“ኮሜዲ ማለት ፍልስፍና ነው”

Wednesday, 30 September 2015 13:41

“ኮሜዲ ማለት ፍልስፍና ነው

ኮሜዲያን አሰፋ ተገኝ

በቅዳሜና እሁድ የሬዲዮ መዝናኛ ፕሮግራም ላይ በሚያቀርባቸው ጭውውቶቹ ይበልጥ ይታወቃል። በቅርቡም በተለያዩ መድረኮች ከሚያቀርባቸው የኮሜዲ ስራዎቹ በተጨማሪ በፊልም ብቅ ብሎ ስለአበበ ቢቂላ በሚተርከው “አትሌቱ” እና “አዶናይ” ፊልሞች ላይ ታይቷል። በቴአትር መስኮት፣ ቦሊቦልና ሌሎችንም ሰርቷል። በቲቪ በርካታ ድራማዎችን የሠራ ቢሆንም በቅርቡ እየጎላ የመጣበት “ቤቶች” ተከታታይ ድራማ ተጠቃሽ ነው። የዛሬው የመዝናኛ እንግዳችን ኮሜዲያን አሰፋ ተገኝ ነው።

ሰንደቅ፡- ለማሟሟቅ ያህል እስቲ ስለጀመርክበት ጊዜ እንጨዋወት?

አሰፋ፡- እሺ እንግዲ ማሟሟቅ ካልከው፤ እኔ እስከዛሬ በዱብዱብ ነበር ማሟሟቅ የማውቀው እስቲ ደግሞ በወሬ እናሟሙቀው። በፕሮፌሽናል ደረጃ ስራ ከመጀመሬ በፊት በትምህርት ቤት “በትምህርት ቤት ሚኒሚዲያ” ውስጥ የነበረኝ ተሳትፎ ቀላል አልነበረም። ያም ጥረቴ ገና ተማሪዎች ሳለን በተለይ በኢትዮጵያ ሬዲዮ የቅዳሜና እሁድ መዝናኛዎች ላይ ጭውውት በማቅረብ እድሉን አግኝቻለሁ። ያኔ ነፍሱን ይማረውና ከአብርሃም አስመላሽ ጋር ነበር የምንሰራው። ከዛ ነው እያልን ወደቲቪና ወደመድረክ ስራዎች ያደግነው ማለት ይቻላል።

ሰንደቅ፡- ፕሮፌሽናል ሆኜ መስራት ጀምሬያለሁ የምትለው መቼ ነው?

አሰፋ፡- ለኔ ፕሮፌሽናል ሆኖ መስራት የመጣው በአንድ ጊዜ አይደለም። በተደጋጋሚ በመስራትና የህዝብን ምላሽ በማስተዋል የሚመጣ ነው። ተመልካችን በተደጋጋሚና በሚያሳምን ብቃት ካስደሰትከው ፕሮፌሽናል ሆነሃል ማለት ነው።

ሰንደቅ፡- እራስህ ሰርተሃቸው እንደአዲስ ራስህን ስለሚያዝናኑህ ስራዎችህ ብንጨዋወት ደስ ይለኛል። ለምሳሌ የትኛውን ገፀባህሪይ በተለይ ታስታውሰዋለህ?

አሰፋ፡- ብዙ ናቸው፤ ለምሳሌ በአንድ ወቅት የአብርሃም ወልዴ ስራ የሆነው “እማ ትርፌ” የተሰኘው ድራማ ላይ “ግዞ” እና “ባይከዳኝ” የሚባሉት ገፀ-ባህሪያት ሲጣሉ እነርሱን ለማስታረቅ የምገባው እኔ ነበርኩ። ነገር ግን በአስታራቂነቴ መካከል የእነሱ ነገር የባሰ ብጥብጥና መደናቆር ሲፈጥር ይታያል። የኔ ገፀ ባህሪይ ሰዎቹን ለማስታረቅ የነበረው ጥንካሬ አሁን ድረስ የማልረሳው ነው።

ሰንደቅ፡- በጣም ታዋቂ አድርጎኛል የምትለው ስራህ የቱ ነው?

አሰፋ፡- እንግዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በቲቪ ብቅ ያልኩት ዘግይቼ ነው። እንደነገርኩህ እኔ የኮሜዲ ጽሁፎችን እየፃፍኩ እሰጣለሁ እንጂ አልተውንም ነበር። አንድ ቀን ግን ትንሽ አጠር ያለው “አቢሎ” እና መኮንን ተፈሪን መድቤያቸው ስራውን ጊዮን ሆቴል ለመስራት ተስማምተን ነበር። ያን እለት “አቢሎ” ሳይመጣ ቀረ ያኔ እኔ ሸፍኜ እጫወታለሁ አልኩና ገባሁበት። ተቀርፆ ሲተላለፍ ለምንድነው እስከዛሬ ይሄን የመሰለ ችሎታ እያለህ የማትሰራው ተባልኩ። ያኔ ታዲያ የኔ ገፀ ባህሪይ “ዘገየ” የሚባልና ሙድ የሚያዝበት ስለነበር፤ በወቅቱ ሰዎች ምግብም አዘው “ዘገየ” ይላሉ፤ ደሞዝም ትንሽ ቀረት ሲል “ዘገየ” ነው እና ያ ገጸ ባህሪይ በጣም ተወዶልኝ ታዋቂ አድርጎኛል ማለት እችላለሁ።

ሰንደቅ፡- በኮሜዲ ስራ ውስጥ አጫጭር ስራዎች ናቸው ወይስ በፊልምና በሙሉ ሰዓት ደረጃ የሚሰራው ነው ላንተ በጎ ተጽዕኖ ያለው የሚመስልህ?

አሰፋ፡- የምትሰራቸው ስራዎች የራሳቸው ባህሪይ አላቸው። ረጅም ስራዎች ሀተታና አስረጂነትን ይጠይቃሉ። ስለዚህ ምክንያቶችህን ለተመልካቹ በአሳማኝ ሁኔታ ማቅረብ መቻል አለብህ። ኮሜዲ በተለይም ጭውውት ውስጥ ሰርተህ የፈለከው ቦታ ላይ በፈለከው አጭር ሰዓት ውስጥ ሰርተህ መጨረስ ትችላለህ። ብቻህንም ሆነ ኮሜዲን መስራት ትችላህ። ለዛም ነው ኮሜዲ የጥበቡ ቁንጮ ነው የሚባለው። ኮሜዲ በሰዎች የውይይት ሃሳብን ብልጭ የሚያደርግ ጥበብ ነው።

ሰንደቅ፡- እስቲ ደግሞ አሁን አንተን ስለሚያዝናኑህ የሀገር ውስጥና የውጪ ኮሜዲያን ንገረኝ?

አሰፋ፡- እንግዲህ ኮሜዲ በራሱ በንግግርና በድርጊት የሚገለፅ ነው። በድርጊት ስለተሞላ ኮሜዲ ሳስብ ሁሉ ነገሩ የሚያስቀኝ ቻርሊ ቻፕሊን ነው። ወደሀገራችን ስንመጣ ግን ብዙ ልጆች አሉ። እከሌ - ከእከሌ አልልም።

ሰንደቅ፡- አንድ ሰው ለመጥቀስ ይቀየሙኛል ብለህ ፈርተህ ነው?

አሰፋ፡- አይደለም!. . . ሁሉም የራሳቸው ችሎታ አላቸው። በተለይ ግን ጥቀስ ካልከኝ ፍልፍሉ በጣም ደስ ይለኛል። ጎበዝ ነው፤ በደንብ ካየኸው ቀልድ ብቻ ሳይሆን ቁም ነገርም የሚያውቅ ሰው ነው።

ሰንደቅ፡- ኮሜዲ ማለት ላንተ ምንድነው የሚሰጥህ ትርጉም?

አሰፋ፡- ኮሜዲ ማለት ሌላ ነገር አይደለም፤ ኮሜዲ የህይወት ፍልስፍና ማለት ነው። ሰዎች ያላዩትን “አንግል” (አቅጣጫ) አጉልተህ ማሳየት ነው። ማህበረሰቡ ከለመደው ነገር ውጪ የሆነ ነገር ይዘህ ስትመጣ ነው ኮሜዲ የሚባለው። ያንን ለማድረግ ግን ሰዉ የለመደውንም ሆነ ያለመደውን ነገር ጠንቅቀህ ማወቅ አለብን። ሁለት የተቃረኑ ስሜቶችን አስታርቀህ በሰዎች ዘንድ አግርሞትና ሳቅ መፍጠር ነው፤ ኮሜዲ ማለት።

ሰንደቅ፡- በኮሜዲ ታዋቂ መሆን በማህበራዊ ህይወት ላይ የፈጠረብህን ጫና ንገረኝ እስቲ?

አሰፋ፡- ኮሜዲያን መሆን አንዳንዴ በማህበራዊ ህይወታችን ላይ ጫና አለው። ሁሉንም ነገር እንደየአመጣጡ ለማስተናገድ መሞከር ግን መዘጋጀት ያስፈልጋል። ለምሳሌ ለቅሶ ቤት ሌላ ሰው ቢሄድም ባይሄድ ምንም ላይመስል ይችላል። የእኔ መሄድ ግን አስፈላጊ ነው፤ ለምን ቢባል እዛ ካሉት ሰዎች ጋር በመጨዋወት ማፅናናት ይቻላልና። በሌላ በኩል ግን ለቅሶ ቤት ሄደህ ባንተ የሚስቁ ሰዎች ለቅሶውን ሊያበላሹት ይችላሉ (ሳቅ) ቁም ነገር ብለህ የምትሰራው ስራ ሁሉ ቀልድ የሚመስላቸው ሰዎች ብዙ ናቸው።

ሰንደቅ፡- እስቲ ደግሞ ስለግል ህይወትህ ንገረኝ፤ አሴ አግብተሃል እንዴ?

አሰፋ፡- ወደዚያው ነኝ፤ ጓደኛ አለችኝ።

ሰንደቅ፡- ትውውቃችሁ እንዴት ነበር?

አሰፋ፡- ህይወት አጋጣሚ ናት። አንተ እንደኮሜዲያን ለህዝብ ነው የምትኖረው፤ ህዝቡ ካንተ አንድ ነገር ይጠብቃል። የትም ቦታ ስትሄድ “እንወድሃለን፤ እናከብርሃለን” ባሉህ ቁጥር ኃላፊነት ነው የሚያሸክሙህ። በዚህ ሁሉ መካከል ያገኘኋት ልጅ ናት። እንግዲህ ሁሉን ችላ አብረን ቀጥለናል ማለት ነው።

ሰንደቅ፡- “ቤቶች” ድራማ ላይ “ባሻን” አሳይተኸናል፤ እንዴት አገኘሃቸው? ባሻ እንዴት አይነት ሰው ናቸው?

አሰፋ፡- ባሻ ለኔ ኢትዮጵያዊ ቀለም ያላቸው፤ አባቶቻችንን በከፊል መወከል የሚችሉ ሰው ናቸው። በየዋህነት የሚሳሳቱ ነገር ግን ስህተታቸውን ቂም የማትይዝበት አይነት ሰው ናቸው። በአካባቢው የተሻልኩ ነኝ የሚሉ፤ ያንተ ልጅ የኔ ልጅ ነው የሚሉ አይነት ገፀ-ባህሪይ ናቸው።

ሰንደቅ፡- “ቤቶች” ድራማ ጀርባ ብዙ የሚያስቁ ነገሮች እንዳሉ ሰምቻለሁ። እስቲ ስላልሰማናቸው ነገሮች አጫውተኝ?

አሰፋ፡- በጣም ብዙ ናቸው። ለምሳሌ በአንድ ወቅት በድራማው ውስጥ የአንድ ሚሊዮን ብር ሎተሪ ደርሶኝ ነበር። በወሬ በወሬ ለካ ሰፈር አካባቢ አንድ ሚሊዮን ብር ደርሶታል የሚል ነገር ተሰምቷል። እውነት መስሎት የተቀበለ ሰው አለ። ታዲያ አንዴ ምን አደረገ ልጆች አሰባስቦ አደራጀና ለስፖርት ትጥቅ ብር እየዞሩ እንዲጠይቁ አድርጎ ወደኔ ቤት ላካቸው። ቤት መጥተው አንኳኩተው ለስፖርት ትጥቅ መግዢያ ምናምን ብለው ጠየቁኝ። እኔም ያለኝን ብዬ 20 ብር ሰጠኋቸው። ለካ ሰውየው እዛው ነበር፤ “መልሱለት ይሄ ቋጣሪ” ብሎ ጮኸ። ምነካህ ኪሴን የማውቀው እኮ እኔ ነኝ ስለው ምን እንዳለኝ ታውቃለህ? “ገብጋባ አንድ ሚሊዮን ብር ሎተሪ ደርሶህ 20 ብር ብቻ ትሰጣለህ” ብሎ እሪ አለ። (ሳቅ) አንዴ ደግሞ “ቤቶች” ድራማን እየተቀረፅን መስሎት ነው፤ እኛ ልጁን አናውቀውም። ለካ እርሱ ያጨሳል፤ ቤተሰቡ ደግሞ ማጨሱን አያውቅም። ድንገት ገብተን ካፌ ከልጁ አጠገብ ቁጭ ከማለታችን እየተቀረፅን መስሎት እየሮጠ መጣና “እኔን ከቤተሰብ ጋር ታጋጩኛላችሁ፤ ሳጨስ የቀረፃችሁኝን አጥፉልኝ” ብሎ አገር ይያዝልኝ አለ። ኧረ እኛ ሻይ ለመጠጣት ነው ቀረፃ ብሎ ነገር የለም። ደግሞም ሕጉ ሳናስፈቅድ መቅረፅን አይፈቅድልንም ብለን አስረድተነው ነው በስንት መከራ የተገላገልነው።

ሰንደቅ፡- ብዙ ጊዜ የምትሰራቸው ገፀ ባህሪያት ሽማግሌዎች በመሆናቸው ስራህ ዕድሜህን የነጠቀህ አይነት ስሜት ተሰምቶህ ያውቃል?

አሰፋ፡- አዎ! ብዙን ጊዜ እኔ በምጽፋቸው ስራዎች ላይ ሽማግሌዎች ካሉ ሌሎች እንዲሰሩ ብፈልግም አብረውኝ የሚሰሩት ሁሉ እኔ እንድሰራ ነው የሚያስገድዱኝ። አንድ ጊዜ እንደውም አንድ ድራማ ሽማግሌ ሆኖ ተሰርቶ ኤዲት እየተደረገ፤ አዘጋጁ ይሄ ቀርቶ እንደገና አሰፋ ይስራው በማለቱ ድጋሚ ገብቼ የሰራሁት ስራ አለ። እናም ባለሙያውም ተመልካቹም የኔን የሽማግሌ ገፀ ባህሪይ ከወደደው ዕድሜዬን ተሰርቄያለሁ ማለት ነው (ሳቅ)

ሰንደቅ፡- ምን ያዝናናሃል?

አሰፋ፡- መጀመሪያ ከተመልካች ሁሉ በፊት እኛ ነን በምንሰራው ስራ የምንዝናናው። እኛኮ ህዝቡ ቢያውቅ ሊከሰን ሁሉ ይችላል። ወደብዙሃን መገናኛው /መድረክ/ ከመቅረባችን በፊት እኛ ስንቴ ስቀን አስተካክለን ነው የምንመጣው። እንደወረደ የሚስቀው ባለሙያው ብቻ ነው። ተመልካቹ የተስተካከለውን ስርዓት የያዘውን አይቶ ነው የሚስቀው እኔ ከቀረፃ /ከመድረኩ በፊት ያለው ጊዜ ሁሉ በጣም ያዝናናኛል።

ሰንደቅ፡- ኮሜዲያን በበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ እየተሳተፋችሁ ነው። እንዴት ተጀመረ?

አሰፋ፡- አዎ! ነገሩ እኛ የጀመርነው ቆየት ብለን ነው። ከሜሪጆይ ኢትዮጵያ ጋር ለረጅም ዓመታት ሰርተናል። ትልቁ ዓላማችን የነበረው ህጻናትን ከጎዳና አንስቶ የመማር ዕድል እንዲያገኙ ነው። አሁን ደግሞ ከሙዳይ በጎ አድራጎት ጋርም እንዲሁ ተቋሙ ህጻናቱን የሚያስተዳድርበት ገቢ እንዳጣ ስንሰማ፤ ለምን አንድ ነገር አናደርግም በሚል ሰብሰብ አልን። ልጆችን ማሳደግ በጣም ከባድ ኃላፊነት ነው። ስለዚህ ተቋሙን ለመርዳትና ለማስተዋወቅ በሚል ሊስትሮ ሆነን ጫማ ጠርገናል። ውጤቱም አሪፍ ነበር፤ በቀጣይም ብዙ እንደምንሰራ ተስፋ አለኝ። በዚህ አጋጣሚ የደገፉንን ባለሀብቶች፣ የሚዲያ ባለሙያዎችና በአጠቃላይ ህብረተሰቡን ማመስገን እፈልጋለሁ።

ሰንደቅ፡- በጫማ ጠረጋው ወቅት ምን አጋጠማችሁ?

አሰፋ፡- ብዙ የሚያስቅ ነገር ገጥሞናል። ግማሹ እየተቀረፁ ነው። ድራማ እየሰሩ ነው ይለናል። ብር ይሰጡናል ብለን ተስፋ የጣልንባቸው አንዳንድ ባለሀብቶች ጋር ስንሄድ ነጠላ ጫማ አድርገው እናገኛቸዋለን (ሳቅ). . . ጫማ መጥረጉ ይቀርና ወደጫማ ማጠብ እንገባለን። አንዳንዱ የሁለት ሺህ ብር ጫማ ጠርገንለት 20ሺ ብር ይሰጠናል። አንዳንዱ ደግሞ ካልሲዬን ቀለም አስነካችሁብኝ ብሎ ኩርኩም ይቃጣዋል። (ሳቅ)

ሰንደቅ፡- በቀጣይ ምን ለመስራት አስበሃል?

አሰፋ፡- የቴአትር ፕሮዳክሽን እየሰራን ነው በቅርቡ ይመጣል። የሙሉ ሰዓት ቴአትር ማዘጋጃ ቤት ሲከፈት ይጀምራል። ሌላው “የማለዳ ፍቅር” የሚል ቴአትር እንዲሁ በብሔራዊ ቴአትር በኩል ይዤ እመጣለሁ። ከዚያ ውጪ የፊልም ስራዎችም አሉ። እንግዲህ በሰፊው በስራ እንገናኛለን። . . . በዚህ አጋጣሚ ለአድናቂዎቼና ለተመልካቾቻችን ሁሉ እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሳችሁ ማለት እፈልጋለሁ። አመሰግናለሁ።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
17494 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1043 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us