈልጎ እንዲያመጣ ወጥራ ትይዘዋለች።

በዚህ ሁሉ መሀል ግን ሙሴን እንደመዥገር የሚቆጥረው ታላቅ ወንድሙ ፍቃዱ (ፍቃዱ ከበደ) እርግዝናውን ተከትሎ ለራሱ የሚያደሉ ሶስት አማራጮችን ሲያቀርብለት እናያለን። ይኸውም፤ የመጀመሪያው “አባትነትህን ካድ” የሚል ሲሆን፤ ይህን ሃሳቡን ለማስረዳትም “ይህ ተግባር ጥንትም የኖረ፤ ዘንድሮም ያለ ወደፊትም የሚኖር እውነት ነው” ማለቱ ለአዳራሹ ወቸው ጉድ የሚያስብ ሳቅ ፈጥሯል። ይህ ሃሳብ ውድቅ ሲሆን ሁለተኛ መላ ተብሎ የቀረበው “ማሳደግ” ነው፤ ይህ ደግሞ እዳው እጅግ በመብዛቱ የገንዘብ ነገር የማይሆንለት ወንድም ፍቃዱ ይሄንን ሃሳብ ቀይሮ ሶስተኛ አማራጭ ያደረገው፣ “ማስወረድን” ነው። አልሸሹም ዞር አሉ እንዲሉ፤ ማስወረጃ ገንዘብ ያጣው ሙሴ ደስ ቢለውም የብር ነገር የማይሆንለት ወንድሙ “ራስህ ተወጣው” በሚል ጥሎት ሲሄድ፣ “ከራስ በላይ ራስ” የመድረኩን ስላቅ ያጦዘዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ከአጎቷ ጋር ወደውጪ ለመሄድ ልቧ የተነሳሳው እንከን የለሽ ገና የሁለት ወር እርግዝናዋን የስምንት ወር ስታስመስለው ማየት የቴአትሩን ኮሜዲነት ሳታየር በር ላይ ያደርሰዋል። ሁኔታዋን የታዘበው፣ ፍቅረኛዋ ሙሴ፣ “ኧረ ባክሽ እንደሚሆን ያድርግሽ” ማለቱ የሳቅ ፀበል ወደተመልካቹ የምትረጭ ንግግር ናት።

“ከራስ በላይ ራስ” ቴአትር ከኮሜዲ ዘውግነቱ ባሻገር በሳቅ መሰላል ላይ ተንጠልጥሎ የሳታየር ኮሜዲን በር ሲረግጥ የሚያሳዩ በርካታ ትዕይንቶችን መጥቀስ ይቻላል። የፍቃዱ (ፍቃዱ ከበደ) ነጋዴነትና ገንዘብ ወዳድነት ድንበር አልባ ሲሆን፤ አንዲት ሳንቲም ጠረጴዛ ላይ ጥሎ ለጎል የተጠለዘ ኳስን እንደሚቀልብ ግብ ጠባቂ ሲፈጠፈጥ ማየት እጅግ የተጋነነ ነው። ሌላው ደግሞ ከውጪ መጡ የተባሉት አቶ ይገዙ (አበበ ተምትም) እንግሊዛዊ ባህሪን በተላበሰ መልኩ በሰው ቤት ውስጥ ያን ያህል መሀረብ የሚያስነጥፍ መንቀባረር ማንሳታቸው ቴአትሩን ወደሳታየር ኮሜዲነት ደጃፍ የሚያንደረድር ሌላኛው ጎማ ነው ማለት ይቻላል።

“ከራስ በላይ ራስ” በሁሉም ለየራሱ ሲተረማመስ ተመልካች በመደመም ራሱን የሚታዘብበት ቴአትር ነው። ነፃነቱን የሚፈልገው ሙሴ የልጁን መውለድ እንደማይፈልግ ሁሉ፤ ውጪ ሀገር የመሄድ ጉጉቷ በልጇ ምክንያት እንዳይበላሽ የምትሰጋው እንከንየለሽም እንዲሁ ማስወረድን እንደብቸኛ አማራጭ ሙጥኝ ብላ እናያታለን። (እዚህ’ጋ ሌላው የሳታየር ደጅ የሚያደርሰን ነገር ወንዱስ ይሁን ሴቷ ውጪ ሀገር ለመሄድ ስትል ብቻ አንድም ጊዜ እንኳን ከማስወረድ ዞር ያለ ሃሳብ ለመጣላት አለመቻሏ ይደንቃል።)

በአንፃሩ ደግሞ ከውጪ መጡ የተባሉት የእንከንየለሽ አጎት ራሷን ችላ ከኔ ጫቃ ላይ እንድትወርድ እፈልጋለሁ ሲሉ፤ የሙሴ ታላቅ የሆነው ፍቃዱ በበኩሉ እንደመዥገር ተጣብቆብኛል ያለውን ወንድሙን በዚህ ሰበብ ትዳር መስርተው ከቤት እንዲወጡ ሴራ ሲጎነጉኑ ማየት፤ አቤት የሰው ነገር ያሰኛል። ዳሩ ግን በዚህ አጋጣሚ ለጡዘቱ መርገብ ምክንያት የሚሆን አንድ ምስጢር ሾልኮ ይወጣል። ውጪ ሀገር 10 ዓመት ኖረው መጡ ይተባሉት አጎት ኬኒያ ውስጥ የአንድ እንግሊዛዊ አሽከር ሆነው በስውር የኖሩ መሆኑን ስንረዳ፤ በመድረኩ ላይ የማታየው የ“አወኩሽ ናኩሽ” ትርምስ ሌላ ጡዘት ይፈጥራል።

በቴአትሩ ውስጥ የታዩና ግር የሚያሰኙ ጥቂት ክስተቶችን በዚህች አጭር ዳሰሳ ወቅት መጥቀሱ መልካም ሳይሆን አይቀርም። የመጀመሪያው ትወና ላይ ነው። በርግጥ አራቱም በብቃት መተውን ችለዋል። ይህ የማይታበል ሀቅ ነው። ነገር ግን ፍቃዱ ከበደ (ፍቃዱ) የሚጫወተው ገፀ-ባህሪይ ራሱ በሀገር ፍቅር ቴአትር ከሚጫወተው “ትዳር ሲታጠን” ቴአትር ሽማግሌ ገፀ-ባህሪይ ጋር ተቀራራቢ ሆኗል። ሌላው ግን በአድናቆት መጠቀስ ያለበት የሄኖክ ብርሃኔ በተለይ በአንደኛው ትዕይንት ላይ ከኪስ ቦርሳው ፎቶ ጋር ሲያወራ የነበረበት መንገድ ፍፁም መሳጭ ነበር ማለት ይቻላል።

ሲለጥቅ መጠየቅ የምንፈልገው የሰራተኛዋ ገፀ-ባህሪይ አስፈላጊነትና በኋላም ስውር ሆኖ መቆየት ነው። ወደመድረክ አለመምጣቷ አንድ ነገር ሆኖ ሳለ እንዳትታይ የተፈለገበት መንገድ ግን አጥጋቢ አይደለም። ለምሳሌ ፍቃዱ ለእንከንየለሽና ለአጎቷ ሻይ ለማፍላት ጉድጉድ በሚልበት እንቅስቃሴ ውስጥ ሰራተኛዋ የት እንዳለች/እንደሄደች አልተነገረንም። ከሁሉም በላይ ደግሞ ለሳንቲም እንዲያ ሲሰገበገብ የምናየው ፍቃዱ ሰራተኛ ቀጥሮ ደሞዝ ሲከፍል ማሰብ ይከብዳል፤ ዳሩ ግን በስተመጨረሻም ቢሆን ይወዳታል የሚል የረገብ ማሳመኛ አግኝተንበታል። ከቀጠራት በኋላ ነው የወደዳት ወይስ ከወደዳት በኋላ ነው የቀጠራት መጥራት ነበረበት።

ሌላውና በሶስተኛ ደረጃ ሊጠቀስ የሚገባው ከሁለተኛው ወደሶስተኛው ትዕይንት በተደረገው የአፍታ ሽግግር ውስጥ የቀናት ልዩነት (መሽቶ ነግቶ) እያለ ሌሎች ተዋንያን (ገፀ-ባህሪያት) ልብስ ቀይረው ሲመጡ አቶ ይገዙ አይነት የአለባበስ ለውጥ አለማምጣታቸው አንድም ውጪ ቆይቻለሁ ከሚሉት ኩሩ ሰው፤ አንድም የቀኑን ርቀት ለማሳየት ከመድረክ ጀርባ ሙሉ ልብሳቸውን ሊሸፍን የሚችል ካፖርት እንኳን ማዘጋጀት ቢቻል መልካም ነበር የሚል ጥቆማ መስጠት ተገቢ ይሆናል።

    “ከራስ በላይ ራስ” በራሳችን ልክ እንደተሰራ መስታወት መሆን የሚችል፤ በራሳችን ላይ እየቀለደ የሚያስቀን፤ ድብቅ ማንነትን፣ ፍቅርን፣ የንፍገትንና የመስጠትን ደረጃ በምፀት የምናይበት በሳታየር የተሟሸ ኮሜዲ ቴአትር ነው ለማለት የሚያስደፍር ልኬቶችን አይተንበታል። መልካም መዝናኛ!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
11155 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us