የዘመናችን ስላቅ - “እያዩ ፈንገስ”

Wednesday, 14 October 2015 13:13

 

በቀላል የመድረክ ግንባታ፤ በከባድ የትወና ስሜቴ፤ በፍልስፍና፣ በጥያቄና በስላቅ የተሞላ በአንድ ሰው ለሁለት ሰዓታት በመድረክ ላይ የሚታይ ቀዳሚ ቴአትር ነው - “እያዩ ፈንገስ” ጓደኛህን ንገረኝና ማንነትህን እነግርሃለሁ ይሉትን የቆየ ብሂል ቀይሮ “የምትጥለውን ቆሻሻ አይቼ ማንነትህን እነግርሃለሁ” የሚለው እያዩ በዘመናችን ላይ እየተሳለቀ ያስቀናል፤ እየተቆጨ ያሳቅቀናል፤ እያለቀሰ ያሳዝነናል።

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የአንድ ሰው የሙሉ ጊዜ ቴአትር ነው የተባለለት “እያዩ ፈንገስ” በበረከት በላይነህ ተፅፎ፤ በግሩም ዘነበ ዝግጅትና ድንቅ ትወና ተውቦ በአበባው መላኩ ፕሮዲዩሰርነት የቀረበ ሲሆን፤ ሙዚቃውን ጆርጋ መስፍን፣ አበጋዝ ክብረወርቅ፣ ግሩም መዝሙር ሰርተውታል። የዜማ ደራሲና ፕሮዲዩሰሩ ደግሞ አለማየሁ ደመቀ ነው። ሙዚቃውን በተዋሃደ ድምፅ ያቀነቀኑት ደግሞ በዛወርቅ አስፋውና ግዛቸው ተሾመ ናቸው። ቴአትሩ በአዶት ሲኒማና ቴአትር፣ በዓለም ሲኒማ እና በአቤል ሲኒማ በመታየት ላይ ይገኛል።  

ሀገሩን በመንደር እየመሰለ፤ ፌስታሉን በገመናችን መሸሸጊያ እየመሰለ “አሽሙራም ሁላ!” ሲል የሚተቸን “እያሉ ፈንገስ”፤ በራሳችን ላይ እንድንስቅና እንድንሳቀቅ ነገር እየጐነጐነ ያጐርሰናል። ቴአትሩ በኢትዮጵያ ታሪክ በአንድ ብቸኛ ተዋናይ የሚከወን ይሁን እንጂ፤ ተዋናዩን የሚያጅቡት ከአስር ያላነሱ ስውር ገፀ-ባህሪያትን ታዳሚው እንዲተዋወቅ ያደርጋል። በተለይ ከእያዩ ፈንገስ ባልተናነሰ በቴአትሩ ውስጥ እውቅናና ሞገስ የሚቸራቸው ሰው “ጋሽ ቆፍጣናው /ቆፍጤ/” ናቸው። ስለጋሽ ቆፍጣናው የሚተርክልን እያዩ “ሀቀኛና ፊት ለፊት ተናጋሪ፤ ታጥቦ የተቀሸረ ሙጢ ናቸው” ይላቸዋል።

ባነሳው ነገር ላይ ሁሉ እንደማጣፈጫ እና እንደነገር ማስረገጫ ጋሽ ቆፍጣናው መጠቀሳቸው ለቴአትሩ ትልቅ ወዝ ፈጥሯል ማለት ይቻላል። (ኧረ እያዩንም ዘና የሚያደርጉት የልብ አውቃው እርሳቸው ብቻ ናቸው።) ስለውሃ ተነሳ፣ ስለስልክ ተነሳ፣ ስለ መብራት ተነሳ፣ ስለ ቲቪ ተነሳ፣ ጋሽ ቆፍጣናው ጣል የሚያደርጉት ስላቅ የተመልካችን ሣቅ ለማፈንዳት እንደተጠመደ ቦምብ በአዳራሹ መፈንዳቱ አይቀሬ ነው።

በእዚህ’ጋ በ“እያዩ ፈንገስ” ቴአትር ውስጥ ብቸኛው ተዋናይ ግሩም ዘነበ ዋናውን ባለታሪክ ይዘውረው እንጂ አጃቢዎቹ በርካታ ናቸው። ከላይ በግንባር ቀደምትነት የጠቀስናቸው ጋሽ ቆፍጣናው እንዳሉ ሆነው፤ ወዳጄ የሚለው ገጣሚው እሱባለው ካሣ፣ እትዬ ምልጃ፣ ወጌሻው ለማ ጉቴ፣ ወጣቱ ጋዜጠኛ፣ “ዳኛውን የሚያውቅ” ተብሎ የተሸሞረበት ጠበቃ፣ የህያውዬ እናት በጉልህ ተጠቃሾቹ ናቸው።

“እያዩ ፈንገስ” በአራት ትዕይንቶች ተከፋፍሎ፤ በስላቅና በሙዚቃ እየተዋዛ ለሁለት ሰዓታት በዘመናችን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ክስተቶች ላይ እንድንስቅ እንድንቆጭና እንድንጠይቅ ኮርኳሪ ሀሳቦችን በቤት ስራ መልክ ለተመልካቹ የሚሰጥ ቴአትር ነው። ይህም ብቻ አይደለም ገና ከአዳራሹ ሳንወጣ እርስ በእርሳችን እንድንጠያየቅና እንድንተዛዘብ፤ በኑሮአችን ምስቅልቅል ጩኸት ውስጥ አደባባይ የሚያቆመንን ከባድ እውነት በቀላል መንገድ የሚነግረን በጥበብ የተቀመመ ስራ ነው።

ስለፍትህ ሲነሳ አገራችን ውስጥ ጠበቆች በሁለት ይከፈላሉ የሚሉት ጋሽ ቆፍጣናው “ሕጉን የሚያውቅና ዳኛውን የሚያውቅ” ሲሉ ታዳሚውን ምሳሌ እየጠቀሱ ያፈርሱታል። የባቡሩን ነገር አንስቶ ተመርቆ የመዘግየቱን ነገር አይደንቅም ብለውን ሲያበቁ፤ በፍጥነቱ ቀርፋፋ መሆን ላይ ግን “ህዝቤ መዋያ አገኘ” ሲሉ ጋሽ ቆፍጤ በነገር ሸንቆጥ እያደረጉ አዳራሹን በሣቅ ያምሱታል። የአገራችንን ፍትህ ሲሳለቅበትም “አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ” ይሉትን የቆየ ብሂል ወዲያ ጣጥሎ፤ “ልጆች ሰባሪ አባት ወጌሻ” አይነት “የፋሚሊ ቢዝነስ” ስለመጀመሩ ሹክ ይለናል።

ከሁሉም በላይ “ጋሽ ቆፍጣናው ለዘላለም ይኑሩ!” እያለ የሚያሞካሻቸው እያዩ፤ ቆስቋሽና ቁጭት ጫሪ በሆነ ድምፀቱ ውስጥ ሆኖ በሣቅ ማዕበል የሚጋልበውን ተመልካች፣ “መሸነፍ ደስ የሚለው ደህና አሸናፊ ሲገኝ ነው፤ መሞትህ ካልቀረ ገዳይ ምረጥ” ሲል ስክን ብሎ ወደራሱ እንዲመለከት ይጋብዛል።

የቴአትሩ በተቃርኖ የተሞላ ስላቅ ከሚያነሳው አብይ ጉዳይ መካከል “ስንዴ ሆይ ፍሬሽ ምን ያህል ነው? ቢሏት ገለባዬን ጠይቁት አለች” በሚሰኘው ብሂል ላይ የተቀመረ እንደሆነ የፌስታሉ ነገር ትልቅ ምሳሌ ነው። እያዩ ቆሻሻችንን ዘርግፎ ይኸው ጉዳችን፣ ይኸው መልካችን፣ ይኸው ገመናችን ሲል፤ ውስጣዊ መልካችን (ስብዕናችን) ቅልብጭ ብሎ የሚታየው በገንዳ ውስጥ እንደሆነ እያሳሳቀ ይነግረናል።

“ሀያሲ በጠፋበት ሀገር ጋሽ ቆፍጣናው ይኑሩልን” እያለ በእርሳቸው አፍ የሚያሸሙረው እያዩ፤ ፊልም ሰሪዎቻችንንም ሆነ ሙዚቀኞቻችንን መስመር አልፋችኋል ሲል ይተቻቸዋል። እናም የበፊቱ ሀበሻዊ ዓይናችንና ቀናነታችን ጠፍቶ አንዱን ለመሸፈን ሌላውን ስለመደበቃችን፣ አንዱን ለመስፋት ሌላውን ስለመቅደዳችን፣ አንዱን ለማጉላት ሌላውን ስለማደብዘዛችን እየዘረዘረ ማታ ቤት ስንገባ ከራሳችን ጋር ጉባዔ መቀመጥ እንደሚገባን የቤት ሥራ ሰጥቶን ያልፋል። እዚህች’ጋ ግን በቴአትሩ ውስጥ ጐልታ ከተሰማች ሙዚቃ የወሰድኳትን ስንኝ ልጥቀስ፤

ምን ይሉት ቅጣት ነው

ምን የሚሉት ፍርድ

ሜዳ ጠፋ ብሎ፣ ተራራ መናድ?

የከተማችንን ገመና በስላቅ ማሳየት የቻለው ይህ “እያዩ ፈንገስ” ቴአትር የግሩም ዘነበን የትወና ብቃት በእጅጉ ጐልቶ እንዲታይ አድርጐታል ማለት ይቻላል። ግሩም ብዙ ችሎታውን ያሳየበት የፊልምም ሆነ የመድረክ ሥራዎች ቢኖሩትም እንዲህ እታች ወርዶ ከፍተኛ ፍልስፍና አዘል ሀሳቦችን ለሁለት ሰዓታት ሳይደክም እና ሳይንገራገጭ ማስኬዱን በስተመጨረሻ ተመልካቹ ከመቀመጫው ተነስቶ በሚሰጠው ፍቅርና ክብር ውስጥ በጉልህ የምትመለከቱት ይሆናል።

“እያዩ ፈንገስ” ሰውነት ሲረክስ፤ ሰውነት ከፍ ሲል፤ የሰብዓዊነት ክፍተትን የሰው ልጅን ከንቱ ሀሳብ ሁሉ በአንድ ጠቅልሎ ማሳየት የቻለ ተውኔት ነው። “በትክክል አለመስጠት ከንፍገት ይብሳል” ይለናል። በቴአትሩ ውስጥ የከተማችን አንገብጋቢ ጉዳይ ሁሉ ተነስቶ ተሳልቆበታል። የኮንደሚንየሞች የግንባታ ነገር ሐሜት ሲገባው ገመናችንን እንኳን መከለል አልቻለም ሲል “ተቀላቅለናል!” ይለናል። የውሃ እጥረቱን ታዝቦ፣ “የከተማችን ቧንቧ የደረቀው ውሃው በላስቲክ ታሽጐ እየተሸጠልን ነው” ሲል ይሳለቃል። የቴሌን ነገር ደግሞ 20/80 ሲል ገልጾታል (ሃያ በመቶ ደንበኛው ይገለገላል፤ ሰማኒያ በመቶ ደግሞ ቴሌ ገንዘብ ይወስዳል ቂ…ቂ…ቂ…!)። እናም ተመልካቹ በቴአትሩ ውስጥ የልቡን ስለሚነገረው ነገሩ የሚያናድድ ቢሆንም በስላቁ ግን በሣቅ ይነፍራል።

በስተመጨረሻም እንደማስታወሻ የሚሆን አንድ ነገር ልጥቀስ። ቴአትሩ በአጃቢና ወቅታዊ ስላቆች መለጠጥ የሚችል እንደሆነ ደግሞ ያየው ሰው ሊገነዘብ ይችላል። ይህንንም ተከትሎ ቴአትሩ እንዳይረዝም ይልቁንም ሁለት ክፍል እንዲኖረው የታሰበ ይመስላል። ይህን ለማለት የሚያስደፍር ሁለት አብይ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል። አንደኛው በቴአትሩ ይፋዊ “ፖስተር” ላይ “እያዩ ፈንገስ ቁጥር ፩” የሚል ነገር መፃፉ ነው። ቁጥር አንድ መባሉ ቁጥር ሁለት ለመኖሩ ምልክት ይሆናል። ሌላው ደግሞ በቴአትሩ መጨረሻ አካባቢ የጠፋው ቀይ ማስታወሻ ደብተር የገፀባህሪውን ወዳጅ ተደርጐ የተጠቀሰው የገጣሚ እሱባለው ካሳ ታሪክ የተተረከበት እንደነበር ይነግረንና ቀጣዩ ደብተር ደግሞ በእነህያው እናት ታሪክ ይሞላል ይለናል። እናም ዘመናችንን እንዲህና እንዲያ እያልን በ“እያሉ ፈንገስ” ውስጥ እናያለን ማለት ነው።

“እያዩ” እስቲ ምን እንደምታደርጉኝ አያለሁ እያለ፤ አልሰማሁም መባባሉን ችለንበት እንጂ እያለ፣ ተቀላቅለናል እያለ ብዙ ጉዳችንን ከጉያችን መንጭቆ እያሳቀ ያሳቅቀናል። እናም በድምሩ እንደ ህያውዬ እናት በፍቅርና በቅንነት ሰውን የምታሸንፍ ሰው እስክናገኝ ድረስ ገፀባህሪይው በሰፈር የመሰላት ሀገራችን “በግ ሆኖ የመጣ ሁላ ፍየል እየሆነ” የሚቀጥል ከሆነ እንዴት እንዘልቀዋለን? “ኑሮ ማለት ለእኔ አንተን (ፈጣሪን) በሰው ውስጥ መፈለግ ነው” ይለናል እያዩ በቴአትሩ መጨረሻ፤ ፈጣሪ ለእያዩ በምንወዳቸው፣ በምናከብራቸው፣ በምንመካባቸው ሰዎች መልካም ስብዕና ውስጥ የሚታይ ነው። በስተመጨረሻም ከቴአትሩ ገላጭ ስላቆች መካከል አንዱን ጠቀሼ ልሰናበት “የወለቀው ልቤ፣ የሚታሸው እግሬ!” ቴአትሩ ግን ከዚያም በላይ ብዙ ብሏልና እስቲ “እያዩ ፈንገስ”ን እያያችሁት ራሳችሁን ታዘቡ።¾   

ይምረጡ
(6 ሰዎች መርጠዋል)
17915 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 968 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us