“ገንዘብ ላይ በጣም ደካማ ነኝ”

Wednesday, 15 July 2015 13:39

ተዋናይ ደሳለኝ ኃይሉ

 

ጤዛ፣ ዴዝዴሞና፣ ድብብቆሽ፣ የመሃን ምጥ፣ ሼፉ 2፣ የሞሪያም ምድር፣ ወርቅ በወርቅ፣ የማይታረቁ ቀለማት፣ በራድ ፍም፣ ፍቅርና ገንዘብን ጨምሮ ከ30 በላይ ፊልሞች የተወነባቸው ናቸው። እንደሱ አጠራር “LA” ወይም “ልደታ ኤሪያ” ተወልዶ ያደገው እንግዳችን ለበርካታ ባለሙያዎች ዕውቀቱን በማጋራት የሚታወቅ ባለተሰጥኦና ባለዕውቀት ነው ይሉታል። በአጫጭር ፊልሞቹም የሚታወቀው ይህ ሰው፤ በቴአትር ዘርፍ በተለይም በውጪ ቋንቋዎች በተሰሩት ትሩፋልዲኖ፣ የወጣቱ በርተር ሰቀቀኖች ላይ ሰርቷል። በቲቪ ድራማም አሁን ላይ በ“መለከት” እየታየ ነው። ይህ ተዋናይ ደሳለኝ ኃይሉ ይባላል። አዝናኝ ቆይታችንን እነሆ፡-

ሰንደቅ፡- ስለትወና ያለህ ዕውቀት በምን ላይ የተመሰረተ ነው ከሚለው ብንጀመርስ?

ደሳለኝ፡- ኮስሞስ ኦዲዮ ቪዥዋል ትሬኒግ ኤንድ ሪሰርች የሚባል በውጪ ሀገር በዘርፉ እስከማስተርስ ድግሪ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ምሁራን ያቋቋሙት ት/ቤት ነው የተማርኩት። ሌላው ግን መረሳት የሌለበት ከእነፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ጋር መስራት በራሱ ትልቅ ዕውቀት እንደማግኘት ነው። ምክንያቱም ፊልም ከንድፈ ሃሳብ በላይ ተግባራዊ ነገርን ይፈልጋል። ስለትወና ያለኝ የዳበረ ዕውቀት በአብዛኛው በማንበብና ከባለሙያዎች ጋር አብሮ በመስራት ላይ የተመሰረተ ነው ማለት እችላለሁ።

ሰንደቅ፡- አንዳንድ ሰዎች ስለአንተ ሲናገሩ ያለውን ዕውቀትና ልምድ ያህል ከካሜራ ጀርባ ብዙም አልሰራም ይሉሃል፤ ለምን?

ደሳለኝ፡- በአገራችን የፊልም ስራ በግለሰቦች ላይ የተንጠለጠለ ነው። ካምፓኒዎች የሉም፤ አሁን ድረስ የፊልም ፖሊሲ እንኳን የለንም። ይህ ሁኔታ ባልተመቻቸበት ፊልም መስራት አስቸጋሪ ነው። መጀመሪያ ብዙ መስተካከል ያለባቸው ነገሮች አሉ ብዬ አምናለሁ። በመሆኑም አሁን የኔ ስራ ፊልም ከመስራት ውጪ አስተምራለሁ፤ ፖሊሲ አውጪዎችን አማክራለሁ፤ ከሙያ ማህበራቱ ጋር እሰራለሁ፤ አሁን ደግሞ በቅርቡ የአፍሪካን ሲኒማ በማመላከት “ፌስባኮ” እና የአፍሪካ ህብረት በጥምረት በሚያዘጋጀት ፕሮግራም ላይ ተሳትፌ የሀገራችንን ድምፅ ለማሰማት እሄዳለሁ። ስለዚህ ከካሜራ ጀርባ ብዙ የምስራቸው ስራዎች አለኝ ማለት ነው።

ሰንደቅ፡- ይህ በኬኒያ የሚካሄደው ፕሮግራም አላማው ምንድነው? ለኢትጵያስ ምን ጥቅም ያስገኛል?

ደሳለኝ፡- የአፍሪካ ህብረት በ2015 ይሆናል ብሎ ያስተላለፈው ውሳኔ አለ። በ2003 በተካሄደ የህብረቱ መደበኛ ጉባኤ ላይ “በኦዲዮ ቪዥዋል እና በሲኒማው ኢንዱስትሪ” አካባቢ የአፍሪካ የሲኒማ ኮሚሽን እንዴት መቋቋም ይችላል በሚል የተነሳ ሃሳብ ነበር። በዚህ ስብሰባ ላይ ከኢትዮጵያም የሚወከሉ ባለሙያዎች ሃሳብ እንዲያቀርቡ ሲጋበዝ የኢትዮጵያ ፊልም ስራዎች ማህበር በባህልና ቱሪዝም ቢሮ በኩል ስለደራሲው ቢሮው ያለኝን አስተዋፅኦ አይቶ እኔን ወክሎኛል። ሐምሌ ውስጥ በሚካሄደው በዚህ ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያን ወክዬ ፊልሞች ያላቸውን የልማትና ዕድገት አስተዋፅዖ እንናገራለን። ከዚህም በተጨማሪ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ባለሙያዎች ጋር ልምድ እንለዋወጣለን ማለት ነው።

ሰንደቅ፡- ምናልባት ከወዲሁ የሌሎች አፍሪካ አገራት የፊልም ኢንዱስትሪዎችን የማየት ዕድሉን አግኝተሃልና እኛ ጋር ምን ይቀረናል ብለህ ትቆጫለህ?

ደሳለኝ፡- በጣም ብዙ ነገር ይቀረናል። በተለይ ደግሞ System (ስርዓት) አለመኖሩ ይቆጨኛል። ለዘርፉ የሚሰጠው ድጋፍና ማበረታቻ በሌሎቹ የአፍሪካ አገራት ያስደንቃል። ባይገርምህ ናይጄሪያ ኢኮኖሚዋን ያፈረጠሙት ሶስት ነገሮች ናቸው። አንደኛው ነዳጅ ሲሆን ሁለተኛው የሚጠቀሰው ሲኒማዋ ነው። ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ በፊልም ምክንያት ገንዘብ ይንቀሳቀሳል። ከ400 ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ፈጥሯል። ስለዚህ እኛም ይህን ዘርፍ በአግባቡ ብናለማው ኢኮኖሚውን ከማሳደግ ባሻገር ለብዙ ወጣቶች የስራ ዕድል ሊፈጥር ይችላል ማለት ነው።

ሰንደቅ፡- እንደባለሙያ ካለፉት 10 ዓመታት ወዲህ በርካታ ፌልሞች እየወጡ ነው። ምንም እንኳን ዘውጋቸው ወደ አንድ ጎን ዘንበል ያለ ቢመስልም፤ አንተ እንዴት ነው የምታያቸው? ፊልም ከጀመርንበት ጊዜ አንፃር ሲታይ ጉዟችን ምን ይመስላል?

ደሳለኝ፡- አጀማመርን ካነሳን እኛ ቀደም እንላለን። ፊልም ማየት የጀመርነው በአፄ ምኒልክ ዘመን ነው። አሁን ለምሳሌ ፊልም ብዙ እየተሰራ በሚመስለን ጊዜ እንኳን በሀገር ውስጥ ከ30 የማይሞሉ ሲኒማ ቤቶች ብቻ እንዳሉን ታውቃለህ። ሲኒማ ቤቶች ላይ ፊልሞች አይቆዩም፤ በመሆኑም ተዋንያኑና ፕሮዲዩሰሮቹ የሚገባቸውን ጥቅም እያገኙ አይደለም። ሌላው ደግሞ የዕውቀት ችግር አለብን። የኮፒ ራይትና የፖሊሲው ነገር በቅርቡ ሲስተካከል ነገሮች ይሻሻላሉ የሚል ተስፋ አለኝ። የተቻለንን እየሰራን ቢሆንም፤ ነገር ግን ብዙ እንደሚቀረን አስባለሁ።

ሰንደቅ፡- በዚህ የፊልም ስራ ሂደት ወሳኝ ተሳታፊ በመሆን አንተም ከ30 ያልተናነሱ ፊልሞችን ሰርተሃል፤ለመሆኑ ሳታምንበት ስለተከፈልህ ብቻ የሰራኸው ፊልም አለ?

ደሳለኝ፡- (ሳቅ) እኔ ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ዳይሬክት ከመደረግ ጀምሮ በራሴ ተማሪዎች እስከመዘጋጀት ድረስ ሰርቻለሁ። እዛ ሁሉ ውስጥ ግን እኔ ፊልም ሰርቼ መውጣትን ብቻ አይደለም የማየው። ፊልም እየሰራሁም ቢሆን ስህተት የመሰለኝ ነገር ካለ የማውቀውን ነገር ለማካፈል በጣም ዝግጁ ነኝ። አንዳንድ ጊዜ በድፍረት ፊልም ለመስራት የሚመጡ ሰዎች አሉ። ለውጥ እንዲመጣ እስከተፈለገ ድረስ ከእነርሱም ጋር ቢሆን እየተመካከርኩ መስራት አለብኝ ብዬ አምናለሁ። በነገራችን ላይ አንድ የሚያስቅ ነገር ልንገርህ “ጤዛ” ፊልምን ከፕሮፌሰር ኃይሌ ጋር ከሰራሁ በኋላ ሌሎች ፊልሞችን ለመስራት በጣም ተቸግሬ ነበር። አንዳንድ ጓደኞቼ እንደውም ከጤዛ በኋላ የሰራዋቸውን ፊልሞች ቆጥረው “የደሳለኝ ሙያዊ ዕድገት እንደካሮት ቁልቁል ነው” እያሉ ይተቹኛል። ይህን ስልህ ግን ተስፋ የሚጣልባቸው የፊልም ባለሙያዎች ጨርሶ የሉም ማለቴ አይደለም።

ሰንደቅ፡- ክፍያ ላይ እንዴት ነህ? ውድነህ? የፊልም ፅሁፍስ ትመርጣለህ ወይስ ያመጠሉህን ከከፈሉህ ትሰራለህ?

ደሳለኝ፡- እኔ ገንዘብ ላይ በጣም ደካማ ነኝ። ሁልጊዜ ለፕሮዲዩሰሮች የምናገረው ምንድነው፤ ሰው ህሊና አለው ብዬ አምናለሁ። መጉዳትም፣ መጎዳትም አልፈልግም። ይገባዋል የሚሉኝን ክፍያ ግን እቀበላለሁ። የፊልም ስክሪብቶችን በተመለከተ አንዱ ከአንዱ ብዙም ርቀት የለውም። ምክንያቱም ብዙዎቻችን ለልምድ እንጂ የፊልም አፃፃፍ ገብቶት የሚፅፍ የለም። ለኔ እየሰራሁ ማስተካከልን እመርጣለሁ። አንዳንዱ ደግሞ እኔ የፃፍኩት ብቻ ይሰራ ብሎ ሙጭጭ ሊል ይችላል፤ ወደገበያው ሲመጣ የሚገባውን (የእጁን) ያገኛል።

ሰንደቅ፡- ክፍያን በሚመለከት ትልቁና ትንሹ ክፍያህ ምን ያህል ነው ልዩነታቸው?

ደሳለኝ፡- ባይገርምህ ትልቁ ክፍያዬ 70 ሺህ ብር ነው። ይሄም ብር በአንዴ እጄ አልገባም ተከፋፍሎ ነው። በጣም ትንሹ የሚባለው በጀማሪነቴ ጊዜ ነው፤ በ4500 ብር ዋና ገፀባህሪን ወስጄ ተጫውቻለሁ (ሳቅ)። ፊልሙ በጣም የተወደደ ነበር ርዕሱን አልነግርህም። በአብዛኛው ግን የምሰራው ከ40-60 ባለው ስፋት ውስጥ ነው።

ሰንደቅ፡- ከሰራሃቸው ፊልሞች በተለየ የምታስታውሰው ገፀ-ባህሪይ?

ደሳለኝ፡- ሁሌም የምረሳቸው የማይመስሉኝ ጥቂት ገፀባህሪያት አሉ። አንደኛው የማንያዘዋል እንዳሻው “ዴዝዴሞና” ፈልም ውስጥ ያለው አብርሃምን ሳስበው ለኔ ስብዕና በጣም ቅርብ ይመስለኛል። ሌላው “የመሃን ምጥ” ላይ ያለው ናቲ በጣም ያሳዝነኛል። በነገራችን ላይ በስራዬ ለትወና በጣም የከበደኝ ገፀ-ባህሪይ ይህ ነው። ሌላው ደግሞ ብኖር ብዬ የምመኘው “ወርቅ በወርቅ” ላይ ያለው ላዕከማርያም የተባለው ገጸ-ባህሪይ ይመስለኛል። ይህን ገፀባህሪይ ኑሮዬ እንደዛ ቢሆን ብዬ ስለምመኝ ነው መሰለኝ በጣም እወደዋለሁ። ይህ ማለት ግን ሌሎች ገፀ-ባህሪያት ሳልወዳቸው የሰራዋቸው ናቸው ለማለት ፈልጌ አይደለም። 

ሰንደቅ፡- በተለየ መልኩ አንተ ላይ ተፅዕኖ ያሳደረብህ ገፀ-ባህሪይ የቱ ነው?

ደሳለኝ፡- እውነቱን ለመናገር “ወርቅ በወርቅ” ፊልም ላይ ያለው ላዕከማርያም የተባለው ገፀ-ባህሪይ ውስጤ ያለውን ነገር ይበልጥ እንዳስበው ያደረገኝ ገፀ-ባህሪይ ነው። እኔ ቢሆንልኝ ከአዲስ አበባ ርቄ በገጠር መኖርን እመርጣለሁ። ይህን ነገር በዚህ ገፀ-ባህሪይ በኩል በጣም አይቼዋለሁ።

ሰንደቅ፡- ከምኞትህ ጋር በተያያዘ እስቲ ምን እንደሚያዝናናህ ንገረኝ?

ደሳለኝ፡- በጣም የምዝናናው በደን፣ በሀይቅና በተራሮች አካባቢ ብቻዬን መሆን መንፈሴን በጣም ነው የሚያነቃቃው። ሌላው ከፊልም ማየት ሁሉ በላይ ማንበብ ደስ ይለኛል። የተለያዩ መፅሐፍትን አነባለሁ። ሳልመርጥ ነው የማነበው። የግል ታሪኮች፣ የሀገር ታሪኮችና የሃይማኖት መፅሐፍትን በትኩረት አነባለሁ። ከዚያ ባሻገር ሙያዬን የሚያዳብሩልኝንም እንደዚያው።

ሰንደቅ፡- ከዚህ በኋላ ብሰራው ብለህ የምትመኘው ገፀ-ባህሪይ አለ?

ደሳለኝ፡- በትወና ብቻ ሳይሆን በዳይሬክቲንግም ቢሆን የኛን የቆየ ታሪክ ማሳየት የሚችሉ ስራዎችን ብሰራ በጣም ደስ ይለኛል። ኢትዮጵያ በሀገርም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ብዙ ፊልም መሆን የሚችሉ ታሪኮች አሏት፤ ያንን መስራት ሁሌም እመኛለሁ። ያን ለመስራት ግን በፖሊሲ የሚመራና ሊያሰራ የሚችል የፊልም መሰረተ-ልማት ያስፈልጋል። በእኔ አዲስ መንገድ፤ የድሮው ከፍታችን ነው የሚታየኝ። እኛ’ኮ ትልልቅ ፈላስፋዎች የነበሩን ህዝቦች ነን። አሁን ግን “አትፈላሰፍብኝ ባክህ” የምንል ሰዎች በዝተናል። እኔ ግን የምመኘው የህይወት ፍልስፍናችንን በፊልም ቀይረን በዓመት በርካታ ፊልሞችን በመስራት አፍሪካን ብቻ ሳይሆን አለምን የሚነቀንቁ ፊልሞች ማሳየት ይቻላል ብዬ አምናለሁ። ይህንን ከግብ ለማድረስ ግን መንግስት ለዘርፉ ትኩረት መስጠት አለበት። በርግጥ የተጀመሩ አንዳንድ ተግባራት አሉ መቀጠልም አለባቸው።

ሰንደቅ፡- እስቲ ደግሞ “የመሀን ምጥ” በተሰኘው ፊልም ላይ ስለተጫወትከው ገፀባህሪይ (ናቲ) ትንሽ አጫውተን?

ደሳለኝ፡- በጣም ይገርምሃል። ደራሲው ዳንኤል በየነ ይባላሉ በጣም ጎበዝ ሰው ነው። የባንክ ባለሙያ ቢሆንም ሲፅፍና ዳይሬክት ሲያደርግ ያለው አቅም በጣም የሚደንቅ ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ “ስክሪፕቱን” ሰጥቶኝ ሳነበው “አንተ የዶክተሩን ገጸባህሪይ ትጫወታለህ” ነበር ያለኝ። እኔ ግን ድርሰቱን ሳነበው ናቲ በጣም መሰጠኝ፤ እንደገና ደግሞ የፊልሙ ዋና ማጠንጠኛ ናቲ ነው። ይህ ገፀ ባህሪይ በደንብ ካልተሰራ ፊልሙ ሊበላሽ ይችላል። ስለዚህ ከዳንኤል ጋር በቀጠሮ ስንገናኝ ናቲን ማነው የሚጫወተው? አልኩት። “እሱን የሚሰራውን ሰው ገና አላገኘሁም” አለኝ። ታዲያ እኔ ለምን አልጫወተውም አልኩት፤ ፈቀደልኝ። በነገራችን ላይ መርጬውና ጠይቄ በህይወቴ የሰራሁት “ካራስተር” እሱ ነው። ብዙ ዋጋም ከፍዬበታለሁ። በቀረፃ ወቅት ጀርባዬን ታምሜ፤ ተፈንክቼ፤ ብዙ አጥንቼ የሰራሁት ገፀ-ባህሪይ ነው። ናቲ ብዙ ነገር የሚያሳይ ይመስለኛል። ኢትዮጵያ ውስጥ ብታምንም ባታምንም ለአእምሮ ህመም የተሰጠው ትኩረት በጣም የሚያሳዝን ነው። አንድ ነገር ልንገርህ በሀገራችን ለመኪኖች መጠገኛ የሚሆን በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ጋራዦች አሉ፤ የአእምሮ ጋራዥ የሚሆን ሃኪም ቤት ግን በአንድ እጅ ጣት የሚቆጠር ነው። ፊልሙ ይህን ችግር ፍንትው አድርጎ ያሳያል። ፊልሙን ስሰራው ከገጠመኝ የማልረሳው ነገሩን በጣም አጥንቼ ስለሰራሁት ቀረፃ ሲጀመር አንዳንዴ አብረውኝ የሚሰሩት ባለሙያዎች ድንገት ሲያለቅሱ ይቋረጥ ሁሉ ነበር። “የመሀን ምጥ” ፊልም ለኔ ልዩ ነበር ማለት እችላለሁ።

ሰንደቅ፡- የሚያውቁህ ደሳለኝ ለኮሜዲ ፊልም አይመችም ይሉሃል፤ ኮሜዲ ፊልም ላይ እንዴት ነህ?

ደሳለኝ፡- (ሳቅ) ብችልበት በጣም ደስ ይለኛል። እኛ የልደታ ሰፈር ልጆች ለቀልድ ቅርብ ስለሆነ የሚሰሩት የኮሜዲ ፊልሞች ብዙም አንስቅም። የከተማው ቀልድ ሁሉ ምንጩ ልደታ ይመስለኛል። እኔ አሁን ኮሜዲ የሚባሉት ፊልሞች አያስቁኝም። የምስቀው ከሰፈር ልጆች ጋር ለቅሶ ቤት ምናምን ሰብሰብ ብለን በምንፈትለው ነገር ብቻ ነው።

ሰንደቅ፡- የዝና ዘነዘናን እንዴት ይዘህዋል?

ደሳለኝ፡- በጣም ይገርምሃል ቀለል ያለ ነገር ይመቸኛል። አሁን ለምሳሌ መንገድ ላይ ፈርምልኝ ሲሉኝ በፍፁም አልፈርምም። ብዙ ጊዜ ከሰዎች ጋር በታክሲም በመንገድም እየተጋፉ መሄድ ደስ ይለኛል። ከስራ ውጪ እንደማንኛውም ተራ ሰው ቀለል ያለ ኑሮ ደስ ይለኛል። አንድ ነገር አምናለሁ ዝና፣ ገንዘብና ስልጣን ሲኖርህ ጥበብ ከሌለህ መጥፊያህ ሊሆኑ ይችላሉ። እኔ በጣም ነፃነቴን የምወድ ሰው ነኝ። ትራንስፖርት ታክሲ ስጠቀም ራሱ አንዳንዴ እንደዕጣን ማጨሻ በር ስር ቁጭ ብሎ መሄድ ደስ ይለኛል (ሳቅ)

ሰንደቅ፡- ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናሁ

ደሳለኝ፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ። ቤተሰቦቼን፣ ጓደኞቼን፣ አብረውኝ የሚሰሩ ባለሙያዎችንና አድናቂዎቼን በአጠቃላይ በጣም ነው የማመሰግነው።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
11078 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us