“ቴአትር እና ፊልም ሊዋዋጡ አይችሉም”

Wednesday, 12 February 2014 11:40

ደራሲ፣ ተዋይና ዳይሬክተር ንጉሱ ጌታቸው (ቅቤው)

 

የዛሬው እንግዳችን በፊልም፣ በቴአትርና በቴሌቭዥን ድራማዎች በተደጋጋሚ ያየነው ቢሆንም፤ የሙያ ባልደረቦቹ አብዝተው የሚያውቁት ግን በድርሰት ስራዎቹ ነው። የታሪካዊ ተውኔቶች ወዳጅነቱን ያስተዋሉ ወዳጆቹ ከሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ጋር ሲያመሳስሉት በአንጻሩ ደግሞ አምራች ፀሃፊነቱን የታዘቡ ሰዎች ከኬኒያዊው ደራሲ ኑጉጊ ዋቴንጎ ጋር ያመሳስሉታል። በትወናው በብዙዎች ልብ የቀረውና በርካቶችም የሚያውቁት “ገመና” በተሰኘው የቴሌቭዥን ተከታታይ ድራማ ላይ በስራውና “ቅባቱ” በተሰኘው ደላላ አማካኝነት ነው። ከአርቲት ንጉሱ ጌታቸው (ቅቤው) ጋር በቢሮው ጥቂት ተጨዋውተናል።

ሰንደቅ፡- አንተን ከማስተዋወቅ ስራዎችህን ማስተዋወቁ የሚቀል ይመስለኛል። ምን ያህል ስራዎችን ሰርተሃል?

ንጉሱ፡- በአብዛኛው የኔ ስራዎች የመድረክ እና የፊልም ፅሁፎች ናቸው። የመጀመሪያው ይፋ ስራዬ 1990 ዓ.ም በሀገር ፍቅር ለመድረክ የበቃው “እምቅ ምኞት” ነው። እዚህ ቴአትር ላይ ጸሐፊና አዘጋጅ ከመሆኔ በተጨማሪ አንድ ገፀ-ባህሪም ተጫውቻለሁ። ቀጥሎ የፃፍኩት “ጥምዝ” ቴአትርን ነው፤ ይህን ያዘጋጀው አብራር አብዶ ነው። አንጋፋ ተዋንያን ተጫውተውታል። ቀጥዬ የሰራሁት ደግሞ “የተቋጠረ ደም” ነው፤ በዚህም ላይ ከድርሰቱ በተጨማሪ በዝግጅትና በትወና ተሳትፌበታለሁ። በመቀጠል በአዲስ አበባ ባህልና ቴአትር አዳራሽ “ክፍተት” የተሰኘ ድርሰቴን ሰርቻለሁ፡፤ ከአብራር አብዶ ጋር በረዳት አዘጋጅነትም ሰርቼበታለሁ። በባህልና ቴአትር አዳራሽ ሌላኛው ስራዬ “ሰንኮፍ” ይሰኛል። ከነዚህ ስራዎች በኋላ ቀጣዮቹ ስራዎቼ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቴአትር ጥበባት ተማሪ ሳለሁ የሰራኋቸው ናቸው። በዩኒቨርስቲ ቆይታዬ በተለያየ የተውኔት ቅርፅ የሰራኋቸው ብዙ ስራዎች አሉኝ። ከህጻናት ተውኔት አፃፃፍ እስከ ቴአትር ለልማት ድረስ ማለት ነው።  

ሰንደቅ፡- ተማሪ እያለህ በባህላዊና ታሪካዊ ስራዎች ላይ እንደምታተኩር ሰምቻሁ፤ እስቲ ስለዚህ ነገር ንገረኝ?

ንጉሱ፡- አዎ! ለምሳሌ “ግርዶሽ” የተሰኘ ተውኔት ቴአትር ለልማት ከሚል አንጻር የተፃፈ ነው። “ግርዘት” የተሰኘ ስራዬ ደግሞ ከትውፊታዊ ተውኔት አንጻር የተፃፈ ነው። “የቡሎ ጫካ ንጉስ” ደግሞ ከህፃናት ቴአትር አንፃር የፃፍኳቸው ናቸው። ሌላው ደግሞ “የነፃነት ድምጽ” የተሰኘ ተውኔት ከሙዚቃዊ ቴአትር አንፃር፤ በሌላም በኩል “ከታብ” ከታሪካዊ ተውኔት አንጻር፤ ይህ ስራ በአፄ ቴዎድሮስና በአፄ ምኒልክ ዙሪያ የሚያጠነጥን ታሪክ ቀመስ ተውኔት ነው። በትውልድ መካከል የታሪክ ክፍተት እንዳይኖር ስለምሰጋ ነው ታሪኮች ላይ የማተኩረው።

ሰንደቅ፡- በርካታ ተውኔቶችን ፅፈሃል። በአንዳንዶቹም ላይ ተውነህባቸዋል፡ ፊልሙስ ላይ ተሳትፎህ ምን ይመስላል?

ንጉሱ፡- አብዛኞቹ በፕሮዳክሽን ሂደት ውስጥ ያሉ ናቸው። የመጀመሪያ ሊባል የሚችል ለኢትዮጵያም ሆነ ለአፍሪካ የፊልም ቅርፅ ፃፍኩት እኔ ነኝ ብዬ አስባለሁ፤ ነገር ግን ጥናቱ የለኝም። ይህም በትሪሎጂ ይሰኛል። (አንድ አይነት ሀሳብ ያላቸው ሶስት ተከታታይ ክፍሎችን የያዘ ስራ መሆኑ ነው) ለምሳሌ ከውጪዎቹ እንደ “Lord of the ring” እና እንደእነ “Matrix” አይነት ቅርፅ ነው የሰራኋቸው። ርዕሱ “የጀግና ምድር” ይሰኛል። በተከታታይ ሲሰራም “የጀግና ምድር፤ ስምበሌት”፣ “የጀግና ምድር፤ ለውጥ” እና “የጀግና ምድር ህብር” ይሰኛሉ። በዚህ ስራ ውስጥ ገፀ- ባህሪያቶቹ ከ1982 እስከ 1990 መጨረሻ ይደርሰሉ። ስራው በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ሰራዊት ላይ ያተኮረ ነው። ይህ ሲባል ግን የአፄ ኃይለስላሴ ጦር፣ የደርግ ጦር፣ የኢህአዴግ ጦር የሚል ሳይሆን በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ጦርን የተመለከተ ነው። የአገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅ መሰዋትነት ለከፈሉ ጀግኖች ሁሉ መታሰቢያ ሆኖ የተሰራ ፊልም ነው።

ሌላኛው ስራ ከዮናስ ብርሃነ መዋ ጋር እየሰራሁት ያለ ነው። “S26” የሚሰኝ ኮሜዲ ፊልም ነው። ይህ ስራ የአንድን ሰው የሙሉ ቀን ውሎ መሰረት አድርጎ የተፃፈ ነው። ሶስተኛው ፊልም “ስጋት” ይሰኛል፤ የቤተሰብ ታሪክ ነው። ይህም በሂደት ላይ ያለ ስራ ነው። አራተኛው ስራዬ ህፀ-ህይወት አበበ እና ሳያት ደምሴ ፕሮዲዩስ ሊያደርጉት የያዙት ስራ ነው በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ታሪክ ላይ የሚያጠነጥን ሙዚቃዊ ፊልም ነው። በዘወጉም አዲስና የመጀመሪያ ነው ብዬ የማስበው ስራ ነው።

ሰንደቅ፡- ከትወናው ይልቅ ወደፀሃፊነት ያጋደልክበት ምክንያት ምንድው?

ንጉሱ፡- አጀማመሬ የሚገርም ነው። የቴአትር ሰው መሆኔን አላውቅም ነበር። ተማሪ እያለሁ ነገር ሲደጋገም ቶሎ እሰለቻለሁ። ለምሳሌ አንድ መምህር ትናንት ያስተማረውን ነገር ዛሬ ሲደግመው ሳይ ደስ አይለኝም። ተወልጄ ያደኩት ልደታ ቢሪም ሜዳ አካባቢ ነው። ቤታችን ከሜዳው ከፍ ብሎ ቢገኝም ከሰፈር ልጆች ሁሉ ኳስ የማልችለውና የማልወደው እኔ ነበርኩ። ያኔ እኔ ተረት ማንበብና ልቦለድ መፅሀፍት ማገላበጥ ነበር ስራዬ። አንዴ ካነበብኩ ደግሞ ታሪኩን ስለማልረሳው ለጓደኞቼ ከኳስ መልስ እተርክላቸዋለሁ። ይህ አጋጣሚ ይመስለኛል ሳይታወቅ ታሪክ ነጋሪ /ፀሀፊ ያደረገኝ። (ሳቅ)

ሰንደቅ፡- ከቴአትር ፅሁፍስ ጋር እንዴት ተዋወቃችሁ?

ንጉሱ፡- እንደነገርኩህ ነገር ሲደጋገም የምሰለች አይነት ሰው ነኝ። በአንድ ወቅት አዲስ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ አንድ መምህሬ ትምህርት ደግመው ሲያስተምሩን ብላክቦርዱ ያጠፋሁበትን “ዳስተር” ለማራገፍ ወደውጪ ወጥቼ ዳስተሩን በር ላይ አስቀምጬ ከክፍል ቀረሁ። የሚገርመው ደግሞ ያን ጊዜ ከዕረፍት ሰዓት ውጪ በግቢው ውስጥ አንድም ተማሪ ዝር አይልም ነበር። ምክንያቱም በጣም የሚፈራና ባሻ የሚባል የጉማሬ አለንጋ ያለው ጠባቂ ነበረን። ተማሪ በሙሉ በጣም ይፈራዋል። አጋጣሚ ዞር ስል ባሻ የሚባለው ጠባቂ አየሁት ከሩቁ። እሱም አየኝ። መሳደድ ጀመርን። የምወጣበት የለኝም። ቢቸግረን ዘልዬ የትምህርት ቤቱ አዳራሽ ውስጥ ዘው አልኩ፤ ያን ዕለት የሰዓሊ መስፍን ኃ/ማርያም እህት የነበረችው ሶፊያ ኃ/ማርያም መድረክ ላይ ቴአትር እየተለማመደች ነበር። ከእርሷ ጋር ኮሜዲያን ፋሲል ተካልኝ) እና ሌሎችም ነበሩ። አዘጋጅ አለ፤ የሙሉ ጊዜ ቴአትር ይሰራሉ። ተንደርድሬ አዘጋጁ’ጋ ቁጭ አልኩ። ባሻ መጣ፤ ፈለገኝ ሊለየኝ አልቻለም ግን ተጠራጥሮኛል። ግን “እዚህ ሮጦ የገባ ልጅ የለም?” ብሎ ሲጠይቃቸው በአንድ ድምፅ ሁሉም፤ “የለም!” አሉት። ባሻ እንደወጣ ከአዳራሹ መውጣት ነበረብኝ፤ ግን ቴአትር አፍዝዞ አስቀረኝ። ለመጀመሪያ ጊዜ ቴአትር የሚባለውን ነገር በልምምድ ደረጃ ሳይ ማለት ነው። ከዚያን ጊዜ በኋላ የክበቡ አባል ሆኜ ተመዘገብኩ።

ሰንደቅ፡- በክበቡ ውስጥ ምን ድርሻ ተሰጠህ?

ንጉሱ፡- ፀሀፊ አደረጉኝ። ትንሽ ቆየት ብሎ ደግሞ አዲስ አበባ ት/ቤቶች የስነ-ፅሁፍ ውድድር መዝጊያው በአዲስ ከተማ ት/ቤት ነበር የሚደረገው። እናም ትምህርት ቤታችን ልዩ ዝግጅት ማዘጋጀት ስለነበረበት እኔ ቴአትር እፅፋለሁ አልኩ። ግጥም አድርጌ የሙሉ ጊዜ ቴአትር ፃፍኩ። ቴአትር ሳላይ ቴአትር ፃፍኩ ማለት ነው። (ሳቅ)

ሰንደቅ፡- ምን የሚል ቴአትር ፃፍክ፤ በምንስ ዙሪያ?

ንጉሱ፡- “የጓደኛይቱ መዘዝ” ይላል፤ የተማሪ እና የትምህርት ቤትን ህይወት የሚያሳይ ቴአትር ነበር። ቴአትሩን አሁን አሜሪካን ሀገር የሚገኘው ሞላ የሚባል ጓደኛ አዘጋጀው። ከዚያን ጊዜ በኋላ የተገኘው ጭብጨባ የቴአትርን ስራ አስቀጠለን። 11ኛ ክፍል ስገባ የቴአትር ኮርስ ወሰድኩ፤ 1984 ዓ.ም “ሞዛርት” የተሰኘ የቴአትርና የሙዚቃ ማዕከል አቋቋምን። በወቅቱ በቴአትር የኛ ክበብ የበላይነቱን ሲይዝ በሙዚቃ ደግሞ “መስታወት ኢንተርቴይነምንት” የሚባሉና እነቴዎድሮስ ካሳሁን፣ እነአብነት አጎናፍርና ጎሳዬ ተስፋዬ የወጡበት ክበብ ነበር። የሚገርምህ ቴዲ ያን ጊዜአፍሮ በትወናም ጥሩ አቅም ስለነበረው እንዲተውን ሁሉ እጎተጉተው ነበር።

ሰንደቅ፡- ቴአትር የተጀመረው በግሪክ ሳይሆን በኢትዮጵያ ነው ብለህ ትሟገታለህ ይባላል፤ መከራከሪያህ ምንድነው?

ንጉሱ፡- አንደኛ ተውኔት በባህሪው የኑሮህ እንቅስቃሴ ነው። ምሁራኖቹ ቴአትር የሚሉት አዳራሹ፣ መድረኩና ተመልካቹ ሲሟላ እንደሆነ ይናገራሉ፡፤ ነገር ግን መድረክ ላይ የሚቀርበው ነገር ቴአትር ሳይሆን ተውኔት ነው። ያ ማለት ደግሞ ተውኔት ሲባል ከግዕዝ የተወሰደው ዕድሜ ለደበበ ሰይፉ ትርጉሙ ድርጊት ማለት ነው። ይህን ለማስረዳትና ቴአትር መነሻው ኢትዮጵያ መሆኑን ለማስረገጥ ኤፌሶን ፈስሶ፣ ጤግሮስ ፈስሶ፣ ኤፍራጢስ ፈስሶ አባይ (ጊዮን) ግን አጠጣ። ጊዮን ደግሞ የኢትዮጵያ ምድር ይከባል ይላል። ይህ ማለት አዳም እዛ ቦታ ነበር ማለት ነው። ይሄን ነገር ፈረንጆችም እያመኑበት የአዳም ዘረመል ተጠንቶ ምስራቅ አፍሪካ ላይ መሆኑ እያረጋገጡ መጥተዋል። ስለዚህ አዳም ከእግዜሩ ጋር ያወራ ነበር። ይህ ማለት ንግግር (ዲያሎግ) አለ፤ ገፀ-ባህሪያት አሉ፤ ገነት የተባው መቼት አለ። ሔዋን ስትመጣ ግጭት መጣ። ይህ ማለት ደግሞ የተውኔት አላባውያን እየተሟሉ ነው ማለት የሚያስደፍር ይሆናል።

ሰንደቅ፡- እነዚያ ሰዎች እየኖሩ ያሉት ኑሯቸውን ነው፤ ታዲያ ቴአትር ነው ሊባል ይችላል?

ንጉሱ፡- እንደ እኔ እንቅስቃሴ ሲጀመር ተውኔቱ ተጀምሯል ባይ ነኝ። ነገር ግን እንዳልከው ወደዕውቀትና ወደካሪኩለም ቀረፃ አምጥተውት በጥቅስ ስናስቀምጠው ቴአትርን ከእይታ አልፈው የመድሃኒት አቅም ከሰጡት አንጻር እነርሱ (ግሪኮች) ይቀድሙናል። ይህም የሆነው ታሪኩ ምን መሰለህ? ከአቴንስ አጠገብ ይኖሩ የነበሩት ስፖርታ የተባሉ ህዝቦች ነበሩ። እነዚህ ህዝቦች ግዙፍና ስፖርተኞች ነበሩ። አቴናውያን ደግሞ የፅሁፍና የንባብ ሰዎች ናቸው። ከዚህም ሌላ ቀጫጭኖችና ደቃቃዎች ናቸው። ታዲያ ስፖርታውያንን ከእንስሳነት ባህሪይ ለማውጣት እንዴት እንዲያነቡ እናርግ የሚል ሀሳብ ተነስቶ የቀረበው መፍትሄ ከስፖርትና ከትግል መጥተው ሲያርፉ እያነበበ የሚመለከተውን ነገር እንፍጠርለት የሚል ነበር። ይህ ነው የቴአትር መነሻ ሊሆን የቻለው ይሉናል። ይህን አድርገው ሳይንሳዊ ፍልስፍናውን በማርቀቅ ደረጃ ግን ግሪኮች ይቀድሙናል ለማለት ነው።

ሰንደቅ፡- ፊልሞች በብዛት እየተሰሩ ቢሆንም፤ ቴአትሮችም በአንድ ቀን በአንድ መድረክ ላይ ሁለት ስራዎች ለተመልካቹ በመቅረብ ላይ ናቸው። አንዱ አንዱን እየዋጠ ነው ብለህ ታስባለህ?

ንጉሱ፡- ቴአትርና ፊልም ሊዋዋጡ አይችሉም። በውጪው አለምም ሲኒማ ከመምጣቱ በፊት ቴአትር ብቸኛው ነበር። ግብጽና አሜሪካም በተለይ ደግሞ ፈረንሳይ በኮሜዲ ስራዎቿ እንሞሊየር በተፈጠሩበት ጊዜ ማለት ነው። ያ ዘመን የቴአትር ወርቃማ ዘመን ነበር። ስፔንም እንዲሁ፤ እንግሊዝም እነሼክስፔርን የፈጠረችበት ወቅት ነበር፡፤ ቴአትር ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ድረስ የመጣ አቅም አለው። ፊልም የመጣው ወደ20ኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ አካባቢ ነው። በጣም የሚገርምህ የፊልምን ፍልስፍና አለም ባወቀው በ15 ዓመት ጊዜ ውስጥ ነበር እኛ ያወቅነው። ግን እዛው ቆመ መሰለኝ ዘገየን። ዓለምም ላይ ቢሆን ፊልም ሲመጣ የቴአትር ተመልካች ቀንሶ ነበር። በእኛም ሀገር ይህ ክስተት ነው የመጣው እንጂ ቴአትር ደክሞ በፊልም ተውጦ አይደለም።

ሰንደቅ፡- የ“ገመና” ድራማ ላይ የተጫወትከው የደላላው ገፀ-ባህሪይ “ቅቤው” የሚለውን ቅፅል ስም አስለጥፎብሃል። እስቲ ስለድራማው እናውራ?

ንጉሱ፡- የሚገርመው ቅባቱን (ደላላውን) እኔ ልስራው አልነበረም። ፕሮዳክሽኑን የሚሰራው ድርጅት ውስጥ ግን ነበርኩኝ። በሜጋ ኪነ-ጥበባት ማዕከል ኤክስፖት ነበርኩ፤ ከኢቲቪ ጋር 40 ክፍል ያለው ተከታታይ ድራማ ለመስራት ጨረታውን አሸነፍን። ሀሳቡ ሲገባ የድራማው ርዕስ “ሰርጎ ገብ” ነበር በኋላ ነው “ገመና” የተባለው። ሀሳቡ በጣም አሪፍ ነው፤ ደራሲው አዶኒስም በጣም ጎበዝ ፀሀፊ ነው። ተፅፎ ተዋንያን ሲመረጡ የደላላው ገፀ-ባህሪይ የተሰጠው ለአለማየሁ ታደሰ ነበር። አሌክስ ደግሞ በዛን ሰዓት ወደ አሜሪካን ለመሄድ ፕሮሰስ ስለነበረው በጣም ተጨነቀ። ተከታታይ ድራማ ስለሆነ ከተጀመረ አቋርጦ መሄድ አይችልም። በመጨረሻ ለስራ አስኪያጃችን ነገረው፤ እሺ ተብሎ እርሱ ሄደ። ከዚያም አዘጋጆቹ ሄኖክ አየለና አሸብር ካብታሙ ቁጭ ብለው ምን እናርግ ሲባል “ይሄንን ገፀ-ባህሪይ ንጉሱ ሊጫወተው ይችላል” ሲል ሄኖክ አየለ ሀሳብ አቀረበ። ኧረ አይሆንለትም ቢሉት በ10 ጣቴ እፈርማለሁ ብሎ እኔ እንድጫወተው ተወሰነ። ከዚያ ሰፈሬ የማውቃቸውን ደላላ ማጥናት ጀምርኩ። የተማሩ አይደሉም፤ ሰራተኛ ሲያስቀጥሩ ግን ፍፁም ታማኝ፣ ፍፁም ባለሙያ አድርገው ነው ተያዥ ሆነው የሚያስቀጥሩት። ይሄኛው የ“ገመና” ገፀ-ባህሪይ ግን ብልጥነት ይጨምራል። ይህ ገፀ-ባህሪይ አሁን ድረስ ተፅዕኖ የፈጠረብኝ ገፀ-ባህሪይ ሆኖ አልፏል። ይህ ተጽዕኖ ደግሞ በጓደኞቼ ድረስ ወርዶ ፀሐፊ መሆኔን ከማመን ይልቅ የደላላ ገፀ-ባህሪይ እንደምጫወት ብቻ የሚያውቁ በዝተዋል።

ሰንደቅ፡- እስካሁን ከሰራሃቸው የምትወዳቸው ባህሪያት የትኞቹ ናቸው?

ንጉሱ፡- “ገመና” ድራማ ላይ የተጫወትኩት ቅባቱ ደስ ይለኛል። በተረፈ ደግሞ “ይሉኝታ” ፊልም ላይ የተጫወትኩትም ገፀ-ባህሪይ ደስ የሚለኝ ነው። ስካር የሚስጥር መደበቂያውን የሚነሳው ገፀ-ባህሪይ ስለሆነ ደስ ይለኛልም፤ ያሳዝነኛልም። ከግሩም ኤርሚያስ ጋር ነው የተጫወትነው።

ሰንደቅ፡- ከልጅህጋ ፊልም ሰርተሃል?

ንጉሱ፡- አዎ! ርዕሱ “ረቂቅ” ይሰኛል፤ ዳይሬክተሩ አለምሰገድ ዘውዱ ነው። በዚህ ፊልም ላይ ዳይሬክተሩ ልጄን ምንያህል እንደምወዳት እያወቀ ክፉ አባት ሆኜ እንድጫወት አድርጎኛል።

ሰንደቅ፡- ልጅህ ወደፊት ያንተን ፈለግ የምትከተል ይመስልሃል?

ንጉሱ፡- ልጄ ያኔት ንጉስ ትባላለች። “ረቂቅ” ፊልም ላይ የሙሉ ጊዜ ድርሻ ተሰጥቷት ትጫወታለች። ራሷ ረቂቅ ናት። እኔ እንኳን በኔ መንገድ ትመጣለች ብዬ አላስብም ነበር። ዳይሬክተሩ ጓደኛዬ ነው። ሌላ ፊልም ለመስራት እኔ ቤት በተገናኘንበት ወቅት ነው ያያትና የመረጣት። አይሆንም ብለውም እኔ ያየውት አቅም አለ ብሎ ነው መሰለኝ ድርቅ አለ። ከዚያ እሺ ተብሎ ከእናቷ ጋር ድርሰት ጥናት ጀመረች። በነገራችን ላይ እናቷም የመከላከያ መዝናኛ ክፍል ኃላፊናት፤ ሻምበል ፍቅርተ አለማየሁ ትባላለች። አጥንታ መጥታ ስትተውን ሁላችንንም አስገርማናለች። ወደፊት በትወናው ከሄደችበት የራሷ ምርጫ የተጠበቀ ነው።

ሰንደቅ፡- ወደፊት በየትኛው ዘርፍ ነጥረህ የምትወጣ ይመስልሃል?

ንጉሱ፡- እንዳልከው ብዙ ነገሮችን እነካካለህ። እተውናለሁ፣ እፅፋለሁ፣ አዘጋጅቻለሁ፣ አስተምሬያለሁ፤ ብዙ ነገሮች አልፈዋል። ይሄ ጉልበት እስካለ ድረስ ነው ሁሉም ቦታ የምገኘው። ግን እየጠራሁ ስሄድ ፀሐፊ ብቻ ሆኜ የምቀር ይመስለኛል። በነገራችን ላይ ፀሐፊ ተውኔት መንግስቱ ለማም ሆኑ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ሲጀምሩ አዘጋጆች ነበሩ። በኋላ ግን ፀሐፊያን ብቻ ሆነው ቀርተዋል፡፤ በተለይም እድሜህ እየጨመረ ሲመጣ የመፃፍ አቅምህም አብሮ ያድጋል ብዬ አስባለሁ።

ሰንደቅ፡- ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ?

ንጉሱ፡- እኔም ስለሰጠኸኝ እድል አመሰግናለሁ።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
7248 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us