የተጋረደው “ምስለ- መንግስቱ”

Wednesday, 19 August 2015 12:30

ካሳንቺስ ተወልዶ ያደገ የኪነ-ጥበብ ባለሙያ ነው። ብዙዎች ከቀድሞው የኢትዮጵያ መሪ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃ/ማርያም ጋር በመመሳሰሉና በተደጋጋሚ ጊዜም በትወናው በማስመስከሩ ያደንቁታል። ወደጥበቡ ዓለም ሲመጣ ከቀበሌ ኪነት ተነስቶ እስከ ጦር ሰራዊቱ ድረስ በድምፃዊነት የሰራ ሲሆን፤ በመሪነት ቴአትርን አንድ ብሎ የጀመረው በ “አዳብና” ነው። በመቀጠልም “ወይ አዲስ አበባ” የተሰኘውንና ለአንድ ቀን ብቻ ታይቶ በቀረው የጌትነት እንየው ቴአትር ላይ ያሳየው የመንግስቱ ኃይለማርያም ገፀ-ባህሪይ በእጅጉ ተወዶ ነበር። ሲቀጥል ግን አርቲስት ሙሉዓልም ታደሰ አዘጋጅታ ፕሮዲዩስ ባደረገችው “አቦጊዳ” ፊልም ላይ ጎልቶ ታይቷል። ከዚያም “አጋአዚ ኦፕሬሽን” እና “የ15 ደቂቃ ኦፕሬሽን” ፊልሞች ላይ ታይቷል፡፡ የዛሬው እንግዳችን አርቲስት ዝናቡ ገ/ስላሴ ሲሆን፤ መሰረቱ ድምፃዊነት ይሁን እንጂ በተደጋጋሚ የሰራባቸው ፊልሞችና ቴአትሮችም የትወና ብቃቱን አሳይቷል።

ሰንደቅ፡- ወደብሔራዊ ቴአትር መቼና እንዴት መጣህ?

ዝናቡ፡- በጣም የሚገርም አጋጣሚ ነው። ማስታወቂያ ወጥቶ ብዙ ሰዎች ሲመዘገቡ እስቲ ልየው ብዬ ያን ያህል ጉጉት ሳይኖረኝ ነው የተመዘገብኩት። ሲጀምር እኔ ድምፃዊ ነኝ። በብሔራዊ ቴአትር አሁን ድረስ በዘመናዊ ድምፅ መደብ ነው የምሰራው። ስንወዳደር 45 ሰዎች ነበር፤ 1991 ዓ.ም ነው። ያሸነፍኩበትን የቀጠሮ ቀን ረስቼው ሁሉ ከእንቅልፌ ተነስቼ ነው አልፌ እዚህ የደረስኩት (ሳቅ)።

ሰንደቅ፡- የእነማንን ስራዎች ነው የምታቀነቅነው?

ዝናቡ፡- ብዙ ጊዜ የራሴን ስራዎች ነው የምሰራው። የራሴ ግጥምና ዜማዎች አሉኝ። ከዚህ በፊት ሙሉጌታ በርጋ፣ አስረበብ ታደገና እኔ ሆነን ለሶስት “ሶስቱ እንጎቻዎች” የሚል አልበም አውጥተን ነበር። ደራሲው ሙሉጌታ መላኩ ነበር። ከዚያም ለብቻዬ በ1990 ዓ.ም “ሙቀጫ” የሚል ካሴት አወጣሁ።

ሰንደቅ፡- ከድምጻዊነት ባሻገር የሙዚቃ መሳሪያዎችን በመጫወትስ?

ዝናቡ፡- የተለያዩ የሙዚቃ መሳሪያዎችን መጫወት እችላለሁ። ለምሳሌ ኪቦርድ፣ ፒያኖ፣ ድራምና ጊታር፣ ከባህል ደግሞ ክራር እጫወታለሁሁ፡ ይህንን ሁሉ ወታደር ቤት እያለሁ ነው የተማርኩት። በነገራችን ላይ እዛ ያስተምሩን የነበሩት እነኮሎኔል አሰፋ ያሬድ ሙዚቃ ት/ቤትም ያስተምሩ እንደነበር አስታውሳለሁ።

ሰንደቅ፡- ወደትወናው እንዴት መጣህ ታዲያ?

ዝናቡ፡- አንድን ነገር እሰራዋለሁ ብዬ ከተነሳሁ በትኩረት እከታተላለሁ። ቴአትር ሲሰራ በጣም ነው ደስ የሚለኝ። ገና በልምምድ ላይ ሆነው ቃለ ተውኔት ሲያጠኑ ሁሉ አዳራሽ ገብቼ በደንብ እመለከት ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ በቴአትር መድረክ ላይ ብቅ ያልኩት “አንድ ምሽት” እና “አምታታው በከተማ” በተሰኙ ቴአትሮች ላይ ሲሆን እሱም ትንሽ ክፍል ሆና አጃቢ ሆኜ የሰራሁበት ነው። የሙሉ ጊዜ ቴአትር በመስራት በደንብ የታየሁት “አዳብና” በተሰኘው በቤተ -ጉራጌ ትውፊታዊ ተውኔት ነው። እዛ ላይ ዋናው ገፀ-ባህሪይ ነበርኩ። ተስፋዬ ገ/ማርያም ነበር የመረጠኝ። ከተመልካቹ የተገኘው ምላሽ በጣም አሪፍ ከመሆኑ የተነሳ ጀማሪ ተዋናይ ሁሉ አልመስልም ነበር። (ሳቅ) ባህሪው የወንድሙን ሚስት የሚጠብቅ ፈሪ ሰው ስለነበር በጣም አስቂኝ ቴአትር ነበር።

ሰንደቅ፡- ይህ ቴአትር የመጀመሪያ ስራህ ከመሆኑ አንጻር የማትረሳው አጋጣሚ ምን ነበር?

ዝናቡ፡- ሁሌም ሳስስበው የሚያስቀኝ አንድ አጋጣሚ አለኝ። ቴአትሩ እንደነገርኩህ አስቂኝና ትውፊት አዘል በመሆኑ “ለድንገቴ ፈጠራ” የተመቸ ነበር። እናም በአንድ መድረክ ላይ አደራ የተሰጠችኝን የወንድሜን ሚስት አንድ ሰው ሲያሽኮረምም ድንገት እደርሳለሁ። የሚያሽኮረምማት ደግሞ በዘፈን ነበር። እኔ አይቼ እንዳላየ አልፍና የሰፈር ጎረምሶችን ሰብስቤ በመምጣት ነው ወንድነቴን የማሳየው። ታዲያ በቃለ ተውኔቱ የሌለ አንድ ነገር ተናግሬ ተመልካቹንም አብረውኝ የሚሰሩትን ተዋንያንንም እኩል ያሳኩበት ጊዜ ነበር። ምንድነው ያልኩት መሰለህ” ፓ! ይንዴት አምሮብሃል ያኛ አርጋው ደባሶ!” ነበር በአሽሙር ያልኩት። ይህን ስል ሁሉም ጀርባውን ሰጥቶ በሳቅ ወደቅን። ይህ የማልረሳው አጋጣሚ ነው። ከዚያ በኋላም ይሄ አነጋገር በቴአትሩ ውስጥ እንዲቀጥል ተብሎ ስንሰራበት ቆይተናል።

ሰንደቅ፡- በቴአትር ከዚያ በኋላ የታወክበት ስራ የቱ ነው?

ዝናቡ፡- ከዚያ በኋላ በጣም ጥሩ ስራ የነበረው የጌትነት እንየው “ወይ አዲስ አበባ” የተሰኘ ሙዚቃዊ ቴአትር ነበር። እኔ የምጫወተው ደግሞ መንግስቱ ኃ/ማርያምን ሆኜ በዋና ገጸ ባህሪይ ደረጃ ነበር፤ ነገር ግን ቴአትሩ በተለያዩ ምክንያቶች መታየት ሳይችል ቀርቷል። አንድ ዓመት ሙሉ ለፍተን ካጠናን በኋላ በመክፈቻው ዕለት የተዘጋ ቴአትር ሆኗል። ለመጀመሪያ ጊዜ ጓድ መንግስቱን ወክዬ የተጫወትኩት ያኔ ነው ማለት ይቻላል።

ሰንደቅ፡- የጓድ መንግሥቱን ገፀ-ባህሪይ ስትጫወት የፈተነህ ነገር  ምንድን ነው? ከዚያ በፊትስ እሳቸውንስ በአካል የማግኘት አጋጣሚው ነበረህ ወይ?

ዝናቡ፡- ጦሩ ቤት እያለሁ ልጆች ሆነን የታዳጊ ኪነት ስንሰራ ሊጎበኙን መጥተው ተያይተናል። ባይገርምህ የታዳጊ ኪነት ተብለን በየዓመቱ ስታዲየም ይከበር ነበር። ያኔ መዝሙሮችን እንዘምር ነበር። እንደውም አንድ ጊዜ እርሳቸው ባሉበት፣ “ከዓለም ህጻናት ጋር እንድንነጋገር፣ አባባ መንግሥቱ አስጎብኙን ውጪ ሀገር” ብለን በመዘመራችን ለ30 ልጆች ሶቭየት ህብረትን እንድንጎበኝ ፍቃድ ተሰጠን፤ ነገር ግን እኛ ሳንሄድ የባለሥልጣን ልጆች በእኛ ስም መሄዳቸውን ቆይቶ ሰማን። (ሳቅ) ስለገጸባህሪው ለጠየከኝ ጥያቄ አንድ ነገር አለ። በቴአትርም ሆነ በፊልም የሚታወቅን ሰው ባህሪይ መጫወት በጣም ከባድ ነው። እንደሚታወቀው ደግሞ የኮሎኔል መንግስቱ ባህሪይ ተለዋዋጭ ነው። ስቀዋል ስትል ይቆጣሉ። ይቆጣሉ ስትል ደግሞ ሊስቁ ይችላሉ። በዚያ ላይ የአይናቸው መሽከርከርና ድምጻቸው ሁሉ ፈታኝ ነበር። ያንን ሁሉ ማምጣት አለብህ። አንዱ ላይ ካልመሰልክ ሰው አልሰራህውም ነው የሚልህ። ሙዚቀኛ ስለነበርኩ ድምጻቸውን ለማምጣት ብዙም አልከበደኝም። ስለካራክተሩ ለማወቅ ያልፈነቀልኩት ድንጋይ የለም። እንደውም አንድ ወዳጄ በጣም ስጨናነቅ አይቶ፤ ወደሶስት ሰዓት የሚሆን ስለርሳቸው የተቀዳ ፊልም አመጣልኝ እርሱን ደጋግሜ ማየት ስራዬ ሆኖ ነበር። በአሪፉ  ቢሰራም “ወይ አዲስ አበባ” ቴአትር ሳይታይ ቀረ።

ሰንደቅ፡- ያኔ ነው ለ“አቦጊዳ” ፊልም የታጨኸው?

ዝናቡ፡- የሚገርም ነው ሙሌ አይታኝ ተቀደምኩ ብላ ተቆጭታ ነበር። “አቦጊዳ” ድርሰቱ ቀደም ብሎ በተስፋዬ ገ/ማርያም ነው የተጻፈው፤ ወደ ስክሪን ፕሌይ ያመጣው ተስፋዬ ማሞ ነው። ሙሉአለም ታደሰ ዳይሬክተርና ፕሮዲዩሰር ነበረች። ቴአትሩ ላይ በደንብ ተለማምጄ ስለነበር ፊልሙን ለመስራት ብዙም አልተቸገርኩም ነበር። አንድ እውነት ግን ልንገርህ እኔ “አግአዚ ኦፕሬሽን” ላይ ሰርቻሁ አሁን በቅርቡ የሚወጣም ሌላ ፊልም ላይ እንዲሁ የጓድ መንግስቱን ገፀ-ባህሪይ ተጫውጫለሁ። በፊልሞቹ ላይ ለዳይሬክቲንግ አስቸግሬ አላውቅም።

ሰንደቅ፡- በወቅቱ ፊልሙ ሲሰራ በዙሪያህ በርካታ አንጋፋ ባለሙያዎች የነበሩ ቢሆንም ከያዝከው ገፀ-ባህሪ አንጻር ውጠሃቸው ነበር። ምን ይሉሃል?

ዝናቡ፡- ባይገርምህ ሁሉንም አሳምኛቸው ነበር። በተለይም እዛ ላይ አብረውኝ ይሰሩ ከነበሩት ውስጥ ዘላለም ብርሃኑ እና አበበ ባልቻ አንተ ሰውዬ ቁርጥ እሳቸውን እያሉ ይናገሩኝ ነበር። ትወናው ላይ ብዙም አልተቸገርኩም። እንዲያውም ከቴአትር ወደፊልም ስመጣ ድምፄ እየጮኸ አስቸግሯቸው፤ “ኧረ ለፊልም ሲሆን ድምፅህን ቀነስ አድርገህ ተናገር ይሉኝ ነበር። (ሳቅ) ከዚያ ውጪ ተግባብተን ነበር ስራውን የጨረስነው። በነገራችን ላይ እዛ ፊልም ላይ  ያለውን የሚሊተሪ ኮስቹም “ስነ-ገፅ” እኔ ነበር የሰራሁት። ወታደራዊውን ስነ-ስርዓት ስልጠና እስከመስጠት ሁሉ ደርሼ ነበር (ሳቅ)።

ሰንደቅ፡- አርቲስት ሙሉዓለሙ ታደሰ ስለስራህ በተለየ አድናቆት ነበራት የሚሉ ሰዎች አጋጥሙውኛል፤ ምንድነው?

ዝናቡ፡- እውነት ነው በጣም ተግባብተንና ሳላስቸግራት ነው የሰራነው። እንደውም በአንድ መፅሔት ላይ “ፊልሜን ፊልም አድርጎልኛል” ብላ ምስክርነቷን እንደሰጠች አስታውሳለሁ። እኔም አመሰግናለሁ።

ሰንደቅ፡- ፊልሙ የወጣ ሰሞን አድናቆት ደርቶልህ ነበር። ምን በተለየ የማትረሳው ነገር ገጠመህ?

ዝናቡ፡- ያን ሰሞንማ የተለየ ነበር። አንድ ጊዜ አስታውሳለሁ ትራፊክ መብራት ላይ ሁለት ሾፌሮች “መንጌ!” ብለው እኔ ላይ ሲያተኩሩ መጋጨታቸው ትዝ ይለኛል። ብዙዎች ደስታቸውን ይገልፁልኝ ነበር። የተመልካቹ ምላሽ መቼም አይረሳም።

ሰንደቅ፡- የተከፉብህ ማለት ጓድ መንግስቱን ጠልተው አንተን ያጣጣሉህ ሰዎች አላጋጠመህም?

ዝናቡ፡- “የ15 ደቂቃ ኦፕሬሽንን” ስንሰራ በቀረፃ ላይ እያለን ከፊልም ውጪ ያለሰው ነው፤ በንዴት ነበር የሚያየኝ። እንደውም ለፊልሙ የለበስኩትን የወታደር ልብስ ምናምን አይቶ “እንዲህ ሆነህ ብቻህን ባገኝህ ግንባርህን ነበር የምልህ” ሁሉ ብሎኛል። ይሄን ያህል ማሳመን ችዬ ነበር። ሌላው ደግሞ “አቦጊዳ” ፊልምን ስንሰራ ጦርሃይሎች ጊቢ ውስጥ ለቀረፃ ገብተን።ካሜራው እስኪዘጋጅ የወታደር አልባሳቱን እንደለበስን ስብስብ ብለን ቆመን ነበር። እና አንድ ወታደር መጣና ትኩር ብሎ አየኝ። እንደመሄድ ብሎ ተመልሶ መጣና ግጥም አድርጎ ወታደራዊ ሰላምታ ሰጠኝ። እኔም ግጥም አድርጌ ሰላም አልኩት። እሱ ከሄደ በኋላ ሁላችንም ተያይተን በሳቅ ነው የወደቅነው። ይሄን ያህል ነበርን።

ሰንደቅ፡- የዘፈን ዝግጅቶችን ስትሰራስ ሰው አስደንግጠህ አታውቅም?

ዝናቡ፡- በጣም የሚገርመው እሱ ነው። በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ ዘፈን ስሰራ ሰው ያብዳል። ነገር ግን ሰው የሚያደንቀው ዘፈኔን አይደለም። “መንጌ! መንጌ!” እያለ ነው የሚጮኸው ያኔ ደሜ ይፈላል (ሳቅ) ከድምፄ ይልቅ መልኬ ላይ ያተኩራል።

ሰንደቅ፡- በፊልም ምርቃት ዕለትም ያንተ ስም ሲጠራ በአዳራሹ የተለየ ድባብ ነበር። እስቲ ስለሱ ቀን አስታውሰኝ?

ዝናቡ፡- ይገርምሃል ያን ዕለት አሁን ድረስ አልረሳውም፤ ከባለቤቴ ጋር ወደብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ እንደገባሁ የተቀመጥኩት ለተዋንያን ተብሎ የተከለለ ቦታ ሳይሆን ተመልካች መካከል ነበር። ጥቁር ቆዳ ጃኬትና ኮፍያ አድርጊያለሁ። ማንም አላወቀኝም። እንደውም አንድ ከአጠገቤ የተቀመጠ ሰው ፊልሙን አይቶ “መንጌን እኮ ቁጭ አደረጉት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ፊልም ይሄን ያህል አድጓል እንዴ?” ያለኝ አይረሳኝም። ትዝ ካለህ ፊልሙ አልቆ ተዋያኑ ወደመድረክ ሲጠሩ ተመልካቹ ከአዳራሽ መውጣት ጀምሮ ነበር። አርቲስት አበበ ባልቻ፣ አርቲስት ተፈሪ አለሙ፣ አርቲስት ዘላለም ብርሃኑ ቀድመው ከተጠሩ በኋላ መድረኩን ይመራ የነበረው ተስፋዬ ማሞ ቀጥሎ “ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም ወደመድረክ” ሲል እየወጣ የነበረው ሰው ሁሉ ግር ብሎ ሲመለስ ትዝ ይለኛል። በአዳራሽ የነበረው ጭበጨባና ፉጨት የተለየ ነበር። ባይገርምህ የማውቀው መድረክ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ መንቀጥቀጤ ትዝ ይለኛል። ያን ጊዜ ልዩ ነበር፤ እግዜያብሔር ይመስገን።

ሰንደቅ፡- ፊልሙ ብዙ ዝና እንዳመጣልህ ጥርጥር የለውም፤ ክፍያውስ?

ዝናቡ፡- በወቅቱ ትልቁ ክፍያ 10ሺህ ብር ነበር መሰለኝ። ለኔ የተሰጠኝ 6 ሺህ ብር ነው፤ በጣም በቂ ነበር። 

ሰንደቅ፡- የጓድ መንግስቱ መኖር እኔን ታዋቂ አድርጎኛል ብለህ ታስባለህ?

ዝናቡ፡- በርግጥ ዝና በተለያየ መንገድ ይገኛል። ነገር ግን እኔ የኮሎኔሉን ገፀ ባህሪይ ባልጫወት ኖሮ ይሄን ያህል ታዋቂ እሆን ነበር ወይ ያጠራጥረኛል። በሌላ በኩል ደግሞ አዘጋጆ ሌላ ፊልም እንዳያሰሩኝ የመንጌ ገፀ-ባህሪ የጋረዳቸውም ይመስለኛል።

ሰንደቅ፡- ብዙ የፊልም ዳይሬክተሮች ሌላ ገፀ ባህሪይ የሚያጫውቱህ ለመንግሥቱ ስለገነንክ ይሆን?

ዝናቡ፡- አዎ! ብዙ ዳይሬክተሮች መልፋት አይፈልጉም። መንግስቱን ሲያስቡ እኔ ነኝ ትዝ የምላቸው። “ታይፕ - ካራክተር” አድርገውኛል። ነገር ግን ከመንጌ ውጪ የሆኑ ባህሪያትን በቴአትርም በፊልምም ውስጥ ሰርቻለሁ። እንደነገርኩህ በቴአትር “አዳብና”፣ “ህንደኬ”፣ “ተውኔቱ” ላይ የተለያዩ ገፀባህሪያት ናቸው። በፊልሙም “ዘውድና ጎፈር” ላይ እንዲሁ በተለየ መጥቻሁ። ግን እኔ እንጂ ሰው ሁሉ በቀደመው ነው የሚያስበኝ። በቅርቡም የሆነ ፊልም ለመስራት ተነጋግሬያለሁ ነገሩ ከመንግስቱ ጋር የተያያዘ ነው ብዙ ጊዜ በሚሰሩ ኮሜርሻል ፊልሞች የማልታየው ለዛ ይመስለኛል። በታሪካዊ (በተለይም መንግስቱን በሚመለከት) ፊልሞች ላይ ዳይሬክተሮች ከኔ ውጪ አያስቡም። ይህ እንግዲህ በአንድ በኩል መታደል በሌላ በኩል ደግሞ መስራት እየቻልኩ ባለመስራቴ እንደመጥፎ ሊታይ ይችላል ማለት ነው።

ሰንደቅ፡- አሁን የሙዚቃ ስራህ ምን ላይ ነው?

ዝናቡ፡- በብሔራዊ ቴአትር በዘመናዊ ሙዚቃ ቡድን ውስጥ እየሰራሁ ነው። በግሌም ሙሉ አልበም ሰርቼ ጨርሼ ቁጭ ብያለሁ። የኮፒ ራይቱ ነገር አሳሳቢ ሆኗል። ያው ግን እየሰራ ነው። በተለያዩ መድረኮም እዘፍናለሁ።

ሰንደቅ፡- ዝናቡ ምን ያዝናናሃል?

ዝናቡ፡- ፒያኖ እየተጫወቱ መዝፈን በጣም ነው የሚያዝናናኝ። አሁን ራሱ ክለብ ውስጥ ስሰራ ኪቦርድ እየተጫወትኩ ነው የምዘፍነው። የሚገርመው ግን ለታዳሚው ሳይሆን ለራሴ እየተጫወትኩ ነው የሚመስለኝ፤ ያንን ሳደርግ በጣም ነው የምዝናናው።

ሰንደቅ፡- እስቲ ስለቤተሰብህ አጫውተኝ?

ዝናቡ፡- ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ነኝ። ባለቤቴ መሰረት ኃ/ሚካኤል ትባላለች።

ሰንደቅ፡- በስተመጨረሻ ማመስገን የምትፈልጋቸው ሰዎች ካሉ ዕድሉን ልስጥህ?

ዝናቡ፡- በመጀመሪያ ደረጃ እንድታይ ያደረገኝና የኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያምን ገፀባህሪይ እንድጫወት ያደረገኝ ጌትነት እንየውን አመሰግነዋለሁ። እሱ ባያየኝ አሁን ያለኝን ክብር አላገኝም ነበር። ከዚያም ሙሉዓም ታደሰን አመሰግናለሁ። በኋላም የአጋዚ ኦፕሬሽንን እና የ15 ደቂቃ ኦፕሬሽን በተሰኙት ፊልሞቻቸው ያሳተፉኝን ሰለሞንን እና ጥላሁን ተፈራን በጣም አመሰግናለሁ። ሌላው ደግሞ ኮሎኔል መንግስቱም መመስገን አለባቸው እኔ ኪነትን የተማርኩት በእሳቸው ጊዜ ነው። በዚያ ላይ ደግሞ ዝናዬ የጨመረው እርሳቸውን መስዬ በመጫወቴ በመሆኑ አመሰግናቸዋለሁ (ሳቅ). . .. እግረ መንገዴን ግን ለዳይሬክተሮች ማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት ሌሎንም ስራዎች መስራት እንችላለን። እዩን ነው፤ እናንተንም በጣም አመሰግናለሁ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
11105 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us