“ላምባ” ጥበብ ለማህበራዊ ፋይዳ የተገለፀበት

Wednesday, 27 May 2015 17:30

 


የበርካቶችን ስቃይ፣ የቤተሰባዊነትን ጥልቅ ፍቅርና ፍፁም መስዋዕትነት እያሳየ ተመልካችን በእንባ እያራጨ በተስፋ እንዲፅናና የሚያደርግ ፊልም ነው። በአንተነህ ኃይሌ ተፅፎ ዳይሬክት የተደረገው “ላምባ”።

ይህ ፊልም ጥበብ በምን መልኩ ለማህበረሰባዊ ፋይዳ መዋል እንደምትችል በትክክል የማሳየት አቅም እንዳለው ብዙ ባለሙያዎች ይስማሙበታል። “በጨለማ እንደከረመ የብርሃንን አቅም የሚረዳ የለም” የሚለው የፊልሙ መሪ ሃሳብ በጉልህ ታይቷል።

“ላምባ” ፊልም በ123 ስቱዲዮ ተዘጋጅቶ በጆሴፍ ኢቦንጎ ፊልም ፕሮዳክሽን የቀረበ ስራ ነው። በፊልሙ ላይ ግሩም ኤርሚያስ፣ ሊዲያ ሞገስ፣ ኤፍሬም ምስጋናው፣ አልማዝ አልቦ፣ አርሴማ አባይነህ፣ ሜሮን እንግዳ፣ ናሆም ጌታቸው እና ህፃን ኤርሚያስ ኢሳያስን ጨምሮ በርካታ ተዋንያን ተሳትፈውበታል።

ደራሲና ዳይሬክተሩ አንተነህ ኃይሌ ፊልሙን ለመስራት ያነሳሳው እውነተኛ ገጠመኝ ስለመሆኑ የሚናገርለት ይህ ስራው በብዙ ጥበባዊ ቅንብር ተዋቅሮ እያደገና እየተወሳሰበ በሚሄድ ታሪክ ላይ ተንተርሶ ይሰራ እንጂ፤ አላማው ግን በኢትዮጵያ ውስጥ ሊገነባ ለታሰበው የኩላሊት ህሙማን ማዕከል አንዳች ነገር ማበርከትን መነሻ ያደረገ ስለመሆኑ ከሳምንታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ፊልሙ በተመረቀበት ወቅት ተነግሯል።

“ላምባ” ፍቅርና ሰላም ባለው ቤተሰብ ውስጥ የተፈጠረን አስደንጋጭ የኩላሊት ህመም ተንተርሶ የሚከሰተውን ትርምስ ጥልቅ በሆነ ስሜት የሚተርክና ለድርጊትም የሚገፋፋ ስራ ነው። ለጋብቻው ከወራት ያነሰ ዕድሜ የቀረው ግሩም (ግሩም ኤርሚያስ) ድንገት የተከሰተውን የታናሽ እህቱን የኩላሊት ህመም ተከትሎ፤ ከጋብቻውና ከስራው ሁሉ ሲስተጓጎል እናያለን።

በፊልሙ ውስጥ ዋናው ገፀ-ባህሪይ ለቤተሰቡ (በተለይም እህቶቹ) የሚከፍለውን መሰዋዕትነት መጠን ገና ከፊልሙ የመጀመሪያ ትዕይንቶች (ሲኖች) ማየት እንድንችል ደራሲና ዳይሬክተሩ አንዳች ጥቆማን ይሰጠናል። በደስተኛው ቤተሰብ መካከል ወደስራ ለመሄድ የሚጣደፈው ግሩም ጫማውን አጥቶ እናቱን ሲጠይቅ የሚያገኘው ምላሽ፣ “እህቶችህ ጫማ ማስቀመጫ ስር ጭነውበት ይሆናል” ይሉታል። ይህ እንግዲህ እንደጥቆማ ከተወሰደ ገፀ-ባህሪው እህቶቹን ለመሸከም የሚገደድበትና የሚችልበት አቅምና የስብዕና ጥንካሬ እንዳለ እንረዳለን።

ፊልሙ ከታሪክ ነገራው በተጨማሪ የቤተሰቡን መከራ አጉልቶ ከሚያሳይባቸው ቴክኒኮች አንዱ የብርሃን አጠቃቀሙ ነው። የበፀሎት (ሊዲያ ሞገስ) ኩላሊት ከጥቅም ውጪ በመሆኑና በየሶስት ቀኑ ለሚያስፈልጋት የኩላሊት እጥበት (ዲያሌሲስ) ወይም ለዘላቂ ህክምና የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሲባል ቤተሰቡ ንብረቱን በሙሉ ሲሸጥ ከትዕይንት ትዕይንት የቤቱ ብርሃን ፍፁም እየቀነሰ ሲመጣ እንመለከታለን። ከዚህም ባሻገር ለፊልም የምንሰማው ሙዚቃ ልብን ሰቅዞ የሚይዝና ስሜት የሚኮረኩር አድርጎታል ማለት ይቻላል።

“ሰው ሲኖር ለራሱ ብቻ አይደለም” የሚል አቋም ያለው ዋናው ገፀ-ባህሪይ ግሩም፤ ሰው ለሰው የሚከፍለውን የመሰዋዕትነት ጥግ በእንባና በተስፋ ጭላንጭል መካከል ሆነን እንድናይ ያደርገናል። ሰው የዘራውንም ያጭዳል፤ መልካም የሰራ መልካሙን ክፉ የሰራም እንዲያው። በፊልሙም ውስጥ የበፀሎት መታመምና ሆስፒታል መግባትን ሴተኛ አዳሪዋ እና ህፃኑ ልጅ ያቅማቸውን ድጋፍ ለማድረግ ሲጥሩ ማየት የበፀሎትን ከሰው ተግባቢነትና ቁምነገረኛነት ከማሳየት አልፎ የእምባ ግድባችንን የመሸርሸር አቅማቸው ከፍ ያለ ነው።

“ላምባ” በምፀት ከሚያሳየን ማህበረሰባዊ ክፍተቶቻችን እና ሰብዓዊ ድክመታችን መካከል እዚህች’ጋ ሁለቱን መጥቀስ ያዋጣል። አንደኛው የግሩም ፍቅረኛ አባት ለልጃቸው ሰርግ ያሰቡትን ገንዘብ ወይም የልጅቷን መኪና በመሸጥ ለህክምና ወጪ እንዲሆን ሲጠየቁ አሻፈረኝ ማለታቸውን ተከትሎ ከመፅሐፉ ቅዱስ ጎን መገኘታቸው ትልቅ ስላቅ ብቻ ሳይሆን እንደማህበረሰብ የሚያስተዛዝበን ነገር ነው።

ሌላኛውና የማህበራዊ ክፍተታችን ማሳያ የአጎትዬው ቂም ያዥነትና ክፋት ነው። ልቡ ከራቀ ዘመድ ይልቅ፤ ልቡ የቀረበልን እና እጁን የሚዘረጋልን ባዳ በስንት ጠዓሙ እንድንል ያስቻለ ፊልም ነው።

በትወናው ረገድ ግሩም ኤርሚያስ ኤ(+) የሚያሰጠውን ነባር ችሎታ ያሳየን ሲሆን፤ አብረውት የተወኑትም ሰዎች እንዲሁ ምስጋናና አድናቆት የሚቸራቸው ናቸው። በዚህ አጋጣሚ የሜካአፕ ባለሙያዋ ሜሮን ደምሴን ይበል የሚያሰኝ ስራ ሰርተሻል ማለቱ አስፈላጊ ነው። በተዋንያኑ የጉስቁልናና የህመም ገፅታ ላይ ሙሉ በሙሉ ስራዋ በይፋ ይታያልና።  

ፊልሙ በአገራችን የኩላሊት እጥበት የሚጠይቀው ከፍተኛ ገንዘብ ለህሙማኑና ለቤተሰቦቻቸው ምን ያህል ፈታኝ መሆኑን በጉልህ ከማሳየቱም ባሻገር፤ ለተግባራዊነቱ ተነሳስተን የኩላሊት ንቅለ-ተከላ ስራን ማከናወን የሚችል የጤና ማዕከል ለማስገንባት የጎላ ፋይዳ አለው። “ላምባ” ፊልም ከቧልት ባለፈ የፊልም ጥበብ በምን ደረጃ ለማህበረሰባዊ ፋይዳ መዋል እንደሚችል በስልት የተሰራ ምርጥ ፊልም ነው።

    በተረፈ ግን “ላምባ” ፊልም በስተመጨረሻ እንዳስተላልፈው መልዕክት ሁሉ፤ “ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለሃምሳ ሰው ደግሞ ጌጡ” ነውና የሁላችንንም ትኩረት የሚሻ ጉዳይ አንስቷል። በዚህም ፊልሙን አይተው እንደጨረሱ በሞባይል 8582 ላይ “Ok” በማለት እየላኩላችንን የበኩልዎን አስተዋፅኦ እንድናበረክት፤ የልበ ደንዳኖችንም ስሜት ሳይቀር የሚፈታተን ጥበባዊ አቅም እንዳለው መመስከር ይችላል። ሰው ለሰው መድሃኒቱም መርዙም ነው። መልካም የመዝናኛ ሳምንት . . . ከ“ላምባ” ፊልም ጋር!

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
10900 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us