“ሰላይ የምሆን ይመስለኝ ነበር”

Wednesday, 01 July 2015 13:12

ተዋናይ ዳንኤል ታደሰ (ጋጋኖ)

 

የሚያውቁት በራሱ መቀለድን የሚያውቅ ነፃ ሰው ነው ይሉታል። ፈተናዎችን ተቋቁሞ የራሱን ምስል በትወና ማምጣት የቻለ ባለሙያ ነው። በሩሲያ የባህል ማዕከል መድረክ ቴአትሮቹና በተለያዩ ጭውውቶቹ ይታወቃል። ከሙሉ ሰዓት ፊልሞቹ መካከልም “ሳምራዊው” አንድና ሁለት፤ “ሄሎ ኢትዮጵያ”፤ “ማህቶት”፤ “አፍሮኒዝም” እና “ዌተሩ” ጥቂቶቹ ናቸው። በቅርቡም ወደ አውሮፓ ተጉዞ በዓለም አቀፉ ፊልም ፌስቲቫል ላይ ተገኝቷል። ለዚያም ያበቃው በትወና የተሳተፈበት ሳይንስ ፊክሽን ፊልም እንደሆነ ይናገራል። ከተዋናይ ዳንኤል ታደሰ (ጋጋኖ) ጋር ያደረግነውን አዝናኝ ቆይታ እነሆ፤  

ሰንደቅ፡- ብዙ ጊዜ ተጠይቀህ መልሰኸዋል። ምናልባት ያልሰሙ አንባቢያን ይኖራሉና ጋጋኖ የሚለው ቅጽል ስም ከየት መጣ?

ዳንኤል፡- ስሙን ያገኘሁት ከቴአትር ገፀ-ባህሪይ ነው። ቴአትሩ እዚህ ፑሺኪን አዳራሽ የተሰራ ሲሆን፤ ድርሰቱ የኒኮላይ ጐጐል ሆኖ ጋሽ አያልነህ ሙላት ነበር ያዘጋጀው። እዛ ላይ ዶክተር ጋጋኖ የተባለ ገፀ-ባህሪይን ሰርቻለሁ። ሰውዬው ሁለት ሰዓት ሙሉ ከመድረክ አይወርድም ነበር። ብዙ ተመልካቾችም ወደውት የማይረሱት አይነት በመሆኑ ስሙን ስሜ አደረጉት ማለት ነው።

ሰንደቅ፡- ይህ ማለት ስምን መልዓክ ብቻ ሳይሆን ገፀ-ባህሪያትም ያወጣሉ ማለት ነው?

ዳንኤል፡- (ሣቅ) ማለት ይቻላል።

ሰንደቅ፡- ወደትወናው ዓለም ስትመጣ የነበሩትን ፈተናዎች ታስታውሳቸዋለህ?

ዳንኤል፡- ባይገርምህ ትወናን የጀመርኩት እንደቀልድ ነው። ትምህርት ቤት ውስጥ ለወላጆች ቀን ሲባል አጫጭር ድራማዎች ላይ መሳተፍ ጀመርኩ። ከዚያ በኋላ ደግሞ በወቅቱ ጥሩ የሚባሉ የቴአትር ክበቦች በየሰፈሩ ነበሩ። እኔ በአጋጣሚ ከእነቴዎድሮስ ለገሰ ጋር ተገናኘሁ። “ዩኒቲ የቴአትር ክበብ” ውስጥ አብሬያቸው እሰራ ነበር። ያኔ ከሰራነው መካከል እንዳጋጣሚ “የልብ እሣት” የተሰኘ ቴአትርን ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት አስገምግመነው አለፈ። ከዚያ በኋላ ከቴአትር መለየት አልቻልኩም። እውነቱን ለመናገር አንዳንድ ሰዎች ሲያዩኝ ቴአትር የምሰራ አይመስላቸውም ነበር። ቀስ በቀስ ግን በራሴም ላይ እየቀለድኩ ሳሳያቸው እየተቀበሉኝ መጡ ማለት እችላለሁ።

ሰንደቅ፡- በራስ ላይ የመቀለድን ጥበብ ከየት አመጣኸው? እራስህንስ የሣቅ ምንጭ አድርገህ ትቆጥራለህ?

ዳንኤል፡- በራስ ላይ መቀለድ ትልቅ ጥበብ እንደሆነ አምናለሁ። ይህን ነገር እንዴት መሰለህ ያዳበርኩት፤ ሰዎች በድብቅ ሆነው ወይም ከኋላዬ ሆነው ሊሉኝ ይችላሉ ብዬ የማስበውን ነገር እኔ በአደባባይና በመድረክ ላይ እቀልድበታለሁ። በተለይ በራሴ አካላዊ ቅርፅ ላይ በጣም ነው ቀልድ የምፈጥረው። በራስ ላይ እንደመቀለድ አሪፍ ነገር ደግሞ ያለ አይመስለኝም።

ሰንደቅ፡- አካላዊ አፈጣጠርህ በዚህ መልኩ በመሆኑ እንቅፋት ሆኖብኛል ብለህ ያማረርክበት ጊዜ አለ?

ዳንኤል፡- አስቤውም አላውቅም። አፈጣጠሬን አምኜውና ተቀብዬው እየኖርኩ ነው። ሌላ ምንም መሆን አልችልም።

ሰንደቅ፡- ከወራት በፊት ወደ አውሮፓ ሄደህ ነበር፤ የሄድክበት ምክንያት ምንድነው? ምንስ አገኘህ?

ዳንኤል፡- ከስፔናውያን የፊልም ባለሙያዎች ጋር የሰራሁዋቸው ዶክመንተሪዎች (ዘጋቢ ፊልሞች) ነበሩ። ባለፈው ዓመት “ችግር አለ” በተሰኘ ፊልም ላይ የሂትለርን ገፀ-ባህሪይ ተላብሼ ሰርተን፣ ጣሊያን ሚላን ውስጥ በተካሄደ የፊልም ፌስቲቫል ላይ ብጋበዝም በአጋጣሚ መገኘት አልቻልኩም ነበር። ባይገርምህ በወቅቱ በትወና ከዓለም ሁለተኛ ደረጃን ነበር ያገኘሁት። ከዚያ ዘንድሮ ደግሞ ቀጥለን “ክራምፕስ” የተሰኘ ሳይንስ ፊክሽን ፊልም ሰራን። ፊልሙ ከአንድ ሰዓት በላይ የሚፈጅ ነበር። ከዚያ በኔዘርላንድ ፊልም ፌስቲቫል ተጋብዤ ነው የሄድኩት። በጣም ደስ የሚል ቆይታ ነበረኝ።

ሰንደቅ፡- ምን አዲስ ነገር ጨመረልህ?

ዳንኤል፡- የመጀመሪያው ነገር ብዙ ሰዎችን የመተዋወቅ አጋጣሚውን አግኝቼበታለሁ። አሁንም ድረስ እየተፃፃፍን ነው። ከተወሰኑ ወራት በኋላ ደግሞ ከስፔናውያኑ ባለሙያዎች ጋር በመሆን ወደ ቻይና በመሄድ የምንሰራው ስራ ስላለ በዝግጅት ላይ ነኝ።

ሰንደቅ፡- በአውሮፓ ቆይታ የማትረሳው ነገር አጋጥሞሃል?

ዳንኤል፡- ይገርምሃል ከባድ ንፋስ ተነስቶ ይዞኝ ሄዶ ነበር። (ሣቅ) እኔ አውላላ ሜዳ ላይ ነኝ፤ ሰው ይሯሯጣል እኔ አላወኩም። አንድ መኪናና አንድ ዛፍ ብቻ ነበር። ነገሩ በጣም ያስደነግጥ ነበር። ነገር ግን በኋላ ላይ ፎቶ ያነሱኝ ሰዎች ሲያሳዩኝ በጣም ያስቅ ነበር። ከዚያን ጊዜ በኋላ ዛፍ በሌለበት አካባቢ መንቀሳቀስ አቆምኩ። (ሣቅ)  

ሰንደቅ፡- እስካሁን ከሰራሃቸው ፊልሞች በተለየ የምታስታውሰው አለ?

ዳንኤል፡- እንደ ገፀ-ባህሪይ ሁሉንም አትረሳቸውም። በተለይ ግን “አሉ” የሚል የተፈሪ ዓለሙን ድርሰት በኢምፔሪያል ሆቴል ሰርተን ነበር። በጣም አንጋፋ አንጋፋ ተዋንያን ነበሩበት። አገር ገዢውን ሆኜ እየተወንኩ ሳለ በጣም ከመመሰጤ የተነሳ የመድረኩን ጫፍ ማስተዋል በመርሳቴ ልውድቅ ነበር። በወቅቱ ዳይሬክተሩ ዘውዱ አበጋዝ ነው፤ በስሜ ጠርቶ “ዳንኤል ጫፍ ላይ ነህ እንዳትወድቅ” ያለኝ። ይሄን ነገር ሁሌም አልረሳውም።

ሰንደቅ፡- ካሜራና መድረክ ላይ ስትቀርብ ምን ይሰማሃል?

ዳንኤል፡- ስራው አስኪጀመር ሁልጊዜ ያስፈራል። ስራውን እንዴት ነው የምወጣው? የሚለውን አስባለው። ከዚያ ውጪ ደግሞ አብረውኝ የሚሰሩትን ሰዎች አቅምም እገመግማለሁ። ለምሳሌ መድረክ ላይ ከሆነ እስክትወጣ ነው። ከዚያ በኋላ ግን ትቀየራለህ። ፊልምም እንደዚያው ነው። በኋላ ላይ የተቀረፀውን ሳይ አንዳንዴ ለራሴም ይገርመኛል።

ሰንደቅ፡- ለመጀመሪያ ጊዜ በሲኒማ አቡጀዲ ላይ የራስህን ትወና ስታየው ምን ተሰማህ?

ዳንኤል፡- በጣም ይገርምሃል። አንድ ጊዜ “አፍሮኒዝም” የተሰኘ ፊልም ውስጥ በፓንት የምታይበት ቦታ ነበረው። ፊልሙን ሳየው በጣም ነው በራሴ የሳኩት። ከዚያ በኋላ ተዋናይ ፍቃዱ ከበደ ፊልሙን አይቶት ምን አለኝ? “ዳኒ በዚህ ቅርፅህ ለምን ቦክስ አትወዳደርም” ብሎ አስቆኛል። ሁሌ ራሴን በፊልም ሳየው እገረማለሁ።

ሰንደቅ፡- ከልጅነትህ መሆን የምትመኘውን ሆኛለሁ ብለህ ታስባለህ?

ዳንኤል፡- በልጅነት ብዙ ጊዜ ከቤት አልወጣም ነበር። ዋናው ተግባሬ ማንበብ ነው። ወንድሜ መጽሐፍትን ማታ ያመጣልኛል፤ ጠዋት ይወስዳል። ብዙ ጊዜ የስለላ መጽሐፍትን ቁጭ ብዬ ሳነብ ነበር የማነጋው። ያኔ ታዲያ ሳድግ ሰላይ የምሆን ይመስለኝ ነበር። ነገር ግን ቀስ በቀስ ሳላውቀው እዚህ ቦታ ተገኝቻለሁ፤ በመሆኑም አሁን ትወናን ወድጄው ነው የምሰራው።

ሰንደቅ፡- እስቲ ደግሞ ጨዋታችንን ቀለል እናድርገው፤ ምን ያዝናናሃል?

ዳንኤል፡- ከጓደኞቼ ጋር ሀሳብ ስንለዋወጥ ደስ ይለኛል። ከተቻለ ደግሞ ከከተማ ወጥቼ ለራሴ ጊዜ ስሰጥ በጣም ዘና እላለሁ።

ሰንደቅ፡- በፊልም ወይም በቴአትር አብሬው ብሰራ ብለህ የምትመኘው ተዋናይ አለ?

ዳንኤል፡- ፈለቀ አበበን ሁሌ እመኘዋለሁ። ይህን ነገር ባለፈው ጊዜም በጋዜጣ ተጠይቄ መልሼዋለሁ። ፈለቀ በጣም ደስ የሚለኝ ባለሙያ ነው።

ሰንደቅ፡- በፊልም ትልቁ ክፍያህ ስንት ነው?

ዳንኤል፡- ይሄን ጥያቄ ዝለለው እባክህ።

ሰንደቅ፡- ከዚህ በኋላ ምን አይነት ገፀ-ባህሪይን ነው፤ ብሰራ ብለህ የምትመኘው?

ዳንኤል፡- በፍቅር ክንፍ ያለን ገፀ-ባህሪይ ወክዬ መስራትን በጣም እመኛለሁ።

ሰንደቅ፡-በድፍረትና በምክንያት መናገር የምትችል ከሆነ እስካሁን ካየሃቸው የአገራችን ፊልሞች የትኛውን ታደንቃለህ?

ዳንኤል፡- በጣም የተመሰጥኩበት ስራ “ዘመቻ ድንግል ፍለጋ” ነው። ፕሮዳክሽኑ ጥሩ ነው። ከታሪክም ከቴክኒክም አንፃር ፊልሙን ወድጄዋለሁ። ይህን ስልህ ሌሎች የሉም ማለቴ ግን አይደለም።

ሰንደቅ፡- በህይወትህ የምትፈራው ነገር ምንድነው?

ዳንኤል፡- አይጥ፤ አይጥን እፈራለሁም፤ እጠላለሁም።

ሰንደቅ፡- ምክንያት አለህ?

ዳንኤል፡- ልጅ ሆኜ አያቴ’ጋ መገናኛ አካባቢ ከልጆች ጋር ስንጫወት ሜዳ ድረስ ትላልቅ አይጦች መጡ። እኛም ደነገጥን እነሱም ደነገጡ፤ ሁላችንም ተሯሩጠናል። ከዚያን ጊዜ በኋላ አይጥ ያስፈራኛል። ሌላው ደግሞ ሊፍት አልወድም፤ እሱም ህፃን እያለሁ ይዞኝ ስለነበር አልወደውም። በዚህ አጋጣሚ ደንበል ላይ ለስራ ብለን ከልጆች ጋር ስንሄድ እነሱ በሊፍት ሲሄዱ፤ እኔ ግን 10ኛ ፎቅ ድረስ በእግሬ ሄጃለሁ። አሁን በቅርቡ አውሮፓ ሄጄ ግድ ስለሆነብኝ ብቻ አንድ ሁለቴ ተጠቅሜያለሁ። (ሣቅ)

ሰንደቅ፡- በቀጣይ ምን የመስራት ሀሳብ አለ?

ዳንኤል፡- አሁን በቅርቡ ለውጪ ውድድር የሚሆን የራሴን የህይወት ታሪክ በዘጋቢ ፊልም ዘውግ ስር እየሰራሁ ነው። ከተወሰኑ ወራት በኋላ ደግሞ የቻይናው ጉዞ አለ። ከእነተመስገን ጋርም አንድ ስራ እየጨረስኩ ነው። እነዚህን ስራዎች ለተመልካች አደርሳለሁ።

ሰንደቅ፡- ከቴአትርና ከፊልም የቱ ይልቅብሃል፤ ለምን?

ዳንኤል፡- ምንም ጥርጥር የለውም ቴአትር ነው። ለምን ካልከኝ አንድ ተዋናይ የትወና አቅሙን መለካት ከፈለገ በመድረክ ተውኔት መታየት አለበት ብዬ አምናለሁ። በዚህ ላይ አሁን-አሁን ብዙ ወጣትና አሪፍ ተዋንያንን በፊልም እያየናቸው ነው። ነገር ግን ቴአትር ላይ አታያቸውም፤ ይህ የሚያሳየው ቴአትር ከባድና ፈታኝ መሆኑን ነው።

ሰንደቅ፡- ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ፤ ቀረ የምትለው ነገር ካለ?

ዳንኤል፡- ምንም የለም። በዚህ አጋጣሚ ግን ቤተሰቦቼን፣ ጓደኞቼን አብረውን የሚሰሩትን ሁሉ በጣም ላመሰግናቸው እወዳለሁ።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
15859 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us