Print this page

የቸርነት፤ ሥዕልና ግጥም ጥምረት በጋላሪያ ቶሞካ

Wednesday, 08 July 2015 14:32

“ቀለማት በስዕል የምናገርባቸው ቋንቋዎቼ ናቸው” ይላል ሰዓሊ ቸርነት ወልደገብርኤል። ቸርነት ሰዓሊም ብቻ አይደለም ጥልቅ ሃሳቦችን የሚረጭ ገጣሚም ጭምር ነው። የዚህ ሰዓሊና ገጣሚ የቅብ ስራዎች በምስልና በግጥም ተቀምመው በተለየ መልኩ በቶሞካ አርት ጋላሪ ለሁለት ወራት መታየት መጀመራቸውን ባሳለፍነው አርብ ሰኔ 26 ቀን 2007 ዓ.ም በተካሄደው መክፈቻ ላይ አዘጋጆቹ ሲናገሩ ሰምተናል።

“የሥዕላዊ እና ቃላዊ ጥበባት ቡረቃ” የተሰኘ ርዕሰ የተሰጠው ይህ የስዕል አውደ-ርዕይ በቶሞካ አርት ጋላሪ ሲካሄድ 16ኛው መሆኑን ያስታወሱት ረዳት ፕሮፌሰር ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ ናቸው። በጋላሪው ጥበባዊ ፋይዳ ያላቸው ስራዎች በተከታታይ መቅረባቸው እንደሚቀጥልም ተነግሯል።

“ስዕልን ለመሳል ሃሳቡ ይምጣ እንጂ የተለየ ቆስቋሽ አልፈልግም” የሚለው ሰዓሊና ገጣሚ ቸርነት ወልደገብርኤል፤ በተለየ ግን በመልክዓ - ምድር አቀማመጥና ለቀለማት በስዕል ስራዎቹ ላይ ትኩረት እንደሚሰጥ ይናገራል። በተለያዩ ቦታዎች በግሉ የስዕል ስራዎቹን በማሳየት ልምድ ያለው ሰዓሊው፤ ቶሞካ አርት ጋላሪ ከግጥም ጋር አጣምሮ ስራዎቹን ለተመልካች ሊያሳይለት ስለመረጠው ከፍ ያለ ምስጋናውን ለአዘጋጆቹ ገልጿል። “ስዕልን በቅርበት የምታይበት ቦታ ቶሞካ ነው” የሚለው ሰዓሊው፤ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ በተሳተፈባቸው የስዕል አውደርዕይዎች ይህን መሰል ብዙ ሰዎች የሚያዩት ቦታ ግን አላጋጠመኝም ይላል።

በቶሞካ አርት ጋላሪ ለዕይታ ያበቃቸው ሃያ አምስት የሰዓሊውን ስራዎች ሲሆን፤ ሁሉም ስራዎች በ2007 ዓ.ም ተሰርተው የተጠናቀቁ ናቸው የሚለው ሰዓሊና ገጣሚ ቸርነት ወ/ገብርኤል፤ ከቦታው ጥበት አንፃር 37 ስራዎች ተመርጠው የተዘጋጁ ቢሆንም የዕይታ ዕድሉን ያገኙት ግን ሃያአምስቱ ብቻ ሆነዋል ይላል።

ስዕል ለተመልካቹ ትርጓሜ የተጋለጠ ነው የሚሉት በስፍራው የነበሩ የሰዓሊው አድናቂዎች፤ አውደ-ርዕይው በግጥም የታጀበ መሆኑ የበለጠ ትኩረትና ጣዕም ይሰጠዋል ባዮች ናቸው። ለመሆኑ ስዕልና ግጥም በቶሞካ አርት ጋላሪ እንዴት ይጣመራሉ? የሚል ጥያቄ ለሰዓሊና ገጣሚ ቸርነት፣ አንስተንለት ነበር። “ሁለቱም ጎን ለጎን እንዲታዩም እንዲነበቡም ሆነው ይቀርባሉ። ስዕል የሚያይ ሰው ግጥም እንዲያነብ ይጋበዛል። እኔ ደግሞ አሪፍ ገጣሚም ስለሆንኩ (ሳቅ) ግጥሜም እንዲነበብ እፈልጋለሁ” ይላል።

ለግጥም የተለየ ፍቅር እንዳለው የሚናገረው ቸርነት፤ “ግጥምና ስዕል የየራሳቸው አየር አላቸው፤ ነገር ግን አንዳንዴ ስዕል ግጥም ይሆናል፤ ግጥምም ስዕል ይሆናል” ሲል ጥምረታቸውን ይገልጻል። ያም ሆኖ ጥልቅ ሃሳቦች ሲመጡ የሚቀናኝ ከስዕል ይልቅ በግጥም መግለፅ ነው ይለናል።

የተለያዩ ነገሮችን በአንድነት ያሳየሁበት የስዕል ስብስብ ነው በሚለው በዚህ የስዕል አውደርዕይ ላይ እኔ አስቀድሜ የሰጠውት ርዕስ “አብሮነት” ቢሆንም የቶሞካ አርት ጋላሪ አዘጋጆች በበኩላቸው “የሥዕላዊና ቃላዊ ጥበባት ቡርቃ” ብለውታል። ይህም የእነርሱ ምልከታና ቤቱን የሚወክል ነው ሲል ሃሳቡን ሰንዝሯል።

ሰዓሊና ገጣሚ ቸርነት ወ/ገብርኤል ካበረከታቸው በርካታ የስዕል ስራዎቹ ባልተናነሰ የሚጠቀሱለት የግጥም ስራዎችና የወግ ስብስቦች አሉት። በ1998 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የባህል ማዕከል አዳራሽ የሚያነባቸውና የበርካታ ተማሪዎችን ጭብጨባ ያገኘባቸውን የግጥም ስብስቦች ይዞ “ኤፍራጥስ” በሚል ርዕስ እነሆ በረከት ብሎናል። በ2002 ዓ.ም ደግሞ “ዲና” የተሰኘ የግጥም ሲዲ አቅርቦልናል። ከነዚህ ስራዎቹ በተጨማሪ ዋዘኛ ወጎችንም በመፅሐፍ መልክ በማስነበብ ይታወቃል።

ስለሰዓሊና ገጣሚ ቸርነት ወ/ገብርኤል በመክፈቻ ፕሮግራሙ ላይ ንግግር ያደረጉት የጋላሪያ ቶሞካ አርት ዳይሬክተር ረ/ፕሮፌሰር ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ እንዲህ ብለው ነበር፤ “ቸርነት ይሞቃል ይቀዘቅዛል፤ ቀለሞቹ ኃይሉን ይናገራሉ ግጥሞቹ ደግሞ ውስጣዊ ችሎታውንና የጥልቅ ሃሳቡን መንፈስ ይገልፃሉ” ብለዋል። አክለውም “እንደቸርነት ያሉ መንቶ ባለሙያዎች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው” ሲሉ ይደመድማሉ።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
16026 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ አሸናፊ ደምሴ