“ቦብ ለኔ የነፃነት አርበኛ ነው”

Wednesday, 23 September 2015 13:35

አርቲስት ዘለቀ ገሠሠ

ከ30 ዓመታት በላይ በሙዚቃው ዓለም ቆይቷል። በበርካቶች ዘንድ የሚታወቅ በሬጌ ስራዎቹ ቢሆንም በተለይም በምዕራባውያኑ ዘንድ ልዩ ስፍራ ከሚሰጣቸው አቀንቃኞች መካከል አንዱ መሆኑን ሚዲያዎቻቸው ይመሰክራሉ። በአልበም ደረጃ በዚህ ሳምንት የለቀቀው “አይዞን”ን ጨምሮ አራት ስራዎች ቢኖሩትም በርካታ ነጠላ ዜማዎችን ግን በመጫወት ይታወቃል። የዛሬው የመዝናኛ እንግዳችን አርቲስት ብቻም አይደለም፤ በበጎ ተግባር ተሰማርቶ ከ30 በላይ ትምህርት ቤቶችንም ማስገንባት የቻለ ሰው ነው። ከአርቲስት ዘለቀ ገሠሠ ጋር በመኖሪያ ቤቱ የነበረን አጭር ቆይታ እነሆ፡-

ሰንደቅ፡-በቤተሰባችሁ ውስጥ ሙዚቃ ልዩ ቦታ ያለው ይመስላል፤ ላንተ ወደዚህ ሙያ መሳብ ምክንያቱ ማነው?

ዘለቀ፡- ባይገርምህ ለኔ የሙዚቃን ፍርቅ ያበዛችልኝ እናቴ ናት። እናታችን ሙዚቃ መስማት ትወድ ነበር። ልጅ ሆነን በቴፕ የሰማነውን እንዘፍን ነበር። እኔ ገና የስምንት ዓመት ልጅ እያለሁ ነው በአሜሪካ ሚሺነሪ ቤተክርስቲያን ውስጥ መዝሙር ስዘምር ያየችኝ። በጣም ነበር የኮራችብኝ። ያ እንግዲህ በሙዚቃውም እንድገፋበት አድርጎኛል። ለምን ከተባለ ከቤት ከተፈቀደልን ነገሮች ጥሩ ይሆናሉ። በተለይ ደግሞ ኢሊባቡር ጎሬ የምትባል ከተማ ውስጥ ከሙሉጌታ ገሠሠ ጋር እንጫወት ነበር።

ሰንደቅ፡-ከድምፃዊነት በሻገር የሙዚቃ መሳሪያዎችን በመጫወትስ ያለህ ተሳትፎ እንዴት ነው የሚገለፀው?

ዘለቀ፡- የሙዚቃ መሳሪያን በተመለከተ ለኔ መነሻ የሆነኝ ትልቁ ወንድሜ መኮንን ገሠሠ ነው። አሁን አትላንታ ነው የሚኖረው፤ የሙዚቃ መምህር ነበር። ጊታር አለው፤ አብሬው በምኖርበት ጊዜ በጣም ይጫወት ስለነበር ቅዳሜና እሁድ አብረን እሞካክር ነበር። ከዚያ ደግሞ ሙሉጌታ ገሠሠ አለ። እሱ ጎሬ እያለን ቤተክርስቲያን ውስጥ ፒያኖም ተምሮ ስለነበር የሙዚቃ መሳሪያ መነካካትን የተማርኩት። ከቤዝ ጊታር ውጪ ግን ሌላ የሙዚቃ መሳሪያ አልጫወትም።

ሰንደቅ፡-ከቤተሰባችሁ ውስጥ ስንቶቻችሁ ናችሁ በሙዚቃው ዓለም ውስጥ ያላችሁት?

ዘለቀ፡- ሰባት ወንዶችና አንድ እህት ነው ያለችን። ከዚያ ውስጥ ሶስታችን በሙዚቃ ውስጥ አለን። አዲስ ገሠሠ ሙዚቃ ማኔጀር ነው። ሌሎቹም ቢሆኑ ግን ለሙዚቃ ፍቅር አላቸው።

ሰንደቅ፡-ለአዲስ ዓመት የሚሆን “አይዞን” የተሰኘ አልበም ይዘህ ቀርበሃል። ይህ ስንተኛ አልበምህ ነው። ምን የተለየስ ስራ አቅርቤበታለሁ ትላለህ?

ዘለቀ፡- “አይዞን” ለአዲሱ ዓመት ገፀ-በረከት ያቀረብኩት ስለሆነ ሰዎች ይወዱታል የሚል ተስፋ አለኝ። ይህ አልበም አራተኛዬ ነው። ከእነዚጊ ማርሌ ጋር ሁለት አልበም ሰርተናል፤ ከዳሎል ባንድ ጋር ደግሞ አንድ አልበምና አራት የሚደርሱ ነጠላዎችን ሰርተናል። “አይዞን” ጥሩ ነው፤ ደስ የሚለው ለመጀመሪያ ጊዜ ሙሉውን አልበም እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው የቀረፅኩት። ከዚህ ቀደም የሰራዋቸው በሙሉ በውጪ ሀገር የተቀረፁ ናቸው። አብዛኞቹ በጃማይካ ቦብ ስቱዲዮ ውስጥ የሰራኋቸው ናቸው። በአዲሱ አልበሜ ውስጥ የተሳተፉት በሙሉ በዳሎል ባንድ ሙዚቃዎች ያደጉ ወጣት አርቲስቶች ናቸው። አልበሙ ከወጣ ጊዜ ጀምሮ ጥሩ ምላሽ እያገኘንበት ነው።

ሰንደቅ፡-ምን የተለየ ነገር በዚህ አልበም ውስጥ አመጣህ? እነማንስ ተሳትፈውበታል?

ዘለቀ፡- የተለየ አገራዊ ዜማ አምጥቼበታለሁ። ለምሳሌ “ሀገሬ” የሚለው ዘፈን ከሬጌ ይልቅ ኢትዮጵያዊነት የተዋሃደው ነው። በዚህ ስራ ለኔ አዲስ አዘፋፈን አሳይቼበታለሁ። ግጥሞቼም በይበልጥ እዚሁ ሆኜ የማየውና ህብረተሰባዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ በመሆኑ ነው “አይዞን” ያልኩት። በዚህ አልበም ውስጥ ሔኖክ መሃሪ እና ኤልያስ መልካ በሙዚቃ ቅንብርና ግጥም፤ ሁናንተ ሙሉ፤ ይህ ልጅ ወጣት የሙዚቃ ፕሮዲዩሰር ነው። ይልማ ገ/አብ ግጥም፣ ጋሽ አየለ ማሞም ተሳትፈውበታል። በዚህ አጋጣሚ ከእነዚህ ሰዎች ጋር በመስራቴ በጣም ደስ ይለኛል።

ሰንደቅ፡-በሙዚቃ ኮንሰርት የት -የት አገራትን ዞረሃል?

ዘለቀ፡- አዎ! ሰሜን አሜሪካና አውሮፓ እንዳለ ሆኖ ካሪቢያን ፣ ኤዥያና ደቡብ አሜሪካ ሁሉ “ሙዚቃ የዓለም ቋንቋ ነው” ብለን ዞረናል። በእውነቱ ከመቶ ሰው እስከ 100ሺህ ሰው የታደመበትን ኮንሰርት የመስራት አጋጣውን አግኝቻለሁ። በሰራኋቸው ኮንሰርቶች ሁሉ የሙዚቃን ኃይል አይቼበታሁ። እንደውም አንድ ጊዜ የሆነ አውሮፓ ሀገር፤ ፊላንድ ይመስለኛል ከዚጊ ማርሌ ጋር ኮንሰርት አቅርበን ሰው እንግሊዝኛ ተናጋሪ አይደለም ግን ግጥሙን ይዘው አብረውን ይዘፍኑ ነበር። ይህ በጣም ይደንቃል። ይህን የሙዚቃ ፌስቲቫል ወደሀገራችን ለማምጣት ብንፈልግም አቅም የሚጠይቅ ሆኗል።

ሰንደቅ፡-ሬጌ የሙዚቃ ስልት ላንተ ምን የተለየ ትርጉም ይሰጥሃል?

ዘለቀ፡- ሙዚቃ ሁሉ ህዝብ ለህዝብ መግባቢያ ነው። ሬጌን በተመለከተ ግን ከኢትዮጵያ ጋር ትልቅ ቁርኝት አለው። በመንፈሳዊው ብትል የሬጌ ምት ጋር የተቀራረበ ነው። ሬጌ ሙዚቃ በይበልጥ ትግልና የተቃውሞ ሃሳብን ለመግለፅ የሚሰራ ነበር የተጀመረው። እኔ ለምሳሌ አሜሪካ እንደገባው ሙዚቃን መማር ስጀምር ክላሲካል፣ ብሉዝና ጃዝ ብቻ ነበር። ሬጌ ሲመጣ ነገር ሁሉ ወዲያው ተለውጦ መልእክቱ ላይ ማተኮር ተጀመረ። እንደውም እነ ቦብማርሌ የሚሉት ምንድነው? የሬጌ ምቱ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የከበሮ ምት ነው የመጣው ይላሉ። ተማሪ እያለን ደግሞ ጥናት ስናደርግ አንዳንድ ዘፈኖች ጊታር ብቻ ጨምረህ ስትጫወተው በቀላሉ ሬጌ ስልትን ይሆናል። ለምሳሌ ለክቡር ዶክተር አርቲስት መሀሙድ አህመድ ጉራጊኛው “አሽቃሩ”ን ተመልከት በሬጌ ስልት ስዘፍነው ቋንቋውን የማያውቁት ብዙ የውጪ ዜጎች ይወዱት ነበር። ሌላው የጋሽ ጥላሁን የኦሮምኛ ዘፈንም እንዲሁ ነው። ሁለቱም የጊታሩ ምት ብቻ ነው የተቀየረባቸው፤ ግን ወዲያው ሬጌ መስለዋል። የጃማይካ ተመራማሪዎች ባደረጉት ጥናት ሬጌ አፍሪካዊነቱ ተረጋግጧል ይላሉ። (ሳቅ)

ሰንደቅ፡-አንጋፋ ኢትዮጵያውያን የሰሯቸውን ዘፈኖች ቋንቋው የውጪ በማይገባቸው ዜጎች ስታቀነቅን አብረውህ ይጫወታሉ። ይህ አይነቱ መግባባት ከምን የመነጨ ይመስልሃል?

ዘለቀ፡- ነገሩ ሙዚቃ የዓለም ቋንቋ ነው፤ ይበልጥ ግን መልዕክት ቢኖረው ጥሩ ነው። የውጪ ዜጎች ከኔ ጋር ብቻ ሳይሆን ከጋሽ መሐሙድ አህመድ ጋርም እንዲሁ አብረውት ሲጨፍሩ ታይቷል። እኔ ምንድነው የማደርገው የሙዚቃውን “ቢት” እለውጠዋለሁ፤ ለምሳሌ የምኒሊክ ወስናቸው “እትት በረደኝ” የሚለውን ዘፈን ወስጄ “Shiver me!” አልኩት፤ ይሄኔ ፈረንጆቹ ያብዱለታል። ነገሩ እንዲገባቸው ያህል በእንግሊዝኛ ፍንጭ እሰጣቸዋለሁ ማለት ነው። (ሳቅ) ለምን ብትል ሬጌን የሚታደም ሰው ግጥም ላይ ያተኩራል ለዛ ነው ፍንጭ የምሰጣቸው።

ሰንደቅ፡-እስቲ የሙዚቃችን ደረጃ የት እንደደረሰ በአንተ ዕይታ አጫውተኝ?

ዘለቀ፡- ባገርምህ የማድረስ ጉዳይ ነው እንጂ በእውነቱ እኮ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቅኝቶች በዓለም የሙዚቃ መዝገበ ቃላት ውስጥ ተፅፈዋል። ይህ እንግዲህ በትምህርት ደረጃ ስታየው ነው። ከገበያ አንፃር ግን ብዙ አልገፋነውም። በ1960ዎቹ አካባቢ በእነጋሽ ሙላቱ አስታጥቄና በእነግርማ በየነ አማካኝነት ወደምዕራባውያኑ የመድረስ አጋጣሚን አግኝቶ ነበር። አሁን ላይ ግን ከሬጌው በስተቀር ለውጪ ዜጎች የምናደርሰው ነገር አጥሮናል። አንዳንድ አርቲስቶች ወደውጪ ሲወጡ ሙዚቃቸውን የሚያቀርቡት በተለይ ለኢትዮጵያውያን ታዳሚዎች ነው። እኔ ያለኝ ልምድ ግን ብዙውን የምሰራው ለውጪ ነው። አንድ ጊዜ ትዝ ይለኛል፤ “ህዝበ ለህዝብ” በሚል የተለያዩ ብሔር-ብሔረሰቦችን ባህልና ሙዚቃ የሚያሳይ ዝግጅት እንደነበር አይተናል። አሁንም ትንሽ ዘመናዊ ነገር ስልቶችን ተከትሎ ማቅረብ ቢቻል ሙዚቃችን ይወደዳል። ባለፈው ፕሬዝዳንት ኦባማ እዚህ በቆዩበት ጊዜ ሙዚቃችንን አይተው፣ “የአፍሪካን ስብጥር ማሳየት የሚችል የሙዚቃ አቅም አላችሁ” አለን፤ እኛ’ኮ ይህን ስንል አርባ ዓመት ሊሞላን ነው (ሳቅ) እና ምንድነው የኢትዮጵያ ሙዚቃ አድራሻ አጣ እንጂ በዓለም ለመታየት የሚበቃ ነበር ባይ ነኝ። አሁንም ቢሆን ጊዜ ይወስዳል እንጂ “International Rage Festival” ብለን ጀምረን የውጪ ሰዎች እዚህ መጥተው የኛን ሙዚቃ እንዲያዩ የማድረግ ሃሳብ አለን።

ሰንደቅ፡- እስቲ ደግሞስለቦማርሌ የሚሰማህን ነገር ንገረን?

ዘለቀ፡- ቦብ ለኔ የነፃነት አርበኛ ነው። አፍሪካዊ ነው። አእምሮን በሙዚቃ የቀየረ ሰው ነው። ለምሳሌ ስቲቪ ዎንደርና ጀምስብራዎን የሙዚቃ ስሜትን ፈጠሩ እንጂ አእምሮን የሚለውጡ መልዕክቶችን ማስተላለፍ የቻለ አእምሮን በማነቃቃት በይበልጥ የሚጠቀሰው ቦብ ማርሌ ነው።

ሰንደቅ፡-የቦብ ማርሌን ሀውልት ተከትሎ የተነሳ የሃሳብ ልዩነት ነበር፤ አንዴት ታየዋለህ?

ዘለቀ፡- ሰዎች ሀሳባቸውን በግራና በቀኝ መግለፃቸው ዲሞክራሲያዊ ነው። ከዚህ ቀደምም ሉሲን በሚመለከት ወደአሜሪካ ሄዳ እንድትጎበኝ የሚል ደብዳቤ ይዤ መጥቼ ነበር፤ ብዙ ሰዎች ነበሩበት እኔም አንዱ ነኝ። ያኔ ብዙ ክርክር ነበር። በኋላ ውጤቱ እንደታየው አሪፍ ሆኗል። አለማወቅ ሃጢያት አይደለም ይላል ፈረንጅ። ቦብን የሚያውቅ ሰው የቦብ ሀውልት ምን ያደርጋል ቢል መብቱ ነው። ጃማይካዎች እኛ “አፅሙ” ወደኢትዮጵያ መጥቶ እንዲቀበር ስንል፤ በፓርላማ ነው ወስነው “አይሆንም!” ያሉት። ለምን ትልቁ የቱሪስት ገቢያቸው ስለሆነ። ባይገርምህ ጀማይካ በቦብ ብቻ በዓመት እስከ 3 ሚሊዮን ዶላር ከቱሪስት ታገኛለች።

ሰንደቅ፡-ሀውልቱ ምን ያህል ጊዜና ገንዘብ ፈጀ?

ዘለቀ፡- ሰዓሊው ሲሰራው ወደ አምስት ዓመት ወስዷል። አጠቃላይ ወጪው ወደ 800 ሺህ ብር ነው። በነገራችን ላይ ኢምፔሪያል አካባቢ ሀውልቱ ሲቆም በማስተር ፕላኑ መሠረት እዛ አካባቢ በቀጣይ ስታዲየም ይገነባበታል ተብሎ ይጠበቃል። ቦብ ማርሌም ስፖርት ይወዳል። ለዛ ቦታው ጥሩ የተገጣጠመ ይመስለኛል።

ሰንደቅ፡-በምን ትዝናናለህ?

ዘለቀ፡- ማንበብ እወዳለሁ፤ ሙዚቃ እሰማለሁ፤ አሁን አንተ ከመምጣትህ በፊት ቤቱን በሙዚቃ ሳደባልቀው ነበር (ሳቅ)። ጉብኝት ደስ ይለኛል። ህይወት አጭር ስለሆነች ሁልጊዜ ዘና ለማለት እሞክራለሁ።

ሰንደቅ፡-ከ30 በላይ ት/ቤቶችን አስገንብተሃል፤ ከሙዚቃ ባለፈ በበጎ ተግባርህ የመታሰብ ፍላጎት አለህ?

ዘለቀ፡- ስሰራው በበጎ ለመታሰብ ብዬ አይደለም። አስፈላጊ ስለሆነ ነው። ዋናው ግን መንፈሳዊ ደስታን ለማግኘትና ለሌሎች ምሳሌ ለመሆን ነው፤ ከ15 ዓመታት በፊት ጀምረን ትምህርት ቤት ለመስራት የወሰነው። ለመጀመሪያ ጊዜ ለአድዋ 100ኛ ዓመት ወደኢትዮጵያ ስመጣ ለጉብኝት ወደሰሜን ሄጄ ብዙ ህጻናት ከትምህርት ውጪ መሆናቸው ነው ወደዚህ በጎ ተግባር የመራኝ። ድህነትን ለማጥፋት ቁልፉ ትምህርት ነው የሚል እምነት ነበረኝ። አሁን ላይ ኮሌጅ የገቡ ልጆችን አፍርተናል (ሳቅ)

ሰንደቅ፡-በስተመጨረሻ ማለት የምትፈልገው ነገር ካለ?

ዘለቀ፡- ሁላችሁንም እንኳን ለአዲስ ዓመት አደረሳችሁ፤ አዲሱ ሙዚቃዬን ሰምታችሁ እንደምትዝናኑ ተስፋ አለኝ። ኦርጅናል ስራውን በመግዛት እንዲያደምጡ እጋብዛለሁ፤ አመሰግናለሁ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
11521 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us