የክቡር ዶክተር አርቲስት ለማ ጉያ አንጸባራቂ ሥራዎች

Wednesday, 22 July 2015 13:31

“ነብይ በሐገሩ አይከበርም፤ ነገር ግን ጊዜው ይቆይ እንጂ በስራው መታወሱ አይቀርም” ይህን የሚሉት የክቡር ዶክተር አርቲስት ለማ ጉያ የረጅም ጊዜ ወዳጅ የሆኑት መምህር መዝገቡ ገ/ህይወት ናቸው። ይህን ምስክርነት ከወዳጃቸው አፍ የሰማነው ባሳለፍነው ቅዳሜ ሐምሌ 11 ቀን 2007 ዓ.ም ደብረዘይት በሚገኘው የክብር ዶክተር ለማ ጉያን የሥነ-ጥበብ ማዕከል በጎበኘንበት ወቅት ነው።

ከሐምሳ ዓመታት በላይ በስዕልና ቅርፃቅርፅ ሙያ በር ዘግተው በመስራት የሚታወቁትና በስራዎቻቸው የሀገርን ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊና፣ መልካምድራዊ አቀማመጥ ከስዕልና በቅርፃቅርፅ ጭምር በማሳየት የሚታወቁት አርቲስት ሻምበል ለማ ጉያ ዘንድሮ ያበረከቱትን የላቀ አስተዋጽኦ ቆጥሮ ጅማ ዩኒቨርስቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ እንካችሁ ብሏቸዋል።

የክብር ዶክትሬትም ለተጨማሪ ስራ እንደሚያነሳሳ የገለፁት የ87 ዓመቱ የዕድሜ ባለፀጋ አርቲስት ለማ ጉያ፤ ተጨዋቾች ከእግር ኳስ አለም ሲሰናበቱ ጫማችንን ሰቅለናል ይላሉ፤ ሰዓሊስ ብሩሹን ይሰቅላል ወይ? የሚል ላነሳንላቸው ጥያቄ ሲመልሱ የሚከተለውን ብለዋል። “እኔ በፍፁም ስዕልን አላቆምም። ይሄ የጉልበት ስራ አይደለም። የአእምሮና የጥበብ ጉዳይ ነው፤ እንደውም አሁን ላይ እየቆየ እንደሚጥም ወይን በጣም ጥሩ ስራ መስራት የምችልበት ዕድሜ ላይ ነኝ። እየሰራሁም ቢሆን ወድቄ እቀራለሁ እንጂ መስራቴን አላቆምም” ብለዋል።

የክብር ዶክተር አርቲስት ለማ ጉያ በብዙዎች ዘንድ አግራሞትና አድናቆት ከሚያስቸራቸው ሁኔታዎች መካከል ከ50 ዓመታት በላይ ለሆነ ጊዜ በሚያቋርጥ የስዕል ስራ በብርታት መቆየታቸው ነው። ለመሆኑ ለዚህ ብርታታቸው ምስጢሩ ምን ይሆን? ብለን ላቀረብንላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፤ “በዚህ በ87 ዓመት ዕድሜዬ ብዙ ነገር አይቻለሁ። ስዕል ደስ የሚለኝና ወድጄው የምሰራው ስራ ነው። በዚህ ላይ ደግሞ በሆነ ባልሆነው አልበሳጭም፤ አልጠጣም፣ አላጨስም። መጠጤ ወተትና ውሃ ነው” የሚሉት አርቲስት ለማ ጉያ፤ ወጣቶችም ስራቸው ላይ በፍቅር እንዲተጉና ጤናቸውን ከሱስ እንዲጠበቁ ይመክራሉ።

“ደስ ያለኝ ቀን ሁለትና ሶስት ስዕሎችን መስራት እችላለሁ። አስመራ በነበርኩበት ጊዜ ብዙ ነጮች ወራት የሚፈጅባቸውን ስራ እኔ በቀናት ውስጥ እየሳልኩ እሸጥ ነበር። የስራ ሁሉ የሚገባውን ያገኛል” የሚሉት አርቲስት ለማ ጉያ፤ “በስራዬ ጨርሼ አልረካም ገና ብዙ ይቀረኛል” ባይ ናቸው።

በስራዬ በእጅጉ ደስተኛ ነኝ የሚሉት አርቲስት ለማ ጉያ፤ የምዝናናው በመሳልና ለስላሳ ሙዚቃዎችን በማድመጥ ነው ይላሉ። ለመሆኑ ዘንድሮ ከበርካታ ዓመታት በኋላ የጅማ ዩኒቨርስቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪውን በ87 ዓመትዎ ስለስጠዎት ዘግይቷል የሚያል ስሜት ይሰማዎታል ወይ የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ሲመልሱ፤ “የዛሬ ሰባት ዓመት የብሔር ብሄረሰቦችን ህብረት የሚያመለክት ስዕል ሰርቼ ነበር። በኋላ በቀድሞው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ስዩም መስፍን በኩል ፓርላማው አንተን መርጦሃል የሚል ደብዳቤ ደረሰኝ፤ እኔም በጣም ጥሩ ለሀገር መስራት እወዳለሁ ነገር ግን አደራችሁን ስብሰባ ውስጥ እንዳትጠሩኝ፤ ስብሰባ በፍጹም አልወድም ብያቸው ተውኝ። በኋላ ስራዬን አይተው የወርቅ ኒሻን ሁሉ ሸልመውኛል። ሽልማት የሚሰሩ ሰዎችን እንደሚያነቃቃ በደንብ አውቃለሁ። በጃንሆይ ጊዜ ታስሬያለሁ፤ በደርግም ጊዜ ታስሬያለሁ አሁን ግን ጊዜውን ጠብቆ ተሸላሚ ሆኛለሁ። አክብረው የክብር ዶክትሬት የሰጡንን በጣም ነው የማመሰግናቸው። እንዲህ መልካም የሚሰሩ ሰዎች በነፍሳቸው እያሉ ቢሸለሙ ይለመልማሉ” ሲሉ አስረድተዋል።

የክብር ዶክተር አርቲስት ለማ ጉያ አብሮ አደግና ወዳጅ የሆኑት መዝገቡ ገ/ህይወት ስለጓደኛቸው ሲናገሩ “ሰው ስለራሱ መናገር አይሆንለትም” ብለው ይጀምራሉ። ለአርቲስት ለማ ጉያ እዚህ ደረጃ መድረስ ሌላም ምስጢር አለ ሲሉ ይቀጥላሉ፤ “ጠዋት ከባለቤትህ ስትለያይ በሰላም ካልወጣህ ውጪ ያለው ነገር ሁሉ አይቀናህም” በምትል ተረት የጀመሩት መምህር መዝገቡ፤ አርቲስት ለማ ጉያ በትዳራቸውም መልካም ስም ያላቸው እንደሆኑና ይህም ለስራቸው ብርታት አስተዋጽኦ እንዳለው ይናገራሉ። ለዚህም በተለየ የአርቲስት ለማ ጉያ ባለቤት የተከበሩ ወ/ሮ አስቴር ለማ በአርቲስቱ ህይወትና ስኬት ውስጥ ሚናቸው ከፍተኛ ነው” ሲሉ ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ።

ሌላውና አስገራሚው በዶክተር አርቲስት ለማ ጉያ ቤተሰብ ውስጥ የተፈጠረው የስዕል ዝንባሌ ነው። የሶስት ሴቶችና የሁለት ወንድ ልጆች አባት የሆኑት አርቲስቱ፤ ሶስቱ ማለትም ዳዊት ለማ ጉያ፤ ነፃነት ለማ ጉያ እና ሰላም ለማ ጉያ ልጆቻቸው የሆኑና በስዕል ስራም ትልቅ ደረጃ የደረሱ ሲሆን፤ ወንድሞቻቸው ቱሉ ጉያና፣ አሰፋ ጉያም የማይናቅ የስዕል ችሎታ እንደነበራቸው ይናገራሉ። ከሁሉም ደግሞ እናቴም በደመነፍስም ቢሆን በቤታችን ውስጥ የስዕል ተሰጥኦን ትገልጽ ነበር ያም በኔ ህይወት ውስጥ በጎ ተፅዕኖ አሳድሮብኛል ይላሉ። “እናቴ ያልተማረች በመሆኗ እዚህ ጋኑን፣ እንስራውን፣ ምጣዱን ስፌቱን እየሰራች ትሸጥ ነበር። ቤትም ውስጥ ግድግዳ ላይ አንዳንድ ስዕሎችን ትሞካክር ነበር። እኔም አመድና ከሰል እየበጠበጥኩ ግድግዳ ላይ መጫር ለመድኩ” የሚሉት የክብር ዶክተር አርቲስት ለማ ጉያ፤ የቅርፃ ቅርፅ ሙያውን በተመለከተ ደግሞ እናቴ ጀበና ስትሰራ እያየሁ በእረኝነት ዘመኔ ከጭቃ ቆንጆ አሸንጉሊት እሰራ ነበር ሲሉ የሚያዝናና ትውስታቸውን አጫውተውናል። በዘመኑ የህጻኑ ለማን አእምሮ ብሩህነት የተመለከቱ ሰዎች አባታቸውን ወደትምህርት ቤት እንዲልኳቸው በመወትወታቸው ምክንያት፤ “በአስራ ሰባት አመቴ ሞፈርና ቀንበር ሰቅዬ ወደትምህርት ቤት ለመግባት ችያለሁ” ይላሉ።

   በስዕልና ቅርጻቅርፅ (በሥነ-ጥበብ) ዘርፍ የተሻለ አቅም ያላቸውና የ87 ዓመት እድሜ ባለጸጋ የሆኑት የክብር ዶክተር አርቲስት ለማ ጉያ፤ በስራዎቻቸው ውስጥ በአብዛኛው እውነታዊነት የሚንፀባርቅ ሲሆን ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ህብረብሔራዊ ስራዎች በጉልህ ይታያሉ። ከዚህም በኋላ ብዙ መስራት እንደሚፈልጉ የሚናገሩት አርቲስቱ፤ “ገና በአለም አቀፍ ደረጃ የሚጠራ ስራን አሳያችኋለሁ ባይ” ናቸው። እኛም ለክብር ዶክተር አርቲስት ለማ ጉያ ረጅም እድሜ ጤንነትና የውጤት ዓመታትን በመመኘት እጅ ነስተን ተሰነባበትን።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
15514 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us