አዲስ ኢንተርናሽናል “የምርጥ ዘጋቢ ፊልሞች” ፌስቲቫል

Wednesday, 17 June 2015 16:43

     

ከመላው ዓለም የተመረጡ 60 ዘጋቢ ፊልሞችን ለዕይታ የሚያበቃው የዘንድሮው አዲስ ኢንተርናሽናል የፊልም ፌስቲቫል ለዘጠነኛ ጊዜ እየተካሄደ ነው። ምንም እንኳን በአዲስ አበባ ከሰኔ 5 እስከ ሰኔ 9 ቀን 2007 ዓ.ም በአሊያንስ ኢትዮ-ፍራሲስ፣ በብሔራዊ ሙዚየም፣ በብሪትሽ ካውንስልና በሀገር ፍቅር ትንሿ አዳራሽ የተመረጡት ፊልሞች ታይተው ያበቁ ቢሆንም፤ ከሰኔ 19 እስከ 20 ቀን 2007 ዓ.ም ደግሞ በአዳማ፣ በሀዋሳ፣ በመቀሌ፣ በድሬዳዋና በባህርዳር ከተሞች በነፃ ለዕይታ እንደሚቀርቡ አዘጋጆቹ ባሳለፍነው ሳምንት በራዲሰን ብሉ ሆቴል ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ይህ የፊልም ፌስቲቫል ለዘጠነኛ ጊዜ የተካሄደ ቢሆንም ምን ትርፍ ተገኘ ለሚለው ጥያቄ የኢኒሼቲቭ አፍሪካ ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ክቡር ገና፤ “አገሪቷን ከማስተዋወቅና የዘጋቢ ፊልሞችንም ጥቅም አጉልቶ ከማሳየት ባሻገር፤ የተመረጡ ሀሳቦችና አስተሳሰቦች በፊልሞቹ አማካኝነት ለተመልካቹ ማድረስ ችለናል” ይላሉ። ከዚህም ጋር በተያያዘ የፊልም ፌስቲቫሉ የተመረጡ ዘጋቢ ፊልሞችን ለዕይታ ከማቅረቡ ባለፈ ትምህርታዊ ውይይቶችና ገለፃዎች መደረጋቸው በመስኩ ፍላጎት ላላቸው ባለሙያዎች የተሻለ ዕውቀትን ለማሸጋገር እንደሚረዳም ጠቁመዋል።

በዚህ ዓመት ለዕይታ የሚበቁት 60 ዘጋቢ ፊልሞች እንደከዚህ ቀደሞቹ ሁሉ በጥናት ላይ የተመሰረቱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ያንጸባረቁ ናቸው። ከዚህ ቀደሞቹን ዘጋቢ ፊልሞች ጨምሮ በርዕሰ ጉዳይ ደረጃ የሚነሱት ሀሳቦች የአካባቢ፣ የስደት፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ የአረጋዊነት ዘመን ፈተናዎችና የአእምሮ ህሙማን የሚደርስባቸው ጫናዎች አካቶ ዘንድሮ በጉልህ የሚታዩ ሃሳቦች ቀርበዋል።

የኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ተሳትፎ ደካማ መሆኑ አሳሳቢ ጉዳይ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ክቡር ገና፤ ምናልባትም በአዲስ ፊልም ፌስቲቫል አማካኝነት የሚገኙ የትምህርት ዕድሎችን ጨምሮ በዚህ ዓመትም አስራ ሁለት የሚደርሱ ባለሙያዎች መጋበዛቸውን አስታውሰው እነዚህም ባለሙያዎች ለኢትዮጵያውያን ትምህርታዊ ውይይትን በዘጋቢ ፊልሞቹ አሰራርና ይዘት ላይ አተኩረው ሃሳብ ይለዋወጣሉ በሚል የተያዘላቸው ፕሮግራም ስለመኖሩ አስረድተዋል። ያም ሆኖ ዘንድሮ ከሚቀርቡት 60 ዘጋቢ ፊልሞች መካከል በዳይሬክተር ትርሲት አግዝ የተሰራው “የበሬው ውለታ” እና ከዳይሬክተር ኃይሉ ከበደ የተሰራው “ትስስር” የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም መቅረቡን ለማወቅ ተችሏል። ያም ሆኖ ወደፌስቲቫሉ የሚመጡ ዘጋቢ ፊልሞች ካሉ ኢትዮጵያውያኑን ለማበረታታት ሲባል የበዛ የጥራት ደረጃ ጥያቄን እንደሚያቀርቡ አዘጋጆቹ ጠቁመዋል።

ከቀረቡት ፊልሞች መካከል ስለአንዳንዶቹ ፍንጭ ለመስጠት ያህን እንደሚከተለው እንጠቃቅሳለን። ከኖርዌይ የተገኘው “Drone” የተሰኘው ዘጋቢ ፊልም በቴክኖሎጂ የሚደረግን የርቀት ጦርነትና ይህን ተግባር ይፈጽም የነበረ አንድ ወጣት የደረሰበትን የሞራል ጥያቄና የስነ- ልቦና ጫና ለማሳየት የተሰራ ነው።

ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የሚስተዋልን ድንቅ ባህሎች በማሳየት የአፍሪካን “ብርሃናማ” ገጽታ አንጸባርቋል የተባለለት ዘጋቢ ፊልም ከወደጀርመን ተሰርቷል። ይህ “35 Cows and a Kalashnikov” የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም በኢትዮጵያ የደቡብ ህዝቦች በሚገኙት የ“ሱርማ” ማህበረሰብ ለጋብቻ የሚሄዱበትን መንገድ ያስቃኛል። በዚህ ዘጋቢ ፊልም ውስጥ በበርካቶች ዘንድ በችግርና በጦርነት ሳቢያ “ጭለማዋ አህጉር” የተሰኘችውን አፍሪካ በጥበብ ብርሃን አሳይቷል።

ሌላኛው ስለኢትዮጵያ ባህላዊ ውዝዋዜ የተሰራው ዘጋቢ ፊልም፤ በፌስቲቫሉ መክፈቻ ወቅት የታየው “Shoulder dancing” የተሰራውም በዳይሬክተር ሩት ሼል ነው። በበርካታ ተመልካቾችም ዘንድ ታይቶ አድናቆትን አግኝቷል። በተያያዘም ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከማስተዋወቅ አንፃር አስኒ “Asni` የተሰኘውና በራቼል ሳሜኤል የተሰራው ዘጋቢ ፊልም በብዙዎች ዘንድ ትኩረትን የሳበ ፊልም በአስናቀች ወርቁ ታሪክ ላይ ተመስርቶ የሚተርክ ነው።

በብዙዎች ዘንድ በእስር ላይ የሚገኙ የአእምሮ ህሙማንን አያያዝ አስመልክቶ ከወደቤልጄም የተሰራው “9999” የተሰኘው ፊልም ሲሆን፤ በዘጋቢ ፊልሙም የአራት ሰዎች አሳዛኝ ታሪክ በሚደንቅ አቀራረብ ለዕይታ በቅቶበታል።

የጦርነት ዘገባን ፈታኝነት ከማሳየት አንጻር ሊቃኝ የሚችለው “E-Team” የተሰኘው ዘጋቢ ፊልም፤ ሮዝ ካፋማን እና ኬቲ ቼቪኒ በሶሪያና በሊቢያ የእስር በእስር ጦርነቶች መካከል ስላለፉባቸው መንገዶችና ስላገኟቸው ድብቅ መረጃዎች የሚተርክ ፊልም ነው።

በ2015 በተካሄደው የአካዳሚ አዋርድ፤ በምርጥ ፊቸር ዘጋቢ ፊልም ዘርፍ ተሸላሚ የሆነው “Citizen Four” ዘጋቢ ፊልም አንዱ ነው። ይህ ፊልም አሜሪካ በሀገር ክህደት ወንጀል የምትፈልገውን አነጋጋሪ ሰው ኤድዋርድ ስኖደንን ማዕከል አድርጎ የተሰራ ሲሆን፤ ትርክቱም የፊልም ባለሙያዋ ሎውራ ፓትራስ እና ጋዜጠኛ ግሌን ግሪንዋልድ በሆንግ ኮንግ ከኤድዋርድ ስኖደን ጋር ተገናኝተው ሚስጥሩን ለአለም ህዝብ እንዴት ይፋ እንዳደረገው የሚያሳይ ዘጋቢ ፊልም ነው።

ሌላው በኢትዮጵያዊው ታምራት ዳዊት የተሰራው “Grandma knows Best?` የተሰኘው ዘጋቢ ፊልም ሲሆን፤ ይህም ፊልም ኢትዮጵያ እና ካናዳ የሚገኙ ሁለት አያቶች ለልጅ - ልጆቻቸው ቆይቶ ስለማግባትና አለማግባት የሚፈጥሩትን የሀሳብ ፍጭትና የማሳመን ሂደት የሚተርክ ፊልም ነው። በፊልሙ ለመጨረሻ ውሳኔ የሚያበቃ የማጠናከሪያ ሃሳብ ከኑሮና ከአካባቢ ጋር ተነፃፅሮ ይቀርባል።

በዚህ ዓመት ከቀረቡት ዘጋቢ ፊልሞች ሁሉ ምናልባትም የአጭር ደቂቃ ስራ ነው የተባለለት በቺርስ ፊሊፕ የተሰራውና “My Favorite Things” የተሰኘው ዘጋቢ ፊልም ሳይሆን አይቀርም። ፊልሙ የ5 ዓመት ዕድሜ ባለው ሔኖክ የተባለ ህጻን ላይ ተመስርቶ፤ የልጆች ጨዋታና የህጻናትን መብት በድህነት ውስጥ ለማሳየት ይሞክሯል።

ከሁሉም ዘጋቢ ፊልሞች በርካታ የፊልም ሽልማቶችን የሰበሰበው ፊልም፤ ከዓመታት በፊት በኢንዶኔዥያ በተፈፀመ የግፍ ግድያ ላይ ተንተርሶ የተሰራው “The look of silence” ሲሆን፤ ከ10 ያላነሱ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችንም ስለማግኘቱ ተነግሮለታል።

  • የዘጋቢ ፊልም ፌስቲቫሉ ተግዳሮቶች?

ለተከታታይ ዘጠኝ ዓመታት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ተወዳጅ የሆኑ ዘጋቢ ፊልሞችን በማሳየት ላይ የሚገኘው አዲስ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል የማሳያ ቦታዎች እጥረት፣ የተመልካች ቁጥር ማነስና የስፓንሰሮች ፍላጎት አለማደግ እንደፈተና መሰናክል እየሆኑበት ስለመሆኑ የኢኒሼቲቭ አፍሪካ ዋና ስራ አስኪያጁ አቶ ክቡር ገና ይናገራሉ። “በተከታታይ ዓመታት ሳናቋርጥ እዚህ መድረሳችን በራሱ ትልቅ ተግባር ነው” የሚሉት አቶ ክቡር፤ ከ300 ሺህ ብር ያልበለጠ መንቀሳቀሻ ይዘን እንግዶችን ጋብዘን ይህን መሰል ትልቅ ዝግጅት መምራትና የፊልሞቹን መብት አግኝተን ይህን የመሰለ ዓመታዊ ፌስቲቫል በየዓመቱ ማካሄዳችን እንደቀላል የሚታይ አይደለም ይላሉ።

የስፖንሰሮች ፍላጎት አለመጎልበት እንዳለ ሆኖ የተመልካቹም ቁጥር ማነስ አሳሳቢ እንደሆነ ተጠቅሷል። ለዚህም በብዙዎች ዘንድ የተነሳው ሃሳብ የተመልካቹ ከዘጋቢ ፊልም ይልቅ ለፊቸር ፊልም ትኩረት መስጠቱ፤ የዘጋቢ ፊልሞቹ ሃሳቦች ጠንከር ማለትና የሚቀርቡበት ቋንቋም ለብዙዎች የሚገባ አለመሆኑ ጥቂት የማይባሉ ተመልካቾች የሚስማሙበት እንቅፋት ሆኗል። ነገር ግን አሁንም ቢሆን ለእውነተኛ ታሪኮችና ለዘጋቢ ፊልሞች ትኩረት የሚሰጡ ተመልካቾች በመኖራቸው በሂደት ሁኔታዎች ይለወጣሉ የሚል ተስፋ እንዳለ ከአዘጋጆቹ ሰምተናል።

“አዲስ ኢንተርናሽናል የፊልም ፌስቲቫል” ለአዲስ አበባም ሆነ ለኢትዮጵያ መልካም ገፅታን ከመፍጠር አንጻር ቀላል አለመሆኑን የሚገልፁት አቶ ክቡር፤ በዘንድሮ ዓመት መንግስት ትብብሩን ለማሳየት የብሔራዊ ሙዚየምንና የሀገር ፍቅርን አዳራሾች ለፊልም ዕይታ ክፍት ማድረጉን ሳያመሰግኑ አላለፉም።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
10708 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us