“አብዛኛው [የፊልም] ባለሙያ እየሰራ የተማረ ነው”

Wednesday, 20 May 2015 13:03

“አብዛኛው [የፊልም] ባለሙያ እየሰራ የተማረ ነው”

ተዋናይ ተስፋለም ታምራት

 

ብዙዎች ከዓመታት በፊት በቅዳሜ ምሽት “የመስኮት” የቴሌቪዥን ድራማዎቹ ያውቁታል። የሬዲዮ ድራማን በ“ማዕበል ዋናተኞች” “ሀ” ብሎ ጀምሯል። የዛሬው የመዝናኛ እንግዳችን በፊልም የታሰረ ፍቅር፣ ሉሊት፣ መዘዝ፣ ጩኸት፣ ንጉስ ናኡሰናይ፣ ያልረገቡ ዓይኖች እና ፍቅር በአዲስ አበባ የሚጠቀሱለት ናቸው። በቴአትር በተለይ የነገው ፍሬ፣ ጣምራ ስለት፣ በስልጣን ማደጐ እና ቤተሰቡ የቅርብ ተመልካቾች ያስታውሱታል። በአሁኑ ወቅትም “ዳና” በተሰኘው የቴሌቪዥን ድራማ ላይ እየሰራ ይገኛል። ከተዋናይ ተስፋለም ታምራት ጋር የነበረን ቆይታ እነሆ፤

ሰንደቅ፡- ትወናን እንዴት ጀመርከው? የመጀመሪያዎቹ ስራዎችህስ የትኞቹ ናቸው?

ተስፋለም፡- ትወና የተጀመረው በትምህርት ቤት ነው። ሐምሌ 19 ትምህርት ቤት ውስጥ ስማር አማርኛ መምህርት አበበችን በፍፁም አልረሳትም። ይህቺ መምህርት በክፍል ውስጥ ገበሬና ዶክተር፤ መምህርና ነጋዴ እያለች ተማሪዎች ጐራ ለይተው እንዲከራከሩ ታደርጋለች። ታድያ በዚህ መካከል መድረክ መሪ ያስፈልግ ነበርና እኔና ዳንኤል የሚባል ልጅ ነበር። (ነፍሱን ይማረው አሁን በህይወት የለም) እየተቀባበልን ፕሮግራሙን በቀልድ እያዋዛን ተማሪውን የምናዝናናው። ይህ ታድያ አጫጭር ድራማዎችንም የመስራት ዕድል ፈጥሮልናል። ዘጠነኛ ክፍል ደርሼ ወደ ኢትዮጵያ ትቅደም ት/ቤት ስገባ የበለጠ ተጠናክሮ በቴአትር ክበብ ውስጥ ሆነን ለወላጆች ቀን ሁሉ ትርዒት ማቅረብ ቀጠልን። ከዚያ ግን ድንገት ቴአትር መስራት አቋርጬ የማርሻል ስፖርት ሰልጥኜ ጥቁር ቀበቶ አግኝቼ ማሰልጠን ጀመርኩ።

ሰንደቅ፡- በምን ምክንያት? እንደገና ወደ ቴአትሩ ተመለስክ?

ተስፋለም፡- መሀል ጓደኛዬ የነበረው ዳንኤል በትወና ስራው ገፍቶበት ከደራሲ ኃይሉ ፀጋዬ ጋር ተገናኝቶ ነበር። “የማዕበል ዋናተኞች” በተሰኘ የሬዲዮ ድራማ ላይ መካኒኩን ሆኖ መስራት ጀምሮ ነበር። አጋጣሚ ስንገናኝ ለምን ድራማ መስራት ተውክ? አለኝና ኃይሉ ፀጋዬን አገናኘኝ በጣም ደስ አለኝ። ኃይሉን ሳገኘው አቋምህ እኮ የስፖርተኛ በመሆኑ በመድረክም ለፊልምም በጣም ጥሩ ነው፤ በሚል አብሬው እንድሰራ ከሌሎች ልጆች ጋር አሰለጠነኝ። ከኃይሉ ጋር አብሬ መዋል ጀመርኩ። ትኩረቴን ወደትወናው ሳደርግ ኃይሉ ፀጋዬ “በማዕበል ዋናተኞች” ድራማ ውስጥ አንድ ገፀ-ባህሪይ እንድሰራ ዕድሉን ሰጠኝ። ለኔ “የማዕበል ዋናተኞች” የመጀመሪያውና ትልቅ የሬድዮ ድራማ ነበር ማለት ነው።

ሰንደቅ፡- በመጀመሪያ የሬዲዮ ድራማ ሲቀረፅና ለህዝብ ሲተላለፍ ምን ነበር የተሰማህ ስሜት?

ተስፋለም፡- በጣም የሚገርም ስሜት ነበረው። ገና ለቀረፃ ወደጣቢያው ስሄድ ደነገጥኩ። ለምን? እኔ የማከብራቸውና የማደንቃቸው ተዋንያን ሁሉ እዛ ነበሩ። እኔ ከእነሱ ጋር ልሰራ ነው። በመጀመሪያ ያደረኩት ነገር ፍርሃቴን መቆጣጠር ነበር። ተቀርፆ ካለቀ በኋላ ደግሞ እሁድ ድራማው ሲተላለፍ ለወዳጅ ዘመድ ሁሉ የአዳምጡልኝ መልዕክት እንደጉድ ተላከ (ሳቅ)። ከኔ በላይ እናቴ ራሷ እሁድ “በማዕበል ዋናተኞች” ድራማ ላይ ልጄን አድምጡት ማለት ጀምራ ነበር። ታዲያ ሬዲዮ ሲከፈት ልቤ በጣም ይመታ ነበር። ከምንም ነገር በላይ ደግሞ ምን ደስ አለኝ መሰለህ መጨረሻ ላይ ከተዋንያኑ ጋር ተስፋለም ታምራት የሚለው ስም ሲጠራ አቤት የነበረው ደስታ። ከዚያ በኋላ በተለይ ቅዳሜ መዝናኛ ላይ ብዙ ድራማዎችን የመስራት እድል አግኝቻለሁ።

ሰንደቅ፡- በቴሌቪዥን መስኮት ራስህን ያስተዋወከው እንዴት ነበር?

ተስፋለም፡- በጣም የሚገርምህ ነገር በቲቪ ለመጀመሪያ ጊዜ ራሴን ያየሁት በማስታወቂያ ውስጥ ነው። ሀሌታ የተባለ የማስታወቂያ ድርጅት ነበር። ከዚህ ድርጅት ጋር የወይን ማስታወቂያ ይመስለኛል ሰራሁ። ያቺ አጋጣሚ ከብዙ ሰው ጋር አስተዋወቀችኝ። ከዚያ በኋላ በቀጥታ የሄድኩት “ኢቲቪ-2” ወደተባለው የመስኮት ድራማ ነው። እዛ ላይ ብዙ አጫጭር ድራማዎችን ከእነፍቃዱ፣ ዳንኤል፣ አለማየሁ፣ ይገረም ፣ ሳምሶን (ቤቢ) ሌሎችም አሉ፤ በደንብ ነበር የምንሰራው። የቲቪ ድራማን መስራቴ ለፊልም ስራ እንድዘጋጅ ሳያደርገኝ አልቀረም።

ሰንደቅ፡- የመጀመሪያው ፊልም እንዴት ተሰራ?

ተስፋለም፡- “የታሰረ ፍቅር” የመጀመሪያው የፊልም ስራዬ ነው። ያኔ ፊልም ገና የተነሳሳበት ጊዜ ነበር። ያው ክፍያው በጣም ያስቅ ነበር። የፊልምን ብዙ ነገሮች እየሰራሁ ነው የተማርኩት ማለት እችላለሁ።

ሰንደቅ፡- ከኃይሉ ፀጋዬ ጋር እንዳለህ ቀረቤታ ከትወና ባሻገር መፃፉ ላይስ እንዴት ነህ?

ተስፋለም፡- የሚገርመው ይህን ነገር ሌላም ሰው ጠይቆኛል። እኔ መፃፍ መክሊቴ አይደለም። ለኔ የተሰጠኝ ትወና ነው። ለመፃፍ ስነሳ በጣም ይጨንቀኛል። ነገር ግን የተፃፈን ነገር ማረምና ማስተካከል ይሆንልኛል።

ሰንደቅ፡- ፊልም ሰርተህ በተለያዩ ሲኒማ ቤቶች በር ላይ የራስህን ምስል ስታየውና የተመልካቹን ሰልፍ ስትመለከት ምን ይሰማሃል?

ተስፋለም፡- ተመልካቹን ስታየው የተለየ ስሜት ነው የሚሰማህ፤ ትዕቢትም አትለው የሆነ ብቻ የሰው ሁሉ ትኩረት መሳብህን ስታስበው ኩራት ይሰማሃል። ከሁሉም በላይ ግን ሰው ፊልሜን አይቶ የሚሰጠኝን አስተያየት በጉጉት ነው የምጠብቀው።

ሰንደቅ፡- እስቲ ደግሞ ስለቴአትር አውራኝ፤ ተመልካችን የመጋፈጥ አቅምህ እንዴት ይገመገማል?

ተስፋለም፡- የመጀመሪያውን ቴአትር የሰራሁት በተስፋ ኢንተርፕራይዝ ውስጥ ነው። “የነገው ፍሬ” የመጀመሪያው ቴአትር ነው። በመቀጠል ደግሞ የኃይሉ ፀጋዬ ድርሰት ሆኖ ሽመልስ አበራ ፕሮዲዩስ ያደረገው “የስልጣን ማደጎ” ቴአትር ነው። በዚህ አጋጣሚ ሽሜን በጣም ነው የማመሰግነው። ስለተመልካች ንገረኝ ካልከኝ ቴአትር ስትሰራ ሁሉ ነገር እዛው ስለሆነ በጣም ነው የሚያስፈራው። ሁላችንም የመድረክ ፍራቻው አለብን፡ ትዝ ይለኛል “የስልጣን ማደጎ” ቴአትርን ስንሰራ ሽመልስ አበራ ከጭንቀቱ ብዛት ከመድረክ ጀርባ ከመቁነጥነጥ አልፎ ይንከባለል ሁሉ ነበር። እኔ ደግሞ ሽንት ቤት አስሬ እመላለስ ነበር (ሳቅ) ምንም ሽንት ሳይኖር ሽንት ቤት የሚያስኬድ ጭንቀት ታውቃለህ?. . . ከዚያ አሁን- አሁን ደግሞ ጥግ ላይ ፀሎት ማድረግ ነው። የቴአትር ትወና ምትሃት ነው የሚባለው ነገር እውነት ይመስለኛል።

ሰንደቅ፡- አሁንም ይህ ጭንቀት አለ? የማትረሳው የመድረክ ጀርባ ገጠመኝህስ?

ተስፋለም፡- ጭንቀቱ ሁሌም አለ፤ ግን መድረኩን ስትረግጠው ሁሉ ነገር ይጠፋል። አሁን በቅርቡ “ቤተሰቡ” የተሰኘ ቴአትር እንሰራ ነበር፤ ሁሉም ከመድረክ ጀርባ ሲርበተበት ስፖርት ሲሰራ፣ ሲፀልይ ታየዋለህ። ለምሳሌ ከማልረሳቸው የመድረክ ጀርባ ታሪኮች መካከል አንዴ ምን ሆነ መሰለህ? “ቤተሰቡ” ቴአትርን ስንሰራ ተዋንያኑ ችሮታው ከልካይ፣ ፍሬሕይወት አሰፋ፣ ሄኖክ ብርሃኑ፣ ቃልኪዳን አበራ እኔና ሁለት ህፃናት ልጆች ነበርን። ቴአትሩ ከአንደኛው ትዕይንት ወደሌላኛው ትዕይንት በፍጥነት ነበር የሚቀያየረው። በዚህ መካከል ሄኖክ ብርሃኑ ልብስ መቀየር ነበረበት። ልክ ከመድረክ ሲወጣ መብራት ይጠፋል፤ ሲበራ ደግሞ እርሱ ሌላ ልብስ ለብሶ መድረክ ላይ መገኘት ነበረበት። የሚጫወተው ደግሞ ከኔጋ ነበርና ልክ መብራቱ ሲበራ መድረክ ላይ የመደነባበር ነገር አየሁበት። ገፀ-ባህሪውን በትክክል እየተጫወተው እንዳልሆነ ገባኝና ቀስ ብዬ ምን ሆነሃል? ስለው “ቆይ እነግርሃለሁ” አለኝ፤ ስራውን ጨርሰን መድረክ ጀርባ ስንመለስ ምን ቢነግረኝ ጥሩ ነው? ለካስ ልብሱን ሲያወልቅ ሱሪውን ከነፓንቱ አውልቀውበታል። (ሳቅ)

ሰንደቅ፡- በተለየ የምታስታውሰው ስራህ የቱ ነው?

ተስፋለም፡- ብዙዎቹን አልረሳቸውም። የሰራኋቸውም የተለያዩ ገፀ-ባህሪያትን ነው። በተለይ ጥቀስ ካልከኝ ግን “ጩኸት” የሚል አንድ የሲዲ ፊልም ነበር። “አልአዛር” የሚባል ገፀ-ባህሪይ ነው። እኔ ጀምበር አሰፋ፣ አድማሱ ከበደና ይገረም ደጀኔ ሆነን ነው፤ የሰራነው። ምንም እንኳን ፊልሙ የተሰራው 1995 ዓ.ም. አካባቢ ቢሆንም አሁን ድረስ ሰዎች በዛ ገፀ-ባህሪይ ምክንያት ያስታውሱኛል። የምር አፍቃሪ ባህሪይ ስለነበር እኔ ራሱ በጣም ወድጄው የሰራሁት ነው።

ሰንደቅ፡- ጥቂት የማይባሉ ስራዎችን ሰርተሃል። ከአሁን በኋላ ብሰራው ብለህ የምትመኘው ምን አይነት ስራ ነው?

ተስፋለም፡- በአንድ ስራ ውስጥ የተለያየ ባህሪያትን የሚያሳይ ትወና ባገኝ ደስ ይለኛል። ለምሳሌ ከዚህ በፊት “ያረገቡ አይኖች” የሚል ፊልም ትዝ ይለኛል። ገፀባህሪይ የኬላ ጥበቃ ኃላፊ ነበርና ኮንትሮባንድ እንዲያሳልፍ ተጠይቆ እምቢ በማለቱ ሚስቱን ያግቱበታል። በዚህ ምክንያት ተገዶ ኮንትሮባንዱን ያሳልፋል። ከዚያ በኋላ ግን ያሰው በፖሊስ መፈለግ ይጀምራል፤ በዚህ ጊዜ ራሱን በተለያየ መልክ እየቀያየረ አካል ጉዳተኛ ምናምን ይሆናል። ያን ስራ በጣም እወደዋለሁ። ነገር ግን በደንብ አልተሰራም። አሁን ላይ ሳስበው ምናለ አሁን ብንሰራው ብዬ ሁሉ አስባለሁ።

ሰንደቅ፡- እዚህ’ጋ ከዚህ ቀደም ሰርተሃቸው የምትፀፀትባቸው ስራዎች አሉ?

ተስፋለም፡- ይኖራል፤ ምን ጊዜም በምትሰራቸው ስራዎች ላይ ያንተም የዕውቀት ደረጃ ከትናንት ዛሬ እየተሻሻለ ሲመጣ “ወይኔ” እንደዚ አድርጌ በሰራሁት ትላለህ። ነገር ግን በተሰራበት ወቅት ጥሩ አልነበረም ማለት አይደለም።

ሰንደቅ፡- በዳና ድራማ ላይ ስለተሰጠህ ወግ አጥባቂ ዶክተር ገፀ-ባህሪይ እስቲ ትንሽ አጫውተኝ? ከተመልካች ምን አይነት ምላሽ አገኘህ?

ተስፋለም፡- የሚገርም “ዳና” ድራማ ላይ ያለውን ዶክተር መጀመሪያ እኔ የተረዳሁት መካሪና ለቤተሰቡ አሳቢ እንደ ነበር ነው። አባቱን በጣም የሚወድና የሚያከብር ወይም አባቱ የቀረፀው ወግ አጥባቂ ሰው ነው። ይህ ወግ አጥባቂነቱ አባቱን ከገዛ ሰራተኛቸው ጋር ማየት አላስቻለውም። አንዳንዴ ትምህርት ባህሪን ላይቀይር እንደሚችል ከገፀ-ባህሪው ማየት ይቻላል። አጋጥሞህ አያውቅም ትልቅ ነው፤ የተማረ ነው ያልከው ሰው የማይሆን ስራ ሊሰራ ይችላል። ያልተማረ ነገር ግን ጥሩ ስብዕና ያለው ሰው አለ። ዶክተር ዮናስ አባቱን ከሰራተኛዋ ነፃ ሊያወጣ በሄደበት የተሳሳተ መንገድ ምክንያት በስህተት ላይ ስህተት እየደራረበ ሲሄድ እናየዋለን ማለት ነው። ተመልካቹ የተለያዩ ምላሽ አገኛለሁ። አንዳንዱ አባትህ ከወደዷት ምናለ ብትተዋት፤ ወጣት አይደለህ ይልሃል። ሌላው ደግሞ የት አባቷ ዋጋዋን ስጣት ይልሃል።

ሰንደቅ፡- የፊልም ስራው እድገትና ከፍያው እንዴት ነው?

ተስፋለም፡- መጀመሪያ አካባቢ የነበረው ክፍያ በመተዋወቅ የሚከናወን ነው። ባይገርምህ 700 ብር የተከፈለኝ ጊዜ ነበር። ያኔ ገና ወደፊልሙ ስንመጣ ዋናው ነገር መስራትህ ነው። ሌላው ደግሞ የፊልም ፅሁፉን ከወደድኩት ዋጋ ላይ ግድ የለኝም። አሁን ፊልሞቻችን በጥሩ እድገት ላይ ናቸው። እውነቱን ለመናገር አብዛኛው ባለሙያ እየሰራ ነው የተማረው ማለት እችላለሁ። ነገር ግን በትውውቅ የመስራቱ ነገር በዚህ ከቀጠለ ለፊልሙ በጣም አደጋ ይመስለኛል። ተመልካች ለከፈለው ገንዘብና ጊዜ ዋጋ ልንሰጠው ይገባል። አንዳንድ ዋጋ ያልከፈልናቸው ተመልካቾች ከሲኒማ ቤት ሲወጡ ሲበሳጩ ብዙ ጊዜ አይቻለሁ። ይህ ደግሞ የተመሳሳይ ታሪክ፣ የተመሳሳይ ትወናና የተመሳሳይ ግሩፕ ስራ ውጤት እንደሆነ መታዘብ ትችላለህ። ፊልም የቡድን ስራ እየሆነ በመምጣቱ ለምሳሌ እገሌ ፊልም እየሰራ ነው ስትባል “OK እነእገሌ- እገሌ አሉበት ማለት ነው” ብለህ ሁሉ ቀድመህ ማወቅ ትችላለህ። ይሄን ያህል ተመልካቹ ቀድሞ የሚውቅህ ሆኗል። 

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
15411 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us