አሳታፊ የህፃናት ቴአትር - “ማጂራ”

Wednesday, 02 September 2015 12:54

“አዲስ አበባ ህጻናትን መዝናኛ የነፈገች ከተማ ሆናለች” የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም። በትምህርት ቤቶች አካባቢ ከሚገኙ ጠባብ የመጫወቻ ሜዳዎችና በጣት ከሚቆጠሩ ቅንጡ ሞሎች ውጪ ህፃናት ቦርቀው የሚያድጉበት ስፍራ ማግኘት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያስቸገረ ይመስላል። በተለይም ህጻናት በተሳትፎና አእምሯቸውን በሚያበለጽጉበት አግባብ የሚዝናኑባቸው ስፍራዎች እጅግ ውስን ናቸው።

በተለይም ቴአትርና ተሰጥኦን በሚመለከት ልጆች ራሳቸውን እያዝናኑ የሚቃኙበት ስፍራ ማግኘት ብርቅ ነው። አገራችን ካሏት ጥቂት ቴአትር ቤቶች ውስጥ ለልጆች የተሰጠው አንደኛውና ብቸኛው የህጻናትና ወጣቶች ቴአትር ቤት ሆኖ ቆይቷል። ይህንን ክፍተት ያጤኑት የአዶት ሲኒማና ቴአትር ሰዎችም በቅርቡ ዘወትር እሁድ ከ4፡00 ሰዓት ጀምሮ የሚከውን የቴአትርና የትርኢት ስራዎችን ለህጻናት ማዘጋጀት ጀምረዋል።

ከሁለት ሳምንት በፊት በይፋ ተመርቆ መታየት የጀመረው “ማጂራ” የተሰኘው የህፃናት ቴአትር የትርኢቱ ዋነኛ የጀርባ አጥንት ነው። ትርኢቱን ለመታደም በተገኘንበት ወቅት በርካታ ህጻናት ከወላጆቻቸው ጋር በአዳራሹ ሲዝናኑ ተመልክተናል። የልጆች ደስታ የወላጆችም ደስታ ስለመሆኑ ማረጋገጫ የሚሆን ህያው አጋጣሚም ስለመሆኑ መታዘብ ችለናል።

ዘወትር እሁድ በሚካሄደው በዚህ የመዝናኛ ዝግጅት ላይ ልጆችን አሳታፊ የሆኑ የዳንስ ትርኢቶች፣ የጥያቄና መልስ እንዲሁም የግጥም ስራዎችን ጨምሮ በደራሲ ሰለሞን መንግስቴ ተፅፎ፤ በማስረሻ ገ/ማርያም የተዘጋጀው “ማጂራ” ተሰኘ የህጻናት ቴአትር ለዕይታ ይቀርባል።

“ማጂራ” ቴአትር ከህጻናት መዝናኛ አንፃር ሲገመገም ከአማራጭነት ባሻገር ይበል የሚያሰኙት በርካታ በጎ ጎኖች አሉት።

ህጻናት በተፈጥሯቸው የሚወዱትን ነገር የመደጋገሙና ትኩረት የሚሰጡ የመሆናቸው ያህል በፍጥነት የሚሰላቹም ጭምር ናቸው። ታዲያ ለህፃናት የሚቀርቡ ቴአትሮች (ትርኢቶች) ልክ እንደአዋቂዎቹ ሁሉ ለሁለትና ለሶስት ሰዓታት በዝምታና በተመስጦ መቅረብ አይቻላቸውም። ለዚህም ለህፃናት የሚቀርቡ ቴአትሮች ይበልጥ አጫዋች፣ አሳታፊ፣ መካሪና አስተማሪ መሆናቸው ላይ ባሙያዎቹ ትኩረት ያደርጋሉ። ለዚህም እንደማሳያ በአዶት ሲኒማና ቴአትር በመታየት ላይ የሚገኘውን “ማጂራ” የተሰኘ ቴአትር መጥቀስ ይቻላል።

የ“ማጂራ” ቴአትር ታሪክ የሚያጠነጥነው “በተፈጥሯችን ሰነፍ ነን” ብለው የሚያስቡ ሁለት የንጉስ ልጆችን ባህሪና አስተሳሰብ በጥበብ ለመቀየር የሚኬድበትን አዝናኝ ትርኢት የሚያሳይ ስራ ነው። ሳራ እና ኪሩቤል የተሰኙት የንጉሱ ልጆች የአባታቸውን ዙፋን መውረስ ሲገባቸው ሰነፍ በመሆናቸው ብቻ ስልጣኑ ለሌሎች የሀገሬው ልጆች ሊሰጥ መሆኑን በመስማታቸው በቁጭት የዕውቀት አባትን ፍለጋ የሚያደርጉትን ጉዞና በስተመጨረሻም የሚገጥማቸውን አስደናቂ ውጤት የሚያሳይ ቴአትር ነው።

በቴአትሩ ውስጥ “ጉብዝና የሚሞላ ሳይሆን በጥረት የሚገኝ” ስለመሆኑ በጽኑ ተደጋግሞ የሚነሳ አብይ ጭብጥ ነው። ለዚህም ልጆቹ “ማጂራ” የተሰኘው አዲስ ቋንቋ ለማወቅ ያሳዩትን ጥረት በሚያዝናና መንገድ ቴአትሩ የሳየናል። ቴአትሩ በተዋንያኑ ብቻ ሳይሆን በተመልካቹ (በህጻናቱ) ተሳትፎ ጭምር የተሰራ መሆኑ ልጆች ፍዝ- ተመልካች እንዳይሆኑና ራሳቸውን የታሪኩ አካል እንዲያደርጉ ረድቷቸዋል።

“ማጂራ” ቴአትር በዘፈንና በግጥም የተዋዛ፤ አሳታፊ ትወናና ብልጭልጭ አልባሳት ያደመቁት፤ ተረት መሰል ክስቶችና አጫዋች ገፀ-ባህሪያት የተካተቱበት በመሆኑ ለህፃናት መልካም መዝናኛ ሆኖ ቀርቧል። ልጆች ያላቸውን ችሎታ ከውጪ ሳይሆን ከውስጣቸው እንዲያወጡት የሚጎተጉተው የቴአትሩ መልዕክት በህጻናቱ እይታ በጭብጨባና በደማቅ ምላሽ ተቀባይነት ያገኘ እንደነበር ተመልክተናል።

አዶት ሲኒማና ቴአትር ልጆችን በስነ ምግባርና በጥበብ ከመቅረፅ አንጻር የራሱን ድርሻ እየተወጣ ስለመሆኑ የተቋሙ አመራሮች ይናገራሉ። በመጫወቻ ማሽኖና በፊልሞች ብቻ ህጻናትን ማቆየት የሚችል ቢሆንም፤ ቴአትርን በሚያክል ትልቅ ጥበብና አሳታፊ ትርኢት ከልጆች ጋር መቆየት የበለጡ ጥቅም አለው የሚሉ በርካቶች ናቸው። አዶት ሲኒማና ቴአትርም መሰል የህጻናት ቴአትሮችን በመስራት እንደሚቀጥል ያስታወቀ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት “ማጂራ” ከተሰኘው የህፃናት ቴአትር በተጨማሪ “ከራስ በላይ ራስ” እና “እያዩ ፈንገስ “የተሰኙ የሙሉ ጊዜ የአዋቂዎችን ቴአትር በማሳየት ላይ ይገኛል።

“ማጂራ” ቴአትር ፕሮዲዩስ የተደረገው በአዶት ሲኒማና ቴአትር በድምፅ ቅንብሩ ገሊላ ገ/ማርያም ስትሆን በመብራት ህይወት ግርማ ተሳትፈውበታል። ዘወትር እሁድ ለዕይታ በሚቀርበው በዚህ ቴአትር ላይ አስታውሺኝ በነጋ፣ ሲሳይ አማረ፣ ሂሩት ይርዳው፣ እየሩሳሌም ትዕዛዙ፣ ዋሲሁን በላይ፣ መልካሙ አለማየሁ እና ማስረሻ ገ/ማርያም እተፈራረቁ ይተውኑበታል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
15391 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us