“ሥዕል መዝናኛዬም ጭምር ነው”

Wednesday, 12 August 2015 12:16

አርቲስት (ሰዓሊ) ነፃነት ለማ ጉያ


ከሳምንታት በፊት በኦሮሞ የባህል ማዕከል የአባትና ልጅ የሥዕል አውደ-ርዕይ ተከፍቶ ነበር። ይህ “Father & Daughter” የተሰኘ መጠሪያ የተሰጠው የሥዕል አውደ-ርዕይ በአንጋፋው ሰዓሊ የክቡር ዶክተር አርቲስት ለማ ጉያ እና የልጃቸው የነፃነት ለማ ጉያ ስራዎች የቀረቡበት ነበር። በፕሮግራሙ ላይ የክብር እንግዳ ሆነው የተገኙት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ አሚን አብዱልቃድር ናቸው። ሚኒስትሩ አውደ ርዕይውን መርቀው በከፈቱበት ወቅት እንደተናገሩት፤ አባትና ልጅ በዚህ ደረጃ በጥምረት ስራዎቻቸውን ማሳየት መቻላቸው አስደሳች አጋጣሚ መሆኑን አስታውቀው፤ “የሥዕል ጥበብ የአገር ጎብኚዎችን ከመሳብም ባሻገር አንድን ሀገር ባህልና ስልጣኔም ለማስተዋወቅ ከፍተኛ ድርሻ አለው” ብለዋል።

ወጣቷ ሰዓሊ ነፃነት ለማ ጉያ በአውደ-ርዕይው ወደ 45 የሚደርሱ የሥዕል ሥራዎቿን ማቅረቧን አስታውቃ፣ “የስራዎቼ ትኩረት ህብረተሰቡ ነው። ማህበራዊ ችግሮች ትኩረት የሚያስፈልጋቸው የበሽታ አይነቶችን እና የሴት ልጆች ብርታት የስዕሎቼ ማዕከላት ናቸው” ስትል ገልጻለች።

በሥዕል አውደ ርዕይው የቀረቡት ስራዎቿ ተሰርተው ለመጠናቀቅ ከ1999 ዓ.ም እስከ አሁን ድረስ የፈጁ ሲሆን፤ ስራዎቹ ደቡብ አፍሪካ አሜሪካና አውሮፓን ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ስም ያላቸው አውደ-ርዕይዎችም ለዕይታ የቀረቡ መሆናቸውን ታስረዳለች። በስራዎችሽ ውስጥ ሴትነትና እርቃን ምስሎች ጎልተው ይወጣሉ፤ ምንን ለማሳየት ፈልገሽ ነው? በሚል ለቀረበላት ጥያቄ ሰዓሊዋ ስትመልስ፣ “ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየታዘብኩት የመጣሁት አንድ ነገር አለ። ሴቶች በብዛት ችግር ውስጥ እያሉ ታግለው ሲወጡ አይታዩም። ደቡብ አፍሪካ በነበርኩበት ጊዜ በርካታ በኤች አይ ቪ /ኤድስ/ የተጠቁ ሴቶች ቢኖሩም ውስጣቸውን መግለፅ ሲቸገሩ አስተውል ነበር። በሽታ አለብህ ማለት የመጨረሻ አይደለም። ይልቅም በሽታችንን በይፋ ተናግረን መድሃኒቱን መፈለግ ይገባናል። ሴቶች በሚጨቆኑበት ትዳር ውስጥ መቆየት አለባቸው ብዬም አላምንም። እነዚህን ነገሮች ለመግለፅ ነው በስዕሎቼ ውስጥ ትኩረቴን ሴቶች ላይ ያደረኩት” ባይ ነች።

ሰዓሊ ነፃነት ለማ ጉያ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሥነ-ጥበባት ትምህርት ቤት ትምህርቷን የተከታተለች ሲሆን፤ በውጪ ሀገርም ከሥዕል ሙያው በተጨማሪ የሥነ-ልቦና (Psychology) ትምህርትን ተከታትላ እንዳጠናቀቀች ትናገራለች። ለመሆኑ ሥዕል እና ሥነ-ልቦና ምንና ምን ናቸው? “ስራዬ አማካሪነት ነው፤ በተለይም “አርት ቴራፒ” ላይ አተኩሬ እየሰራሁ ነው” የምትለው ነፃነት ሥዕል ለሰው ልጆች መንፈስ ከሙዚቃ ያልተናነሰ የአዳሽነት ሚና አለው ባይ ነች።

ወደሌላ የስራ መስክ መጠጋቷ ምናልባትም ሥዕል ለኑሮ አይሆንም የሚሉ አስተያየቶችን የሚያጠናክር ይሆን ወይ በሚል ለቀረበላት ጥያቄ ሰዓሊዋ ስትመልስ፣ “ኢትዮጵያ ውስጥ ሥዕል ያኖራል ወይም አያኖርም ብሎ በርግጠኝነት መደምደም ይቸግረኛል። ነገር ግን አባቴ ደግሞ ዕድሜውን ሙሉ እንደኖረበት መረሳት የለበትም” ስትል ምሳሌ ትጠቅሳለች።

በተለያዩ ምክንያቶች ሥዕልን ለመስራት ስቱዲዮዋን እንደምትዘጋ የምትናገረው ሰዓሊ ነፃነት፤ በተለየ ግን ሀዘን ሲሰማኝ ለሥዕል ስራዬ እነሳሳለሁ ትላለች። “መከፋት በጣም ያነቃቃኛል፤ ደስ ሲለኝ እንደውም ሥዕል መስራት አልችልም” ባይ ናት።

የአባቷ የክብር ዶክተር አርቲስት ለማ ጉያ የሥዕል ስራዎች “እውነታዊነት” (Realistic) ሆነው ሳለ፤ እርሷ “አብስትራክት” የተሰኘውን የአሳሳል ዘውግ መከተሏ ከአባቷ ተጽዕኖ ነፃ መውጣቷን የሚያሳይ ነው ወይ? የሚል ጥያቄ ያቀረብንላት ሲሆን በመልሷም፣ “አልፎ አልፎም ቢሆን አባቴ ይናገረኛል “ምንድነው የምትሰሪው” ሁሉ የሚለኝ ጊዜ አለ። እኔ ግን የራሴን ዘይቤና ቀለም ፈጥሬያለሁ ብዬ አስባለሁ። አሁን ግን እየገባው ስለመጣ እንደአንድ ዘውግ ይሁን ብሎ ተቀብሎ ትቶኛል” ስትል በእርሷና በአባቷ መካከል ያለውን የአሳሳል ልዩነት ታስረዳለች።

በአውደ ርዕይው በርካታ ሰዎች የእርሷን ስራዎች ለመጎብኘትና ለመዝናናት በመምጣታቸው ደስታ እንደሚሰማት የምትናገረው ሰዓሊ ነፃነት ለማ ጉያ፤ ከስራዋ ውጪ መዝናኛዋ ምን እንደሆነም ጠይቀናት ነበር። “ሥዕል ስራ ለኔ እንደመዝናኛም ጭምር ነው። ነገር ግን ብቻዬን ሆኜ ሙዚቃ ሳዳምጥና ከእንስሳት ጋር አብሬ ስሆን በጣም ደስ ይለኛል” ስትል መንፈሷ ታድሶ ለስራ ስለምትነቃቃበት መንገድ ታስረዳለች።

የተለያየ ቀለምና መልዕክት ያላቸውን ስራዎች በኦሮሚያ ባህል ማዕከል ከአባቷ ከክብር ዶክተር ለማ ጉያ ጋር ለዕይታ ያበቃችው ወጣቷ ሰዓሊ ነፃነት ለማ ጉያ፤ በቀጣይም በመሰል አውደ-ርዕይዎች ሌሎች ያልታዩና አዳዲስ ስራዎቿን ይዛ እንደምትቀርብ ከወዲሁ ቃል ገብታለች።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
11250 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us