“ፍየል ወዲያ፤ ሽመል ወዲህ”

Wednesday, 24 June 2015 11:57


ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ የአገራችንን ሲኒማ ቤቶች ተቀላቅሎ በበርካቶች ዘንድ በመታየት ላይ ያለ ፊልም ነው። የስብዕናን ጠረፍ፤ የባህልና የቋንቋን ጣጣ፤ የፍቅርና የክብርን ድንበር፤ የታሰበው ቀርቶ ያልታሰበው ጐልቶ የሚታይበት አስቂኝ የፍቅር ፊልም ነው፣  “ሼፉ-፪”። ይህ ዳሰሳ ስለ ፊልሙ ጥቂት ለማለት ይሞክራል።

የካም ግሎባል ፒክቸርስ ስምንተኛ ፊልም የሆነው “ሼፉ-2” ፊልም በቢኒያም ወርቁ ተጽፎ፤ በኪሩቤል አስፋው አዘጋጅነትና ፕሮዲዩሰርነት የቀረበ ስራ ነው። ኪሩቤል አስፋው ከዚህ ቀደም “አማላዩ” እና “ሼፉ-1” ፊልሞችን በፕሮዲዩሰርነት እንዲሁም “ፍቅር ሲመነዘርን” ደግሞ በዳይሬክተርነት ጭምር ሰርቶ ለተመልካች ያቀረበ ባለሙያ ነው። ደራሲው ቢኒያም ወርቁ በበኩሉ ከካም ግሎባል ፒክቸርስ ጋር በተለይ የሚታወስለትና ውርስ ትርጉም የሆነውን “ወደገደለው?” ፊልም የፃፈና በበርካታ ስራዎቹም በድርሰትና በዝግጅት ስሙ በተደጋጋሚ የሚነሳ ባለሙያ ነው።

“ሼፉ-2” ከመጀመሪያው የወረሰው ወይም ያስቀረው “እርሾ” መኖሩ በዚህኛው ፊልም ላይ ቢታይም ሁሉም በሚያስብ ደረጃ ግን አዲስ (ቀዳሚው ላይ ያልታዩ) ተዋንያን የተሳተፉበት ስራ ነው። በቀዳሚው “ሼፉ-1” ላይ ትወናውን ሚካኤል ሚሊዮን፣ ማኅደር አስፋ፣ አለምሰገድ ተስፋዬ እና ስምኦን ፀጋዬ በመሪነት ዘውረዋል።

በ“ሼፉ-2” ደግሞ አንጋፋውን ተዋናይና ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሠሠን ጨምሮ፤ የትናየት ታምራት፣ ደሳለኝ ኃይሉ፣ ሄኖክ ወንድሙ፣ ቤዛዊት መስፍን እና ቃልኪዳን ታምሩ የሼፉን ፊልም ባህር እንደየ ገፀ-ባህሪያቸው ይቀዝፉበታል።

ቀላል ታሪክ ይዞ በቋንቋ እየተጫወተ የፍቅርን ኃያልነትና የሰዎችን የማንነት ደረጃ የሚፈትሸው “ሼፉ-2” ፊልም በበርካታ ተቃራኒ ሀሳቦችና ባህሪያት ዙሪያ የሚሽከረከር ከመሆኑ አንፃር፤ “ፍየል ወዲያ፣ ሽመል ወዲህ” የሚያሰኙ ክስተቶችን ያስተናግዳል። በተለይም በሦስት መሠረታዊ ልዩነቶች ፊልሙን የሳቅና የታሪክም ፍሰቱ እንዲጠብቅ የተደረገ ይመስላል። በኑሮ ልዩነት፣ በባህሪይ ልዩነትና በቋንቋ ልዩነት “ሼፉ-2” ፊልም ከወዲያ ወዲህ ይዘውራል።

የባቢሎን ቅቦች

በፊልሙ ውሰጥ ቋንቋ እንደመግባቢያ፣ እንደማደናገሪያ፣ እንደኑሮ ማሳያና እንደ እንጀራ ሲገለባበጥ ማየት ለተመልካች የሣቅ ምንጭ ሆኗል። አልፎ አልፎም የገፀ-ባህሪያቱ ቋንቋ እንደባቢሎን ዘመን ሰዎች ድብልቅልቁ ይወጣል። በጥቂት የህንድ ቃላት ስር ተሸፍነው እንጀራቸውን የሚጋግሩ የጨርቆስ ልጆችን የቪዲዮ ቤት ድባብ በፊልሙ ውስጥ ማግኘት ያዝናናል። ይህ ቋንቋ ለእንጀራ ሲውል የምናይበት ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ የአካባቢው ልጆች ሲጠቀሙ የምንሰማውን የአራዳ ቋንቋ መስማት ሌላው ነገር ነው።

ይህም ሆኖ አባት (ተስፋዬ ገሠሠ) የልጃቸው የሉሊትን (የትናየት ታምራት) የበዛ የእንግሊዝኛ አጠቃቀም መጥላትና በተገላቢጦሽ በቤታቸው ባስጠጓቸው የጨርቆስ ልጆች “የአራዳ ቋንቋ” መማረካቸው ነገሩን “ፍየል ወዲህ…” የሚያሰኝ ነው።

የባህሪይ ግራና ቀኝ

ሰው ከኑሮው ካደገበት ቦታና ከተማረው ትምህርት ጋር የራሱ የሆነን ባህሪይ ያሳድጋል። ደህና የሚባል ቤተሰብ ውስጥ ያደጉት ሉሊት (የትናየት ታምራት) እና አቤል (ደሳለኝ ኃይሉ) በባህሪይ በኑሮ ዘይቤም ከማይመስሏቸው ከሃብታሙ (ሔኖክ ወንድሙ) እና ከሣራ (ቤዛዊት መስፍን) ጋር ተገናኝተው እናያለን። ይሁን ፍቅር የማይገባበት የለም ብለን እንለፈው። ነገር ግን በተለይ የአቤል እና የሣራ ወዳጅነት መንሰኤና መጀመሪያው በግልፅ አለመቀመጡ ለተመልካች ጥያቄን ይፈጥራል።

ደሃን የምትንቀው ሉሊት፤ ለፍቅር መስዋዕት ለመክፈል የተዘጋጀችው ሉሊት፤ በቅንጡ ኑሮ ጣሪያ የነካችው ሉሊት እንዴት ወርዳ ተገኘች የሚለውን ከፊልሙ የታሪክ ፍሰት የምናገኘው ሲሆን፤ በአንፃሩ ለሴት ልጅ ትልቅ ክብር ያለው፤ በሃብታቸው ለሚመፃደቁና በጉልበታቸው ለሚመኩ ሰዎች ንቀትና ጥላቻ ያለው ሀብታሙ ካሉለት ጋር የሚገጥሙትን የባህሪይ ጦርነት መመልከት አሁንም “ፍየል ወዲያ፣….” ያሰኛል።

የኑሮ ልዩነት

በፊልሙ ውስጥ ሌላኛው እንደቅመምና ታሪክ ማጠንጠኛ ሆኖ የቀረበው የተደበቀ ማንነትና የኑሮ ደረጃ ልዩነት ነው። እንደ ብዙዎቹ የሃገራችን ፊልሞች በ“ሼፉ-2” ላይም ሀብታሞች ደሃዎችን ሲያፈቅሩ እንድናይ ተገደናል። ነፃነቷን የምትናፍቀው የባለስልጣን ልጅ መክሊት (ቃልኪዳን ታምሩ) የምትናፍቀውን ነፃነት የሚያሳያት ሳምሶምን በአጋጣሚ ተዋውቃው እፍ-ክንፍ ስትል እንመለከታታለን። በዚህ ሁሉ መካከል ግን የባለስልጣን ልጅ መሆኔን ካወቁ ይርቀኛል በሚል በዝምታዋ የፀናችው መክሊትና፤ ራሱን በንግድ ስራ እንደወጠረ ባተሌ የቆጠረው የጨርቆሱ ልጅ ሳምሶን መካከል የቋጠሩት ሲፈታና የደበቁት ሲጋለጥ በሚፈጠረው ውጥረት የፊልሙን ሰንሰለት ይወጠራል። በሃብታሞች ኑሮ እና በድሆች ኑሮ መካከል ያለውን ልዩነት “ሼፉ-2” እንደቀዳሚው ሁሉ በጉልህ ለማሳየት ችሏል። በዚህም የኑሮ እርቀት “ፍየል ወዲያ፣ ሽመል ወዲህ” ያሰኘኛል። ሁሉንም ግን አንድ የሚያደርግ የሰውነትና የፍቅር ኃይል በ“ሼፉ-2” በጉልህ ታይቶ ይጠናቀቃል።

ለመሆኑ በፊልሙ ውሰጥ የታዩ ቀላል የሚመስሉ ግድፈቶችን በአጭሩ ጠቁመን ዳሰሳችንን እናብቃ። “ሼፉ-2” ከአማርኛ ሌላ ለሚናገሩ ሰዎች ይረዳ ዘንድ የግርጌ ጽሁፍ መጠቀሙ በእጅጉ መልካም ነው። ነገር ግን አብዛኛው “የአራዳ ቋንቋ” ተብለው በፊልሙ ላይ የሚነገሩት ቃላቶች በራሳቸው ወደአማርኛ የግርጌ ጽሁፉ መምጣት ያለባቸው ናቸው። ይህም ፊልሙን ለመታደም የመጣውን ተመልካች እንደማገዝም እንደግዴታም ሊቆጠር ይገባዋል።

ሌላኛው ቀላል ስህተት ጓደኛዎን ፍለጋ ስልክ የደወለችው መክሊት “ቦሌ ነው ያለነው” በሚል ምላሽ ብቻ “እዛው አካባቢ ነኝ” በሚል መጣሁ ብላ መገናኘታቸው ነገሩ እንዴት ነው ያሰኛል።

በተረፈ ግን የሚታይ ለውጥ በፊልሙ ውስጥ እንድንገነዘብ የተደረገበት መንገድ መልካም እንደሆነ መጥቀሱ አስፈላጊ ነው። የገፀ-ባህሪያቱን የአመለካከት ለውጥ በቋንቋና በቦታ ለውጦ ለማሳየት የተሞከረበት ዝግጅት ይመስጣል። ለምሳሌ መክሊት የአራዳ ቋንቋ ለመቻል ያላትን ጉጉትና ከምትወደው ልጅ ጋር ለመመሳሰል የምታደርገውን ጥረት በተመለከተ በቋንቋ፣ “ጨርቆስን ተመችቶኛል” ማለቷ ሊጠቀስ ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ሉሊት በሀብታሙ ፍቅር መሸነፍን ዳይሬክተሩ በግልፅ የሚያሳየን ሾፌሯ ሆኖ ትቀመጥበት ከነበረው የመኪናው የኋላ መቀመጫ ወደፊት መምጣቷ ሌላኛው ማሳያ ሊሆን ይችላል።

    በአጠቃላይ “ሼፉ-2” ፊልም የፍቅርን አስፈላጊነት በአባትየው አንደበት ሲገልፀው፤ “ግንብ ያለ ሰው ኦና ነው” ከሚለው ኃይለ ቃል በተጨማሪ፣ “ከብረት ምርኩዝ የሰው ምርኩዝ ይበልጣል” በሚል አፅንቶ ያሳየ አዝናኝ የፍቅር ፊልም ነው ማለት ይቻላል።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
9419 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us