የንባብ ለህይወት “አምባሳደሮች”

Wednesday, 05 August 2015 14:05

 

ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የንባብን ነገር ጉዳዬ ያለው “ንባብ ለህይወት” የመፅሐፍት አውደ-ርዕይ ባሳለፍነው ሳምንት ከሐምሌ 23 እስከ 26 ቀን 2007 ዓ.ም በአዲስ አበባ ኤግዚቪሽን ማዕከል በማስተር ፊልም ፕሮዳክሽን ፊታውራሪነት ተከናውኗል። ፕሮግራሙ በርካታ የተለየባቸው ክንውኖችን አካቶ የተጠናቀቀ ቢሆንም ለዛሬ ግን በመክፈቻው ዕለት በመድረክ የተሰየሙትን አስራ ሁለት ዕውቅ ኢትዮጵያውያንና የንብባ አምባሳደሮች እነሆ፤ ለዕለቱ በመድረኩ በክብር እንግድነት ከተጋበዙት ደራሲን መካከል፤ የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ዘንድሮ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ይገባቸዋል ሲል አድናቆቱንና አክብሮቱን የገለፁላቸው የክቡር ዶክተር ደራሲና ተርጓሚ ሳህለስላሴ ብርሃነማርያም ነበሩ። አምባሳደሮቹም የኃላፊነት ምስክር ወረቀታቸውን የተቀበሉት ከእኚሁ ድንቅ ኢትዮጵያዊ ፀሐፊና ተርጓሚ እጅ ነው።

·        ኬሚካል ኢንጂነሩ ጌታሁን ኤራሞ

የቀለማትን አይነትና ባሪያት በጥልቀት የተመራመሩ ባለሙያ ናቸው። ከዚህ ትምህርታቸው ባሻገር “አንቱ” የተባሉ አንባቢ ስለመሆናቸው ምስክሮቻቸው ይበዛሉ። እርሳቸውም፣ “ውሎና አዳሬ “አማዞን ነው” ይላሉ። (አማዞን ዶ ኮም አለማቀፍ የኦን ላይን ቤተመፅሐፍት እንደሆነም ይታወቃል) እናም እኚህ ሰው በዚህ ትውልድ ላይ የንባብ አምባሳደር በመሆን ተሹመዋል። ንባብን በይበልጥ ለትውልዱ ለማስተዋወቅም በመድረኩ ላይ ቃል ገብተዋል።

·        ደራሲና ጋዜጠኛ ዓለማየሁ ገላጋይ

አጥቢያ፣ ኩርቢት፣ የብርሃን ፈለጎች፣ ወሪሳ፣ መልከዓ ስብሃት (በአርታኢነት) እና ሌሎችም መፅሐፍትን ለንባብ ያበረከተ ደራሲ ነው። ይህ ሰው በተለያዩ መፅሔቶችና ጋዜጦችም ላይ በሚያስነብባቸው ፅሑፎች ይታወቃል። “ንባብ ለህይወት” የ2008 ዓ.ም የንባብ አምባሳደር ሁነኝ ብሎ በሾመው መድረክ ላይ የሚከተለውን ዋዘኛ ንግግር ተናግሮም ነበር፣ “እንደቻይናዎቹ ባይሆንም የባህል አብዮት እንደሚያስፈልገን አስባለሁ። ለምሳሌ ከዚህ በኋላ አራስ ስንጠይቅ የሁለት ብር ቅቤ ይዞ ከመሄድ የ12 ብር መፅሐፍ ብንወስድ፤ የታመመ ስንጠይቅ ከፍትፍት ይልቅ መፅሐፍ፤ ለቅሶ ስንደርስ እዝን ይዘን ስንሄድ ሀዘንተኛው ሲረጋጋ የሚያነበው መፅሐፍ ይዘን ብንሔድ መልካም ነው። ከዚህ ሁሉ በላይ ግን ለምሩቃን ድግስ መፅሐፍትን መስጠት ሲገባን ሙዝና ብርቱካን ይዞ መሔድ ተገቢ ነው?” ሲል በስላቅ ጠይቆ ታዳሚውን ፈገግ አሰኝቷል።

·        አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ጋር በተያያዘ ስማቸው ተደጋግሞ የሚነሳ አሰልጣኝ ናቸው። ከበርካታ ወጣት ተጫዋቾች ጋር ይውላሉና ወጣቶችን ለንባብ ለማነሳሳት ቅርብ ናቸው በሚል የ2008 የንባብ ለህይወት አምባሳደር ሆነው ተሾመዋል። “በህይወቴ ከተጠራሁባቸው መድረኮች ሁሉ እንደዚህ አይነት የበለጠ ምሁራን ባሉበት በመገኘቴ የተሰማኝን ኩራት እየገለፅኩ፤ ህይወቴን በሙሉ ያሳለፍኩት ከወጣቶች ጋር ስለሆነ ወጣቶችን እንዲያነቡ እጋብዛሁ።  ይህንንም ኃላፊነት በትክክል ለመወጣት ቃል እገባለሁ” ብለዋል።

·        ደራሲና ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ

በዘጋቢ ፊልም ስራዎቹ፣ በአጫጭር ልቦለድ ስራዎቹና የፈላስፎች ጉባኤና የተለያዩ ደራሲያን ስራዎችን በማሳተም ይታወቃል፡፡ በተለይም “ህይወቴ” የተሰኘውን የተመስገን ገብሬ መፅሐፍ በአርታኢነትና በማዘጋጀት ሰርቷል። ከበርካታ ተግባራት ጀርባ ያለ ሰው ነው። በተለያዩ መፅሔቶችና ጋዜጦችም (በሰንደቅ ጋዜጣ በቋሚ አምደኝነት ኪነጥበብና ባህልን”) የሚያስተዋውቁ ስራዎችን በመስራት ይታወቃል። ደራሲና ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ የንባብ ለህይወት የ2008 ዓ.ም አምባሳደር ሆኖ ተሹሟል። “ማንበብ ሰውን ከእንስሳት በእጅጉ የሚለየው ጥበብ ነው” አፅንኦት የሰጠበት የመድረክ መልዕክቱ ነበር።

·        አቶ ታደሰ ጥላሁን፤ የናሽናል ኦይል ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ

በስራ አመራር ክህሎታቸው ይታወቃሉ። ላለፉት 40 ዓመታት በተለያዩ የሥራ መስኮች በኃላፊነት አገልግለዋል። የንባብ ባህልን ለማዳበር በመትጋትና ፕሮግራሙንም በመደገፍ ያበረከቱት አስተዋፅኦ ቀላል አለመሆኑ ከመድረኩ የምስክርነት ቃል ተችሯቸዋል። የናሽናል ኦይል ኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅና ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ታደሰ ጥላሁን የ2008 ዓ.ም የንባብ ለህይወት አምባሳደር ሆነው ተሹመዋል። የፕሮግራሙን አዘጋጆች ያመሰገኑት አቶ ታደሰ፣ “ትውልድና ሀገር የሚገነባው በንባብ ነው። ከራሱ ያልተጣላ ሰው ማለት ያነበበ ሰው ነው። ለዚህ ሹመት ያለኝን አክብሮት በመግለፅ እስከመጨረሻው ድረስ ኃላፊነቴን ለመወጣት አብሬያችሁ እንደምሰራ አረጋግጣለሁ” ብለዋል።

·        ተዋናይ ግሩም ኤርሚያስ

በ1990ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ የኢትዮጵያ ፊልም ማነቃቃት ሲጀምር የተከሰተ ድንቅ ተዋናይ ነው። በስርየት፣ ትዝታህ፣ 400 ፍቅር፣ ላምባ፣ ይሉኝታህ፣ 862 እና ፅኑ ቃል የተሰኙ ፊልሞችን ጨምሮ ከ14 ያላነሱ ፊልሞች ሰርቷል። አራት ጊዜ የፊልም ሽልማት አሸናፊ ሆኗል። ይህ ተዋናይ ከአንባቢነቱ በዘለለ ፀሐፊነቱንም ያሳየበት “መሰረታዊ የትወና መማሪያ” የተሰኘ ትርጉም መፅሐፍም አበርክቷል። ተዋናይ ግሩም ኤርሚያስ የ2008 ዓ.ም የንባብ ለህይወት አምባሳደር ሆኖ ሲሾም፣ “የንባብ አምባሳደር ሆኖ መሾም ለኔ ትልቅ ቅድስና ነው፤ አብረንም እንሰራለን” ብሏል።

·        የበርካታ ቤተመፅሐፍት መስራቿ ወ/ሮ ማህሌት ኃ/ማርያም

ከ97 ያላነሱ ቤተ-መጽሐፍትን በተለያዩ ክልሎች ገንብታ ወጣቶችና ታዳጊዎች የንባብ ልምዳቸውን እንዲያዳብሩ የሰራች ግለሰብ ነች። የ2008 ዓ.ም የንባብ ለህይወት አምባሳደር ሆና ካባዋን ስትለብስ፣ “ከትላልቅ ሰዎች ጎን እኔንም አምባሳደር አድርጋችሁ ስለሾማችሁኝ አመሰግናለሁ። የበለጠም እንድስራ ያደርገኛል” ብላ ነበር።

·        ፕሮፌሰር ዓለምፀሐይ መኮንን

በኬኒያ ከሚገኝ አግሮፎረስተሪ ተቋም ለፈፀሙት መልካም የመሪነት ተግባር በ2015 ተሸላሚ ሆነዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በ2009 ዓ.ም የወርቅ ተሸላሚ ሆነዋል። በጀርመን ሀገርም እንዲሁ በተደጋጋሚ ጊዜ ለሰሩት ስራ እውቅናን የሚሰጥ ሽልማት አግኝተዋል። በበርካታ ዓለምአቀፍ የምርምር መፅሔቶች ላይ ሀሳባቸው አስፍረዋል። እኚህ ትጉህ ተመራማሪ፤ በሀገራችን ብቸኛዋ ሙሉ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ የተሰጣቸው ፕሮፌሰር የዓለምፀሐይ መኮንን የ2008 ዓ.ም የንባብ ለህይወት አምባሳደር አድርጎ ሾሟታል። “እንደመምህርነቴ ወጣቶች በንባብ እንዲተጉ እመክራለሁ” ሲሉ ቃል ገብተዋል።

·        ድምጻዊ አለማየሁ እሸቴ

ለዘመናት ስለትምህርት ሲነሳ፣ “ተማር ልጄ” የተሰኘው ዘፈኑ ይታወቃል። ለንባብ ያለውን ትኩረትና በጎ ፈቃደኝነት ተመልክቶ ንባብ ለህይወት የ2008 ዓ.ም የክብር አምባሳደር አድርጎ ሾሞታል። በዕለቱ በአዳራሹ በአጋጠመው የጤና እክል ምክንያት አይገኝ እንጂ የፕሮግራሙ ዓላማ ደጋፊ በመሆኑ የንባብ አምባሳደርነት ክብር ተሰጥቶታል።

·        ወ/ሮ የትነበርሽ ንጉሴ

በንግግር አቅሟ በይበልጥ ትታወቃለች። በሴቶችና በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ በትጋት የምትንቀሳቀስና በንባብም ራሷን ለትልቅ ደረጃ ያበቃች ሴት ናት። ወ/ሮ የትነበርሽ ንጉሴ፣ “በእኔ እምነት ማንም በምንም አይነት ሁኔታ ውስጥ ቢሆን መፅሐፍትን ማንበብ ይገባዋል። እኔ የልጆች እናት ነኝ፤ እባካችሁ ለልጆች መጫወቻ ሽጉጥ ሳይሆን መፅሐፍትን ስጡ” ጎልቶ የተሰማ የመድረክ መልዕክቷ ነበር።

·        ደራሲና ገጣሚ በዕውቀቱ ስዩም

በርካታ አጫጭር ልቦለዶችን ፅፏል። በወጎቹ ጥሩ ታዛቢ መሆኑንም እያዋዛ ይነግረናል።  መግባትና መውጣት፣ እንቅልፍን ዕድሜ  (ቤሳ ልቦለዶቹ ናቸው) ስብስብ ግጥሞቹ ተነበውለታል። አቅሙ ከስራው በላይ እንደሆነ የሚታመንበት ይህ ወጣት ደራሲና ገጣሚ በዕውቀቱ ስዩም፣ የ2008 ዓ.ም የንባብ አምባሳደር ሆኖ ተሹሟል። “በልጅነቴ አንድ ህልም ነበረኝ። ሳድግ በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር እሆናለሁ ብዬ ነበር። ይህውና እሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ ሆኜ የንባብ አምባሳደር ሆኛለሁ ለማንኛውም ደሞዙ አልተነገረንም” ሲል በአዳራሽ የሚገኘውን ሰው ሁሉ ፈገግ አሰኝቷል። አክሎም “ቀደም ሲል ደራሲና ጋዜጠኛ ዓለማየሁ ገላጋይ እንዳለው አንድ ሰው ሲታመም በምግብ ፋንታ መፅሐፍ ይዘንለት እንሂድ ብሏል። እኔ ከታመምኩ ወይም አዝኜ ልታፅናኑኝ ከመጣችሁ ግን መፅሐፍና በውስጡም አንድ አምስት መቶ ብሮች አኑሩበት” በሚል ንግግሩ ሳቅ በአዳራሽ ያፈነዳ ሲሆን፤ ሁለቱም አስፈላጊ ናቸው ምግብና ገንዘብ አንድ ላይ ቢኖሩን መልካም ነው። ማንም ሰው የኔን መፅሐፍ እያፋሸከ እንዲያነብ አልፈልግም” በማለት የአምባሳደርነት ሹመቱን በተቀበለበት ወቅተ ተናግሯል።

·        ረዳት ፕሮፌሰር በቀለ መኮንን

መምህር ነው፣ ትጉህ የሥነ-ጥበብ ባለሙያም ጭምር፤ በአውሮፓ፣ በአሜሪካ፣ በአፍሪካና በኢትዮጵያም ጭምር ከትላልቅ ሰዓሊያን ጋር ስራዎቹን ያሳየ ሰው ነው። የኢትዮጵያ ፊልም ዕድገት ውስጥ እምርታ እንዲመጣ የትምህርት ተቋም ያስፈልጋል ከሚሉ ሞጋቾች ጎን ተሰልፎ የተሳካለትም ሰው ነው። ይህ ሰዓሊና ቀራፂ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሥነ-ጥበብ ትምህርት ቤት መምህር ነው፤ ረዳት ፕሮፌሰር በቀለ መኮንን የ2008 ዓም የንባብ ለህይወት አምባሳደር ሆኖ ተሾሟል።

ይህ ፕሮግራም በቋሚነት፤ ጎን ለጎን ደግሞ በየዓመቱና ዓመቱን ሙሉ የሚቀጥል እንደሆነ አዘጋጆቹ ያስታወቁ ሲሆን፤ በቀጣይም በተለያዩ ቦታዎች መሰል ፕሮግራሞች ይሰናዳሉ ብለዋል።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
15691 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us