“ፊልም መሥራት የጀመርኩት በአጋጣሚ ነው”

Wednesday, 10 June 2015 11:45

 


በይበልጥ የታወቀችበት ፊልም “ፍቅር ሲመነዘር” ይሰኛል። ከዚህ ፊልም በፊትና በኋላም ቢሆን ግን “ወርቅ በወርቅ” እና በቅርቡ የሰራችውን “ያነገስkኝ” የተሰኙ ፊልሞች ትታወቃለች። በዚህ ሳምንት የተመረቀውን “ሼፉ-2” ፊልምን ጨምሮ በ“ዳና” ድራማ ላይም እናያታለን። ከዛሬዋ የመዝናኛ እንግዳችን ከየትናየት ታምራት (ሚሚ) ጋር ያደረግነውን አዝናኝ ቆይታ እነሆ፡-

ሰንደቅ፡- የፊልም ስራን እንዴት ጀመርሽው?

የትናየት፡- ፊልም መስራት የጀመርኩት በድንገት ነው። አጋጣሚውን ያመቻቸችልኝ ደግሞ ጓደኛዬ ሮማን አየለ ትባላለች። (የሰራዊት ፍቅሬ ባለቤት ናት) ሊሰራ የታሰበው ፊልም የወንድ ገፀ-ባህሪን ወደሴት አስቀይራ እንድጫወት የገፋፋችኝ እርሷ ናት፤ ፊልሙም “ወርቅ በወርቅ” ይሰኛል፤ የመጀመሪያ ስራዬ ነው።

ሰንደቅ፡- በጣት የሚቆጠሩ ፊልሞችን ብትሰሪም ተሳክተውልሻል፤ ምንድነው የተለየ ምክንያቱ?

የትናየት፡- አላውቅም፤ ግን ሰዎች ፊልም ላይ እንድሰራ ሲመድቡኝ የሚመርጡልኝን ገጸ ባህሪይ በተመለከተ እኔ ላይ ያዩት ነገር ሳይኖር አይቀርም፡ ገፀ-ባህሪይ ሲሰጠኝ በደንብ ለማወቅና እስከመሆን ደርሼ መስራት እሞክራለሁ። ከዚያ ውጪ ስራዎቼን ሁሉ እየተዝናናውባቸው ስለምሰራቸው ነው መሰለኝ ይቀሉኛል።

ሰንደቅ፡- የፊልም ሙያ ከልጅነትሽ ያሰብሽው ስራ አልነበረም፤ አሁን ግን እየታወቅሽበት ነው። የልጅነት ፍላጎትሽ ቀረ ማለት ይቻላል?

የትናየት፡- በልጅነት በውስጤ የማስበውን ሙያ መፈለጌ መቼም አይቆምም። በርግጥ ልጅ እያለሁ አድጌ መሆን የምመኘው “ኬሚስት” ነበር፤ ያሰብኩት አሁን ባይሳካም “ኢንተሪየር ዲዛይን” ላይ ስለምሰራ በቀለሞች ዲዛይን በተወሰነ መልኩ ኬሚስትሪን እየሰራሁት ነው ብዬ አምናለሁ። ነገር ግን ድሮ መሆን የምፈልገውና አሁን የሆንኩት አንድ አይደለም። ግን ደግሞ መሆን የምፈልገውን ለመሆን የሚገድበኝ እድሜ ላይ አይደለሁም። ትምህርት ጊዜ ስለማይገድብ መማሬ አይቀርም። አሁን ለምሳሌ እናቴ ከኔ ጋር ትማራለች። አብረንም ተመርቀን እናውቃን። ስለዚህ ትምህርት ስለማላቆም አንድ ቀን ኬሚስት እሆናለሁ የሚል ተስፋ አለኝ። አሁን ያለሁበትን ሙያ በተመለከተ ግን በአጋጣሚ የገባሁበት ቢሆንም በጣም ደስተኛ ነኝ።

ሰንደቅ፡- በቅርቡ የወጣውን “ያነገስከኝ” ፊልም ከመተወንም በላይ ፕሮዲዩስ አድርገሻል። ፕሮዲዩሰርነት ምን የተለየ ነገር አለው?

የትናየት፡- ፕሮዲየሰር መሆን ብዙ ፈተናዎች አሉት። ምክንያቱም የምትሸከመው ኃላፊነት ብዙ ነው። ሙሉ የፊልሙ ባለሙያ ባንተ ኃላፊነት ስር መሆናቸው፤ ፊልሙ ለህዝብ ይጠቅማል ወይ የሚለው ጭምር ያንተ ኃላፊነት ነው። ዋናው ነገር ደግሞ በፋይናንስ መደገፉ ያንተ ኃላፊነት ነው። በአጠቃላይ ፕሮዲዩሰር መሆን ብዙ እንቅልፍ የማያስተኙ ነገሮች አሉት። በተለይ ደግሞ እንዲህ ታሪክ ቀመስ ፊልም መስራት ጥንቃቄ ይጠይቃል ባይ ነኝ

ሰንደቅ፡- ለ“ያነገስከኝ” ፊልም ያወጣሽውን ያህል አግኝተሻል? ከተመልካችስ የጠበቀውን ምላሽ መጥቷል?

የትናየት፡- እውነቱን ለመናገር ያወጣሁትን ያህል አገኛለሁ ብዬ አላምንም። ምናልባት ውጪ ሀገር “ቱር” ሳደርግ ሊሳካ ይችላል። ነገር ግን በገንዘብ ላገኘው የማልችለውን ብዙ ነገሮች አግኝቻለሁ። ለምሳሌ ከሳምንት በፊት ባህርዳር ሄጄ፤ ፊልሙን አሳይቼ ነበር። የተመልካቹ ምላሽ በጣም አሪፍ ነበር። እኔ ተውኜበት ፕሮዲዩስም አድርጌው የተሰራ ፊልም በዚህ ደረጃ ሲወደድ ሳይ በጣም ነበር ደስ ያለኝ። ሰዎች ስልኬ ላይ ይደውላሉ፤ በፌስ ቡክ የሚሰማቸውን ይገልፁልኛል። ብዙ አስተያየትና ፍቅር ይሰጡኛልና ይሄንን በገንዘብ ላገኘው ስለማልችል ደስተኛ ነኝ።

ሰንደቅ፡- ይህንን ታሪክ ቀመስ ፊልም ለመስራት ምን አነሳሳሽ?

የትናየት፡- ቢሮዬ የተለያዩ የፊልም ጽሁፎች ይመጡልኛል። አብዛኞቹ የከተማ ውስጥ ታሪኮች የሴትና የወንድ ፍቅር ላይ ብቻ ያተኮሩ ናቸው። እነዚህን ጽሁፎች መጥላቴ አይደለም። ነገር ግን እንደፊልም ፕሮዲዩሰር ለተመልካች ምንድነው ማድረስ ያለብኝ ብዬ አስብ ነበር። ፖለቲከኞች ሰለሀገር አስተዳደር እንደሚያስቡ ሁሉ፤ ሃኪሞች ስለበሽተኞችን እንደሚያስቡ ሁሉ፤ የጥበብ ሰውም ስትሆን ለማህበረሰቡ ስለሚያቀርበው ነገር መጨነቅ አለበት ብዬ አምናለሁ። በፊልሙ ውስጥ የሚጠቀሰው ታሪክ ሰው ቢያውቀው ጥሩ ነው ብዬ አሰብኩ። እና በፊት ወርቅ ጭነን ባህር አቋርጠን የሰው ቤት መቅደስ የምናሰራ ሰዎች ነበርን እንዴ? እንደዚህች አይነት ንግስት ነበርን እንዴ? እንዲህ አይነት ተርፎን እርዳታ የምንሰጥ አገር ነበርን እንዴ? ከ3ሺህ ዓመታት በፊት እንደዚህ አይነት ህዝቦች ከነበርን አሁን ለምን እንዲህ ሆንን? ብሎ ለመጠየቅ የተዘነጉ ታሪኮችን በፊልም ውስጥ ማስታወሱ ተገቢ ስለመሰለኝ ነው፤ ከማነባቸው የፊልም ፅሁፎች ይህንን የመረጥኩት።

ሰንደቅ፡- በፊልሙ ውስጥ በሚገባ ስለንግስተ ሳባ ታሪክ ተናግረናል ብለሽ ታስብያለሽ?

የትናየት፡- እውነቱን ለመናገር ታሪኩን በሚባለው ደረጃ አልሰራውም። ዓላማችን የነበረው ታሪክ ተጠቅሶ የረሳነውን ነገር ማስታወስ ነው። ለኔም ታሪኩ አዲስ ነገር ነግሮኛል ለብዙ ወጣቶችም እንደዛ ይሆናል ብዬ አስባለሁ። አንድ ነገር ግን እውነት ነው በጥቂቱም ቢሆን ስለታሪካችን ኮርኩረናል።

ሰንደቅ፡- ስለአገርሽ ታሪክ ምን ያህል ታውቂያለሽ?

የትናየት፡- ብዙ አላውቅም፤ ነገር ግን ብዙ ለማወቅ ዝግጁ ነኝ። እውነቱን ለመናገር ይህንን ፊልም ካነበብኩ በኋላ ብዙ የተደበቁና ፊልም ሊሆኑ የሚችሉ ኢትዮጵያዊ ታሪኮች እንዳሉን ተረድቻለሁ። አንድ የማረጋግጥልህ ነገር ቢኖር ከዚህ በኋላ በኔ (ስፓትስ) ፊልም ፕሮዳክሽን በኩል ተሰርተው የሚወጡ ፊልሞች በሙሉ የኢትዮጵያን ታሪክ የተመለከቱ ብቻ ይሆናሉ።

ሰንደቅ፡- በ“ፍቅር ሲነመዘር?” ፊልም ላይ የሰራሻት ገፀ- ባህሪይ ትንሽ ፈታኝ ነበረች። ለፊልሙ የሚፈለገው ድርጊትም የሚፈትን ነበር፤ እንዴት እሺ ብለሽ ሰራሻት?

የትናየት፡- ይሄ የሚገርም አጋጣሚ አለው። አንተም እንዳየኸኝ እኔ በስራ በጣም ተወጥሬ ነው የምውለው። የፊልም ፅሁፎች ሲመጡ እናቴ ናት የምታነባቸው። እናቴ አንብባ ታሪኩን በአጭሩ ትነግረኛለች። እናቴ ጥሩ ታሪክ ነጋሪ ነች። የ“ፍቅር ሲመነዘር”ን ታሪክ ስትነግረኝ ልብ የሚናነካ ነበር። እናቴ ምን አለችኝ መሰለህ፣ “ታሪኩን ሳነበው መጨረሻ አካባቢ ትንሽ ከባህላችን ወጣ ያለ ነገር አለው። ነገር ግን እንደናት አትስሪው ማለት ቢኖርብኝም ስሪው ብዬ ማበረታታቱን እፈልጋለሁ አለችኝ። መሳሳም ካለው ለምን እሰራለሁ? ስላት የምትሳሳሚው ዝም ብሎ ለመሳሳም አይደለም፤ ታሪኩ ስለሚያስገድድና ለማስተማር ነው። የምታስተምሪው ሁላችንንም የሚነካ ነገር ነው። በርግጥ አንቺ በፊልም ውስጥ ስትሳሳሚ በሚያይ ሰው ምላሽ የመጀመሪያዋ ቅር የሚለው ሰው፤ እንደእናት እኔን ነው። ግን ደግሞ የምታስተምሪው ነገር ስለሚበዛ፤ ሰዎች ፊልሙን አይተው ሲወጡ ተምረውበት የሚወጡትን ተመልካቾች እንጂ መሳሳምሽ ላይ ብቻ የሚያተኩሩት ሰዎች አያሳስቡኝም በሚል ነው የገፋፋችኝ፤ እናም ሰርቼዋለሁ።

ሰንደቅ፡- በፊልሙ ውስጥ መሳሳም እንዳለ ስትረጂ ቀጥሎ ከማን ጋር እንደምትሳሳሚ አሳስቦሽ ነበር?

የትናየት፡- አዎ! የሚገርምህ ነገር ሰለሞን ቦጋለን ከዚያ በፊት ሲሰራ አይቼው አላውቅም። ብዙ ጊዜ ፊልም አላይም ነበር። ጊዜ ስለሌለኝ ፊልምን የሚከታተል አይነት ሰው አይደለሁም። ሰለሞን ማን እንደሆነ እንኳን አላውቀውም።፡ ግን ፕሮዲዩሰሩን (ኩሩቤል አስፋውን) ምን አልኩት? ምንም እንኳን የበዛ መሳሳምም ባይሆን በተቻለ መጠን ራሱን የጠበቀ ሰው “ካስት” ቢደረግ ደስ ይለኛል አልኩት። ተስማምተን ነው የሰራሁት።

ሰንደቅ፡- ከቀረፃ በፊት በልምምድ ላይ እንዴት ነበራችሁ?

የትናየት፡- (ሳቅ) የሚገርም በጣም ተግባብተን ነው የሰራነው፤ ሰለሞን እንደውም ኧረ ቶሎ “አክሽን” በሉንና እንሳሳምበት ሁሉ እያለ ይቀልድ ነበር። (ሳቅ)

ሰንደቅ፡- የተሰጠሸን ገፀ-ባህሪይ ተላብሰሽ ለመጫወት ያለሽ ቁርጠኝነት ምን ያህል ይሄዳል?

የትናየት፡- መሄድ ያለብኝ ድረስ እሄዳለሁ። ስራው አሳማኝ ይሁን እንጂ መክፈል ያለብኝን መሰዋትነት ለመክፈል ዝግጁ ነኝ። ቅድም እንዳልኩህ ሰለሞንን ከዚያ በፊት አላውቀውም፤ አንዳንድ ሰዎች ግን ጓደኛሞች ሁሉ መስለናቸዋል። ነገር ግን ለፊልሙ የሆነው ነገር ነው። ለተሰጠችኝ ገፀ-ባህሪይ ስል ያን ያህል እሆናለሁ። የተሰጠኝን “ካራክተር” አበላል፣ አነጋገር፣ አካሄድና አስተሳሰብ ሁሉ ለማወቅ እጥራለሁ። እግዚአብሔር ይስጣቸው አብረውኝ የሚሰሩትም ሰዎች ሙሉ ነፃነት ስለሚሰጡኝ እኔ በተረዳሁት መጠን አሪፍ አድርጌ ለመስራት ችያለሁ።

ሰንደቅ፡- ብዙዎች የምትሰሪያቸውን የፊልም ባህሪያት እያዩ ደፋር ነች ይሉሻል። እውን ደፋር ነሽ?

የትናየት፡- ደፋርነት እንደሁኔታው ይለያያል። እኔ የምፈልገውን ነገር ለማግኘት ወደኋላ የምል ሰው አይደለሁም። አስተዳደጌም በነጻነት እንጂ በክልከላ የተሞላ አይደለም። በመነጋገር ከሚያምን ቤተሰብ ውስጥ ነው የወጣሁት። ሰዎችን አከብራሁ እንጂ ስሜቴን ለመግለፅ አልፈራም።

ሰንደቅ፡- ምን ያስፈራሻል?

የትናየት፡- ተሳስቼ ሰውን ማስከፋት፣ ምክንያቱም የሚያለማህም የሚያጠፋህም ከእግዚአብሔር ቀጥሎ ሰው ነው። ስለዚህ ሰው አያውቅብኝም ብዬ ጥቅሜን ብቻ ማስቀደም በጣም ነው የሚያስፈራኝ። ሰውን ማስቀየም በህይወቴ የምፈራውና የምጠላው ነገር ነው።

ሰንደቅ፡- በስራዎችሽ ላይ የተመልካቹ ምላሽ ምን ይመስላል?

የትናየት፡- በጣም ዕድለኛ ነኝ። በትንሽ ስራዎች ያውም ሙሉ ጊዜዬን ሰጥቼ ሳልሰራ ይሄን ያህል የተመልካችን ቀልብ መግዛት ዕድለኝነት ነው። እስካሁን ወቀሳ ደርሶኝ አያውቅም።

ሰንደቅ፡- ወደሆሊውድ የመድረስ ሃሳቡ አለ?

የትናየት፡- አይቀርም። ነገር ግን እኔን ብቻ ሳይሆን የእኛን ሀገር ፊልም በአለም ደረጃ ማሳየት ብንችል ደስ ይለኛል። ለዚህም እየሰራን ነው።

ሰንደቅ፡- ከፊልም ስራ ውጪ ምን ትሰሪያለሽ?

የትናየት፡- በ “ኢንተሪየር ዲዛይን” ሙያ ተሰማርቼ እገኛለሁ። ከተለያዩ ሰዎች ጋር በጋራ የምሰራቸው ስራዎችም አሉኝ። አሁን ለጊዜው ስራ አቁሟል እንጂ ማተሚያ ቤትም አለኝ።

ሰንደቅ፡- ምን ያህል የፊልም ፅሁፎች ቢሮሽ አሉ?

የትናየት፡- ባይገርምህ ይሄን ሰሞን ብቻ እንኳን ወደ 10 የሚደርሱ ፅሁፎች መጥተውልኛል። እናቴ እያነበበቻቸው ነው። ታሪኮቹን እየሰማሁ ቢሆንም እስካሁን ያን ያህል የማረከኝ የለም፤ አንድ ጥሩ ታሪክ ያለው ፅሁፍ ሰምቻለሁ እርሱን ለማንበብ ቸኩያለሁ።

ሰንደቅ፡- በምን ትዝናኛለሽ?

የትናየት፡- ብዙ የመዝናኛ ጊዜ የለኝም። ብዙ ሰዎች የሚያዝናኟቸው ነገሮች እኔን አያዝናኑኝም። እኔን የሚያዝናናኝ ከከተማ ብቻዬን መውጣት፤ ከልጄ ጋር ቤተክርስቲያን መሄድ ደስ ይለኛል። ከጓደኞቼ ጋር መጨዋወት ደስ ይለኛል። ሌላው ግን ሰለምሰራቸው ስራዎች ቢሮዬ ውስጥ ቁጭብዬ በፅሞና ማሰብ ያዝናናኛል።

ሰንደቅ፡- ከዚህ በኋላ ብሰራው ብለሽ የምትመኚው ገፀ-ባህሪይ ምን ዓይነት ነው?

የትናየት፡- ብሰራና ወጣ አድርጌ ራሴን መፈተን የምፈልገው የባላገር ሴትን ህይወት የሚወክል ቢሆን እመርጣለሁ፤ በባዶ እግሯ፤ እርጉዝ ሆና፣ እንጨት ሰብራ፣ ውሃ ቀድታ ምናምን የሚያሳይ የገጠር ሴት ታሪክ ብሰራ በጣም ደስ ይለኛል።

ሰንደቅ፡- በስተመጨረሻ ለአድናቂዎችሽ ምን ማለት ትፈልጊያለሽ?

    የትናየት፡- ፊልሞቼን አይተው ወደው አስተያየታቸውንና አድናቆታቸውን ለቸሩኝ ሁሉ አክብሮት አለኝ። እኔ በጣም ነፃና ግልጽ ሰው ነኝ። ማንም ሰው የመሰለውን አስተያየት ቢሰጠኝ በመቀበል ዝግጁ ነኝ። ምክንያቱም እነሱ ስላከበሩኝና ስላዩኝ ነው እዚህ ያለሁት። እኔ የእነርሱ አካል እንደሆንኩ እንዲያውቁልኝ እፈልጋለሁ። እወዳችኋለሁ፤ ለሁሉም አመሰግናለሁ በልልኝ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
15585 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us