“በማህበራዊ ህይወቴ ደስ ይለኛል”“በማህበራዊ ህይወቴ ደስ ይለኛል”

Wednesday, 16 September 2015 13:36

በበርካታ የሬዲዮና የቴሌቭዥን ድራማዎቿ እንዲሁም በተለያዩ ፊልሞችና ቴአትር ችሎታዋ የምናውቃት፣ የምናደንቃትና የምንወዳት አርቲስት ሰብለ ተፈራ (እማማ ጨቤ) መስከረም 1 ቀን 2008 ዓ.ም በድንገተኛ የመኪና አደጋ ህይወቷ ማለፉ ይታወሳል፡፡ የአርቲስቷ ስርዓተ ቀብር ሰኞ መስከረም 3 ቀን 2008 ዓ.ም በድስት ስላሴ ካቴድራል ቤ/ክ ተፈፅሟል፡፡ ለአርቲስቷ ቤተሰቦች፣ ወዳጆችና አድናቂዎች የዝግጅት ክፍላችን መጽናናትን እየተመኘ ሚያዚያ 16 ቀን 2005 ዓ.ም ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር አድርጋው የነበረውን አዝናኝ ቆይታ እነሆ ለትውስታ አቅርበንላችኋል፡፡

ሰንደቅ፡- ሰብሊ ‘‘ጌታም ሎሌም’’ ሆነሽ በትወናሽ ለበርካታ ተመልካቶችና አድማጮች እየደረሽ ነው። ‘‘በትናንሽ ፀሐዮች’’ እማማ ጨቤን፤ በ“ቤቶች” የቴሌቪዥን ድራማ ደግሞ ትርፌን ሆነሽ ትሰሪያለሽ አንቺ የቱ’ጋ ነሽ?

ሰብለ፡- ሰብለ’ጋ… (ሳቅ)… የሚገርምህ ነገር ማንኛውም ስራዬ ከማንኛውም ጋር አላበላልጥም። ሁለቱም ለኔ ደስ የሚል ስሜት እየተሰማኝ የምሰራቸው ስራዎቼ ናቸው። እንዲሁ ግን የሚገርመኝ ነገር አለ፡፡ ‘‘ትንንሽ ፀሐዮች’’ ወይም ‘‘እማማ ጨቤ’’ ሲደመጥ አድማጭ ለኔ ያለው ነገር የተለየ ነው። አንዳንድ አድማጭ እስከሚያየኝ ድረስ የሚያስናፍቀው ዓይነት ይመስለኛል።

ሰንደቅ፡- እውነቱን ለመናገር የእማማ ጨቤ ተፅእኖ ጉልበት አለው። በአዲሱ ፊልምሽ ‘‘አልበም’’ ላይ ራሱ ከስምሽ ቀጥሎ ‘‘እማማ ጨቤ’’ የሚለው ቅጥያ ተቀምጧል። አድማጭ ተመልካቹ ስለ እማማ ጨቤ ምን አይነት ምላሽ ቢሰጥሽ ነው ከስምሽ’ጋ የለጠፍሻቸው?

ሰብለ፡- ትክክል ነው። እኔ በ‘‘አልበም’’ ፊልሜ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የእማማ ጨቤን ስም ልጠቀም እንጂ፤ ሌሎች ስራዎችን ከሰዎች ጋር ሰርቼ ወደተለያዩ ቦታዎች እየሄድን ስንሰራ እኔን ሳያስፈቅዱኝ ‘‘እማማ ጨቤ’’ የሚለውን ቅፅል ስም ከስሜ ጋር ያስተዋውቁበት ነበር። በርካታ ተመልካችም ያንን ሰምቶ ይመጣል። በርግጥ ‘‘እማማ ጨቤ’’ ከብዙ ሰው ጋር አስተዋውቀውኛል። ነገር ግን ተመልካቹ እንዲህ በአካል ሲያየኝ ‘‘እማማ ጨቤ’ ይህቺ ነች እንዴ? ይህቺ’ኮ ወጣት ናት” ሲሉኝ እሰማዋለሁ። እናም በሌሎቹ ስራዎች ላይ ያሳደሩትን ተፅእኖ ስላየሁ እኔም ለምን አልጠቀምበትም ብዬ ነው ባዘጋጀሁትና ፕሮዲዩስ ባረኩት ፊልሜ ላይ ከስሜ ቀጥዬ የ‘‘እማማ ጨቤ’’ን ስም ተጠቅሜያለሁ ለዚህም የደራሲውን ፍቃድ አግኝቻለሁ።

ሰንደቅ፡- እስቲ ስለምትጫወቺያቸው ሁለት የለተያዩ ገፀ-ባህሪያት ንገሪኝ። ‘‘እማማ ጨቤ’’ ቁጡ፣ አሽሟጣጭና የዋህ ሰው ናቸው። በአንፃሩ ደግሞ ትርፌ የዋህ ነገር ግን ለሆዷ የማትመለስ አይነት ሴት ናት። አንቺ ምን ይሰማሻል?

ሰብለ፡- እውነት ነው። ‘‘እማማ ጨቤ’’ መቀለድና ማሽሟጠጣቸው፤ መተረባቸው ብቻ አይደለም ትልቅ ቁም ነገር አላቸው። ህብረተሰቡን ያነፁ ትልቅ ሴት ናቸው ማለት ይቻላል። ያ ማለት እማማ ጨቤ ሀብታም ስለሆኑ ብቻ አይደለም። እውነቱን ለመናገር ከእማማ ጨቤ ኑሮ ያነሰ ማህበረሰብ፤ የተቸገረን መርዳት እንደሚችል አይተንበታል። በድራማው ውስጥ አመዶን ከጐዳና አንስተው ‘‘ሰው’’ አድርገውታል። ፍቅር ሰጥተውታል። ፍቅር ደግሞ የሁሉም ነገር መሰረት ነው ብዬ አምናለሁ። የድራማው ተፅእኖ ቀላል አልነበረም። ‘‘ትንንሽ ፀሐዮች’’ን ከሰማው በኋላ ሰው አስጠግቻለሁ፤ ሰው ረድቻለሁ የሚሉ መልካም ለውጦች ደርሰውናል። በርካታ ማህበራዊ ችግሮችን የሚያነሳ ድራማ በመሆኑ ብዙዎች ከልባቸው ይከታተሉታል።

ሰንደቅ፡- እዚህ’ጋ አንድ ጥያቄ ላንሳ፤ ምናልባት አንቺ ትክክለኛው መላሽ ላትሆኙ ትችያለሽ፡፡ ነገር ግን ድራማው በየሳምንቱ ወቅታዊና ሰሞነኛ ጉዳዮችን የሚያነሳ ነው ምናልባትም በዚህ ሳምንት ስለቦስተኑ ማራቶን ጥቃት ያነሳ ይሆናል። (ቃለ-መጠይቁ የተካሄደው የቦስተኑ ጥቃት በደረሰበት ሰሞን አርብ ዕለት ነው) ድራማውን ከሌሎች ስራዎችሽ ጋ ስታነፃፅሪው ምንድነው የሚለየው?

ሰብለ፡- የ‘‘ትንንሽ ፀሐዮች’’ ድራማ አካሄድ ከተለመደው ትንሽ የተለየ ነው። ይህ የደራሲና አዘጋጁ ስልት ነው። ምናልባትም ይሄ ይሆናል ላለፉት አራት አመታት ሳንሰለች እንድንዘልቅ ያደረገን። ሰዎች በባህሪያቸው የሰሞኑን ጉዳይ ተዋዝቶ ድጋሚ መስማት ይፈልጋሉ። እግረ መንገዳቸውንም መረጃ ያገኙበታል። ከዚያ ውጪ ግን ድራማ እንደማንኛውም ድራማ ነው።

ሰንደቅ፡- በትወና ተሳትፈሽ የሰራሽባቸው ፊልሞችም ሆኑ ድራማዎች ካለፉ በኋላ ስትመለከቻቸው ምንድነው የሚሰማሽ ስሜት?

ሰብለ፡- ይገርምሃል አንዳንድ ጊዜ የሌላ ሰው ስራ እስከማይ ድረስ ከቤተሰቦቼና ከጓደኞቼ ጋር ሆኜ ስራዬን ሳየው በጣም ነው የሚያስቀኝ። አሁን ለምሳሌ ‘‘ቤቶች’’ ድራማ ላይ ትርፌን ሆኜ ሞባይል አልቅሼ አስገዛሁ አይደል? በቀረፃ ወቅት ደጋግመን ሰርተነው፤ ኤዲት ሲደረግ ስቱዲዮ ገብቼ አይቼው፤ እቤት ገብቼ ከባለቤቴ ጋር ቁጭ ብዬ ሳየው ልቤ ውልቅ እስኪል ድረስ ነው የሳኩት። እና በራሴ ስራ እንደማንኛውም ኦዲየንስ (ተመልካች) ነው የምዝናናው ማለት ይቻላል።

ሰንደቅ፡- ለመጀመሪያ ጊዜ ‘‘አልበም’’ የተሰኘ ፊልም ፕሮዲዩስ አድርገሻል፤ እስቲ ደግሞ ስለሱ አጫውቺን?

ሰብለ፡- እንግዲህ ‘‘አልበም’’ ፊልምን መረጥኩ እንጂ ፊልሞችን ፕሮዲዩስ ለማድረግ መምረጥ ከጀመርኩ ቆየት ብያለሁ። ካየኋቸው የፊልም ፅሁፎች (ስክሪቶች) ‘‘አልበም’’ የተሻለ ስለነበር እርሱን ፕሮዲዩስ አድርጌዋለሁ።

ሰንደቅ፡- ‘‘አልበም’’ ፊልም በምን ተለይቶ ባንቺ ዘንድ ተመረጠ?

ሰብለ፡- ‘‘አልበም’’ ፊልምን ከሌሎቹ የመረጥኩበት ምክንያት፤ እስካሁን ካየኋቸው ፊልሞችና ካነበብኳቸው መፅሐፍት የተለየ ታሪክ የሚተርክ በመሆኑ ነው። በዚህ ላይ አጨራረሱ ከማንም ግምት ውጪ ነው። በአስደናቂ መልኩ ነው የሚጠናቀቀው። ፊልሙ ወጪን በሚቆጥብ መልኩ መሰራት የሚቻል በመሆኑ መርጬዋለሁ። በፊልም ፕሮዲዩሰርነት የመጀመሪያ ስራዬ ቢሆንም ከዚህ በፊትም ቴአትር ስሰራ የሚደግፈኝ አባቴ ነው። ባለኝ ነገር ላይ ትንሽ እንዲጨምሩልኝ ቤተሰቦቼን ባስቸግር እሰራዋለሁ ብዬ ስላሰብኩም ነው የመረጥኩት።

ሰንደቅ፡- ምናልባት ከፊልም ቀድመሽ ቴአትር ፕሮዲዩስ አድርገሽ ነበር፡፡ እስቲ ስለእሱ አስታውሺን።

ሰብለ፡- አዎ! ቴአትሩ በአማተር ተዋንያን ይሰራ የነበረ ቴአትር ነው። ‘‘እርጥባን’’ ይሰኛል ርዕሱ፤ ልጆቹ ለምን ቴአትራችንን አታይልንም አሉኝ። ያን ሰሞን ፕሮዲዩስ የማድረግ ፍቃዱን አግኝቼ የነበረ በመሆኑ ቴአትሩን ሳየው በጣም ጥሩ ስለነበር ፕሮዲዩስ አድርጌ ለግምገማ ቀርቦ አልፎም-በባህልና ቴአትር አዳራሽ ለሰባት ሳምንታት ታይቶ ቆመ።

ሰንደቅ፡- ለምን ቆመ? ተመልካች አጣ?

ሰብለ፡- ከሰባት አመት በፊት ነው። ያን ጊዜ ‘‘ቴአትር ሞተ’’ ምናምን የሚባልበት ጊዜ ነው፤ ነገሩ ቴአትር መቼም አይሞትም። እንደነገሩ ግን ተመልካች የጠፋበት ጊዜ ስለነበር ብዙም አዋጪ ሳይሆን ቆመ። ከዚያን ጊዜ በኋላ የሌሎች ሰዎችን ስራዎች ስሰራ ቆይቼ፤ ቴአትርም ፊልምም ፕሮዲዩስ የማድረግ ሀሳቡ ስለነበረኝ ባለፈው አመት (2004) ወደፊልሙ አመዝኜ ይህንን ‘‘አልበም’’ የተሰኘ ፊልም ሰርቻለሁ። አሁን ደግሞ አንድ ቴአትር ፕሮዲዩስ ለማድረግ እየተንቀሳቀስኩ ነው።

ሰንደቅ፡- ፕሮዲዩሰርነት የገንዘብ አቅም ይጠይቃል፤ ምን ውጤት አገኘሽ?

ሰብለ፡- እንደፕሮዲዩሰር ካየኸው ፊልምና ቴአትርን ስትሰራ ገንዘብህ ያሳስብሃል። እኔ ‘‘በአርቱ’’ ውስጥ የመጣው (ያለፍኩ) በመሆኔ ቅድሚያ ለጥበቡ ነው የምሰጠው። ገንዘቡን አልፈልግም እያልኩህ ግን አይደለም። ነገር ግን ፊልም የሰራሁት ‘‘ቢዝነስ’’ ልስራ በሚል አስተሳሰብ አይደለም። ለምሳሌ በፊልሜ ‘‘ፖስተር’’ ላይ ከምታያቸው ተዋንያን በተጨማሪ ስም ያላቸው የሚባሉ አክተሮች ማለትም አልማዝ ሐይሌ፣ የትናየት ታምሩና ጀንበር አሰፋ አሉ። እነርሱን በ‘‘ፖስተሬ’’ ላይ ባወጣ ተመልካች ልስብ እችላለሁ። ነገር ግን በታዋቂ ሰው ስም፤ አንድ መስመር የተናገረውን ሰው እያሳዩ የሌላውን ዋጋ ማሳጣትና ተመልካችን መሸወድ ጥሩ አይመስለኝም። በርግጥ ሲኒማው አካባቢ ‘‘እነማን ሰሩበት?’’ እንጂ ‘‘ምን ተሰራ?’’ አይባልም አንድ ነገር መታወቅ ያለበት እነዚህ ወጣቶቹም ግን አሪፍ ይሰራሉ። ተመልካቹም ‘‘ፊልሙን’’ መገመት ያለበት አይቶ መሆን ይኖርበታል። በስራዬ መዳኘት ነው የምፈልገው።

ሰንደቅ፡- ቴአትርም ፊልምም በተለያየ ጊዜ ፕሮዲዩስ አድርገሻል። እስቲ ስለአዋጪነትና ፕሮዲዩስ ማድረግን በተመለከተ የሁለቱን መስኮች አንድነትና ልዩነት እንጨዋወት?

ሰብለ፡- አዋጪነቱን በተመለከተ ለመጀመሪያው ቴአትር የመድረክ ገፅ ግንባታን የአክተሮችና የደራሲን ጨምሮ ወደ 33ሺህ ብር አውጥቼ ነበር (ከ7 አመት በፊት)። ከስሬያለሁ ብሎ ማለት አልፈልግም። ተምሬበታለሁ። በንፅፅር ለማስቀመጥ ግን የሚያመሳስላቸው ሁለቱንም ባሳየህበት ልክ ተመልካች ካገኘህ ገንዘብ ታመጣባቸዋለህ። የፊልምህን ማስተር ይዘህ ከሲኒማ ቤት ሲኒማ ቤት ሄደህ ታሳያለህ። ቴአትርም ተዋናዩን ይዘህ እየዞርክ ታሳየዋለህ። ልዩነቱ ምንድነው ፊልም አንዴ ከተሰራ አክተሩ ኖረም አልኖረም ታሳየዋለህ። ቴአትር ግን ይከብዳል። እንደውም የቴአትር አክተር ስትሆን መሞት ሁሉ አይፈቀድልህም (ሳቅ)

ሰንደቅ፡- ሰብለ አንቺ በምትሰሪያቸው ድራማዎችና ፊልሞች ተመልካቹን ታዝናኛለሽ፤ አንቺስ በምንድነው የምትዝናኚው?

ሰብለ፡- ብዙም የተለየ ነገር የለኝም። መፅሐፍትን በማንበብ እዝናናለሁ። ፊልም ማየት ያዝናናኛል። ከምንም በላይ ግን በማህበራዊ ህይወቴ ደስ ይለኛል። ከጓደኞቼና ከቤተሰቦቼ ጋር የማሳልፈው ጊዜ ደስ ይለኛል።

ሰንደቅ፡- ፊልምሽን ስትሰሪ ምን አጋጠመሽ?

ሰብለ፡- የተለየ ነገር አልገጠመኝም፤ ነገር ግን እኔ የሰራኋት ገፀ-ባህሪይ (ሃና ትባላለች)… ‘‘አልበም’’ን ዳይሬክት ስለማድረግ የሰፋ ሚና እንዲኖረኝ አልፈለኩም። እናም ሃና ከሰብለ ጋር የሚያመሳስላት ነገር አለ። በተለይ-በተለይ እንቅልፍና ፖሊስ መፍራቷ የራሷ የሰብለ ነው፤ እንደውም ጓደኞቼ ፊልሙን አይተው ሲጨርሱ ይደውሉልኝና ‘‘አንቺ የሰራሽው የራስሽን ካራክተር (ባህሪይ) ነው’’ ሲሉኝ እስቃለሁ።(ሳቅ)

ሰንደቅ፡- ስለፊልም አውርቶ ስለሲኒማ ቤት አለማውራት ተገቢ አይደለም። እንደፕሮዲዩሰርም እንደባለሙያም የሲኒማ ቤቶችን አሰራር እንዴት ትገልጫቸዋለሽ?

ሰብለ፡- የመጀመሪያ ስራዬ እንደመሆኑ በርካታ መሰናክሎች ገጥመውኛል። ከሰው ጋር መጋጨት አልፈልግም። የሚያበረታቱ ተስፋ የሚሰጡ መልካም የሆኑ የሲኒማ ቤት ባለሙያዎች እንዳሉ ሁሉ የማዝንባቸው፣ የሙያውን ዲሲፕሊን የማያውቁና በግልፅ ብር እንዲሰጣቸው የጠየቁኝ የሲኒማ ቤት ገምጋሚዎች ገጥመውኛል። አንዳንዶቹ ቦታ አይሰጡህም (ቦታ ማለት ፊልም የሚሳያ ጊዜ ማለቴ አይደለም) በአግባቡ እንኳን ሊያናግሩን ፍቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች አሉ። በሬዲዮ ላይ ስፖንሰር አድርጌ፤ ፕሮግራም አስተዋውቄ ካበቃሁ በኋላ በዕለቱ ስሄድ መለወጡን የነገረኝ ሲኒማ ቤት አለ፤ ይህ በጣም አሳፋሪና አስቸጋሪ ገጠመኝ ነው። እንደውላለን ብለው አሁንም ድረስ እየጠበኩ ነው። ፊልሜ ጥሩ እንደሆነ ተነግሮኝ በሰዎቹ ምክንያት ብቻ ምላሽ ሳላገኝ የምቀር ከሆነ የሲኒማ ቤቱንም ሆነ የግለሰቡን ስም ጠቅሼ አንድ ሚዲያ ላይ እውነቱን እናገራለሁ። እኔ በመጀመሪያ ስራዬ ሲኒማ ቤቶችን መውቀስ ጀመርኩ፤ ይህ ያሳፍራል። በአጠቃላይ በአንዳንድ ሲኒማ ቤቶች አካባቢ ሙስና ተንሰራፍቷል ማለት ይቻላል። አንድ ፊልም ሰርቼ ብዙ ልናገራቸው የማልፈልጋቸውን መጥፎ ነገሮች አይቻለሁ።

ሰንደቅ፡- መፍትሄው ምንድነው ትያለሽ?

ሰብለ፡- የመጀመሪያው ፕሮዲዩሰሮቹና ሲኒማ ቤቶቹ በቀናነትና በመግባባት መስራትን መልመድ አለባቸው። ሲቀጥል ደግሞ ምናልባት የሲኒማ ቤቶች መበራከት ችግሩን ይቀርፈዋል ብዬ እገምታለሁ። አንድ ነገር ግን መታወቅ አለበት፤ ዋነኛው ችግር የፊልም መብዛትም ነው። ብዛቱ ከጥራቱ ጋር ስላልተጣጣመ የሲኒማ ቤቶች ጉልበት በፊልሞቹ ላይ እንዲበረታ አድርጐታል። ፊልሞቻችን በጣት የሚቆጠሩት ብቻ ናቸው በባለሙያዎች ተሰርተው የሚቀርቡት፤ የተቀረው ግን ገንዘቡ ስላለው ብቻ የሚሰራው ሆኗል። ድርሰት የተሰጥኦ ጉዳይ ስለሆነ (መክሊቱ ያለው) ማንም ሰው መፃፍ ይችላል። ዳይሬክት ማድረግና ኤዲት ማድረግ ግን ተጨማሪ የሆነ ቴክኒካል ዕውቀትን ይጠይቃል። ቢያንስ እንኳን ባለሙያዎችን አማክሮ መስራት ጥሩ ነው።

ሰንደቅ፡- በእናንተ በባለሙያዎቹ በኩልስ ያለው ችግር እንዴት ይገለፃል? ጥራት ያለውና አማራጭ መሆን የሚችልን ስራ ከማቅረብ አንፃር ማለቴ ነው?

ሰብለ፡- ልክ ነው፤ በተመሳሳይ ታሪክ ተመሳሳይ አክተሮች ፊልም በመስራት ተመልካቹ ከኮሜዲ ውጪ እንዳያይ በማድረግ ምርጫ የሚያሳጡት ብዙ ሰዎች አሉ። ለምሳሌ የኔ ፊልም ‘‘አልበም’’ ልብ አንጠልጣይ የቤተሰብ ፊልም ነው። ያማከርኳቸው ሰዎች ግን ከኮሜዲ ውጪ መስራቴን አንዳቸውም አልወደዱትም። ኮሜዲ መብዛቱ ቁም ነገር ያለው ከሆነ ጥሩ ነው። ነገር ግን ‘‘ውሳኔ’’ እና ‘‘ቀዝቃዛ ወላፈን’’ የመሳሰሉ ፊልሞች በሰልፍ መታየታቸው መዘንጋት የለበትም።… የሚያሳዝን ነገር ልንገርህ፡፡ አንድ ሲኒማ ቤት ፊልሜን ገምግሞ ሲያበቃ ፊልሙ ጥሩ ነው፣ ታሪኩም፣ ምስልና ድምፁም ጥሩ ነው ነገር ግን ኮሜዲ ፊልም ስላልሆነ እኛ’ጋ አይታይም። ለምን ስትለው - የኛ ተመልካች ኮሜዲን ብቻ ነው የሚወደው የሚል ድፍን መልስ ታገኛለህ። እንግዲህ እንዲህ አይነት ባለሙያዎች ናቸው ፊልምህን የሚገመግሙት።

ሰንደቅ፡- ምን አይነት ፊልሞች ይመስጡሻል?

ሰብለ፡- የፍቅር ፊልሞች ደስ ይሉኛል። ከሀገራችንም ‘‘ማክቤል’’ እና ‘‘ስርየት’’ በጣም ደስ ያሉኝ ፊልሞች ናቸው።

ሰንደቅ፡- በቀጣይ ምን ለመስራት አስበሻል?

ሰብለ፡- ፊልሙን ጀምሬዋለሁ እቀጥልበታለሁ። ቴአትሩም ቢሆን በቅርቡ ለመድረክ የሚበቃ ስራ አለኝ። አብረውኝ የሚሰሩትን ባለሙያዎች ሁሉ አመሰግናለሁ። የኛ ስራ ከአዳራሽ እስከቤት የሚደርስ በመሆኑ የስራዬን ባህሪይ ለተረዱልኝ ቤተሰቦቼም ከፍተኛ ፍቅርና ምስጋና እንዳለኝ መግለፅ እፈልጋለሁ። በተለይ ለአባቴ!

                                            (የአርቲስት ሰብለ ተፈራን ነፍስ በአፀደ ገነት ያኑርልን!)

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
10357 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us