ጠያቂው ገጣሚ እና “እስኪ ተጠየቁ. . .”

Wednesday, 03 June 2015 14:13

      “እስኪ ተጠየቁ. . .” የተሰኘው የግጥም መድብል የገጣሚና መምህር ዮሐንስ አድማሱ የበኩር ስራ ነው። ይህ የግጥም መድብል በ1990 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ከታተመ በኋላ በድጋሚ ዘንድሮ ጥቅምት ወር ላይ ለአንባቢያን እንዲደርስ ሆኗል። ባሳለፍነው እሁድ ግንቦት 23 ቀን 2007 ዓ.ም ደግሞ እናት ማስታወቂያና የጀርመን ባህል ማዕከል ከኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ መፅሐፍት ኤጀንሲ ጋር በመተባበር በሚያዘጋጁት ወርሃዊ የመፅሃፍት ውይይት መድረክ ላይ ለውይይት ቀርቦ ነበር።

በገጣሚ ዮሐንስ አድማሱ “እስኪ ተጠየቁ. . .” የግጥም መድብል ላይ የውይይት ሃሳብ ያቀረበው አርክቴክት ሚካኤል ሽፈራው ነው። ሚካኤል በፀሐፊነት በሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን የግጥም ስራዎች ላይ ትንታኔ ያቀረበበትን ፣ “ሚስጢረኛው ባለቅኔ”፣ “የወፍ ማስፈራሪያ” እና በአርታኢ አለማየሁ ገላጋይ በተዘጋጀው መልክዐ ስብሃት መፅሐፍ ላይ ሃሳብ በማስፈር ይታወቃል። በዕለቱም ስለገጣሚው ህይወት፣ ስለስራዎቹና ስራዎቹ አሁን ድረስ ስላላቸው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ምልከታዎች “እስኪ ተጠየቁ. . .”ን ተንተርሶ ለቤቱ የውይይት መነሻ ሃሳብ አቅርቧል።

ገጣሚና መምህር ዮሐንስ አድማሱ ብቸኝነት የሚያጠቃው፤ መጨቆንን በእጅጉ የሚጠላና በይፋ የሚቃወም፤ ሀገሩን ከልቡ የሚወድና ስለማህበረሰቡም ግድ የሚለው ጠያቂ ገጣሚ እንደነበር ከመድረኩ ተሰምቷል። እንደአወያዩ ሃሳብ ከሆነ ዮሐንስ አድማሱ በአገሩ ጉዳይ ያገባኛል ብሎ ጥያቄዎችን በአደባባይ መጠየቅ የጀመረው የ23 ዓመት ወጣት ሳለ ነው። ይህም የዘመኑ ሁኔታ ሳይሆን እንደማይቀር አወያዩ መላምቱ ይጠቁማል።

በትምህርቱ ጥሩ ውጤት የነበረው ዮሐንስ አድማሱ፤ በ1959 ዓ.ም ያቋረጠውን የዩኒቨርስቲ ትምህርት አጠናቆ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በቋንቋዎች አካዳሚ ውስጥ መምህር ቢሆንም ከአስተዳደሩ ጋር መግባባት ሳይችል በመቅረቱ ወደ ዓለማያ እርሻ ኮሌጅ በመሄድ እንዳገለገለ ጭምር በቁንፅል ታሪኩ ተገልጿል። በ1967 በእድገት በህብረት ዘመቻ ላይ ሳለ ህይወቱ ሲያልፍ የ38 ዓመት ጎልማሳ ነበር። ለሞቱ ምክንያት ተደርጎ የሚጠቀሰው የህክምና ማስረጃ “ኒሞኒያ” ቢሆንም በቤተሰቡና በቅርብ ወዳጆቹ አካባቢ ጥርጣሬ እንዳለ አወያዩ ይጠቁማል። ለዚህም የገጣሚው ጠያቂነትና እውነት ፈላጊነት ጠላት ሳያፈራበት እንዳልቀረም ይገመታል።

በመድረኩ ለውይይት ከቀረበው ቆስቋሽ ሃሳብ መካከል የገጣሚ ብቸኝነት ሀዘንተኝነት ተጠቅሷል። ለዚህም እንደምክንያት የመነሻ ሃሳብ አቅራቢው አርክቴክት ሚካኤል ሽፈራው የሚከተለውን ይጠቅሳል፤ “ምናልባትም ተወልዶ የኖረበት አጭር ዘመንና ያሳለፈበት ኢትዮጵያ በትምህርትና በተስፋ ረገድ የድካምና የተስፋ ማጣት ደመና ተጭኗት የነበረ ሳይሆን አይቀርም” ሲል ግምቱን ያስቀምጣል። ለዚህም በግጥሞቹ ውስጥ የሚገለፁትን የተሰበረ መንፈስ ሸክሞች እንደማስረጃ ይጠቅሳል።

መጠኑ አልመጥኖኝም ለኔ ለመጠኔ

ትክ ብዬ ባየው አተኩሬ ባይኔ

ኧረ ይኽ መሬት ይኽ ዓለምና እኔ።

ሲል የዘመኑን ዳመናማ ገፅታ ስለመከተቡ ሃሳብ አቅራቢው ያትታል። ሌላም ምሳሌ ተመዟል።

መከራ ተረግዞ ተወልዶ ችግር

ስቃይ ተሞሽራ ሲዘፈን ባገር

ሀዘን ስትዘፍን አታሞ ስትመታ

ድህነት ሲሸልል እየመታ እምቢልታ

ረሃብ ሲያቅራራ በጣለው ሰለባ

ቀጠና ደረሰ ድምፁ እያስተጋባ

ቡትቶም አጊጣ ከድሪቶ ጋራ

ዝተትና ማቅም ሆኑ በየተራ

መጡ ከኔ ዘንድ አብረውኝ ሊኖሩ

ተስማምተው ደረሱ እየተባበሩ።

ገጣሚ ዮሐንስ አድማሱ የወቅቱን ሥርዓትና ሁኔታ በእጅጉ የሚፀየፍ አመዛዛኝ አእምሮ የነበረው ሰው መሆኑን የሚናገረው ሃሳብ አቅራቢው ሚካኤል ሽፈራው እማኝ አድርጎም የሚከተለውን ግጥም ይጠቅሳል፡-

የበሸቀጠ ነው እንዲህ ያለኑሮ

የአእምሮ መሸርሞጥ የህሊና ሮሮ

መኖር በዚህ ስፍራ ከንዲህ አይነት ቦታ

ልቦናን በመንሳት ያደርጋል አውታታ

ይሻለኛል ለኔ ከዚህስ መራቅ

ከሰው ተለይቼ ቢቀርልኝ ጠንቅ።

“ስነ- ግጥም በኔ እምነት እንደሙዚቃ መንፈሳዊ ተራክቦ የገጣሚውን ሃሳብ ከዓመታት በኋላም ቢሆን በቃላት አማካኝነት የሚያስተላለፍ ሲሆን ነው።” የሚለው ሃሳብ አቅራቢው፤ ገጣሚው በዚያ ዘመን የፃፈው ስራ አሁን ድረስ እንዲሰማን ማድረጉ የነበረውን ትልቅ አቅም የሚያሳይ ነው የሚሉ ታዳሚያንን አግኝቷል።

የገጣሚውን ሌላኛ ትካዜ በሌላ የግጥም ስራ ውስጥ እናያለን፤ በዘመኑ በቁም ሞት ታሰረዋል በሚላቸው ወጣቶች ታዝቦና አዝኖ የሚከተለውን ግጥም ጽፏል።

ሬሳው ለሬሳ እንባውን አንብቶ

ያለቅሳል አምርሮ ስሜቱ ተነክቶ

በሀዘን ኮስምኖ

መሬቲቱም ነቃች ተሰምቷት ሀዘኑ

ከሷ አያልፍምና ይህ ሁሉ መጠኑ

ለዚህ ነው ሀዘኔ

ከንቱ መባከኔ።

“እስኪ ተጠየቁ. . .” በቋንቋ ረገድ ገላጭ ከመሆኑ የተነሳ ገጣሚው ስዕል እያየ የሚፅፍ ይመስላል የሚል ሀሳብ ተነስቷል። ገጣሚው የነበረበት ዘመን ድቅድቅ ጨለማ ወቅትን በጉልህ ማሳየት ችሏል።

ገጣሚው ከሀገሩ ጋር ያለውን የመንፈስ ቁርጠኝነት መመልከት ተችሏል። ከፋሽስት ኢጣሊያ ስንብት ማግስት ጀምሮ እስከ ደርግ ድረስ ያለችውን ኢትዮጵያ የታዘበበት መንገድ፣ “ሀዘንተኛ እናቴ” በሚለው ግጥሙ ይተርክልናል።

ሀዘንተኛ እናቴ ሀዘንሽ ቢበዛ

መልክሽ ጠቆረብኝ ሆነብኝ ቀዛዛ

ምንም ቤትሽ በፈርስ ኑሮሽ በደረባ

እግርሽ ቢሰነከል ብትሆኚ ሰለባ

ዳግመኛ እንዳትመጪ ይታየኛል እኔ

ለልቤ ደስታ ሐሴት ለዘመኔ።

ገጣሚው ከእናቱና አባቱ ሲነገረው ያደገው የዮፍታሄ ንጉሴ የሥነ-ግጥም ስራዎች እስከ እድሜው ማብቂያ ድረስ በውስጡ እንዳኖራቸው ራሱ በፃፋቸው ስራዎቹ ውስጥም አሳይቶናል። ለዚህ ታላቅ የሥነ-ፅሁፍ ሰው መታሰቢያ ይሆን ዘንድም ይመስላል፤ “ተወርዋሪ ኮከብ” በተኘው ግጥሙ ያትታል። በዚህ ግጥም ውስጥ ከዮፍትሄ ንጉሴ በተጨማሪ ሌሎችም ለሀገር ክብር መስዋዕትነት የከፈሉ ሰዎች ተስለዋል ሲል ሃሳብ አቅራቢው ያስረዳል።

ተወርዋሪ ኮከብ የደረሰው ቦታ የጨለመ ምድር

አይታይም ነበር

ጨለማ አካል ገዝቶ

ይዳሰስ ነበር በየቦታው ገብቶ።

ሌላውና ዋነኛው የመፅሐፍ ራስ የሆነው “እስኪ ተጠየቁ . . .” የተሰኘው ግጥም ዮሐንስ አድማሱ የጠየቃቸው በርካታ ጥያቄዎች ናቸው።

ቸገረኝ ጨነቀኝ ብጠይቅ አጥብቄ

ምላሽ አጥቼለት ለልቤ ጥያቄ

ያንጀት ለቅሶ ሆኖ የዘመኑ ሳቄ

ዐወቅሁ ተማርሁ ስል ሁሉንም ጠንቅቄ

ከደመና በላይ ሐሳቤ ቢርቅ

ከተራውም ደሃ እውቀቴ ቢልቅ

በውቀቴ ሳልረዳው የሚጠብቀኝን በተስፋ ህሊና

የኔ እውቀት የምለው ሆኖ ቀረ መና።

በዚህ ግጥም ውስጥ ስለምሁራኑና ስለካህናቱን፣ ስለባለስልጣናቱን ሁሉ ሙታኑን በጥያቄ ይወጥራቸዋል።

“እስኪ ተጠየቁ. . .” የገጣሚ ዮሐንስ አድማሱ ታሪክ፣ ትዝብትና ጥያቄ በተካተተበት ስራ ነው።፡ የአንዳንድ ግጥሞቹ ርዝመት አንባቢን ሊያደክም ቢችልም “እየታረፈ ቢነበብ፤ በተመስጦ ቢጤን ብዙ ቁም ነገር እንዳለው” ሃሳብ አቅራቢው ይመክራል።

በመመዘክር አዳራሽ ውይይት የተደረገበት የገጣሚና መምህሩ ዮሐንስ አድማሱ “እስኪ ተጠየቁ. . .” ስራ ከ60 በላይ ግጥሞችን አካቶ በ162 ገፆች፤ በ40 ብር ዋጋ ለአንባቢያን ቀርቧል። 

ይምረጡ
(10 ሰዎች መርጠዋል)
9853 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us