“የተያዙና ያልተያዙ ቦታዎች” የሥዕል ትርዒት በጋለሪያ ቶሞካ

Wednesday, 07 October 2015 14:25

 

አርብ መስከረም 14 ቀን 2008 ዓ.ም አመሻሽ ላይ 17ኛው የጋለሪያ ቶሞካ የሥዕል ትርዒት “የተያዙና ያልተያዙ ቦታዎች” ወይም “Playing with Positive & Negative Spaces” በሚል ርዕስ ስር የቀረቡ 43 የሰዓሊ ቃልኪዳን ሾቤን ሥራዎች ለእይታ አብቅቷል።

“ምንም ነገር ከምንም አያንስም እንዲሉ፤ የሰዓሊ ቃልኪዳን ሾቤ የኪነ-ቅብ ሥዕላት ይዘትና ቅርፅ መነሻዎች፤ እንደማንኛውም ሰው ሁሉ በዕድሜ ጉዞዎቹ ያስቀራቸው የልምድ አሻራዎች ናቸው። ይኸውም፤ ተወልዶ በልጅነት ያደገባትና የተማረባት ሐዋሳ ከተማ እና በወጣትነቱ የጥበብ እውቀትንና ክህሎትን የቀሰመባት አዲስ አበባ ከተማ፤ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የህይወት ጐዳናዎቹ ብቻ ሳይሆኑ የፈጠራ ጥበቡ መገኛና ነፀብራቅ ናቸው።” ይህን ሀሳብ የተወሰደው  ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ ስለ ወጣቱ ሰዓሊ ቃልኪዳን በተዘጋጀው ካታሎግ ላይ ካሰፈሩት የሚነበብ ነው።

በዕለቱ የወጣቱ ሰዓሊ ወዳጆች አድናቂዎችና የስዕል አፍቃሪያን በተገኙበት ሳር ቤት በሚገኘው ጋለሪያ ቶሞካ በይፋ የተከፈተው ይህ የስዕል ትርዒት፤ ለቀጣዮች ሁለት ወራትም እንደሚቆይ ታውቋል። ስዕልን መጠበብ የጀመረው ገና በልጅነቱ እንደሆነ የሚናገረው ወጣቱ ሰዓሊ ቃልኪዳን ሾቤ፤ የእናቱን ወደጥልፍና ዲዛይን ማዘንበል ተከትሎ ለእሳቸው በሚሰራቸው ምስሎች እየተበረታታ ወደሙያው ፍቅር ረጅሙን መንገድ ስለመጀመሩ ይናገራል።

በጋለሪያ ቶሞካ ለብቻው ያቀረበው ሁለተኛ የስዕል ትርዒት ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም ከመሰል ሙያ አጋሮቹ ጋር ከስምንት ያላነሱ የጋራ የስዕል አውደ-ርዕይዎችን ለዕይታ ስለማብቃቱም ወጣቱ ሰዓሊ ያስታውሳል፤ ስለ ስዕል ሥራዎቹ ሲናገርም፤ በአብዛኛው በከተማው ውስጥ ባለው ምልከታ ላይ ተመስርቶ የሰራቸው ሥራዎች መሆናቸውን የሚገልፀው ቃልኪዳን፤ የከተማው ፈጣን ለውጥ በእኔ አዕምሮ ውስጥ የፈጠረውን ልዩ ምስል ነው በሥራዬ ላይ የከተብኩት “የስዕሎቼ ቀለማትና መስመሮች ሁሉ የከተማውን የተለያየ የለውጥ ጡዘት የሚያሳዩ ናቸው” ይላል።

በጋለሪያ ቶሞካ መፅሔትም ላይ ስለ ሥራዎቹ ባሰፈረው አስተያየት እንዲህ ይላል፤ “በዋናነት ስነ-ቅብ ላይ ባተኩርም ሌሎች የሥነ-ጥበብ ሥራዎችንም እሰራለሁ። በሙከራና በፍለጋ ላይ አተኩሬ እሰራለሁ። የሰው ልጅ ስሜቶች የተለያዩ እንደመሆናቸው፤ እነዚህ ስሜቶች ለየትኛውም ሰዓሊ የተመስጦ ምንጮች እንደሚሆኑ ይሰማኛል። ዓይኖቼ ንቁ ናቸውና ለምፈልገው ቅርፅ፤ መስመሮችና ቀለማት ምርጫዬ በሚገባ እጠቀማቸዋለሁ። በጥድፊያ የተሞላው፤ በከፍተኛ ለውጥ ውስጥ የሚገኘው የከተማ ህይወት በርዕሰ-ጉዳይ ላይ እንዳልቸገር በሚገባ አግዞኛል። በስራዎቼ ከአካባቢዬ ጋር የሚኖረኝ ግንኙነት ፈጣን ምላሽ ለመስጠት አልቸገርም። ከተማዬን፣ አካባቢዬን በጥሞና ተመልክቼ፤ ጃዝ ሙዚቃን እየኮመኮምኩ ደስ ብሎኝ ስስል እውላለሁ” ሲል ሥነ-ጥበባዊ አስተያየት ባለው ማስታወሻው ላይ አስፍሮ አንብበናል።

የአንድ ዓመት የስዕል ስብስቦችን ለዕይታ ያበቃው ወጣቱ ሰዓሊ፤ 43 ሥራዎቹን ለተመልካቹ አቅርቧል። በእነዚህም ሥራዎቹ ውስጥ “ ስዕል ማለት ለእኔ እያንዳንዱን ሀሳብ ለመግለፅ የምጠቀምበት የበለፀገ ቋንቋዬ ነው” የሚለው ወጣቱ ሰዓሊ፤ በሥራው አማካኝነት በከተማችን ውስጥ የሚታዩትን በጐና እኩይ ትዕይንቶች ለማሳየት ስለመሞከሩ ይገልፃል።

ለስዕል ሥራ በስቱዲዮ መሀፀን ውስጥ እንዲቆይ ስለሚያደርገው ቆስቋሽ ምክንያቶቹን ሲናገር ደግሞ እንዲህ ይላል፤ “ለስዕል የተዘጋ ስሜት የለኝም። እያንዳንዱን ስሜቴን እገልፅበታለሁ፤ ሳዝንም ስደሰትም በስዕል ሥራዬ ላይ ማውጣት እችላለሁ። እንደሚታወቀው ስቱዲዮ የብቻህ ቦታ ነው። ከራስህ ጋር ጉባዔ የምትቀመጥበትና እጅግም ተመስጦ የሰፈነበት ቦታ ነው ለእኔ” ባይ ነው።

በሙዚቃ በጣም እንደሚዝናና የሚናገረው ወጣቱ ሰዓሊ ቃልኪዳን፤ በስቱዲዮ ቆይታውም ከስዕል ሥራው ጋር ሙዚቃን በእጅጉ እንደሚያደምጥ ይናገራል። “ጓደኞቼ ሙዚቀኞች ናቸው። እነሱ በባንድ ሲለማመዱ እንኳን አብሬያቸው የማሳልፈው ግዜ በጣም ደስ ይለኛል። በአጠቃላይ ግን ከጥበብ ጋር የተገናኙ ዝግጅቶችን መታደም ያዝናናኛል” ባይ ነው።

የስዕል አሳሳል ፍልስፍናውን በማመላከት “ሥራዎቼ በይበልጥ ሙከራዊና ፍለጋዊ አይነት ናቸው” የሚለው ወጣቱ፤ ለዚህ አሳሳሉም አይነተኛ አርአያ የሚያደርገው አንጋፋውን ሰዓሊና ገጣሚ ገ/ክርስቶስ ደስታን እንደሆነ ይገልፃል። ከውጪ ተፅዕኖ ያሳደሩበት ሰዓሊያን ቢኖሩም፤ የገ/ክርስቶስን ያህል የሚወደው አርቲሰት ግን እንደሌለ አስረግጦ ይናገራል።

ወጣቱ ሰዓሊ ቃልኪዳን ሾቤ፤ በስዕል ሥራ ብቻ መኖር በሀገራችን ትንሽ ፈታኝ እንደሆነ ጠቅሶ፤ እርሱም ቀኑን ሙሉ በራሱ ስቱዲዮ በስዕል ሥራው ላይ ተጠምዶ ቢውልም፤ ሀርመኒ የፋሽንና ዲዛየን ኢንስቲትዩት ውስጥ የ“Creative Art” መምህር ሆኖ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ይናገራል። አክሎም፤ “አብዛኞቹ ሥራዎቼ ገንዘብ ተኮር ስላልሆኑ መቼ እንደሚሸጡ በፍፁም አላውቅም፤ ስለዚህ የገቢ ጉዳይ በመምህርነቴ ይካካሳል” ሲል ይገልፃል።

ከመስከረም 14 ቀን 2008 ዓ.መ ጀምሮ በመጐብኘት ላይ የሚገኘው የሰዓሊ ቃልኪዳን ሾቤ ሥራዎች ለሁለት ወራት ያህል በጋለሪያ ቶሞካ የሚቆይ ሲሆን፤ የስዕል ሥራ አድናቂዎችም በቦታው ተገኝተው እንዲጐበኙ እና የስሜቱ ተጋሪ እንዲሆኑ በነፃ ስለመጋበዛቸው ወጣቱ ሰዓሊ ይገልፃል።¾  

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
16654 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1041 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us