የአደም መስታወቶች

Wednesday, 21 October 2015 14:23

 

ከ2007 ዓ.ም መጨረሻ እጃችን የገባ የግጥም መድብል ነው። በገጣሚ አደም ሁሴን የተፃፈውና “እሳት ያልገባው ሐረግ” የተሰኘው ስብስብ ግጥሞችን የያዘው መፅሐፍ በ106 ገፆች ውስጥ 86 አናት ያላቸው የግጥም ስራዎች ቀርበዋል። ገጣሚ አደም ሁሴን አዳማን ተንተርሶ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በሚዳስሱት የግጥም ስራዎቹ የራሳችንን ህይወት፤ ደስታና ሀዘን፤ ፍቅርና ጥላቻ፤ ማግኘትና ማጣት፤ ማን አለብኝነትና ፍትህን፤ ነፃነትንና መንፈሳዊ ከፍታን ሁሉ እንካችሁ በመነፅሬ በኩል እዩልኝ ይለናል።

የዘመኑን ግራ አጋቢነትና የሰውን ልውጥውጥ ባህሪይ በሚያሳየው ግጥሙ የሚከተለውን ሁለት ስንኝ እንዲህ ያስነብበናል።

ድንገት ዛሬ ነቃሁ ካልተኛሁት እንቅልፍ

እባብ እየሳመኝ እርግብ ስትናደፍ።

                  (ገጽ÷ 63)

ገጣሚው በቃላት ከሚያደርገው ጨዋታ በላይ፤ እንደግጥም ስርዓት እጥር ምጥን ባለ መልኩ ቦምብ የሆኑ ሃሳቦችን የእያንዳንዱ ርዕሰ ጉዳይ ስር ያፈነዳል። አይተናቸው እንደዘበት ያለፍናቸውን ጉዳዮችና ክስቶች ሁሉ ገጣሚው በተለየ መልኩ እንካችሁ ይሉናል። ከተንኮልና ከሀሜት ሽሽትን የሚመርጠው ገጣሚው፤ ይባስ ብሎ ፍጥረቴ ቢቀየርስ ሲል ይሞግታል።

ካልጋገሩት ቆርሰው

ካልጠመቁት ቀድተው

ካልዘሩት ከሚያጭዱ ከትውልድ በሽታ

ከጉንጭ አልፎ ወሬ ሁካታ ጫጫታ

ከምቀኞች ሽሽት ቤቴ በድር ታጥሮ

ካልቀረስ መመኘት ዳግመኛ ተፈጥሮ

የሰው ዓይን ካላየው የተረሳ ቦታ

ምነው ባደረገኝ ሸረሪትን ላፍታ።

                  (ገፅ÷30)

በግጥሞቹ ውስጥ ገጣሚው (ተራኪው) ተደጋግሞ የሚጠቀስ ሲሆን፤ እንዲህ ባደርግ፣ እንዲህ ብሆን፤ እንዲህ አድርጌና እንዲህ ሆኜ የሚሉ ሀሳቦች ተደጋግመው በስራዎቹ ውስጥ ይንፀባረቃሉ። አንዳንዴም በግጥሞቹ ውስጥ የሚያውቃቸውን ሰዎች እያስታወሰና እነሱን እያሰበ እንደፃፈ ከግጥሞቹ ግርጌ በሚተውልን ማስታወሻ እንረዳለን፡፤ ለምሳሌ ለአንድ ጓዴ ብሎ የጻፈውን “ቅፅበቴ” በተሰኘው ግጥም እንመልከት፡-

አየሁሽ ወደድኩሽ ከዚያም ተመኘሁሽ

መሃላ ላመሌ ያልሽኝን እንዳሻሽ

ቃሌን ደረደርኩት ዓለምን ሰጠሁሽ!

ሁሉን በአንድ ሌሊት አወቅሽኝ አወኩሽ።

በተስፋ ተሞልተን ሌቱ ለኛ ቆሞ

የስሜት ግለቱ ትግሉ ተፋፍሞ

ድል በድል ስንሆን ሃጢያቴን ሳስነጥስ

ጋልቤ ዱብ ስል ከስሜቴ ፈረስ

ቅፅበት ቃሌን ክቦ ቅፅበት ቃሌን ሲያፈርስ

ግልገሌን ስጠልቅ ታየው ስተራመስ።

                        (ገፅ ÷ 16)

በግጥሞቹ ውስጥ ስለእኛ የተጻፈ አለ፤ በስደት ኑሮ ላይ ስለሚገኙ ወገኖች የተጻፈ አለ፤ ለህሊና እስረኞች የተቀመጠ ቅኔም እንዲሁ። ከዚህም በላይ ገጣሚ አደም ሁሴን ስንኝ የቋጠረባቸው የሀገር ጀግኖችና ባለውለታዎችም አሉ። ለማስታወስ ያክል “ለጀግናው በላይ ዘለቀ እና ለሀገራችን አንድነት ለደሙ፣ ለቆሰሉ፣ በተለየ መንገድ ዋጋ እየከፈሉ ለሚኖሩ ወገኖቼ” ሲል ካሰፈረው ግጥም እንቆነጥራለን፤

“በላይ ነኝ ለናቴ”

በዱር በገደሉ

ያዙኝ አሳዳችሁ

ጣሉን አበሻቅጡኝ

ባኮርባጅ ግረፉኝ።

ቆዳዬም ተልጦ

አጥንቆቼም ገጦ

ዝንቦች ይደግሱ

ይውረሩኝ ትሎቹ።

አንገቴም ሲጥ ይበል

ስጋዬም ይንጠልጠል

ባልዋልኩበት ቦታ መዋል መሰተሬ

ይሄ ነው ወይ ግብሩ ውለታሽ ሀገሬ!?

                        (ገፅ÷29)

ቀጣዩ ግጥም ለክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ማስታወሻ ያደረገው ነው። ግጥሙ ምናልባትም በመፅሐፉ ውስጥ ካለውና “የበረሃ ሀረግ” ከተሰኘው ስራ ለጥቆ ረጅም ሳይሆን አይቀርም። ርዕሱ “ጥላ. . .ሁን ለነፍሴ” ይላል፤ ለመቆንጠር ያክል ጥቂት ስንኞችን እንካችሁ።

ግማሽ ዘመን ሙሉ

እመድረክ ላይ ነግሰህ

ደንሰህ አልቅሰህ

እኛን መሰለህ እኛን ኖርህ

ውስጣችን እንኳኩተህ

እርግጥ ነው. . .

ሰው መቼም ሞትን ይሞታል

ያለነው በፊትም

ሞትን ግን ማሸነፍ

በስራ ተግባሩ

አንተ ድል አድርገህ

      ዘመን ሲሻገሩ

አየሁት በግርምት እስከ ሙሉ ክብሩ

ዕድሜ ጠግቦ ዛሬ በግም ትንሳኤ

      ሞትና ልደቱ።

አሀዱ እንዳልክባት እንደ “ጥላ ከለላ”

      ሺ ዘመን ትኖራለህ

ቅርስ ነህ ላገርህ ሙሽራ ሁን ለኛ።

                        (ገጽ÷ 58)

ገጣሚው ሌላም ተወዳሽ ይጠቅሳል። እውቋን ገጣሚ ፊርማዬ አለሙን፤ እናም በቁጭት ተሞልቶ ፊርማዬን በማጣቱ የተሰማውን ስሜት እንዲህ ያስነብበናል።

ጎበዝ ምን ተሻለ

ገበታው ቀለለ

ሌማቱም ሳሳብኝ

የግጥም አዝመራ

የጥበቤ ችግኝ።

ሳይሮጡ መሸነፍ

ሳይተኩሱ መክሸፍ

ፀንሰው መጨንገፍ

ሳያብቡ መርገፍ

ምን ይሉታል ይሄን

ምቀኛ ሰው በላን?

            (ገፅ÷59)

ማህበራዊ ሰንኮፋችንን ለመዳሰስ፤ ግለሰባዊ ፅናታችንን ለመፈተሸና መልካም ጊዜን ስለመመኘት የቋጠራቸው ስንኞች በርካታ ናቸው። ምኞት ፍላጎታችን ሁሉ እኛኑ የሚጎዳን እንደሆነ ሊያሳየን ሲፈልግ እንዲህ ስንኝ ይቋጥራል።

የምኞት አንድ ጫፍ

የግራው ጫማዬ ቀኙን እየሻተ

ቀኙ ልኩን አጣ ግራ ተጫመተ።

                  (ገፅ÷80)

እኛን በራቡ እየመሰለ ልክ -ልካችንን የሚነግረን (የሚገስፀን) ገጣሚው የዘመናችንን ስራ ፈት ሀብታሞች እንዲህ ይገልፃቸዋል። “አቋራጭ” የግጥሙ ርዕስ ነው።

ድንገት ባጋጣሚ

ህሊናዬን ከቤት

ቆልፌው ብወጣ

ሀብታም ሆኜ መጣሁ

ምንም ሳላወጣ።

      (ገፅ ÷24)

የመድብሉን መጠሪያ “እሳት ያልገባው ሐረግ” ይበለው እንጂ የግጥሞቹ ሁሉ የውል መጠለያ ያደረገው ገጣሚው በስብስቦቹ ውስጥ አስነብቦናል። አደም ሁሴን ግጥሞቹን የፃፋቸው ለራሱ በሚሰጠው ስሜት ልክ ቢሆንም፤ በጋዜጦች፤ በመጽሔቶች፣ በሩሲያ የባህል ማዕከል አዳራሽ እና በፌስቡክ በርካታ አንባቢያን ወደውለት የተመረጡ ስለመሆናቸው በመፅሐፉ መግቢያ ላይ ይጠቁማል። እኛም ከገጣሚው ከዚህ የላቁ ስራዎችን በቀጣይ እንጠብቃለን። መንፈስን በሚያድሱና በሚኮረኩሩት የገጣሚ አደም ሁሴን ስራዎች መልካም የመዝናኛ ሳምንት እንዲሆንላችሁ ተመኝተናል።n

ይምረጡ
(5 ሰዎች መርጠዋል)
11777 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us