“ቀሚስ የለበስኩ’ለት” የተፈጠረ ስህተት

Wednesday, 05 February 2014 15:14

የጊዜቤት ምስሎች ከጃዝ አምባ ኢንተርቴይንመንት ጋር በመተባበር ያቀረበው፤ በደራሲና አዘጋጅ ዘሪቱ ከበደ ተሰርቶ በሄኖክ አየለ መራሄ ምስል ለዕይታ የበቃው “ቀሚስ የለበስኩ’ለት” ፊልም በበርካታ ሲኒማ ቤቶች በመታየት ላይ ይገኛል። ድራማዊ የፍቅር ዘውግነት ያለው ይህ ፊልም የሚመራን ማነው… እምነት? ጊዜ ወይስ ስሜት? ሲል ይጠይቃል።

     “ቀሚስ የለበስኩ’ለት” ፊልም ቁንፅል ታሪኩ፤ የእህት ያህል የምትቀርባት የጐረቤት ልጅ ሰርግ ላይ ቀሚስ ለብሳ የደመቀችው ሳምራዊት (ዘሪቱ ከበደ) ከሙሽራዋ ወንድምና አፍቅሮ ከተከዳው መሳይ (ይስሃቅ ዘለቀ) ጋር ያን ዕለት ምሽት በተፈጠረ የስካር ሞቅታ ስህተት ላይ ተመስርቶ የሚያጠነጥን ነው። ይህም የአንድ ቀን ስህተት ተዳፍኖ ቢቆይም ሳምራዊት በኮሌጅ የፍቅር ጥያቄ ያቀረበላትን ልዑል (ዲበኩሉ ታፈሰ) መልስ ሳትሰጥ በመወላወል ላይ ሳለች እርጉዝ መሆኗን ታውቃለች። በዚህ መሀል የቀድሞው ፍቅረኛውን ለመርሳት ሲል ከመጠጥ ምሽግ ወጥቶ ራሱን በስራ ለማጥመድ የሚታትረው መሳይ (ይስሃቅ ዘለቀ) በስራ አጋጣሚ ከተዋወቃት አይዳ (ቃልኪዳን ታደሰ) ጋር አዲስ ፍቅር መስርቶ በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ወደ ጋብቻ ሲንደረደሩ፤ ድንገት የሳምራዊት (ዘሪቱ ከበደ) ከመሳይ ማርገዝ ይፋ ይሆንና የሁለቱን ወጣቶች ህይወት ፈተና ውስጥ ሲጥለው እንዲሁም ለውሳኔ ሲያስቸግራቸው የሚያሳይ ፊልም ነው።

ፊልሙ ሊያስተላልፈው የፈለገው ትልቅ መልዕክት ቢኖርም በተበጣጠሱትና በተቆራረጡት የመቼት ትስስራቸው በላላና የታሪክ አገነባባቸው በተሰነጣጠቁ ሂደቶች ምክንያት ጭብጡ ከተመልካች ልብ ጠብ እንዳይል ጐታች ሆኖበታል።

በኮሌጅ የስነ-ልቦና ትምህርትን እያጠናች የምናያት ሳምራዊት (ዘሪቱ ከበደ) ጠንካራና የዓላማ ፅናት ያላት እንደሆነች እንድንረዳ በራሷ የምትተማመንና ቆራጥ መሆኗን በመጀመሪያ የልዑልን (ዲበኩሉ ታፈሰ) የፍቅር ጥያቄና የጓደኛዋን “እሺ በይው!” ውትወታ ወደጐን ማለት ያሳየናል። ያም ሆኖ የራስዋን ጊዜ ስትጠብቅ እንደቆየች ሁሉ የልዑል ውትወታ እየሸረሸራት ወደ ፍቅር መንገድ ገብተዋል ባልንበት አንደኛ ወር ላይ፤ “አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ” እንዲሉ ነገሮች በድንገትና በፍጥነት ሲለዋወጡ በፊልሙ ውስጥ እናስተውላለን።

በፊልሙ ውስጥ የገፀ-ባህሪያት አሳሳል ከተነገረን ጋር በጥብቅ ተያይዞ ሲገለፅ አይታይም። ለምሳሌ ሳምራዊት አራት ወንድሞች አሉኝ ብላ የምትናገርላቸው ልጆች በግልፅ የወንድምነት ባህሪይ አልታየባቸውም። የጐረቤት ልጅ የሆነውና አብሮ አደጓ መሳይ (ይስሃቅ ዘለቀ) በፍቅር ታስበው፣ አታስበው እንኳን ለተመልካች ለጓደኛዋም ግልፅ መልስ ሳይሰጥ በእንጥልጥል የቀረ ጉዳይ ሆኖ ተቀምጧል።

በፊልሙ ውስጥ ከገፀ-ባህሪያት ስብዕና ግንባታ አንፃር በትክክል ሊጣጣም የሚችለው ምናልባትም የአይዳ (ቃልኪዳን ታደሰ) ብቻ ነው ማለት ይቻላል። ይህቺ ገፀ-ባህሪይ በህፃንነቷ ተጥላ የተገኘችና በሰው ቤት ያደገች ስትሆን፤ ይህን የቤተሰብ ክፍተት በራሷ ያየችው በመሆኑ በስተመጨረሻ ፍቅረኛዋ መሳይ ከሳምራዊት ልጅ ማግኘቱን ስታውቅ አብራው መቀጠል እንደማትፈልግ፤ ዳሩ ግን አብራው መቀጠል ካለባቸው አሳማኝ ምክንያት እንዲያቀርብላትና እንዲያስረዳት ሽንጧን ገትራ ስትሞግተው እናያለን።

በአንፃሩ ደግሞ ይህን መሰል የእርግዝና አጋጣሚ እንዳይፈጠር መጠቀም የነበረባትን መድሃኒት ስለመጠቀሟ የምትነግረን ሳምራዊት (ዘሪቱ ከበደ)፤ ዶክተሯ ባማከረቻት መሰረት ልጁን ለመውለድ ስትወስን ከቤተሰቦቿና ከራሱ ከመሳይ (ካረገዘችለት ልጅ) የቀረበላትን የአብሮ መኖር ጥያቄ ውድቅ ስታደርገውና “ያቺስ ሴት ብትሆን ምን ይሰማታል?” ስትል ትጠይቃለች። እርግጥ ጥያቄዎቹ ተገቢ እና የስብዕና ሞራሏን ደረጃ ያሳያል ቢባልም፤ በፊልሙ ውስጥ ግን ተገቢውን መልስ አግኝቷል ለማለት አያስደፍርም።

“ቀሚስ የለበስኩ’ለት” ፊልም በፈጣን ተለዋዋጭ ታሪኮቹና ትዕይንቶቹ መካከል የተቋጠረ እና መልስ የሚሆን ነገር ሳይነግረን በእንጥልጥል አስቀርቶታል። ከቤተሰቦቿ ቤት የወጣችው ሳምራዊት መጨረሻ.... በግልፅ አልተቀመጠም። የልዑልና የሳምራዊት ንፁህ ጓደኝነት መንገድ የት ድረስ ይሆን? ፍቅራቸውስ በልጅ ምክንያት መሰናከሉ ለምን?.... የመሳይና የአይዳ ትዳርስ በአሳማኝ ምክንያት ይቀጥል ይሆን? ወይስ ይለያየሉ?... ሁሉም ጥያቄዎች መልስ ያላገኙና በእንጥልጥል የቀሩ ናቸው።

ሳምራዊት መድሃኒት ተጠቅማ እንደነበር በፊልሙ ብንጠቆምም ውጤቱ እንዲያ ሆኖ በመቅረቡ በርካታ ተመልካቾች በመድሃኒት ላይ ያላቸውን መተማመን የሚያሳጣ ሆኖ ቀርቧል።

“ቀሚስ የለበስኩ’ለት” ፊልም የመቼት ጥድፊያ በተመልካች ዘንድ ጥያቄን የሚያጭር ነው። ፊልሙ ከግማሽ ጊዜው በላይ ግልፅ ያላወጣልንን የእርግዝና ጉዳይ በስተመጨረሻ አጣድፎ ልጅ ሁሉ ያሳየናል። ችግሩ ያለው የተረገዘው ልጅ መወለዱ ላይ ሳይሆን ደርዝ ያለው ታሪክና ምክንያታዊ የጊዜ ቅደም ተከተልን ከተገቢ ፍጥነት ጋር አለማየታችን ነው። መሣይ የሠርግ ወረቀት እስኪያሳትም ድረስ የሳምራዊት እርግዝና በደንብ ሊለይ አለመቻሉ (በሰውነት ቅርፅ ላይ ማለቴ ነው) ጥያቄ የሚያጭር ጉዳይ ነው።

የፊልሙ ጠንካራ ጐኖች

“ቀሚስ የለበስኩ’ለት” ፊልም የራሱ ድክመቶች እንዳሉበት ሁሉ ሊጠቀሱ የሚገባቸው በርካታ ጥንካሬዎች መኖራቸውን አለመጥቀስ አግባብ አይደለም። የመጀመሪያውና ግልፁ ጉዳይ አዳዲስ ተዋንያንን በስክሪን ማሳየቱ ነው። የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዝዳንትና የስነ-ጽሁፍ ባለሙያዋን ወ/ሮ ሙሉ ሰለሞንን በዚህ ፊልም እንድናይ ተደርገናል። ይህ መልካም ነው። ነገር ግን የተሰጣቸውን ገፀ-ባህሪዋን በብቃት ተወጥተውታል ብሎ ለመናገር የሚያስደፍር አይደለም። ይህ ድክመት የመነጨው ምናልባትም ከታሪኩ ሊሆን ይችላል። እናት ለልጇ ያውም የሀብታም ልጅ አመለጠሽ ብላ ያን ያህል “አይንሽን ላፈር” ማለቷ የሚዋጥ አይደለም።

ሌላው መሳይን ሆኖ የተወነው ይስሃቅ ዘለቀ እና የልዑልን ገፀ-ባህሪይ የተላበሰው ዲበኩሉ ታፈሰ በፊልሙ ልዩ ብቃትና የትወና አቅማቸውን ካሳዩት አዳዲስ ፊቶች መካከል ተጠቃሾች ናቸው። እዚህ’ጋ የአይዳን ገፀ-ባህሪይ የምትጫወተውን ቃልኪዳን ታደሰን መርሳት የማይታሰብ ነው። እነርሱ ብቻ አይደሉም። በሙዚቃው ዓለም ስማቸው የገነነላቸው ድምፃዊት ዘሪቱ ከበደ እና ሄኖክ መሪሪም በፊልም ስክሪን እንድናያቸው መደረጉ መልካም ሆኖ ሳለ ለመራሄ ምስል ባለሙያው ሄኖክ አየለ ብዙ ሰራ ሆነውበት ለዚህ ደረጃ እንዳበቃቸው መገመት ይቻላል።

ፊልሙ ካነሳው ሀሳብ አንፃር ቁም ነገሩን የምንወድለትን ያህል፤ ፊልሙን ፊልም አሰኝተው ያወጡትን የካሜራ፣ የኤዲቲንግ፣ የድምፅና የምስል ቅንብር ባለሙያዎችን ሁሉ ዋጋ በመስጠት “አበጃችሁ” ማለቱ ተገቢ ይሆናል።

     “ቀሚስ የለበስኩ’ለት” በጥቅሉ አንድ ቀን ድንገት በሚከሰት ስህተት መካከል በፍቅርና በውሳኔ፤ በተስፋና በቅራኔ የሚወዛወዝ፤ ነገር ግን ለፈጠረብን ጥያቄ መልሱን ከራሳችን የሚጠብቅ “የቤት ስራ” የሆነ ፊልም ነው!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
17587 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1022 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us