ሽሽት የበዛበት “አብስትራክት”

Wednesday, 29 July 2015 17:26

ይህ ፊልም የደራሲው ስምንተኛ ፊልም ነው። ደራሲ ደመረ ፅጌ ከዚህ ቀደም፤ ጉዲፈቻ፣ ንጉስ ናሁሰናይ፣ ስደት፣ የነቀዘች ህይወት፣ ስውር ችሎት፣ ስጋ ያጣ መንፈስ እና ፍሬ ህይወት የተሰኙ ሰባት ፊልሞችን ለተመልካች አድርሷል። እነሆ ስምንተኛ ፊልሙን በቅርቡ “አብስትራክት” ሲል ፅፎ በማዘጋጀት አቅርቦ ለሲኒማ ታዳሚው በመታየት ላይ ነው።

“አብስትራክት” ፊልም በዘመነ ፊልም ፕሮዳክሽን ተሰርቶ ለእይታ የቀረበ የድራማ ዘውግ ያለው የቤተሰብ ፊልም ነው። በአጉል በዓል ሰበብ በባሏ የተካደች ሚስት፤ ልጇ በወንድ ጓደኛዋ የምትጠረጥራት እናት፤ ኑሮ ያልሞላላትና አጋጣሚዎች ፊቷን የለወጧት ሴት ናት ጥሩዬ (ኤልሳቤት መላኩ)፣ የፊልሙም “አብስትራክት” መልኩና የታሪኩ ሸክም የወደቀው ከሰዓሊው ስራ በላይ በዚህች ሴት ፊትና ህይወት ውስጥ ነው።

የነጋዴ ጭንቅላት ያለው አባት፤ ልጁን ለወዳጁ ልጅ ለመዳር የሚታትር አባት፤ በኢትዮጵያ ይበጃታል የተባለ ኢንጂነር ከእንግሊዝ ድረስ አስመጥቶ ለራሱ ጥቅም የሚራወጥ ስብእናው የገረጀፈ ሰው ነው።

እናቷን በልጅነቷ አጥታ ከአባቷ ጋር ያደገችው ሮማን (ቃል ኪዳን ተስፋዬ) እሩቅ የሚመስላትን ፍቅር ቤታቸው እንግዳ ሆኖ ከመጣው ኢንጂነርና ሰዓሊ ያም ቢሆን ቅናት አቅሏን ሲያሳጣት የምናይበት ፊልም ነው፤ “አብስትራክት” የሚገርመው ሰዓሊው ኢንጂነርም እናቱን ገና በለጋ የህፃንነት ዕድሜው አጥቶ በማደጎ ያደገ መሆኑ ነው።

የሰዎች ምስጢር፤ ክፋት፣ ፍቅርና ቅናት፤ ማግኘትና ማጣት ሁሉ በተደበላለቀ የሽሽት ስሜት ውስጥ ይፋ የሚወጣበት ፊልም ነው፤ “አብስትራክት”። ፊልሙ እውነትንና ክስተትን በእጅጉ የሚሸሹ የታሪክ ባለቤቶችን አሳይቶናል። ከክፉ ትዝታቸው፤ ከሚናፍቁት ማንነታቸው፤ መጋፈጥ ከሚገባቸው እውነታ ሁሉ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ሽሽት የገጠሙ ገፀባህሪያት ሞልተውታል።

“እኔ በተፈጥሮዬ ችኮ ነኝ” የምትለው ሮማን እንደአሽከር ከፍ ዝቅ ልታደርጋት የቤት ሰራተኛዋ ጥሩዬ ጋር ሲላት ምስጢር ለማውራት ስትሞክር፤ ሲላት እንደመቆጣት ሲቃጣት ይባስም ብሎ ከሰዓሊ ኢንጂነሩ ጋር በፍቅር ወድቃለች እስከማለት በሃሳቧ ስትባክን እናያለን። ይህ አዲስ የግጭት ስልት ሆኖ በፊልሙ ይከሰታል።

ሌላው በፊልም ውስጥ የሚነሳው ስውር ሽሽት ከአሜሪካን ድረስ ለሮማን የፍቅር ጥያቄውን ለማቅረብ የመጣው አፍቃሪ አንድም ቀን በሚገባ ስሜቱን ሳይነግራት፤ ከአባቷ ጋር ግን የጓደኛ ያህል ሲያወሩ ስናይ አዘጋጁ ለሰዓሊ ኢንጂነሩ ልጅቷን እያቆየለት ይሆን? እንድንል ያስገድደናል።

በሌላም በኩል ኢትዮጵያ ድረስ ተጋብዞ የመጣው የእንግሊዙ ተመራማሪ ኢንጂነር አንድም ከመጣበት ጉዳይ ጋር የሚገናኝ ስራ ሲሰራ ሳናየው በስዕልና በፍቅሩ ተተብትቦ ሲቀር እንታዘጋለን። የገፀ-ባህሪው ገፅታና ስነልቦናዊ ግዝፈትም ከተዋናዩ ጋር አብሮ መሄድ አልቻለም።

“ተንኮል ቦታ አይመርጥም ጊዜን እንጂ” የምትለው እትዬ ጥሩዬ (ኤልሳቤጥ መላኩ) ለበርካታ ጊዜያት ሸሽጋ የኖረችውን፤ ምስጢር የምታፈነዳው እንደ “ሰው” ለሚቆጥሩትና ለሚያከብ ሰው (ሰዓሊና ኢንጂነሩ) ነው። በሰዓሊና ኢንጂነሩ በኩል የተፈታው የቤተሰቡ የምስጢር ቋጠሮ መጨረሻው የአብስትራክቱን ሙሉ ምስል ያሳየናል።

በፊልሙ ውስጥ እንደመልካም የሚጠቀሱት፤ አዳዲስ የትወና ፊቶችን ከአንጋፎች ጋር አጣምሮ ያመጣበት መንገድ አንዱ ነው። ሌላው ደግሞ አንድም ጊዜ ቢሆን በምልሰት ታሪኩ በድርጊት የተተረከበት ሂደት እጅግ የሚያምር ነበር። የብርሃንና የድምፅ አመጣጠን ላይም የጎላ የኤዲቲንግ ክፍተት አልታየም ማት ይቻላል።

በጉልህ ከሚጠቀሰው የፊልሙ ግድፈት መካከል ግን በዋናነት ሜካፕ ነው። የፊልሙ ልዩነት የሚታየውም ሆነ ጥፋቱ የሚጎላው በዚህ መስክ ይመስላል። በፈነዳ ሲሊንደር ሳቢያ በግማሽ ፊቷ ላይ ክፉ ጠባሳ የቀረላት ጥሩዬ (ኤልሳቤጥ መላኩ) በሜካፕ የኮንቲኒቲ ስህተት ምክንያት በተደጋጋሚ ጊዜ ቅርፁን ሲያጣ እንመለከታለን። ሲለው አፏ ይገጥማል፤ ሲለው ደግሞ በከፊል ይከፈታል። ይህ ፊልሙን በትኩረት ለሚመለከተው ተመልካች ጉልህ ስህተት ሊሆን ይችላል።

በተረፈ ግን ድፍረት የጎደላቸው፤ በስጋትና በፀፀት፣ በፍቅርና በቅናት፣ በተስፋና በትዝታ የሚዳክሩና ሽሽት የሚያደክማቸው ባለታሪኮችን የያዘው “አብስትራክት” ፊልም ተመልካችን በፍርድ ችሎት እንደተቀመጠ ዳኛ ለውሳኔ የሚያስቸግር ሆኖ አግኝቼዋለሁ። እስቲ እናንተም አይታችሁ ፍረዱ። መልካም መዝናኛ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
15489 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us