የ“ሌላሰው” ሌላ ገፅታ

Wednesday, 26 August 2015 13:24

“መጽሐፉ ትልቅ ማኅበራዊና ሥነ-አዕምሮአዊ ክፍተቶችን ለመሙላት የተሰናዳ ነው። ለአገራችን ሥነ-ጽሁፍም አዲስ ስልት ሆኖ የቀረበ ይመስለኛል። ከዚህ ቀደም ደራሲ ፍቅረማርቆስ ደስታ በአንድ ማኅበረሰብ ዘር፣ ባህልና እምነት ላይ በሚያተኩረው (Anthropological) ዘርፍ ያለውን እውቀት በውብ ስነ-ጽሁፍ እንዳስነበበን ሁሉ፤ ዶ/ር ምህረት ደበበም የሰዎችን ሥነ-ልቦናዊና ስነ-አዕምሮአዊ ጉዳዮች በቀላል ቋንቋ እንድንረዳው አድርጐ አስነብቦናል” ይህን ያሉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሥነ-ጽሁፍ የማስተርስ ዲግሪ ያላቸውና የተለያዩ ስራዎችን በጽሁፍ ያቀረቡት አቶ መኮንን ዘገየ ናቸው።

ሚዩዚክ ሜይዴይ በየአስራ አምስት ቀኑ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መፃሕፍት ኤጀንሲና ከኢትዮጲስ ኮሌጅ ጋር በመተባበር በሚያሰናዳው የንባብ ውይይት ባሳለፍነው ሳምንት ነሐሴ 17 ቀን 2007 ዓ.ም በወመዘክር አዳራሽ ተካሂዶ ነበር። ለውይይት በቀረበው የዶ/ር ምህረት ደበበ “ሌላሰው” ረጅም ልቦለድ መጽሐፍ ላይ ሀሳብ አቅራቢው አቶ መኮንን ዘገየ ነበሩ። መጽሐፉን ከሳይኮ አናሊስስ (በተለይም ደግሞ ከገፀ-ባህሪያቱ ሥነ-ልቦና አንፃር) የትንታኔ ሀሳብ አቅርበዋል።

በውይይት መድረኩ መጀመሪያም የሚከተለውን ሀሳብ ለታዳሚው አቅርበዋል። “በመጽሐፉ ውስጥ የጠለቀ የበታችነት ስሜት፣ የራስን ችግር በሌሎች ላይ ማንፀባረቅ፣ በፀፀት መናጥና መጥፎ የነበረን ያለፈ ታሪክ በጥሩ ለመተካት የሚደረግ ጥረት በጉልህ ይንፀባረቃል” ይላሉ።

በ“ሌላሰው” መጽሐፍ ውስጥ የተንፀባረቀውን የገፀ-ባህሪያት ሥነ-ልቦና ለመተንተን ከፀሐፊው አንፃር፣ ከአንባቢው አንፃርና ከገፀ-ባህሪያቱ አሳሳል አንፃር ማየት ይቻላል የሚል ሀሳብ ያነሱት አወያዩ፤ በመሆኑም ይህ መጽሐፍ ከሴራትንታኔ ይልቅ ስነ-ልቦናዊ ጉዳዮች ስለሚበዙት በጭብጥ ላይ አተኩሬ መመልከትን ወድጃለሁ ሲሉ ሀሳብ ያቀረቡበትን ጥግ ለታዳሚው አሳውቀዋል። “ሳይኮ-አናሊስስ” ትንተና የገፀ-ባህሪያቱን የልጅነትና የኋላ ታሪክ በማጥናት ላይ ተንተርሶ የሚሰራ ያስረዱት አወያዩ፤ በመጽሐፉ የተደበቁ የሰዎች ባህሪያትን ይፋ እናይበታለን፤ እንዲሁም ያደረሱትን ተጽዕኖ በሚገባ እናነባለን ይላሉ።

ከመጽሐፉ ርዕስ በመነሳትም “ሌላሰው” መባሉ በራሱ መጽሐፉን የመግለጽ አቅም ያለውና ምፀታዊ መሆኑ የርዕሱን ልከኝነት እንደሚያሳይ ሀሳብ አቅራቢው አቶ መኮንን ዘገየ ይናገራሉ። ለዚህም እንደማሳያ ያሉትን ከመጽሐፉ ታሪክ ሲጠቅሱ የዝናሽን አሟሟትና ሰዎች ራሳቸውን ከተጠያቂነት የሚያሸሹበትን ሁኔታ ያስቀምጣሉ። ዝናሽ ለተባለችው ገፀ-ባህሪይ አሟሟት ሁሉም ሌላውን ሰው ተጠያቂ ማድረጉን በጉልህ አሳይተዋል። በሌላም በኩል ሌላሰው የተሰኘው ዋናው ገፀ-ባህሪይ ሲራክ ስለተባለው ሰው የሚገልፅበትን አካሄድ ተከትለው ባለታሪኮቹ ሁሉ በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት በአደባባይ የሚታወቀው ማንነታቸውና በስውር የሚንፀባረቀው ስብዕናቸው አንድም ሁለትም ያደርጋቸዋል የሚል ሀሳብ ተሰንዝሯል።

ከርዕሱ በተጨማሪ የመጽሐፉ ሌላኛው ጥንካሬ ተደርጐ የተጠቀሰው የግጭት አነሳሱና አንባቢን ለመያዝ የሚፈጅበት ጊዜ አጭር መሆኑ ላይ ነው። ገና በመጽሐፉ የመጀመሪያ ገጾች ላይ ዋናው ገፀ-ባህሪይ (ሌላሰው) አባቱ የጣሉበትን የሙት አደራና በውስጡ የምትመላለሰውን የልጅነት ወዳጁን ፍለጋ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ወስኖ በመነሳቱ አሜሪካ ከምትገኘው የልጆቹ እናት (ሚስቱ) ጋር ከፍተኛ ተቃርኖ ውስጥ ሲገባ በማሳየት መጀመሩ በበርካቶች ዘንድ እንደመልካም ተጠቅሶለታል።

በሌላ በኩል ቋንቋ አጠቃቀሙና የታሪክ ፍሰቱን በተመለከተ የተዋጣለት እንደሆነ የውይይት ሀሳብ አቅራቢው አቶ መኮንን ዘገየ ቢያስረዱም፤ አንዳንድ ተወያዮች ግን ደራሲው የተጠቀመበትን “ጉራማይሌ ቋንቋ ነው” ከማለት አልፈው ገፀ-ባህሪያቱን የማይወክል አነጋገር አይተናል ሲሉ ሞግተዋል። ይህንንም በከፊል ሀሳብ አቅራቢው የሚጋሩት ሆኗል።

በመጽሐፉ ውስጥ ቤተሰባዊ ግጭት፣ አስተሳሰባዊ ግጭት፣ በፍቅርና በጥርጣሬ ላይ የተመሰረተ ግጭት ሁሉ ታሪኩን የሚያንደረድሩት ሆነው ቀርበዋል። በእነዚህ ግጭቶች ውስጥ የገፀ-ባህሪያቱን ችግርና የችግሮቻቸውንም መንስኤ በምልሰት ያስቃኘናል። ለዚህም ችግር ብቻ ሳይሆን መንስኤን ማመላከቱ ለአንባቢው የሚጨምርለት አንዳች ነገር መኖሩ እሙን ነው የሚል ሚዛናዊ አስተያየት ከመድረኩ ተነስቷል።

በመጽሐፉ ውስጥ ከተነሱት ደካማ ጐኖች መካከል በአወያዩ ከተጠቀሱት ቀዳሚው የአመክንዮ ልልነት ነው። ለዚህም በመጽሐፉ የመጀመሪያ ግጭት ሆኖ የሚጠቀሰው የሌላሰው ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ሲሆን፤ ለዚህም ሚስትና ልጆች ያሉት ሰው ድንገት ተነስቶ አገሬ እገባለሁ ሲል፤ በደራሲው የቀረበልን ምክንያት በእጅጉ የሳሳ ነው ተብሏል።

ገፀ-ባህሪያቱ የቱንም ያህል ጠንካራ ቢሆኑ የራሳቸው ውስጣዊና ሥነ-ልቦናዊ ቀውስ እንዳለባቸው ይስተዋላል የሚሉት የውይይት ሀሳብ አቅራቢው፤ በተለይም የሆነን ድርጊት/ታሪክ ለመካድ የሚታትሩ ስንፈታቸውን ላለመቀበል የሚውተረተሩ ስለመሆናቸው ጠቅሰዋል። አንዳንዶቹ (ኤደን) ራሳቸውን ለመግደል መድሃኒት መቃማቸውን፤ አንዳንዶቹ (ሌላሰው) ያለፈን መጥፎ ታሪክ ለመሸሽ እውነታን ለማቃጠል መሞከራቸውን፤ አንዳንዶች (ሲራክ) ሽንቁር ማንነቱን ለመሸሽ መውተርተሩን ይጠቃቅሳሉ። ለዚህም ገፀ-ባህሪያቱ እንደሰው ፍፁም ሳይደረጉ መሳላቸውን መልካም ነው ብለውታል።  

ማንም ሰው ከሥነ-አዕምሮ መዛባት/መታወክ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ነፃ አይሆንም የሚል እንድምታ የታየበት “ሌላሰው” መጽሐፍ፤ ከአስራ አራት በላይ የሥነ-አዕምሮ ህመሞች መንስኤና መፍትሄ ገፀ-ባህሪያቱን መሠረት አድርጐ በዝርዝር ቀርቧል።

መጽሐፉ በሰፊው የማኅበረሰባችንን ሥነ-ልቦናዊ ሽንቁር በጉልህ ያሳየ፤ በተዋዛና ባልተንዛዛ መንገድ የቀረበ መሆኑ እንዳለ ሆኖ፤ ጥቂት በማይባሉ የውይይቱ ተሳታፊዎች በደራሲው ቀደምት ሥራ “የተቆለፈበት ቁልፍ” እንደታየው ሁሉ በዚህ ስራ ውስጥም ተመሳሳይነት ያለው ቋንቋና ገፀ-ባህሪያት ተመሳሳይ ስም አጠቃቀም ታይተውበታል ያሉም ነበሩ። ያም ሆኖ የሥነ-አዕምሮን ጉዳይ ደራሲው ለሌሎች አንባቢያን በቀላሉ ለማስረዳት የመጡበትን ርቀት ማድነቅ ተገቢ ይሆናል።

እኛም ለዛሬ በስተመጨረሻ ከዶክተር ምህረት ደበበ “ሌላሰው” መጽሐፍ መጀመሪያ ላይ የሰፈረውን ሀሳብ በማስታወስ እንሰነባበታለን። “ግራጫ ነጭ የሚጠቁርበትና ጥቁርም የሚነጣበት ሰፊ ግዛት ነው። የህይወት መልክ አስር እጁ ጥቁርና ነጭ፤ የቀረው ደግሞ ግራጫ ነው ሊባል ይችላል። ግራጫ ግን የብርሃን ኩርፊያ ወይም የጨለማ ፈገግታ ሆኖ ይታያል። … ከአንደኛው ወገን አይደለም።… የራሱም መልክ የለውም ብሎ መከራከርም ይቻላል። በሌላ በኩል ሁሉም ቀለማት በየመልካቸው ሰፊ የግራጫ ደርዝ አላቸው። ሰው የመሆን ሌላነትና ህያውነትም በራሱ ሰፊ ግራጫነት ውስጥ …… ተገልጧል። እያንዳንዱ ሰው ሌላ ሰው፤ ሌላው ሰውም ያው እንደኛው መሆኑን መረዳት አንዱ ግራጫ የህይወት አስተያየት ነው” ይለናል። መልካም ንባብ!

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
16836 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us